በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለሚ ከሚባለው አካበቢ ማልደን ተነስተን ወደ መርሐቤቴ እየተጓዝን ነው። ከአካባቢው ብዙ ሳንርቅም የጠዋቱ ብርድ ያልበገራቸው ጥቂት ሰዎች ‹‹በቃሬዛ›› የታመመ ሰው ተሸክመው ለተሽከርካሪ አመቺ ባልሆነው መንገድ በእግራቸው ሲኳትኑ ተመለከትን። የሰዎቹ ሁኔታ ታዲያ የአካበቢውን ህዝብ ምን ያህል በተሽከርካሪ እጥረትና መንገድ እጦት እየተንገላታ እንደሚኖር አስገነዘበን። ተገንዝበን ብቻ አልቀረንም፤ ጠጋ ብለን ስለሁኔታው እንዲያስረዱን ጠየቅናቸው።
አቶ ክብሩ ይስፋ ጓደኞቻቸው ዳሎታ ከሚባለው ቆላማ ሥፍራ የታመመ ሰው ተሸክመው ወደ ለሚ ከተማ ለህክምና እየመጡ መሆኑን አጫወቱን። እንደእርሳቸው ገለጻ፤ በአካባቢው የተሽከርካሪ እና የመንገድ እጦት ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ፤ ከደጋው ማህበረሰብ ጋር ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር፣ ህክምና ለመሄድ እና ምርቶቻችን በጥሩ ዋጋ ለመሸጥ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
«ከቆላው ደጋማ አካባቢ ለመድረስ ከሁለት ሠዓት በላይ ተጉዘናል። ታዲያ የመኪና መንገድ አለመኖርና ተሽከርካሪ ወደ አካባቢው አለመግባቱ ማህበራዊ ሕይወታችንን በከፍተኛ ደረጃ አዛብቶታል» በማለት የተናገሩት ደግሞ አቶ ጠለሎ ተስፋም የተባሉት ግለሰብ ናቸው። የመንገድ እና ተያያዥ መሰረተ ልማት አለመሟላት አካባቢው ለዘመናት ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን አድጎታል የሚል እምነት አላቸው።
እንደነዋሪዎቹ ማብራሪያ፤ የዚህ መንገድ ግንባታ እንዲከናወን ከአርባ ዓመታት በላይ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል። ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ጥያቄው ሰሚ አግኝቶ የኦሮሚያ እና አማራ ክልል የሚገኙትን ሁለቱን ሰሜን ሸዋ ዞኖችን የሚያስተሳስረው የሙከጡሪ- ለሚ-ዓለም ከተማ መንገድ ግንባታ ቢጀመርም የነዋሪዎቹ ቅሬታ አሁንም ቀጥሏል።
አበራ ተሾመ ለሚ አካባቢ መገንጠያ በሚባል ሥፍራ የሚኖር ወጣት ሲሆን፤ በንግድ ሥራ ይተዳደራል። ታዲያ የመንገድ ግንባታው የወፍጮ ቤት እና የንግድ ሱቆቹን ብሎም በርካታ ዛፎችን ስለሚነካት 400 ሺ ብር ተገምቶለታል። እርሱ ግን በዚህ ደስተኛ ባለመሆኑ ካሳውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም።
በአርሱ እይታ ዓመታዊ ገቢ 300 ሺ ብር ነው በሚል ለመንግሥት ግብር ሲከፍል ቆይቷል። ይህንንም ወረዳውም ሆነ በቅርበት ጉዳዩን የሚረዱ አካላት ያውቁታል። ታዲያ ይህ ሆኖ ሳለ በካሣ ግምት የተነሳ ገቢዬ ለምን ከዚህ ያንሳል የሚል አመክንዮ አንስቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ ዕሮብ ገበያ አካባቢ ነዋሪ የሆነው አርሶ አደር ደረጀ ካስዬ ደግሞ ካሳ ይሰጣል የተባለውን 20 ሺ ብር ሲጠብቅ በጋው አልፎ ክረምቱ ቢያልፍም የመንገድ ግንባታው ፋይዳ ከካሳው በላይ ዋጋ አለው ሲል ይናገራል። «ካሣውን ለመቀበል ተስማምቼ ከዛሬ ነገ ይሰጣል ሲባል ነበር። ግን ይህ አልሆነም» ይላል። ጎረቤቶቹ የካሳ ግምት ወስደው እርሱ ዛሬም መጠባበቁ አልተዋጠለትም። በዚህ ሁኔታ የመልካም አስተዳደር ችግር ከመፈጠሩም በላይ የመንግሥትን አሠራር ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት መሆኑን ይገልጻል።
እንሳሮ ወረዳ ኮኮብ መስክ ነዋሪ የሆነው አቶ ገለታው በለጠ በበኩሉ፤ መንገዱ በሚሠራበት አካበቢ ሦስት የሚከራዩ ክፍሎችና ዳቦ ቤት አለው። ከክፍሎቹና ከዳቦ ቤቱ የሚያገኘውም ገቢ እርሱን ጨምሮ አራት ቤተሰቦቹን ያስተዳድራል። ይሁንና ከመንገድ ግንባታው ጋር ተያይዞ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆኑት እነዚህ ሶቆቹ እንደሚፈርሱበት ተነግሮታል። በተለይ ደግሞ የተገመተለት የካሳ ክፍያ የቤቱ ግንባታ ላይ ያወጣውን ወጪ እንኳ የማይሸፍን መሆኑን ተጨማሪ ኀዘን ፈጥሮበታል። የካሳ ግምቱ እንዲሻሻልለት
በተደጋገሚ ቢጠይቅም እስከአሁን ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ይገልጻል።
የውጫሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደዮሐንስ አበራ እንደሚሉት፤ ይህ የመንገድ ግንባታ አማራ እና ኦሮሚያ ክልልን የሚያስተሳስር ሲሆን በአካባቢው ከፍተኛ የሆኑ ማዕድናትና የእንስሳት ሀብት ስላለ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ዕድል ይፈጥራል። በመሆኑም ለግንባታው መፋጠን ወረዳው አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ነው።
ከካሳ ጋር ለሚነሳ ቅሬታም ገማች ኮሚቴው ከወረዳ እና ቀበሌ መሬት አስተዳደር እንዲሁም ክልሉና የፌዴራል መንግሥት ያስቀመጡት አሠራር በመከተል በባለሙያ የሚከናወን መሆኑን ያስረዳሉ። ግምቶቹ በሳይንሳዊ ዘዴ በመሃንዲሶች የሚሠሩ እንጂ ግለሰቦች እንደፈለጉት የሚያደርጉት አለመሆኑንም ይገልጻሉ።
ሆኖም አንዳንድ የዘገዩ የካሳ ክፍያ ጉዳዮች መኖራቸው ከህረተሰቡ ዘንድ ብዥታ መፍጠሩንና ይህም ግንዛቤ በሚገባ ባለመፈጠሩ የተከሰተ መሆኑን ይናገራሉ። ቅሬታ ካላቸውም ማስተካከል ግዴታችን ነው ይላሉ።
የእንሳሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደምሰው መንበሩ በበኩላቸው፤ ሙከጡሪ፣ ለሚ፣ ዓለም ከተማ መንገድ ግንባታ ጥያቄ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ አስፋልት እንዲያድግ መደረጉ ለህዝቡ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ያስገኘ መሆኑን ያስገነዝባሉ። ከከሳ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠትም ከቅሬታ ሰሚ በተጨማሪም ችግሩን በሚገባ እንዲከታተሉ ተጨማሪ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅሰው ለቅሬታው በአጭር ጊዜ እልባት እንደሚሰጠው ይጠቁማሉ።
የፌዴራል ሆነ የክልሉ መንግሥት በቂ ባለሙያዎችን መመደቡንና በዚያውም ልክ ተገቢው ካሳ እንዲሰጥ አቅጣጫ መቀመጡን ይናገራሉ። ‹‹በማናቸው መመዘኛ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ አሠራር እንጂ ለግለሰብ ፍላጎት የምንሠራው ሥራ የለም። የከተማዋንም ሆነ የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚቀይር ሥራ ላይ እናተኩራለን። በካሳ ቅሬታ ልማት እንዲደናቀፍ ዕድል አንሰጥም ችግር ቢኖር እንኳን በውይይትና በመተማመን እንፈታለን›› ይላሉ።
የመርሐቤቴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ አስፋው በበኩላቸው፤ ሙከጡሪ- ለሚ- ዓለም ከተማ መንገድ ግንባታ የዘመናት ጥያቄ ሲሆን በእንዚህ ጥያቄዎች እንዲጓተት አንፈቅድም ይላሉ። ከካሳ ጋር የሚነሳው ጉዳይም በዋናነት የአርሶ አደሩ ወይንም የከተማው ነዋሪ ሥራ ሳይሆን የእኛ ዋንኛ አጀንዳ ነው ይላሉ።
ነዋሪው የማይስማማበት ሥራ ማከናወን አግባብ ባለመሆኑ ከላይ እስከታች በመናበብ የምንሠራ ሲሆን ቅሬታዎችን በአጭር ጊዜ እንፈታለን ባይ ናቸው። በፌዴራሉም ሆነ በክልሉ መንግሥት የሚያሠራ አቅጣጫና አመቺ ሁኔታ መዘርጋቱንም ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር