ከጨዋታው መጀመር በፊት በርካታ ኹነቶች ተካሂደዋል፡፡ የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የበላይ አመራሮች ተገኝተዋል። ደጋፊዎችም ጨዋታው በሰላም እንዲጠናቀቅ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ላይ፡፡
በተለይ ደግሞ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተወከሉ 21 እናቶች ፊት የሁለቱ ክለብ የበላይ አመራር የሆኑት አቶ አብነት ገብረመስቀልና መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እርቀ ሰላም አውርደው በአንድ ላይ ተቃቅፈው የታዩበት ክስተት ትኩረት የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል፡፡ ሰላም በራቃቸው የስፖርት ማዘውተሪያዎች ላይ ተመሳሳይ ክንውን መንጸባረቅ እንደሚኖርበት በስፖርት ቤተሰቡ የተሰነዘረ ሀሳብ ነው።
በአዲስ አበባ ስታዲየም የታየውን ተግባር እንደ አማራና ትግራይ ክልል በሚገኙ ክለቦች መካከል ያለውን መፋጠጥ የሚያረግብ ስራ መስራት ይጠይቃል። ስፖርታዊ ጨዋነት ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት እየተራዘመ የሚገኘውን መደበኛው መርሀ ግብርን ጠብቆ እንዲሄድ ከክልል ክለቦች ጋር በጥብቅ መሥራት እንደሚያስፈልግ ከስፖርት ቤተሰቡ እየተነገረ ነው።
ቡና እና ቅዱስጊዮርጊስ ደጋፊዎች መካከል የታየው የአንድነት ፍቅር፣ ስፖርታዊ ሥነ ምግባር ወደ ክልል ክለቦችም መጋባት ይኖርበታል። በውድድሩ ላይ መተማመኛ ለመፍጠር የሰላም እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮች በስታዲየም በመገኘት ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ ነው።
በዚህ መልኩ የተከናወነው የሸገር ደርቢ ያለምንም ግብ ተጠናቋል። የአዲስ አበባን ሁለቱ ዝነኛ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።
የዘንድሮው የሊግ አጀማመሩ የተቀዛቀዘ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማው ሽንፈት እና ከሁለት ግብ አልባ ጨዋታዎች በኋላ በተስተካካይ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን መርታት ችሏል። በተመሳሳይ መልኩ ውጤት ርቆት የሰነበተው ኢትዮጵያ ቡናም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ባገኛቸው ድሎች ወደ መጀመሪያው መልካም አጀማመሩ የተመለሰ መስሏል።
ሁሌም ቢሆን ትኩረትን የሚስበው የሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ አጋማሽ ካሳኩት ድል በኋላ ነበር የተገናኙት። የአብዛኛውን የእግር ኳስ ቤተሰብ ቀልብ ስቦ የነበረውና ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል የሚል ግምት ነበር። ይሁንና የሸገር ደርቢ የተጠበቀውን ያህል አልነበረም። የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ማራኪነት የጎደለው እንቅስቃሴ ታይቶበታል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ያለግብ መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሪ መሆን ችሏል፡፡
የሸገርን ደርቢ ለመመልከት በሺዎች አዲስ አበባ ስታዲየም ማልደው የሚገኙበት ጨዋታ መሆኑ ይታወቃል። ሁለቱ ቡድኖች ከ1991 የውድድር ዓመት ጀምሮ 38 ጊዜ የተገናኙት ሲሆን፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በ14 አጋጣሚዎች ደግሞ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።73 ግቦች በተስተናገዱባቸው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 49 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 24 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን በአራት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ ሲሆን፣ በሦስቱ ደግሞ ያለግብ ከሜዳ ወጥቷል። በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ የቀሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ካስመዘገቧቸው ሰባት ግቦች ውስጥ ስድስቱን በሁለተኛው አጋማሽ የተቆጠሩ እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
ዳንኤል ዘነበ