አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ እየተስተዋለ ለሚገኘው ዝቅተኛ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እስከዛሬ የነበረው የአሰራር ጉድለት ምክንያት እንደሆነ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ተገለጸ ።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር ባደረገው የምክክር መድረክ እንደተገለጸው፤ በአገሪቱ ባለው የአሰራር ክፍተት ምክንያት መንግሥት ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር የነበረው ትብብር መልካም አለመሆን የቱሪዝም ዘርፉ ተጎድቷል፡፡ የሀገሪቱ ቱሪዝምን በተፈለገው እርምጃ እንዳያድግ እና ኢትዮጵያም ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዳትሆን ማነቆ ሆኖ ዘርፉን አቀጭጮታል።
የፓራዳይዝ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ኃላፊ አቶ ፍጹም ገዛኸኝ እንደገለጹት፤ ለቱሪዝም ዕድገት በዘርፉ የሚገኙ የግል ድርጅቶች ተሳትፎ የላቀ ቢሆንም መንግሥት የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ አይደለም። የሀገሪቱ የቱሪዝም ድርጅት ሲቋቋምም የግሉን ዘርፍ የማሳተፍ ዓላማ ይዞ ቢሆንም፤ ይህ ግን በተግባር አልታየም። ይልቁንም መንግሥት የግሉን ዘርፍ ያገለለ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፤ በሚያወጣቸው ዕቅዶችና በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይም ተሳታፊ ባለማድረጉ ተቋማቱ የአብሮነቱን መንፈስ ተነፍገዋል።
መንግሥት በተፈለገው ደረጃ የግል ዘርፉን አጣምሮ ባለመጓዙ ኢትዮጵያ ከዓለም የቱሪዝም ካርታ እንድትነጠልና በአሁኑ ጊዜም በተለያዩ የዓለም አቀፍ ንግድ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ እንዳይኖራት ምክንያት ሆኗል ያሉት አቶ ፍጹም፤ በካርታው ዳግመኛ ለመካተትም ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ እንደተገለጸው ቱሪዝም ኢትዮጵያ በሚል ስያሜ የተዋቀረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በተቋቋመበት የቱሪዝም አዋጅና ሥልጣን መሰረት ባለመሥራቱ የየዘርፉን እንቅስቃሴ በእጅጉ ሲጎዳው እንደቆየ ተጠቅሷል።
ከተቋሙ ባለሙያዎች የዕውቀት ዝግጁነት ጀምሮ የቁሳቁስና የሰው ኃይል አቅርቦት ችግር እንዳለበት የጠቀሱት የሰንራይዝ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ያዕቆብ መላኩ በበኩላቸው፤ ለቦታው የሚመጥን ባለሙያ በመመደብ የተዳከመውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማነቃቃት የግድ እንደሚል ተናግረዋል።
የተጠቀሱት ክፍተቶች መኖራቸውን በማመን በመድረኩ ለተነሱ ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን፤ በዘርፉ በየጊዜው የሚቀያየረው አመራር ለችግሩ መስፋት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። እስከዛሬ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የነበረውን ክፍተት በማጥበብ በጋራ ለመሥራትና ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ስኬትም «ሁላችንም በጋራ እንተባበር » ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በቱሪዝም ኢትዮጵያ የዕለቱ መድረክ አስተባባሪ አቶ ወልደ ገብርኤል በርሄ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቱሪዝሙ ዘርፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስትመዝን ከ138 ሀገራት መካከል 118ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ሁኔታም በቱሪዝም ደህንነት፣ በንጽህና አጠባበቅ፣ በትራንስፖርት አቅርቦትና ምቹነት፤ በሌሎችም መስፈርቶች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠች ተናግረዋል።
አስተባባሪው በመድረኩ ላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎችም ችግሮች ለቱሪዝም አለማደግ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በዚህ ዓመት በተቋሙ ዘርፉን ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እንደሚከናወኑ በመግለጽም፤ ከነዚህ መካከልም ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የቱሪስት መመዝገቢያ ሳተላይት አካውንት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት በተመሳሳይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/20111
በመልካምስራ አፈወርቅ