ቡራዩ፡- ለውጡን ተከትሎ የተፈጠሩ ግጭቶች ካስከተሎት የሰው ሞትና ንብረት ውድመት ማግስት የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የህዝቦችን ደህንነት ከማስጠበቅና የህዝብ አመኔታና ድጋፍ ከማግኘት አኳያም የህግ የበላይነት የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል፡፡
የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ኃላፊ ኮሚሽነር ሰለሞን ታደሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በከተማው በ2011 መግቢያ ላይ የህዝቡን ሰላም በማደፍረስ ለውጡን ለማደናቀፍ በሚፈልጉ ኃይሎች የጸጥታ ችግር ነበር፡፡ በዚህም የሰው ህይወት አልፏል፤ ንብረትም ጠፍቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የጸጥታ መዋቅሩን አጠናክሮና ህዝቡንም አሳትፎ በመሠራቱ ከህዝቡ ሰላም ፈላጊነት ጋር ተዳምሮ አሁን የጸጥታው ሁኔታ ከሌሎች ከተሞች በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡
እንደ ኮሚሽነር ሰለሞን ገለጻ፤ ከተማዋ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉባት እንደመሆኗ፤ ለአዲስ አበባም ቅርብ ከመሆኗ፤ እንዲሁም የኮትሮባንድ መዘዋወሪያ አመቺ መስመር ላይ ከመገኘቷ አኳያ የከተማዋ ሰላም እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ:: ችግሩን ከመከላከል አኳያ ህብረተሰቡን አሳትፎ ከመሥራት ባለፈ ከአዲስ አበባ፣ ከኦሮሚያና ከፌዴራል ፖሊሶች እንዲሁም ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ተግባር ውጤታማነትም የችግሮችን ምክንያትን መከሰቻ ስፍራ የመለየት ሥራ ተከናውኖ ዕርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል::
በተለይ ህዝቦችን በብሔርና በሃይማኖት የማጋጨት ተግባራትና አዝማሚዎች መበራከት፤ በሕገወጥ መልኩ ለመጠቀም በሚደረጉ ጥረቶች በሚፈጠር የጥቅም ግጭት እና ሌሎች ደረቅ ወንጀሎች መስፋፋት መኖሩ ተለይቶ ችግሮቹን ከምንጫቸው ለማድረቅ የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል::
አሁን በከተማዋ ለተገኘው ሰላም የመንግሥት መዋቅሩ ድርሻ ቢኖረውም የሰላም ጉዳይ የህዝብ ጉዳይ ነው:: በመሆኑም አሁን የተገኘውን ስላም ከማስቀጠልና መሰል ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ተሠርቷል:: ሆኖም ህዝቡ በጸጥታ ኃይሉ እምነት ኖሮት የበለጠ አጋዥ እንዲሆን የሕግ የበላይነት የማስፈን ሥራው በትኩረት እየተሠራ ሲሆን፤ በተለያየ ወንጀል ተሳታፊነት ተጠርጥረው ከተያዙ 370 ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ ጉዳያቸው ውሳኔ እንዲያገኝ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡
ኮሚሽነር ሰለሞን፣ እስከአሁን በተወሰዱ ዕርምጃዎችና በተከናወኑ ተግባራት የተገኘው የከተማዋ ሰላም እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም በትኩረት ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ በተለይ ህዝቡን በብሔርና በእምነት የማጋጨት አካሄዶች አሁንም የደረቅ ወንጀሎች በመኖራቸው የጸጥታ መዋቅሩ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ወንጀል ፈጽመው በከተማዋ የሚሸሸጉ ግለሰቦች መኖር፤ አልፎ አልፎ ህገወጥ መሳሪያ በምሽት ይዞ መንቀሳቀስና የተኩስ ድምፅ በማሰማት ህብረሰተቡ እንዳይረጋጋ የማድረግ ተግባራት፤ እንዲሁም አዲስ አበባን ከአጎራባች ከተሞች ጋር የማጋጨት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ችግሩን ከመቆጠር አኳያ የድርጊቱ ፈጻሚዎችን የማጥራት፣ የመያዝና ዕርምጃ የመውሰድ ተግባር እየተከናወነ ከአዲስ አበባ ፖሊስና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋርም በጋራ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2012
ወንድወሰን ሽመልስ