አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስድስት ወራት በግጭት ለተፈናቀሉና ለችግር ለተጋለጡ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ ዕርዳታዎች፤ እንዲሁም ለራስ አገዝ ስራዎች 280 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስታወቀ፡፡
በማህበሩ የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ፤ የገቨርናስና የዓባላት ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን አሊ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ማህበሩ ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ከ572 ሺህ በላይ ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ እንዲሁም በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ 400 ሺህ ለሚደርሱ ለአደጋ ተጋላጭ ወገኖች ማህበረሰብ ተኮር የልማት ስራዎች ሰርቷል፡፡
ማህበሩ በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች አልሚ ምግቦችን፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ፣ ብድር ልብሶችን፣ ፍራሾችን፣ የህክምና ዕቃዎችንና የመጠጥ ውሃ ጭምር ድጋፍ ማድረጉን ዶክተር ሰለሞን ገልጸው፤ ማህበሩ ከአደጋ ምላሽ መስጠት ጎን ለጎን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራዎችን እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራትም ለአብነት ያህልም 40 ሺህ የሚሆኑ ከሳውዲ ዓረቢያ ከስደት የተመለሱ ዜጎችን በዘላቂነት የማቋቋምና በተደጋጋሚ በድርቅ አደጋ ለሚጋለጡ በሞያሌ፣ በሱማሌና በሌሎች አካባቢዎች አነስተኛ የውሃ ቁፋሮ በማከናወን በግብርና ስራዎች እንዲሰማሩ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ለግብርና ስራዎቻቸው ውጤታማነትም ምርጥ ዘርና የተለያዩ ምርታማ የእንስሳት ዝርያዎችን ድጋፍ እንደሚያደረግም ገልጸዋል፡፡
‹‹ባለፉት ሦስት ዓመታት ከኢሊኖ ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎች፤ እንዲሁም በግጭቶች መከሰት የተነሳ ለልማት የምናውለውን ሀብት ለአደጋ ምላሽ እንድናውል እየተገደድን ነው›› ያሉት ዶክተር ሰለሞን፤ ማህበሩ ዘላቂ የሀብት ምንጩን ለማሳደግም በአዲስ አበባ ፍልውሃ አካባቢ 30 ፎቅ መንትያ ህንጻ በአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ፤ በክልሎች ደግሞ 40 የሚሆኑ ህንጻዎችን ያስገነባና እያስገነባ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ፤ ቀይ መስቀል በአሁኑ ጊዜ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት ሳይጨምር በ400 አምቡላንሶች 24 ሰዓት መደበኛ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና ዕርዳታና ነጻ የአንቡላንስ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አምቡላንሶቹ በመንገድ ዳር ተጎድተው የወደቁ ወጎኖችንና ነፍሰ ጡር እናቶችን ታድገዋል፡፡ በቀጣይም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች በአምቡላንስ አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር በስልክ ጥሪና አቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂፒየስ) በመጠቀም በቅንጅት ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ማህበሩ በ2010 በጀት ዓመትም ለ908 ሺህ ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከዛሬ 83 ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሲመሰረት 300 በጎ ፈቃደኞች አባላት የነበሩት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት 47 ሺ በጎ ፈቃደኞች አባላት ሲኖሩት፤ ቋሚ አባላቱ ደግሞ ስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ቻርተር መሰረት የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ሁሌም የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/20111
በጌትነት ምህረቴ