ቡራዩ፡- ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት ለሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በድምቀትና በሰላም መጠናቀቅ የቡራዩ ከተማ ድርሻ ወስዶ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ። እንግዶችን ተቀብሎ ከማስተናገድ ጀምሮ እስከበዓሉ ፍጻሜ የሚያግዙ ከ100 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በከተማ አስተዳደሩ መዘጋጀታቸውም ተጠ ቁሟል።
የቡራዩ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ቃበቶ አልቤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በፊንፊኔ ለሚካሄደው 14ኛው የብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል መሳካት እንደ ክልል እቅድ የወጣ ሲሆን፤ ይሄው እቅድ በከተማ አስተዳደሮች፣ ለዞንና ወረዳ ምክር ቤቶች ወርዶ ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን
እንዲወጡ ተደርጓል። ቡራዩ ከተማ አስተዳደርም በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ ቅርብ ከሆኑ ከተሞች አንዱ እንደመሆኑ ከክልሉ ጋር በጋራ በመሆኑ ለበዓሉ መሳካት እየሠራ ይገኛል።
አቶ ቃበቶ እንደሚናገሩት፤ በህብረተሰቡ ውስጥ ድርሻ አለው የሚባለው የወጣት ክፍልም ለበዓሉ ሰላማዊ መሆንና ድምቀት የማይተካ ሚናውን ሊወጣ የሚችልበት አሠራር የተፈጠረ ሲሆን፤ በዚህም ወጣቱ ከህብረተሰቡ ጋር ከሚወጣው ድርሻ ባለፈ እንደ ከተማ አስተዳደር ከ100 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማደራጀት እስከ በዓሉ ፍጻሜ የሚሠሩበት አግባብ ተፈጥሯል።
በዚህም የሚመጡ እንግዶችን ከህብረተሰቡ ጋር አቀባበል ከማድረግ ጀምሮ፣ ወደተዘጋጀላቸው ስፍራ ከማድረስና ባረፉበትም አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እስከማድረግ የሚዘልቅ ተግባርን ያከናውናሉ። ለምሳሌ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ በከተማዋ ከሚደረግላቸው አቀባበል ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ የእነዚህ ወጣቶች ድጋፍና እገዛ የማይለያቸው ይሆናል።
‹‹እንግዳ የሚመጣው ወደቤታችን፤ የኦሮሚያ እንብርት ወደሆነችው ፊንፊኔ ነው፤›› የሚሉት አቶ ቃበቶ፤ የኦሮሞ ህዝብ ባለው የገዳ ስርዓት እንግዶቹን ተቀብሎ ማስተናገድ፣ እንግዳ ተቀባይነትና አሳታፊነቱን በተግባር መግለጽ እንዳለበት ተናግረዋል።
በኖረ እሴቱ መሰረት እንግዶቹን በመስተንግዶው አስደስቶ በሰላም ወደቤታቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል። ከተማው ውስጥ የሚኖረው የአዲስ አበባ ህዝብም እንግዶቹ ወደቤታቸው የሚመጡ መሆኑን አውቀው መገለጫቸው በሆነው እንግዳ ተቀባይነት ከኦሮሞ ወንድሞቻቸው ጋር ሆነው ለበዓሉ ድምቀትና ስኬት የድርሻቸውን እንዲወጡ፤ ለሰላማዊነቱም የማይተካ ሚናቸውን እንዲያበረክቱ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2012
ወንድወሰን ሽመልስ