የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የሚመራ የሊግ ኮሚቴ እንደሚቋቋም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ለዚህ የሚሆን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ጥር 7 ሁሉም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አንድ ሰው መርጠው በመላክ 16 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የሊግ ኩባንያ (PLC) ለመመስረት የመሰረት ድንጋይ እንደሚጣል የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ አመልክቷል።
ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ክለቦች ራሳቸው ባቋቋሙት የሊግ አስተዳደር መመራት አለባቸው በሚል ለማዋቀር ቢታሰብም በክለቦች መካከል መተማመን በመጥፋቱ ሀሳቡ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወቃል። በ2010ዓ.ም ወደ ሥልጣን የመጡት የፌዴሬሽኑ አመራሮችም ክለቦች የራሳቸውን ውድድሮች ራሳቸው መምራት አለባቸው የሚል አቋም ወስደዋል። በዚህም የ2011ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት ላይ አደረጃጀቱን እንዲያስፈፅሙ፤ አቶ ሰላሙ በቀለ፤ አቶ አስጨናቂ ለማ እና አቶ ሸረፋ ዴሌቾ መመረጣቸው ይታወቃል።
ለወራት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየው ኮሚቴውም በቅርቡ ተጨባጭ በሆነ መልኩ ወደ ተግባር ሊገባ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም መግለጻቸውን ዘገባው ይጠቁማል።
ኮሎኔል አወል «የሊጉ ባለቤት የሆኑት ክለቦች ሊጉን ሊመሩ ይገባል። ሌላ ሞግዚት አካል መኖር የለበትም። ኮሚቴ ብሎ ዘመናዊ እግርኳስን መጠበቅ አይቻልም። በትርፍ ጊዜ በሰዎች ፍላጎት ላይ ተገድቦ የሚሠራ ሥራ አያዋጣም» ብለዋል።
ሊጉ ውድድሮችን ከመምራት ባለፈ የተሻሉ ትልልቅ ሀሳቦች የሚተገበሩበት ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚስብ ውድድር መሆን እንዳለበትም ኮሎኔል አወል ገልጸዋል።
የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዳሉት፤ በፌዴሬሽኑ በኩልም ሊጉ በክለቦች እንዲመራ ፅኑ አቋም አለ፤ ለዚህ የሚሆን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችም ተጠናቀዋል። በዚህም መሰረት በመጪው ጥር ወር የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች 16 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የሊግ ኩባንያ (PLC) ለመመስረት የመሰረት ድንጋይ የሚጣልበት ቀን ይሆናል። ለእግር ኳሱ እድገት ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ፌዴሬሽኑ ቆርጦ እንደገባበትም ነው።
ሊጉ በአዲስ አካሄድ መከናወን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የውይይት እና ክርክር አጀንዳ ሆኖ የቆየውና ክለቦች ሊጉን አቋርጠው እስከመውጣት የደረሱበት ራሱን የቻለ የሊግ አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት ይቋቋማል ተብሎ ሲነገር ቢቆይም ክለቦች ሳይስማሙ በልዩነት እየወጡ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
ብርሃን ፈይሳ