የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሄር ብሄረሰቦች በዓል አከባበር ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲሆን የተለያዩ ዝግጅቶች አድርጎ ማጠናቀቁን ከቀናት በፊት አስታውቋል። በዓሉን ተሰባስቦ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህልና እሴቶችን ከማስተዋወቅ ባለፈ፤ ልዩነቶቻችን ለአንድነታችን ውበት ሆነው እንዲጎሉ በማድረግ ላይ ግን ክፍተት ነበር ብለዋል።
ለ14ኛ ጊዜ ነገ በሚከበረው በዓል ባለፉት ጊዜያት የነበሩትን ክፍተቶች በመሙላት ጠንካራ ጎኑን በማስቀጠል የሚከወን መሆኑን አዘጋጆቹ ገልፀዋል። አከባበሩ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲሆን የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጉን ሰምተናል። ይህን ደማቅ ክብረ በዓል በማስመልከት የተወሰኑ ብሄረሰቦች ባህል እና ልዩ ልዩ ስርአት የተመለከቱ ጉዳዮችን ከየክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነውን መረጃ በምንጭነት ተጠቅመን ልናስተዋውቅ ወደናል።
የወይባ ጢስና የአርጎባዎች ውበት
የአርጎባ ብሄረሰቦች በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በሀረሪ ክልሎች ይኖራሉ። «አርጎባ» የሚለው መጠሪያም የተገኘው «አረብ ገብ» ከሚለው አባባል በመነሳት እንደሆነም የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። የአርጎባ ብሄረሰቦች የራሳቸው ቋንቋ ፣ አለባበስና የሰርግ ስነስርአት አላቸው። የአርጎባ ሴቶችን ከሌሎች ለየት የሚያደርጋቸው ደግሞ ዘመናትን የተሻገረው በወይባ ጢስ የመዋብ ልምዳቸው ነው።
የወይባ ጢስ ለአንዲት የአርጎባ ሴት የውበት መገለጫዋ ነው።ወይባ በአካባቢው የሚገኝ የእንጨት አይነት ሲሆን አብዛኞቹ ሴቶች እንጨቱን በጢስነት በመጠቀም ለውበት አገልግሎት ይጠቀሙበታል።አንዲት ሴት ለወይባ ጢስ ስትዘጋጅ መላ ሰውነቷን ቅቤ ትቀባለች።አስቀድሞ በተቆፈረውና እሳት ባለበት ጉድጓድ ላይ በተዘጋጀ መቀመጫ ላይ ተስተካክላ ተቀምጣ ጭሱን ትታጠናለች።ይህ ከመሆኑ በፊት ግን እሳቱ ወደሰውነቷ ዘልቆ እንዳይጎዳት የበሬ ቁርበት በመልበስ አካሏን ትጠብቃለች።
አንዲት ሴት ወይባውን በደንብ ከሞቀች በኋላ ሰውነቷን ትታጠብና «አዝጋሮ» የተባለውን እንጨት ትሞቃለች። ይህ መሆኑ በወይባ ጠረን የቆየውን ሽታ ለመቀየር ያግዛል። ጭሱ ደግሞ የበለጠ ውበት እንዲኖራትና በእጅጉ አምራ እንድትታይ ያደርጋል። የወይባ ጢስ ከውበት ባለፈ ፍቱን የጤና መድህን እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።አንዲት ወልዳ የተነሳች አራስ እሱን ብትጠቀም በቶሎ ለመጠንከር ያግዛታል።የወገብ ህመም ላጋጠማት ሴትም ወይባን ደጋግሞ መጠቀሙ መፍትሄ ያስገኝላታል ተብሎ በብሄረሰቡ ይታመናል።
የሀመር ብሄረሰብ
የሐመር ብሔረሰብ በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን በዋናነት በዞኑ ውስጥ በሐመር ወረዳ ይኖራል። ‹‹ሐመር›› የሚለው ቃል የብሐረሰቡ መጠሪያ ቃል በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹በተራራ እና በድንጋይ መካከል የሚኖሩ፣ የተዋሃዱና የተቀላቀሉ ሕዝቦች›› የሚል ፍቺ እንዳለውና ይህም ትርጉም ታሪካዊ መሠረት እንደያዘ ከብሔረሰቡ አዛውንቶች የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ትውፊት ሐመሮች በጥንት ዘመን በትላልቅና ሰንሰለታማ ተራሮች መካከል የሚገኙ የተቦረቦሩ ቋጥኞች ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የሚያመላክት እንደሆነ እንዚህ የዕድሜ ባለፀጋዎች ይናገራሉ።
የብሔረሰቡ አባላት ዋነኛ መተዳደሪያ ከብት እርባታ ሲሆን፣ ከዚህ ጐን ለጐን ንብ በማነብ እና በዝቅተኛ ደረጃ ደግሞ በቆሎና ማሽላ ለዕለት ፍጆታ በማምረት ኑሮአቸውን ይመራሉ። የብሔረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥ ጥንት ከ ‹‹ካራ››፣ ከ‹‹ኦሪ›› እና ከ‹‹መርሲ›› በመጡ የተለያዩ ማኀበራዊ ቡድኖች ውህደት የዛሬው የሐመር ብሔረሰብ እንደተገኘ ከብሔረሰቡ ታዋቂ ግለሰቦችና የሀገር ሽማግሌዎች የተገኘ አፍአዊ መረጃ ያስረዳል። ከእነዚህ የትውፊት መረጃ እና ከላይ የተጠቀሱትን አራት መነሻ ሥፍራዎች መሠረት በማድረግ ብሔረሰቡ ውስጥ ስድስት ማኀበራዊ ቡድኖች መኖራቸውን ይናገራል።
‹‹ቶርቶሮ›› የሐመር ብሔረሰብ አባላት በአመት አንድ ጊዜ አደባባይ በመውጣት የሚያከብሩት ባህላዊ በዓላቸው ነው። የሚከበረውም በሰኔ ወር መባቻ በእሸት ወቅት ነው። በዓሉ በድግስና በጭፈራ ይከበራል። የጭፈራው ዋነኛ ተዋናዮችም ያገቡ ወጣቶች ጎልማሶችና አዛውንቶች ሲሆኑ ፣ ያላገቡ ወጣቶችና ኮረዶች ሚና ደግሞ ድግሱን በማዘጋጀትና በማስተናገድ ላይ ብቻ የተወሰነ ነው።
‹‹ኢቫንጋዲ ›› የሐመር ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ብቻ የሚሳትፉበት ባህላዊ ጭፈራ ነው። ጭፈራውም በየሦስት ቀን አንዴ እያሰለሰ በሐመር መንደሮች በምሽት ጨረቃ ይካሄዳል። ‹‹ኢቫንጋዲ›› በአዝመራ ወቅት በሥራ የደከመን አእምሮና አካል ለማዝናናት ሲባል የሚደረግ ባህላዊ ጭፈራ ሲሆን፣ የሐመር ወጣቶች ከማኀበራዊ ሕይወት ጋር የሚተዋወቁበት አዳዲስ ባህላዊ ዘፈኖችና ጭፈራ ሲሆን፣ የሐመር ወጣቶች ከማኀበራዊ ሕይወት ጋር የሚተዋወቁበት አዳዲስ ባህላዊ ዘፈኖችና የአጨፋፈር ስልቶችን የሚቀስሙበት አጋጣሚ ነው። ከእነዚህ በተጨማሪ ሐመሮች የተለያዩ አጋጣሚዎችን ምክንያት በማድረግ የሚጫወቱት ‹‹ኤሬ›› የተባለ ባህላዊ ጨዋታ አላቸው። ኤሬ ወደ ሌላ አካባቢ ወይም ወደ ዘመቻ ለመሄድ ሲታሰብ በፉከራ መልክ የሚከወን ባህላዊ ጨዋታ ነው።
የሐመሮች ባህላዊ ቤት ከእንጨት የሚሠራ ሲሆን፣ ጣሪያው በሣር ይከደናል። ተባዮችን ለመከላከል በሚል ግድግዳው አይመረግም። ባህላዊ ቤቱ የውስጥ ክፍሎች የሌሉት ልቅ በመሆኑ የቤት ውስጥ የመገልገያ ቁሳቁስ ከቆጥ ላይ ይሰቀላሉ። በቤት ግንባታው ሂደት ዋነኛቹ ወንዶች ሲሆኑ፣ ሴቶች ደግሞ በሣር አቅርቦት ይሳተፋሉ። ‹‹ሙና መቱቆ›› (ኩርኩፋ)፣ ‹‹በላሽ›› (በማሽላ ቂጣ)፣ ‹‹ዳንጵደ›› (ፎሰሴ) እና (ዝጉ) (ከማሽላና ከበቆሎ የሚዘጋጅ ቂጣ) ዋነኛ የሐመሮች ባህላዊ ምግቦች ናቸው። ‹‹ፐርሴ›› (ቦርዴ) እና ‹‹አላ›› (የማር ብርዝ) ደግሞ ባህላዊ መጠጦቻቸው ናቸው።
የአመጋገብ ሥርዓታቸውን በተመለከተ የቤቱ አባወራ ከሁሉም ቀድሞ ይመገባል ። እናት በመጨረሻ ለብቻዋ የምትመገብ ሲሆን፣ አንዳንዴም ከልጆቿ ጋር ትመገባለች። ሆኖም ግን አባወራው በምንም አጋጣሚ ከመጀመሪያ ወንድ ልጁ ጋር አይመገብም ይህን እንዳይፈጽም ባህላዊ ሥርዓቱ እንደሚከለከለው የብሔረሰቡ አዛውንቶች ይናገራሉ።
የሐመር ልጆች በተለይም ሴቶች ሀፍረተ ሥጋቸውን ለመሸፈን ሲሉ ከቆዳ የሚዘጋጅና በሐመርኛ ‹‹ሺራን›› የሚባል ግልድም ያገለድማሉ። ከላይ ደረታቸውን ለመሸፈን ደግሞ ጥብቆ ‹‹ቃሼ›› ያጠልቃሉ። ሴቶች በዕድሜ ከፍ ሲሉ ደግሞ ከፊት ለፊታቸው ‹‹ቶቆ›› ከወደ መቀመጫቸው ደግሞ ‹‹ፋላንቲ›› የተሰኘ ከቆዳ የሚዘጋጅ ባለ ጥንድ ጉርድ ቀሚስ ይለብሳሉ። ካገቡ በኋላ ደግሞ ከወገብ በታች ማለትም በፊት ለፊት ‹‹ኢኮርባ›› ከኋላ ‹‹ቡድኮርባ ›› የሚባል ከፍየል ቆዳ የተዘጋጀ ጥንድ ቀሚስ ይለብሳሉ። ከወገብ በላይ ደግሞ ‹‹ቃሼ›› ጥብቆ ያጠልቃሉ።
ቤንች ማጂ
ቤንች ማጂ ከአዲስ አበባ 561 ኪ.ሜ ርቅት ላይ ትገኛለች። ዞኑ ከባህላዊ መስህቦች በተጨማሪ፤ የበርካታ ማራኪ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት እንደሆነ የተለያዩ መዛግብቶች ይገልፃሉ። በቤንች በዋናነት ከሚኖሩት ስድስት ብሄረሰቦች ውጪ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችንም በጋራ ታኖራለች። ባህልን ተወራርሰው ተከባብረው እና ተፈቃቅረው በጋራ ይኖራሉ። በስፍራው ለሚቆይ ማንኛውም ጎብኚ እጅግ ማራኪ የሚሆነው፤ ሁሉም ማህበረሰቦች ወግ ባህላቸውን የሚያዘጋጁት ትርኢት ነው። የቤንች ብሄረሰብ ሴቶች «ያሳ» በመባል የሚታወቀውን የወገብ ጨሌ በወገባቸው ላይ አጊጠው፤ የሱርማ፣የዚልማሞ እንዲሁም የመኤኒት የማህበረሰብ ክፍሎች በባህላቸው መሰረት ተውበው፤ ወንዶች ከበሮ፣ ጦር እና ጋሻ በመያዝ፤ በደማቅ ባህላዊ ሙዚቃ አቀባበል ያደርጋሉ።
ከእሸት በቆሎ የሚዘጋጅ «ኪጆ» ወይም «ካን ቡድ» የተባለ ጣፋጭ ባህላዊ ምግብ በቤንች ማጂ ቆይታችሁ ማጣጣም ትችላላችሁ። ያልተበረዘ ባህል እና ሙዚቃን እየኮመኮሙ፤ ኬሚካል ጭርሱኑ የማይደርስበት ምግብን መመገብ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል። ከሁሉም ደግሞ ማህበረሰቡ በፍቅር አብሮ ሲኖር መመልከት አስደሳች ነገር ነው።
ቡናና ቤንች ማጂ በከፋ ዞን ለአይናችሁ እስኪታክታችሁ የምትመለከቱት የጫካ ቡና ማግኘት እጅግ ቀላሉ ነገር ነው። ማህበረሰቡ በግብርና ላይ የተሰማራ ሲሆን ሰፊውን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የቡና ምርት ነው። ቁንዶ በርበሬ፣ ጥምዝ፣ ኮረሪማ፣ እርድ እንዲሁም የጫካ ማር የቤንች ማጂ ሀብት ነው።
ጌዴኦ ብሄረሰብ
ጌዴኦ በኢትዮጵያ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኝ ብሔር ነው። የጌዴኦ ብሔረሰብ በዋናነት በጌዴኦ ዞን ውስጥ ባሉ ስድስት ወረዳዎች በስፋት የሚኖር ሲሆን ከዞኑ ውጪም በሲዳማ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል በቦረና እና በጉጂ ዞኖች በሚገኙ አጎራባች አካባቢዎች በብዛት እንደሚገኙ ይገመታል። የጌዴኦ ብሔረሰብ በዋናነት በሚገኝባቸው የከተማና የገጠር አካባቢዎች ሌሎች የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የሲዳማ፣ የወላይታ በተለይም ደግሞ በከተሞች የጉራጌ እና የስልጤ ብሔረሰብ አባላት ከብሔረሰቡ ጋር በስብጥር ይኖራሉ። በሰሜን ከሲዳማ በደቡብ፣ በምስራቅ እና በምዕራብ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ጋር ይወሰናል።
የጌዴኦ ብሔረሰብ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ጌዴኦኛ ሲሆን በብሔረሰቡ አባላት ጌዴኡፋ በመባል ይጠራል። በኩታ ገጠም ወይም አጎራባች ሥፍራዎች ያሉ የብሔረሰቡ አባላት ከጌዴኦኛ በተጨማሪ ሲዳምኛንና ኦሮሚኛን እንዲሁም በከተሞች ያሉ ደግሞ አማርኛን በሁለተኛ ደረጃ ይጠቀማሉ።
የጋብቻ ስነ ስርዓት
በጌዴኦ ብሔረሰቡ ዘንድ ተግባራዊ የሚደረጉ የተለያዩ የጋብቻ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን እነዚህም “ካጃ” (ህጋዊ ወይንም የስምምነት ጋብቻ) ፣ ቡታ” /የጠለፋ ጋብቻ/፣ጃላ፣ ኪንቾ፣” አደባና” ፣ ሀዋዴ፣ ዋራዬ ኦልታ፣ “ሰባ” እና “ጊንባላ” በመባል ይታወቃሉ። ከነዚህ መካከል “ካጃ” እና “ሀዋዴ” የተሰኙት የጋብቻ ዓይነቶች በብሔረሰቡ ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን “ቡታ” እና “ዋራዬ ኦልታ” የተሰኙት በአፈፃፀማቸው በህገ ወጥነት ይፈረጃሉ። እንደነዚህ ያሉ የጋብቻ ዓይነቶች ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ ቢፈፀሙም በመጨረሻ ውስጥ ለውስጥ በሚደረግ ስምምነት እና ባህላዊ አስተዳደርና እምነት ፍራቻ ሕጋዊነታቸው ይፀድቃል። “ሰባ” የሚባለው ጋብቻ በወንዱና በሴቷ ወላጆች ይሁንታ ወይንም መፈቃቀድ የሚከናወን ሲሆን “ሀዋዴ” የሚባለው ደግሞ በሌላ ሶስተኛ ሰው አግባቢነት ወንዱና ሴቷ ስምምነት ላይ የሚደርሱበት ከዚህም በኋላ ወደ ሴቷ ቤተሰቦች ሽማግሌ በመላክ የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ነው።
በቤተሰብ ስምምነት በሚፈፀመው ሕጋዊ ጋብቻ ወቅት ተጋቢዎች በተጋቡ በሶስተኛው ቀን የሙሽራው ወላጆችና ቤተዘመድ በወንዱ ቤት ተሰባስበው የጉርሻ /ጊጫ/ ሥነ ሥርዓት በማከናወን ለሙሽሪት የተለያዩ ስጦታዎችን የሚሰጥበት ሥርዓት አለ። በዚህ ዕለት የሙሽራው ዘመድ አዝማድ በተገኘበት ሙሽራዎች (ወንዱ በስተቀኝ ሴቷ በስተግራ በመሆን) ከተሰብሳቢዎች ፊት ለፊት ቁጢጥ ብለው የሚከናወነውን የጉርሻ (የስጦታ) ሥነ ሥርዓት ለመፈፀም ይጠባበቃሉ።
ጉርሻው /ስጦታው/ የሚጀመረው ከሙሽራው አባት ወይንም አባት ከሌለ ከተሰብሳቢዎች መካከል አንጋፋ ከሆነው ሰው ስለሆነ ሙሽሪት ቀደም ብላ በተዘጋጀችበት መሠረት ጉርሻውን (ስጦታውን) ለመቀበል ወደ አባት ወይንም አንጋፋው ሰው ተጠርታ ትሄዳለች። በዚህ ሥነ ሥርዓት ወቅት ሙሽሪት ከወንዱ ቤተሰብ የምትፈልገውንና የምትጠብቀውን ስጦታ እስከምታገኝ ድረስ የሚሰጣትን ጉርሻ አትቀበልም። ስለዚህ በጥሪው መሠረት የልጁ አባት ወይንም አንጋፋው ቤተዘመድ አጉራሽ “ ይህን ያህል ብር ሰጠሁሽ ይላታል። “ እሷም “ አይበቃኝም” ትላለች። በመቀጠል “ ይህን ያህል መሬት ሰጠሁሽ” ይላል። አሁንም መልሳ “አይበቃኝም” ትላለች። ከዚያም “ይህንን ያህል ከብት ሰጠሁሽ” ሲላት “ አይበቃኝም አይበቃኝም “ እያለች ከቆየች በኋላ ከአጉራሹ (ከስጦታ ሰጪ) ዘንድ የምትፈልገውን ያህል ስጦታ ስታገኝ ጉርሻውን ትቀበላለች። በዚህ መልኩ የተሰበሰበውን ቤተ ዘመድ በሙሉ በማዳረስ ለጎጆ መውጫ የሚሆናትን በቂ ሀብትና ንብረት ታገኛለች።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር