አዲስ አበባ:- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማትን በመጪው ማክሰኞ ኖርዌይ ኦስሎ ከተማ በመገኘት እንደሚቀበሉ የሽልማት ኮሚቴው አስታወቀ።
በኖርዌይ የሚገኘው የኖቤል ኮሚቴ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ መሆናቸውን መስከረም 30 ቀን በ2012 ዓ.ም ማሳወቁ ይታወሳል። አሸናፊነታቸውንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሽልማቱን ለመቀበል የፊታችን ማክሰኞ ወደ ኦስሎ እንደሚያመሩ ታውቋል።
በሽልማቱ ዕለትም በኦስሎ ከተማ የስብሰባ አዳራሽ በመገኘት ማብራሪያ እንደሚሰጡ ከሽልማት ኮሚቴው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በኖርዌይ ቆይታቸው ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልቤርግ እና ከኖርዌይ ንጉስ ሐራልድ አምስተኛ ጋር ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን የሀገሪቱን ፓርላማም እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
በሽልማቱ ዕለት ግን ዶክተር ዐብይ ከጋዜጠኞች ለሚቀርብ ጥያቄ ምላሽ እንደማይሰጡ ስለመገለጹ የሽልማት ኮሚቴው አስታውሶ፤ በመድረኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለምልልስ እንዲያደርጉ የኮሚቴው ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል። ሃሳባቸውን ለሬውተርስ የመገናኛ ብዙኃን የሰጡት የኖቤል ኮሚቴ ጸሃፊ ኦላቭ ጆኤልስታድ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ እና ገለልተኛ ሚዲያዎች የሰላም ሽልማቱ አንዱ አካል ናቸው ብለው እንደሚያምኑ እና ከጋዜጠኞች ጋር ጥያቄና መልስ እንዲያካሂዱ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የኖቤል ሰላም ተሸላሚ የነበሩት የቀደሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እ.አ.አ. በ2009 በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ያልተገኙ ተሸላሚ መሆናቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የነበረውን ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀ ቅራኔ ወደ ሠላም በመመለስ፣ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባትና በሱዳንና ደቡብ ሱዳን የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ ባደረጓቸው ጥረቶችና ባስመዘገቧቸው ስኬቶች ለኖቤል ሽልማቱ አሸናፊ ካደረጓቸው ስራዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው። ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻክሮ የነበረው የጅቡቲና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካከል የነበራቸው ሚና ተመራጭ አድርጓቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሸናፊ በሆኑበት 100ኛው የኦስሎ የሠላም የኖቤል ሽልማት ከወርቅ የተሰራ ሜዳሊያ እና ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደሚበረከትላቸው ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር