ናማ ናማ፤ ብለህ ባታስጨንቀን፤
ኋላማ የአንተ ነን፤ ከአፈር አትለየን::
ብሎ አዝማሪው ለሞት እንደተቀኘው፤ የሰው ልጅ ከሞት እንደማይቀር ሌላው ቀርቶ መዘግየት አሊያም መፍጠን ሟች መብት እንደሌለው በቃላት ጥምረት ይነገራል:: አዝማሪው ‹‹ኖሮ ኖሮ ከመሬት፤ ዞሮ ዘሮ ከቤት›› እንደማይቀር ሁሉ ‹‹ኋላማ የአንተ ነን›› ከአፈር አትለየንም ሲል፤ እኛ የሰው ልጆች ሞተን መጨረሻችን አፈር መሆን ነው፤ ሲል ይናገራል::
ገጣሚ እና ሠዓሊ ገብረክርስስ ደስታ በበኩሉ፤ ‹‹ሞኜ ተላሌ›› በሚል አንድ ግጥሙ ሞት፣ ሕይወትና የሰዎችን እሳቤ ተመርኩዞ ከፃፋቸው ግጥሞች ይህን የመግቢያ ሃሳብ ወስደናል:: እንዲህም ሲል ገጥሞ ነበር::
በአራቱ እግሩ ሲቆም፤ ሲሄድ በሁለቱ
ሲያጌጥ ሲለባብስ፤ የሰው ልጅ ኩራቱ
ይኖር ይመስለዋል፤ ዓለም እንዲህ ጣፍጣ
መድከም መንገዳገድ፤ እርጅና ሳይመጣ
ወዙ ሲያብለጨልጭ፤ ፈገግታው ሲያበራ
ሰው እኔ ነኝ እኮ፤ ማን አለ ጠንካራ
ብሎ ሲደነፋ፤ ቆሞ ሲንጠራራ
ፍፁም አያስብም፤ ሰዓቱ ሲቆጥር
ነገ ዛሬ ሆኖ፤ ወደትናንት ሲዞር::
ገብረክርስቶስ ደስታ በዚህ ግጥሞ ውስጥ ሞት አይቀሬ ለመሆኗ እና ሰዎች ልጆች ጥንካሬ ሆነ ጀብድ ሁሉ ከመቃብር እንደማይቀር በጣፈጡ ቃላት ከትቦታል:: በዛሬ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምዳችን ላለፉት 15 ዓመታት በደብረሊባኖስ ገዳም የመቃበሪያ ጉድጓድ ‹‹ ፉካ›› ሲያስቆፍሩና ሲያሠሩ የቆዩትን አባት ውሎ፣ ሥራና አኗኗራቸውን እንቃኛለን::
አባ ገብረመስቀል
የሰው ልጅ ሞትን ይሙተው እንጂ አኗኗሩ እና መቃብሩም እየተዘማደ የመጣ ይመስላል:: ድሃ ሆነህ ስትኖር ድሃ ሆነህ ትቀበራለህ፤ ወይንም በድህኛ ቋንቋ ይለቀስልሃል:: ሀብታም ስትሆንም በሀብታምኛ ተለቅሶልህ በሀብታም ቅላፄ ተቆላምጠህ በሀብታም ፉካ ትቀበራለህ:: በእርግጥ በህይወት ኖረን ልዩነት እንዳለን ሁሉ ስንሞትም አቀባበራችን ልዩነት እንዳለው በግልጽ መረዳት ይቻላል::
አባ ገብረመስቀል ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በሚያሠሩት የመቀበሪያ ፉካ 800 ሰዎችን የሚይዝ ፉካዎችን ያዘጋጁ ሲሆን፤ እስከአሁን 600 የሚደርሱ ሰዎች ተቀብረዋል:: ይህ የፉካ ቁፋሮ ከተጀመረም ከ15 ዓመት በላይ ሲሆን አባ ገብረመስቀል በዚህ ሂደት ውስጥ በርካታ ፉካዎችን እያስቆፈሩ፣ ላለፉት 15 ዓመታት በዚያው ኑሯቸውን አድርገዋል:: በርካታ አባቶች የተመደቡበት ቦታ ላይ ሆነው ይህን መቆጣጠርና ማስተዳደር ሲሆን፤ የሚሠሩት ሥራ ከገዳሙ በረከት ከማግኘት በዘለለ ብዙም ለኪሳቸው የሚገባ ገንዘብ አያስፈልገንም ብለው የሚያምኑ ናቸው:: በዚህ የመቃብር ሥራ በርካታ የውጭ ዜጎች አጽም እንዳለ ይናገራሉ:: ከአውሮፓ፣ አሜሪካ እና ከተለያዩ የዓለም አገራት የሚመጡ እስክሬኖችም በክብር እንዲያርፍ ተብሎ በጥንቃቄ ፉካ ተሠርቶላቸዋል ይላሉ:: ገንዘብ የሌለው ሰው በዚህ ስፍራ ይቀበር ይሆን ብዬ ለአባ ገብረመስቀል ጥያቄ አቀረብኩላቸው:: አዎ ምድር የማትቀበለው ሰው የለም:: ሁሉም አንደ አቅሙና ፍላጎቱ ይቀበራል:: አቅም ያጣ የሚረዳው የሌለው ሰው ደግሞ መሬት ላይ ጉድጓድ ተምሶ በአፈር ይቀበራል ይላሉ::
በገዳሙ ካረፉ ጀግኖች መካከል
በዚያን ጫካ ውስጥ ያለው ድባብ እንኳንስ በሕይወት ላሉት ቀርቶ፤ እስከ ወዲያኛው ያሸለቡቱ በአፀደ ነፍስ ሆነው ነብሳቸው እልል የምትልበት ስፍራ ይመስላል:: በአራቱም አቅጣጫ በልምላሜ እና በሰዎች ግርግር የተሞላው ሥፍራ በጣም ደስ የሚል ነው:: በዚህ ስፍራ ጀብድ የሠሩ ሰዎች አጽም አርፏል:: በዚህ ሥፍራ በርካቶች ተቀብረዋል:: ስፍር ቁጥር የሌለው ታሪክ የሠሩ፤ ሁሌም ሥማቸው ጎልቶ የሚነሳ ታሪካቸው በደማቅ ቀለም የተጻፈ ሰዎች ስም እና አጽም ከዚህ ገዳም አንዳለ አባ ይናገራሉ:: ለአብነት የአጼ ኃይለሥላሴ አማካሪ የነበሩት ሚስተር ኩርት ሌንዝ አፅም በዚሁ ገዳም ያረፈ ነው:: የአፄ ሚኒሊክ የጦር መሪ የነበሩት ራስ ጎበና ዳጬ አጽማቸው በገዳሙ አርፏል:: በርካታ የውጭ ዜጎችም ከዚህ ስፍራ አርፈዋል:: ለአብነት ዶክተር ያንግ ሆ ቾ ከኮርያ ተወልደው ባለቤታቸው ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ብቻ በዚህ ገዳም ተቀብረዋል:: በዚህም የተነሳ የውጭ አገር ጎብኚዎች በብዛት እንደሚጎበኙት ይናገራሉ:: ታዲያ አባ ገብረመስቀል እነዚህን አጽሞች እየተመላለሱ ይጎበኟቸዋል:: ፎቷቸው እንዳይጫጫር፣ ከላይ የተፃፈው ጥቅስ እንዳይደበዝዝ ይጠነቀቁላቸዋል::
70 ሺ ለመቀበሪያ
በዚህ ስፍራ ለዘላቂ መቀበሪያ ተብሎ የሚሸጥ ፉካ ከ50 እስከ 70ሺ ብር ግምት ወጥቶለታል:: በአሠራራቸው ስፋት ያላቸው ፉካዎች እስከ 70ሺ ብር ድረስ የሚሸጡ ሲሆን፤ በመጠናቸው ጠበብ ያሉት ደግሞ ዋጋቸው ይቀንሳል:: በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ገድል የተፃፈላቸው እና የሚፃፍላቸው ጀብደኞች ታሪካቸው በጉልህ ደምቆ ተጽፎ በዚህ ሥፍራ ይቀበራሉ:: አጽማቸውም በክብር ከዚህ ስፍራ ይጠበቃል:: በአንድ ፉካ አንድ ሰው የሚቀበር ሲሆን፤ እስከ ሰባት ዓመት ሌላ ሰው አይቀበረበትም ይላሉ አባ ገብረመስቀል:: ይህንንም በሚገባ እንደሚቆጣጠሩትና የሟች ቤተሰቦችም እንደሚከታተሉት ይናገራሉ:: ይሁንና ከሰባት ዓመት ቆይታ በኋላ የቆዩ አጽሞች በአቦጀዴ ጨርቅ ይደረግና እዚያው ይቀመጣል:: በሳጥኑ ደግሞ ሌላ ሰው ይቀበርበታል:: በዚህ ሂደት በአንድ ፉካ ውስጥ በየሰባት ዓመቱ እየተቀያየረ በርካታ ሰዎች ይቀበሩበታል::
ሞት ጠባቂዎች
ዝንጀሮ ‹‹ቅድሚያ ለመቀመጫዬ›› ያለችው ብሂል በሰዎችም ይገለፃል:: በህይወት ሳሉ ስለሞታቸው የሚያስቡ ሰዎችም ይታያሉ:: ቀድሞውኑ ሞትን ተሸክመን ነው የተፈጠርነው ብለው ከመሞታው በፊት የመቀበሪያ ስፍራቸውን የሚያዘጋጁ ሰዎችም አሉ:: ቀድመው የመቀበሪያ ሥፍራ ገዝተው በሚፈልጉት ስፋትና ቁመት አዘጋጅተው ሞትን የሚጠባበቁ በርካቶች እንደሆኑ ነው አባ የሚናገሩት::
እነዚህ ሰዎች የመቀበሪያ ስፍራቸውን በሚገባ አሠርተው ክፍያም ፈፅመው እንኳንስ በህይወት ሳሉ ሞተውም ሰዎችን ላለማስቸገር የተዘጋጁ ሰዎች እንደሆኑ ይናገራሉ:: እነዚህ ሰዎች የማይፈቀድላቸው ነገር ቢኖር ከመቀበራቸው በፊት በመቃብር ቦታቸው ላይ ፎቷቸውን ማስመቀጥ ወይንም ደግሞ ‹‹ሞቻለሁ›› ብለው ጥቅስ ማፃፍ አይችሉም:: ከዚህ ውጭ ግን በጥንቃቄ ስለመያዙ፣ ዝናብ፣ ፀሐይና ሌላ ባዕድ አካል ጉዳት እንዳያደርስበት የማየትና በሥርዓት እንዲያዝላቸው የመቃብር ስፍራ አስተዳዳሪዎችን የመጠየቅ መብት አላቸው::
ሰዎች ምን ይላሉ?
ለመሆኑ እነዚህን ውብ የመቃብር ስፍራዎችን ሲመለከቱ ሰዎች ምን ይላሉ? የሚል ጥያቄ ለአባ አቀረብኩላቸው:: ሰውማ ምን ይላል፤ እጁን ከአፉ ላይ ጭኖ ወቸ ጉድ! እያለ ይገረማል አሉኝ:: በተለይም ደግሞ በዚህ ደረጃ ለሰዎች የመቃብር ሥፍራ ዋጋው ንሮ ሲመለከቱ ይገርማቸዋል:: አንዳንዶች ግን ነገ የት እንቀበራለን ሲሉ ይሠጋሉ፤ ይጠይቃሉ:: ከምንም በላይ ግን መሬት ሀብታም ድሃም ሳትል መቀበልን መዘንጋታቸው ነው ይላሉ:: ስለሆነም ሰዎች ስለመቀበሪያቸው ሳይሆን እስከ ዕለት ሞታቸው ድረስ የሚሠሩት ሥራ ብቻ ሊያስጨንቃቸው ይገባል ሲሉ ይመክራሉ:: በተለይም ደግሞ ሰው በምድር ላይ ሲኖር ሞት እንዳለ አውቆ ከሞቱ መንደር በጥሩ ስም እንዲጠራ ከመቃብሩ በላይ ከፍ ብሎ ለመንገሥ ስም ሳይሆን መልካም ሥራ ይቀድማል ሲሉ ይመክራሉ:: በመሆኑም ሰው ሞትን ተሸክሞ የሚሄድ በመሆኑ ስለሞቱ ብቻ ሳይሆን ከሞት በኋላ ስላለው መልካም ስም ቢጨነቅ ይበጃል ሲሉ ይመክራሉ::
የአባ ጭንቀት
አባ ገብረመስቀል አበበ ስለ ሥጋዊ ነገር ሳይሆን የሚያስቡት ስለ ዘላለማዊ ሕይወታቸው ነው:: ግን ከምንም በላይ የሚያስጨንቃቸው ነገር ግን አንድ እና አንድ ነው:: በገዳሙ እስከወዲያኛው ያሸለቡ ሰዎች ምቾታቸው እንዳይነካ ይጸልያሉ:: ለአገራቸው ክብር የተዋደቁ ጀግኖች ክብራቸውን የሚያሳንስ ተግባር እንዳይፈጸም ይተጋሉ:: አስፈላጊውን ጥበቃና ከለላ ሁሉ ያደርጋሉ:: በተለይም ደግሞ እነዚህ ሰዎች የተቀበሩበት ‹‹ፉካ›› ዝናብ እንዳይነካው፤ ወጨፎ እና ፀሐይ እንዳያርፍበት፣ ብርድ እንዳይፈራረቅበት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ::
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርበር