አዲስ አበባ፡- ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በፅኑ እንዲጠበቅና የፌዴራል ሥርዓቱ በተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥል ትኩረት የሚሰጥበት ወቅት ይሆናል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ገለጹ።
ወ/ሮ ሎሚ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በዓሉ የአገሪቱ ታሪክ የሚጎላበት ብሎም የብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ሳይሸራረፍ የሚንፀባረቅበት መሆኑን አብራርተዋል። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትም በፅኑ እንዲጠበቅና የፌዴራል ሥርዓቱ በተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥል ትኩረት የሚሰጥበት ወቅት ይሆናል ብለዋል።
ለ14ተኛ ጊዜ ለሚከበረው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን 52 ሚሊዮን ብር የተበጀተ ሲሆን፤ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 40ሺ ዜጎች እንደሚሳተፉ አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሎሚ በዶ አክለው እንደገለጹት፤ ለ14ተኛ ጊዜ ለሚከበረው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል 52 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። በዚህም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ እና ባህላቸውን የሚወክሉ ከ35 እስከ 40ሺ የሚደርሱ ዜጎች ይሳተፋሉ።
በበዓሉ ወቅት የተለያዩ ባህላዊ እሴቶችን የተላበሱ ትርዒቶችና ሙዚቃዎች እንደሚቀርቡ አስገንዝበዋል። ለበዓሉ መርሐ ግብር የተለያዩ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን መንግሥት 49 ሚሊዮን ብር መድቧል። በተጨማሪም ሌሎች አካላት የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን፤ በድምሩ 52 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
እንደ አፈ ጉባኤዋ ገለጻ፤ የተለያዩ አካላት ቀደም ሲል የበዓሉን ድምቀት ለማጉላት ሲባል ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው እንደ መሶብ፣ ጀበና እና የመሳሰሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት ግን ከዚህ በተለየ ሁኔታ መታሰቡን ጠቁመዋል። ይህ አሠራር የተለመደና ተደጋጋሚ በመሆኑም ለየት ባለ ሁኔታ በዓሉን ለማድመቅ መታቀዱን ተናግረዋል።
እንደ ወይዘሮ ሎሚ ከሆነ፤ የበዓሉን ድምቀት ለማጉላት ሲባልም የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ማንነትና የኢትዮጵያን ታሪክ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የመፅሐፍ ገለጻ እንደሚኖር አስገንዝበዋል። ከዚህም በተጨማሪ 1ሺ 600 ሕፃናት የሚያቀርቡት ትዕይንተ ህዝብ መኖሩን ገልጸዋል።
በዓሉ በሠላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የክልሉ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር መፈ ጠሩን ብሎም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል።
የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል አከባበር በ1998 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን፤ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን ይከበራል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር