የኢትዮጵያ ክለቦች አጭር፣ መካከለኛ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት ዓመታዊ ሻምፒዮና በመከላከያ ክለብ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠና ቀቀ። የመከላከያ ክለብ በሁለቱም ፆታዎች እና ለአጠቃላይ አሸናፊነት የተዘጋጁትን ሦስቱንም ዋንጫዎች ወስዷል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም ለተከታታይ ስድስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ፍጻሜውን ባገኘው በዚህ ሻምፒዮና ማጠናቀቂያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ላይ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ በመገኘት ለአሸናፊዎች የሜዳልያና የዋንጫ ሽልማት ሰጥታለች። ከፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መካከልም ዶ/ር በዛብህ ወልዴ፣ አቶ ፈሪድ መሃመድ እንዲሁም የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
በዚህ ዓመታዊ ሻምፒዮና መከላከያ በሴቶች 152 ነጥብ 5 ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፣ በወንዶች በተመሳሳይ 165 ነጥብ 5 በማስቆጠር በሁለቱም ጾታዎች የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል።
መከላከያን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ሲዳማ ቡና ሆኗል። ሲዳማ ቡና በሴቶች 134 ነጥብ ሲያስመዘግብ በወንዶች ደግሞ 128 ነጥብ በመሰብሰብ ውድድሩን አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሻምፒዮናው ጥሩ ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች አንዱ የነበረ ሲሆን፣ ውድድሩን ግን ያጠናቀቀው ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ነው፡፡ ንግድ ባንክ በሴቶች 107 ነጥብ የሰበሰበ ሲሆን በወንዶች ደግሞ 74 ነጥብ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ መካተት ችሏል።
በሻምፒዮናው በሁለቱም ጾታዎች የተመዘገበው አጠቃላይ ድምር ውጤት ታይቶም የአሸናፊዎች አሸናፊው ተለይቷል። በዚህም መከላከያ በ318 አንደኛ በመሆን የዘንድሮውን ውድድር ሻምፒዮና በመሆን አጠናቋል። ክለቡ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ሻምፒዮና የነበረ ሲሆን፤ በ459 አንደኛ በመውጣት የዋንጫ አሸናፊ ነበር። በዘንድሮው የውድድር ዓመትም ተመሳሳይ የድል ባለቤት በመሆን ማጠናቀቅ ችሏል። ክለቡ አጭር፣ መካከለኛ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት እያስመዘገበ ያለው ውጤት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን በሚገባ ያስመሰከረ ተብሎለታል።
በዓመታዊ ሻምፒዮናው በነጥብ ድምር በሁለተኛ ደረጃ 262 አጠቃላይ ነጥብ መሰብሰብ የቻለው ሲዳማ ቡና ሆኗል። ከዚህ በፊት በነበረው የውድድር ዓመት ብዙም ውጤታማ ያልነበረው ክለቡ ፣ በዘንድሮው ውድድር ራሱን በሚገባ አጠናክሮ በመቅረብ ውጤታማ መሆን እንደቻለም ተነግሯል።
በዓመታዊው ውድድሩ ጥሩ ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ181 አጠቃላይ ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። አምና በነበረው ውድድር ላይ በ121 ነጥብ ሁለተኛ በመሆን ማጠናቀቃቸውም ይታወሳል።
ዓመታዊው ሻምፒዮና ለአጭር፣ መካከለኛ፣ የሜዳ ተግባራትና የርምጃ ተወዳዳሪ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር፤ በክለቦች መካከል የውድድር ዕድል ለመፍጠር፤ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትን ዓላማ ያደረገ ነው። ለአሸናፊዎቹም በየደረጃው የተዘጋጀ የገንዘብ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፤ በግል አንደኛ ለወጣ 2000፣ ሁለተኛ ለወጣ 1500 እና ሦስተኛ ለወጣ 1000 ብር ሽልማት የሚበረከትላቸው ሲሆን፣ በቡድን 4 በ 400 ድብልቅ፣ 4 በ 800፣ 4 በ 1500 ሜትር እንዲሁም 4 በ 100 ሜትር ከብር 5000 እስከ 2000 የገንዘብ ሽልማት እንደየደረጃቸው ተበርክቶላቸዋል፡፡
በውድድሩም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ 25 ክለቦች የተውጣጡ 706 አትሌቶች በሻምፒዮናው ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ለተወዳዳሪዎች በድምሩ ከ200 ሺ ብር በላይ ሽልማት ተዘጋጅቷል። የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተጀመረው ታህሳስ 16 እስከ ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ተጠናቅቋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
ዳንኤል ዘነበ