• ፋብሪካውን በሽርክና የሚያለማ ድርጅት አልተገኘም
አዲስ አበባ፡- የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን በያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ የባንክ ዕዳና ወለድ ምክንያት በራሱና በሚያስተዳድራቸው ፋብሪካዎች ህልውና ላይ ከባድ አደጋ ማንዣበቡን አስታወቀ። የፋብሪካውን ቀሪው ሥራ በማጠናቀቅ በሽርክና ለማልማት ጨረታ ቢወጣም ሸሪክ ማግኘት አለመቻሉን ገልጿል።
በኮርፖሬሽኑ፤ የፕሮጀክት ጥናትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ዋለልኝ፤ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ዕዳ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው የሙገር ሲሚንቶ፣ የአዳሚ ቱሉ ጸረ ተባይ ፋብሪካ ፣ የአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ፣ የባቱ ኮስቲክ ሶዳ ፋብሪካ እና የጎማ ዛፍ ልማት ፕሮጀክት ድርጅቶች ላይ የህልውና ስጋት ፈጥሯል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ መንግሥት ከባንክ 10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብድር ወስዶ ፋብሪካውን እንዲገነባ ለብረታ ብረትና ኢንጅነሪግ ኮርፖሬሽን 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ከፍሏል። ብድሩን ከወሰደበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ለወለድ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍሏል። ሆኖም ፋብሪካው በተገባው ውል መሰረት አልተጠናቀቀም።
‹‹ኮርፖሬሽኑ ከሐምሌ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለዕዳውና ለወለዱ በየሦስት ወሩ 398 ሚሊዮን ብር መክፈል ነበረበት›› ያሉት አቶ ዳዊት ሆኖም ኮርፖሬሽኑ መክፍል ባለመቻሉ የሁለት ጊዜ ክፍያ 796 ሚሊዮን ብር ዕዳ ባለቤት ሆኗል። እንዲሁም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ አንድ ነጥብ 592 ቢሊዮን ብር ዕዳ መክፍል የሚጠበቅበት ሲሆን እዳውን መክፈል ቢጀምር ለማጠናቀቅ 11 ዓመታት ይፈጃል።
ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ድርጅቶች የሚያገኘው ዓመታዊ ትርፍ 145 ሚሊዮን ብር መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዳዊት ዓመታዊ ትርፉ የአንድ ወር ዕዳ የማይሸፍን መሆኑን አስታውቀዋል። መንግሥት በዕዳው ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበት አንስተው ይህ ካልሆነ ግን በኮርፖሬሽኑና በሚያስተዳድራቸው ድርጅቶች ህልውና ላይ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ጠቅሰዋል። በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥም ለመንግሥት ሪፖርት እያዘጋጀ ነው ብለዋል።
አቶ ዳዊት እንዳሉት ፤ የፋብሪካው ግንባታ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከተነጠቀ በኋላ መንግሥት የግንባታውን ቀሪ ሥራ በማጠናቀቅ በሽሪክ፣ አቅሙ ከፈቀደ እስከ 900 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ በመበጀት ማጠናቀቅ ወይም ግንባታውን በማቆም በእንፋሎት ኃይል የሚመረተውን 90 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማምረት እንዲሁም የድንጋይ ከሰል በማውጣት ከውጭ የሚገባውን መተካትና ለማዳበሪያ ፋብሪካ የተገነባው መሰረተ ልማት ለግብርና ማቀናበሪያ እንዲውል የሚል ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
መንግሥት በሽርክና ለመሥራት ፈቃደኛ የሚሆኑ ድርጅቶች ካሉ ቀሪውን ሥራ በማጠናቀቅ አብሮ ለመሥራት ወስኖ ጨረታ ቢወጣም አብሮ ለመሠራት ፍቃደኛ የሆነ ድርጅት አለመገኘቱን ተናግረዋል።
በድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ ለማምረት የፋብሪካው ግንባታና ማዳበሪያውን ለማምረት ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስከትል የሚያነሱት አቶ ዳዊት በጋዝ አማካኝነት ከሚያመርተው ፋብሪካ እስከ 150 በመቶ ጭማሪ አለው። በድንጋይ ከሰል ማዳበሪያ ትርፋማ ለመሆን በዓመት ከ600 ሺ ቶን በላይ ማምረት አለበት። የያዮ ፋብሪካ በዓመት ያመርታል ተብሎ የታሰበው 300 ሺ ቶን ነው። በዚህ ሁኔታም ከውጭ አገር ከሚገባው ጋር መወዳደር እንደማይችልም ገልጸዋል።
ግንባታው 730 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣ ተገምቶ ሥራው ቢጀመርም ተጨማሪ እስከ 900 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጠናው ጥናት ያመላክታል። ግንባታው ቢጠናቀቅም በገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችል ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ 85 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ የሚተዳደረው በግብርና ነው። ለግብርና ግብዓት የሚሆነውን ማዳባሪያ በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን በላይ ማዳበሪያ በውጭ ምንዛሬ ከዓለም ገበያ ትሸምታለች።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ