ከሰማኒያ ሁለት ዓመታት በኋላ እርጅና ጓዙን ሰብስቦ ለብዙዎች እናት፤ ቤተሰብ ላጡት ማረፊያ ወደሆኑት እናት ቤት ከገባ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። ከሰፊውና የበርካታ ሥራዎች መናኸሪያ ከሆነው ግቢ ውስጥ አንዲት ሰፋ ያለች ክፍል የሙሉ ቤት አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች። የክፍሉ ዙሪያ ገባ በሕፃናት ማደሪያ የጥናት ቤት፤ መመገቢያ ክፍሎችና የሕፃናት መንከባከቢያ የተከበበ ሲሆን ከፎቁ ላይ ደግሞ የማዕከሉ ቢሮዎች በሥራ ላይ ናቸው። ወደ ክፍሉ ሲገቡ ቀጥታ እንደ እንግዳ መቀበያ (ሳሎን) ቤት ሶፋ ቴሌቪዥን፤ ወንበርና ጠረጴዛ ከነወንበሩ ያገኛሉ። ዓይንዎን ወደ ቀኝ ሲያማትሩ ደግሞ እንደ መኝታ ቤት ሰፊና የሚያምር አልጋ ይታዮታል፤ በስተቀኝም ሙሉ የማእድ ቤት ዕቃ የያዘ ቡፌ በግራና በቀኝ በባህላዊ ጥልፍ ባሸበረቁ መሶቦች ታጅቦ ተቀምጧል።
በዛች ትንሽ ግቢ በምትመስል ክፍል መግቢያ በር ደግሞ የብዙሃን እናት፤ አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ፤ የእጓለማውታ መሸሸጊያ በሚልና በሌሎች የፍቅር ስሞች የሚጠሩት የክብር ዶክተር አበበች ጎበና በሀገር ባህል ልብስ ተሞሽረው ወንበር ላይ ተቀምጠዋል። የክብር ዶ/ር አበበች እየተጫናቸው የመጣው እርጅና የማስታወስ ችሎታቸውን ቀንሶ ንግግራቸውን ያዝ እያደረገ አካላዊ ለውጥ ቢፈጥርባቸውም ለዘመናት የዘለቀውን ርህርሄ የተሞላው የእናትነትነት ፈገግታቸውን ግን ሊነጥቃቸው አልቻለም።
የክብር ዶ/ር አበበች ካለ ስጋ ልጅ ለሺዎች እናት ለመሆን በቅተዋል። የብዙዎች ቤተሰብ ያጣውን ደስታ በእሳቸው አግኝቷል። ብዙዎችን ከፈረሰ ቤተሰብ አወጥተው የራሳቸውን ቤተሰብ ለመመስረት እንዲበቁም አድርገዋል። ለመፈጸም ሳይሆን ለማሰብ የሚከብደውን ትልቅና ሰፊ ቤተሰብ ለዓመታት ተሸክመው ኖረዋል። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ያሳደጓቸው ልጆች በአንድ ቃል “እዳዬ” እያሉ ይጠሯቸዋል። እዳዬ የሚለው ስም የልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችም የሚጠሯቸው ሁለተኛ ስማቸው ነው።
የክብር ዶ/ር አበበች ጎበና ጥቅምት አስር ቀን 1928 ዓ.ም ነበር ከአባታቸው ከአቶ ጎፌ ሄዩ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ወሰኔ ብሩ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ ሸበል በምትባል መንደር ይህችን ምድር የተቀላቀሉት። ዓመት ሳይሞላቸው ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረሯን ተከትሎ በነበረው ጦርነት ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ወላጅ አባታቸውን አጥተዋል። እዳዪ አስራ አንድ ዓመት ሲሆናቸው በቤተሰብ ግፊት ወደ ትዳር ለመግባት ተገደዱ። እንደ ሴት ልጅ መከራን መጋፈጥ የጀመሩትም ከዚን ጊዜ ጀምሮ ነበር። በወቅቱ በትዳር መኖርን አምኖ መቀበል ስላልሆነላቸውና ያሰቡትን ለመፈጸም ሲሉ ከትዳራቸው አምልጠው ወደ እናታቸው አቅንተው ነበር። ግና እናታቸው “እንዴት ታዋርጅናለሽ” ብለው መልሰው ለባላቸው ይሰጧቸዋል። ባላቸውም ሥራቸውን በማየት ደግማ እንዳትሞክረው በማለት በር ዘግተው ጠባቂ አስቀምጠው ከእስር ባልተናበነሰ ሁኔታ ከቤት ያቆዩዋቸዋል።
ነገር ግን የሸፈተን ልብ ምንም አይመልሰው ሆነና ነገሩ አበበች በውድቅት ሌሊት የደሳሳዋን ጎጆ የሳር ጣራ የማምለጫ ቀዳዳ አድርገው ለመጠቀም አስበው ጊዜ እየመረጡ ይሰነብታሉ። አንድ ቀን ያሰቡት ሁሉ ይሳካና በውድቅት ሌሊት የደሳሳዋን ጎጆ የሳር ጣራ ፈልቅቀው ያመልጣሉ። ወዴት? እማ ዘንድ ? እንደሚሄዱ ግን አያውቁም ለሳቸው ዋናው ነገር ካሉበት የቁም እስር ማምለጥ ብቻ ነበር። እናም ሦስት ቀን እየተደበቁና መንገድ ዳር እያደሩ በእግራቸው ይጓዛሉ። በመጨረሻ የጭነት መኪና ያገኙና ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ይሆናል። አዲስ አበባ ሲደርሱም በጉዞ ወቅት የነበረውን ነገር ሲከታተሉ ስለነበርና ባመጣቸው ሹፌር ላይ እምነት ስላልነበራቸው ከመኪና እንደወረዱ ጥጋት ፈልገው ከአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ስር ግንብ ስር ይደበቃሉ። ቆይተውም ወደ ፒያሳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ አቅንተው የዛሬው እሳት አደጋ መስሪያ ቤት አጥር ስር ይቀመጣሉ።
ቀኑ ጨልሟል አዲስ አበባ ግን በኤሌክትሪክ መብራት ግማሽ ቀን ሆናለች ይሄነ ነበር የህይወታቸውን ምዕራፍ ሁለት የከፈተው አጋጣሚ የተፈጠረው። የያኔዋ ጉብል ወይዘሮ አበበች ግራ ገብቷቸው በዛች ጥግ እንደተቀመጡ አቶ አስራት የሚባሉ ሰው ይመለከቷቸዋል። አቶ አስራት በዘመኑ የተከበሩ ታላቅ ሰው ስለነበሩ በብዙ ሰው ታጅበው እየሄዱ ነበር። በጨለማ ብቻዋን የተቀመጠችውንና ግራ የገባትን የአስራ አንድ ዓመት ታዳጊ ሁኔታ ካዩ በኋላ አልፈው መሄድ አልቻሉም። እናም ወይዘሮ አበበችን ጠጋ ብለው ያነጋግሯቸውና እቤት ይዘዋቸው በመሄድ እንደ ልጅ እየተንከባከቡ ያሳድጓቸው ጀመር። ዝምድናቸው ይጠናከርም ዘንድ በዘመኑ አገላለጽ ጡት ያጣቧቸውና በወቅቱ በነበረውም የእጅ ሥራ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ ያደርጋሉ።
ከዓመታት በኋላ በልዑል አልጋ ወራሽ ትእዛዝ ከተማሪዎች መካከል ጎበዞች ተመርጠው ወደ እንግሊዝ ሀገር እንዲላኩ ሲደረግ የክብር ዶ/ር አበበች ዕድሉን ያገኙና የአንድ ዓመት ስልጠና በሃዋሳ ከተማ ከወሰዱ በኋላ የጉዞው ቀን ሲደርስ በመታመማቸው ሳይሳካ ይቀራል። ከዚህ በኋላ ጤናቸው ሲስተካከል በእህል ሰብል ድርጅት ተቀጥረው በመሥራት ትምህርታቸውን እስከ ስድስተኛ ክፍል ይከታተላሉ። የክብር ዶ/ር አበበች የረጅም ጊዜ እቅድ መንኩሶ በገዳም መኖር ቢሆንም በጓደኞቻቸውና በቤተዘመድ ግፊት ትዳር ይመሰርታሉ። የአብራካቸው ክፋይ የሆነ ልጅ ባይኖራቸውም ጥሩ ቤተሰብ መስርተው በትዳር የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ ዓመታትን ያሳልፋሉ።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነበር የክብር ዶ/ር አበበች የአርባ ዓመታት አንጸባራቂ የብዙ ቤተሰብ ምስረታ ውጤታማ ጉዞ የተጀመረው። ጊዜው በ1972 ዓ.ም ነው፤ ወይዘሮ አበበች ለራሳቸው የነፍስ ድህነት ፍለጋ በመስከረም ሃያ አንድ የሚከበረውን የጊሸን ማርያም በዓል ለማንገስ በቀድሞ ስሙ ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር ያቀናሉ። በጉዞ ላይ ሳሉም በወቅቱ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ተከትሎ ሞት ከፊታቸው የተደቀነባቸውን ሁለት ሕፃናትን ያገኛሉ። አጋጣሚው ለወይዘሮ አበበች ሁለተኛ የህይወት ፈተና የጀመረበት ቢሆንም በሌላ በኩል ለሁለቱ ሕፃናት ብቻ ሳይሆን የሺዎችን ቤት የሚጎበኝ መልካም ዕድል የተፈጠረበትም ትልቅ የጭንቅ አጋጣሚ ነበር። የክብር ዶ/ር አበበች የጀመሩት የመልካምነት ጉዞ ፈተና ይገጥመው የጀመረው ውሎ ሳያድር ነበር፤ ለዚያውም ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው። በውጤቱም ለብዙዎች ቤተሰብ ለመሆን ሲሉ የራሳቸውን ቤተሰብ ለመሰዋት ተገደዋል።
በወቅቱ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ያገኟቸውን ሕፃናት ይዘው ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ። ምንም እንኳ በእጃቸው ሁለት ልጆችን ብቻ ይዘው ቢመጡም በልባቸው ብዙ አስበው ነበርና የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ቁጥር ከሁለት ወደ ሦስት ከሦስት ወደ አራት እያሳደጉ በአንድ ዓመት ውስጥ ሃያ አንድ ያደርሱታል። ጅማሬውን በጸጋ የተቀበሉት ባለቤታቸው አቶ ከበደ ኮስትሬ ደግሞ ነገሩ እየከበዳቸው ሲመጣ ወደ ምክርም ወደተግሳጽም ገቡ፤ ወይዘሮ አበበች ግን አሻፈረኝ አሉ። ለሽምግልና የተሰበሰበውም ቤተ ዘመድ ተናግሮ ባለመደመጡ በአንድ ድምፅ እንዲህ ዓይነት ሥራ የጤና ሳይሆን የበሽታ ስለሆነ “አበበች አብዳለች!” ጠበል ትግባ የሚል ምክር ያቀርባል።
በዘመኑ ሀብታም ከሚባሉ ሰዎች ተርታ የሚሰለፉና ጥሩ የሚባል ህይወት ይኖሩ የነበሩት የክብር ዶ/ር አበበች ምላሽ ግን በተቃራኒው ነበር። በውሳኔያቸውም መሰረት ከዚያ ከረሀብ ከዚያ ከስቃይ ያወጧቸውን ልጆች መርጠው ትዳራቸውንም ሀብታቸውንም ትተው ከሕፃናቱ ጋር በአንድ የሳጠራ ጎጆ ዛሬ ለመቶ ሺዎች ቤተሰብ የሆነውን ኑሮ በድፍረት ያለማንም ረዳት “ሀ” ብለው ጀመሩ። የመጀመሪያውም መንግሥታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል የሕናት ማቆያ ድርጅት በዚያው መሰረቱን ለመጣል በቃ።
የክብር ዶ/ር አበበች በዘመኑ በአዲስ አበባ፤ ሙሎና፤ ፍቼ በሚባሉ አካባቢዎች አስራ ሁለት ወፍጮዎች ነበሯቸው። በዚያ ዘመን ደግሞ አንድ ወፍጮ ያለውም ሰው እንደ ትልቅ ሀብታም ይታይ ነበር። ትልቅ የዘመኑ ፋሽን ቪላ ቤትም ነበራቸው። ከቤታቸው ሲወጡ ግን ጥቂት ልብስና የወርቅ ጌጣጌጦቻቸውን ብቻ ይዘው ነበር። እናም ከቤታቸው ፊት ለፊት በአንዲት የሳጠራ ቤት ውስጥ በስጋ ያልወለዷቸውን ሃያ አንድ ልጆች ይዘው በፀሐይ ፍጥነት ከባለጸግነት ወደ ድህነት በመውረድ ዛሬ ድረስ የዘለቀውንና የሺዎች ቤተሰብ የሆነውን ማዕከል መሰረት ያስቀምጣሉ። ግና ወርቁም ልብሱም እነዚያን ሆድ ብቻ ይዘው የመጡ ሕፃናት ተሸክሞ መዝለቅ ስላልቻለ ሌላ የገቢ ምንጭ መፈለግ ግድ ሆነ። በወቅቱ ለወይዘሮ አበበች ተመራጭና አዋጭ የነበረው ሥራ ቆሎና ንፍሮ እያዘጋጁ መሸጥ ነበር። ይህም ቢሆን በአንድ ሰው እየተከወነ እነዚህን ሁሉ ሕፃናት ማሳደር ስለማይችል ከጣት ጣት ይበልጣል እንዲሉ ትንሽ ከፍ ከፍ ያሉትን ልጆች የተዘጋጀውን ቆሎና ንፍሮ እያዞሩ እንዲሸጡ እስከ ማድረግ ደርሰው ነበር። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ከባላቸው ክስ ይመጣባቸዋል።
ግና በልባቸው ሃሳብ ቆርጠው ነበርና ሁሉንም በድፍረት እየተጋፈጡ ይቀጥላሉ። ጉዞው ግን እጅግ ፈታኝ ነበር። ከአልጋ ወርዶ መደብ መተኛት፤ ሰልባጅ መልበስ፤ ልብሳቸውን ቀዶ ለሕፃናት ሰፍቶ ማልበስ፤ ልጅ አብልቶ ጾም ማደር፤ የሰው ፊት ማየት ከፈተኗቸው መከራዎች መካከል ይጠቀሳሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ ጊዜው ሄዶ በ1983 ዓ.ም አንድ በአካል የሚያውቁት ሰው በመሳሪያ አስፈራርቶ ሊዘርፋቸው ሞክሮ ነበር። የሚገርመው ከዓመታት በኋላ ሰውየው ለእስር ይዳረግና ልጆቹ መውደቂያ ማጣታቸው የክብር ዶ/ር አበበች ጆሮ ይደርሳል፤ ምንስ ቢሆን ሰዎች አይደለን ይሉና ልጆቹን በሙሉ ሰብስበው ያሳድጋሉ።
የክብር ዶ/ር አበበች ጅምራቸውን ይበልጥ ለማስፋት ህጋዊ ለመሆን ያስቡና ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ያቀርባሉ አምስት አባል እንደሚያስፈልግ ሲነገራቸው ደግሞ ሌላ ፈተና ይሆናል። በወቅቱ እንደሳቸው የነፍስና የህሊና እርካታ ብቻ የሚፈልግ ሰው ማግኘቱም ሌላ እዳ ነበር። ይህንንም ራሳቸውን አንድ ብለው ዓላማቸው ከገባቸው ዘመድ አዝማድ መካከልም ለምነው ህጋዊ ለመሆን ይበቃሉ። ከዚህ በኋላ ነበር ሲ አር ሲ ሜንሽን ፎር ሜንሽንና ሌሎች የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶችም ድጋፍ ለመስጠት እጃቸውን መዘርጋት የጀመሩት። ወይዘሮ አበበች እግር በእግርም የቆሎውን ንግድ ወደ ጠጅ መጣል፤ ከዚያም አልፎ ቅመማ ቅመም በማዘጋጀት ማስፋፋት ይቀጥላሉ። ባልትናቸው እንዲህ እንዲህ እያለ ዛሬ ድረስ በመዝለቅ ስልሳ አምስት ዓይነት የባልትና የምግብ ግብአት ምርቶችን በማምረት ከሁለት መቶ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ምርቶቹም እንደ ሸራተን አዲስ ሆቴል ፤ ፍልውሃ ሆቴል፤ ግዮን ሆቴል፤ ሰሜን ሆቴል፤ ግሎባል ሆቴልና ሌሎችንም መዳረሻ በማድረግ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ከፍቶ ይገኛል።
እንዲህ እንዲህ እያለ ያ ሰፊ ቤተሰብም ባለፉት አርባ ዓመታት ከሦስት ሺ አምስት መቶ በላይ ሕፃናትን የልጅነት ጊዜያቸውን በማቆያው እንዲያሳልፉ በማድረግ ለወግ ማዕረግ አብቅቷል። በአሁኑ ወቅትም በአመት ከ7 ሺ 500 በላይ ሕፃናትን በተለያዩ ፕሮግራሞች በአዲስ አበባ፤ ጉደርና፤ ቡራዮ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ሙሉ ለሙሉ ወጪያቸው የሚሸፈን ያሉ ሲሆን ከዘመድ አዝማድ ጋር እየኖሩ የተወሰነ ድጋፍ ብቻ የሚደረግላቸውም አሉ። 34 ሕፃናት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በማህበሩ ስር እየኖሩ ናቸው። የአደራ ቤተሰብ በሚለው የድጋፍ ዓይነትም ጥናት ተሠርቶ ወጪ ተችሎ ልጅ የሚሰጣቸው ቤተሰቦችም አሉ። ወይዘሮ አበበች ለልጆች ለየት ያለ ፍቅር ያላቸው እናት ናቸው። በተለይም ለጨቅላ ሕፃናት በዚህም የተነሳ በተቋሙ ሁሌ የሚተገብሩት አንድ ያልተጻፈ ህግ አላቸው። በምንም ምክንያት ዓመት ያልሞላቸው ሕፃናት ወደ ማዕከሉ ከመጡ የመጀመሪያዎቹን ቀናት አልያም ሳምንታት እሳቸው ጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው ብለው እስከሚያምኑ ድረስ የሚቆዩት በእሳቸው እጅ ብቻ ነው።
የክብር ዶ/ር አበበች በታሪካቸው ለአገልግሎታቸው አንድም ቀን ደመወዝ ተቀብለው የማያዉቁ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጌጣ ጌጥና ልዩ ልዩ ስጦታዎች ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ቢበረከትላቸውም አንዱንም ለራሳቸው ጥቅም አውለው አያውቁም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከእንግሊዝ ሀገር ወርልድ ቢዝነስ አዋርድ፤ ሁለት ጊዜ የዓመቱ በጎሰው ሽልማት፤ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ የክብር ዶክትሬት፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሞያቸው የላቀ አስተዋጽኦ ስላበረከቱ 50 ኛ የኢዩቤልዩ ሜዳሊያ፤ ማዘር ትሬዛ ኦፍ አፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ የሚጠቀሱ ናቸው።
ዛሬ የማዕከሉ እንቅስቃሴም ሆነ የተጠቃሚው ቁጥር በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ቢሆንም የክብር ዶክተር አበበች ጎበና የመዘንጋት የጤና እክል ገጥሟቸው ከቤት ለመዋል ተገደዋል። ከአንድ ስማቸውን ቀይረው ከሚጠሯቸው የአክስታቸው ልጅ በቀርም የሚያስታውሱት ነገር የለም። ለህመማቸው መንስኤው ደግሞ እርጅና ብቻ ሳይሆን በየወቅቱ ይገጥማቸው የነበረው ጭንቀት ነው። እናም በዛች ትንሽ ግቢ በሆነች ሰፊ ክፍል ውስጥ ሦስት መደበኛና ሁለት ተመላላሽ ሞግዚት ተቀጥሮላቸው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ሲሆን አንድ የአዕምሮ እንዲሁም አንድ ጠቅላላ ሀኪምና አንድ በየቀኑ የምትከታተላቸው ነርስ ተመድባላቸው በማዕከሉ ውስጥ ይኖራሉ።
መረጃውን የሰጡን የአበበች ጎበና የሕፃናትና ክብካቤና ልማት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እሸቱ አረዶ እና በአበበች ጎበና ሕፃናት ክብካቤና ልማት ማህበር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ የሖኑት አቶ ይትባረክ ተካልኝ ናቸው።
አዲስ ዘመን አርብ ህዳር 26/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ