በመላው ዓለም የሴቶች እግር ኳስ ውድድሮች ፈተና እንደበዛባቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየተገለጸ ይገኛል። በአርጀንቲና የሴቶቹ እግር ኳስ ውድድሮች በቂ የቴሌቪዥን ስርጭት አያገኙም እየተባለ ሲብጠለጠል ቆይቷል። ነገሩ በአርጀንቲና ከረር ያለ ይሁን እንጂ በአብዛኛው የአፍሪካ እና ያደጉ አገራትም ጭምር እንደሆነ ይስተዋላል።
በሌላ በኩል የአፍጋኒስታን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ደግሞ በሃይማኖት አክራሪዎች ምክንያት እራሳቸውን ከቡድኑ ውጪ እስኪያደርጉ ድረስ ጫና እንደሚደርስባቸው መረጃዎች አመልክተዋል። በኢትዮጵያም ቢሆን ከሴቶቹ ይልቅ ለወንዶቹ እግር ኳስ የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑ አሳሳቢ ነው። እንዲሁም የሴቶቹ ጨዋታ በሚደረግበት ወቅት የሚገኘው ተመልካች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው። የቅርቡን ለማስታወስ ያህል እንኳ በወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ከትናንት በስቲያ የተካሄደውን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡናን ደርቢ ጨዋታ ለመመልከት በስታዲየም የተገኘው ደጋፊ በርካታ ነበር። ከዚህ ውስጥ ግን አስር በመቶውን ያህል እንኳ ለሴቶቹ ጨዋታ እንደማይገኝ ይታወቃል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ክለብ ስር የሚጫወቱ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያቸው የአለቃ እና የሎሌ ያህል የተራራቀ መሆኑን መታዘብ ይቻላል። ተመሳሳይ መለያ የምትለብሰው ሴት ተጫዋች የሚከፈላት ደመወዝ ከወንዱ ተጫዋች ይልቅ በአስር እና አስራ አምስት እጥፍ ማነሱ ለሴቶቹ የተሰጠውን አነስተኛ ትኩረት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሴቶቹን ከእግር ኳሱ እንዳያርቃቸው እየተፈራ ይገኛል። እንዲህም ሆኖ ግን አሁንም በኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ነው። ችግሮችን ተቋቁመው የቀጠሉ እንስቶችም ችሎታቸውን በሜዳ እያሳዩ ይገኛል።
ያለፈው ቅዳሜ በተካሄዱ የኢትዮጵያ ሴቶች የመጀመሪያ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ጨዋታዎች አዳማ ከተማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአልሸነፍ ባይነታቸው ቀጥለዋል። በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተጫወቱት አዳማ ከተማዎች ጌዲኦ ዲላን በሦስት ለባዶ ውጤት ሸኝተውታል። ግብ በማግባቱ እና በፈጣን እንቅስቃሴዋ እየተደነቀች የምትገኘው የአዳማ ከተማዋ የፊት መስመር ተሰላፊ ሴናፍ ዋቁማ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ እና ሁለተኛው አጋማሽ ማጠናቀቂያ ላይ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችላለች። ተጨማሪዋን ግብ ደግሞ ሰርካለም ጉታ ማስቆጠሯን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ቅዳሜ እለት ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል አዲስ አበባ ከተማ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሴቶች ቡድንን ያገናኘው ነው። በጨዋታው አዲስ አበባ ከተማዎች ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። በሌላ በኩል ቅዱስ ጊዮርጊስን ሃዋሳ ላይ ያስተናገዱት የደቡቦቹ ሃዋሳ ከተማዎች ሦስት ለምንም ማሸነፍ ችለዋል። ባህር ዳር ከተማ ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ጥረት ኮርፖሬት ደግሞ አንድ አቻ አጠናቋል። እሁድ እለት በተካሄደው ብቸኛው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ ሦስት ለሁለት በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
12 ክለቦች በሚሳተፉበት እና ስድስተኛ ሳምንቱን ባጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር አዳማ ከነማ የመሪነት ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አዳማ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፎ በአንዱ አቻ በመውጣት 16 ነጥብ ይዟል። ከአዳማ ጋር በተመሳሳይ ነጥብ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አዳማ ዘጠኝ ንፁ ግብ ሲኖረው ንግድ ባንክ በበኩሉ ሰባት ንጹህ ግብ አለው። መከላከያ እና ጌዴኦ ዲላ ክለቦች በአንጻራቸው በተመሳሳይ 12 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የወራጅ ቀጣናው ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በተመሳሳይ ሶስት ነጥቦችን ብቻ አስመዝግበው 11ኛ እና 12 ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሁለቱም ክለቦች እንደየደረጃቸው ሦስት እና አስር የግብ እዳዎችን ተሸክመዋል። በሴቶች በአንደኛ ዲቪዚዮን ህግ መሰረት ወራጅ የሚሆኑት የመጨረሻዎቹ ሁለት ክለቦች ናቸው። በመሆኑም ክለቦቹ ከመውረድ አደጋ ለመትረፍ በቀሪ ጨዋታዎቻቸው በቂ ነጥብ መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የአዳማ ከተማዋ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዋ ሴናፍ ዋቁማ በስድስት ግቦች እየመራች ትገኛለች። የሃዋሳ ከተማዋ ነጻነት መና፣ የድሬዳዋ ከተማዋ አይዳ ዑስማን እና የአዳማ ከተማዋ ሰርክአዲስ ጉታ ደግሞ በተመሳሳይ አራት ግቦችን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አግቢነት ፉክክሩን በሁለተኛነት ደረጃ ይከተላሉ።
ሊጉ ብቃት ያላቸው በርካታ ሴት እግር ኳስ ተጫወቾች የሚገኙበት መሆኑን የውጭ አገር አሠልጣኞች ጭምር አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይስተዋላል። በመሆኑም ክለቦች ለወንዶች የሚሰጡትን ትኩረት ለሴቶቹም ይኖርባቸዋል። የስፖርት ቤተሰቡም ሳቢ ፉክክሮች የሚታዩባቸውን ውድድሮች በመከታተል ለሴቶቹ ያለውን ድጋፍ ቢለግስ ለስፖርቱ ዕድገት መልካም ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
ጌትነት ተስፋማርያም