አገር ቅርስ አላት። ወይ የሚዳሰስ፤ ወይ የማይዳሰስ፤ ወይም ሁለቱም። ሁለቱም ካላቸው ጥቂት አገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። የሚዳሰሱም የማይዳሰሱም ቅርሶች አሏት፤ ለዛውም የትየለሌ። አጥኚዎች “ፀጋ” ሲሉ የሚጠሩላትም ይህንኑ ነው።
የሰው ልጅ ሁለት አይነት ሀብት አለው። ቁሳዊ እና መንፈሳዊ። ሲኖር ሁለቱም የሱ ናቸው። ሲሞት ሁለቱንም ለትውልድ አውርሶ ወደ ‘ማይቀረው ይጓዛል። ከእነዚህ ከሚያወርሳቸው የልፋቱ ውጤትና የተሰጠው ፀጋም አንዱ መንፈሳዊ ሀብቱ የሆነው ሥነ ቃል ነው።
ከቃላዊ ተዋረድነቱ በመነሳት ስያሜውን ያገኘው ሥነ ቃል የራሱ ማንነት፣ አላማ፣ ፋይዳ፣ አቀራረብ፣ ባለቤት (ማህበረሰቡ)፤ እንዲሁም የግሉ የሆኑ አይነቶች፣ ባህሪያት፣ ቅርፆች እና የመሳሰሉት ያሉት የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ነው።
ሥነ ቃል የግለሰቦች ምጡቅ አዕምሯዊ ፈጠራ ውጤት ይሁን እንጂ በባህሪው ማህበራዊ ነው። ባለቤቱ ህዝብ እንጂ ግለሰብ አይደለም። የዚህ ምክንያት ደግሞ ያው የተለመደው “ባለቤቱ ተለይቶ ስለማይታወቅ . . .” የሚለው ነው።
ሥነ ቃል ከፅሁፍ ፅንሰትም ሆነ ውልደት በፊት ህያው መሆኑ ጥበቡን ከሁሉም የተለየ የሚያደርገው ሲሆን ተግባሩ ደግሞ ከሌሎች ሁሉ ይበልጥ ያጎላዋል። ለምን? ቢባል በሥነ ቃል ያልተነገረ፣ በሥነ ቃል ያልተገለፀ፣ በሥነ ቃል ያልተገሰፀ፣ ያልተሻረና ያልተሾመ፤ በሥነ ቃል ያልተሞገሰና ያልተወደሰ፣ በሥነ ቃል ያልተተረከ፣ በሥነ ቃል ያልተፈከረ የለምና ነው።
ሥነ ቃል በሥሩ ከሚያካትታቸው ቅርጾቹ መካከል ቃል-ግጥም አንዱ ነው። ቃል ግጥም በሥነ ቃል ዘርፍ እጅግ ተዘውታሪ ሲሆን ለበርካታ ማህበራዊ ፋይዳዎችም ሲውል ይታያል። ቃል ግጥም ለሰምና ወርቅ ቅኔ፤ ለፉከራ፣ ሽለላና ቀረርቶ፤ ቃል ግጥም ስለ ሀገርና ሰው፣ ስለአርበኛና ባንዳ . . . ሁሉ ለመግለፅ ዋነኛና ሁነኛ መሣሪያ ሆኖ ቆይቷል። ቀጥሎ የምንመለከተው ቃል ግጥም ስለአብሮነት (ዛሬ የክርስትና ስሙ “መቻቻል” የሆነው) የሚናገር ሲሆን፤ አብሮነታችን፣ አብሮ መብላት መጠጣታችን፤ አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ መተሳሰባችን ዛሬ ያልተጀመረ መሆኑን ሁሉ ያስረዳናል። በተቀራኒውም የሚለው አለው።
ከሰው የበሉት ይሸታል፣
ብቻ የበሉት ያሸታል።
ይህ ቃል ግጥም (ሁለተኛው “ሸ” ይጠብቃል) ከአጠቃላይ ቃል-ግጥማዊ ብቃቱ ባሻገር ይዘቱ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ፤ ምንዥላቶቻችን ምን ያህል የአብሮነትን አሰፈላጊነትና የተናጠል ህይወትን አላስፈላጊነት አስቀድመው እንደተረዱ ሁሉ ያመለከታል።
ሥነ ቃል፤ በተለይም ቃል ግጥም ስለአገርና ምንነት ከወፋፍራም ጥራዞች በላቀ ደረጃ፣ ስልትና ጥልቅ ስሜት ያለ አቻ የመግለፅ ብቃቱ ሁሌም ሲመሰከርለት ይሰማል። ምሳሌውም፤
አባት የሞተ እንደሁ ባገር ይለቀሳል፣
ወንድም የሞተ እንደሁ ባገር ይለቀሳል፣
አገር የሞተ እንደሁ በማን ይለቀሳል።
ይህንን ቃል-ግጥም እዚህ ጋር ለመተንተን መሞከር ማበላሸት ስለሚሆን እንዝለለውና ወደ ሌላውና ስለባህል ወረራ፣ አዕምሯዊ ቅኝ መገዛት፣ ሥነ-ምግባር ዝቅጠትና ስለመሳሰሉት ፀረ-ማህበረሰብና ማንነት ተግባራት የሚናገረውን እንመልከት።
የልጃገረድ አውታታ
ከመንገድ ዳር ተኝታ
ተነሽ በሏት ምነው
ይህ ሁሉ አለማፈር ነው።
ዛሬ ሊጠራርገን የተነሳውን “ግሎባላይዜሽን” እንበለው “የባህል ወረራ” ምን ያህል አያት ቅድመ አያቶቻችን ቀድመው እንዳዩትና አስከፊነቱን እንደተረዱት ይህ ድንቅና ምርጥ ቃል-ግጥማቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ቃል-ግጥም መሪን ከዘመን አጣምሮ፤ መከራና ችግርን ካለው ከወቅቱ ተጨባጭ እውነታ ጋር አስማምቶ፤ ውስጣዊ ስሜትን፣ የታፈነ ድምፅን፣ ብሶትን፣ አገዛዝን ሁሉ በአንድ ሰብስቦ፣ አዋህዶና አጣጥሞ እንዲህ ሲል ያቀርባቸዋል።
በኢያሱ ዳቦ ነው ትራሱ፣
በዘውዲቱ ተደፋ ሌማቱ፣
በተፈሪ ጠፋ ፍርፋሪ።
በጣም ከቆየው ወደ በጣም ቅርቡ ስንመጣም የምናገኛው ተመሳሳይ ነው። መቸም በደርግ አስራ ሰባት ዓመታት ያልሆነና ያልተደረገ ነገር እንደሌለ ብዙዎች የሚናገሩት ነው፡፡ ከነዛ ሁሉ አገዛዙ ከፈፀማቸው ጉዶች ውስጥ ግን ሁለት የተለያዩ ሁነቶችን ብቻ ጠቅሰን እንለፍ። አንዱ “ነጭ” እና “ቀይ” ቀለም የተሰየመው የወጣቱ እልቂት ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ “ሠፈራ”። የወቅቱ ያገዛዙ ሰለባዎችና ገፈቱን የቀመሱት እንዲህ ብለውት፤ ለኛም አስተላልፈውልን አልፈዋል።
መላኩ ተፈራ የግዜር ታናሽ ወንድም፣
የዛሬን ማርልኝ ሁለተኛ አልወልድም።
ቀና ብዬ ባየው ሰማዩ ቀለለኝ፣
አንተንም ሰፈራ ወሰዱህ መሰለኝ።
እነዚህ ሁለቱም የወቅቱን ፖለቲካ በሚመረምሩና ታሪክን እያጠኑ ባሉ ምሁራን ሥራዎች ውስጥ የተሰጣቸውን ስፍራ፤ ያገኙትን የተለየ ትኩረትና ማህበረ-ባህላዊ ዋጋ ለሚያውቅ ሰው ምን ማለት እንደሆኑ በቀላሉ ይረዳዋል። ይህን ዕድል ያላገኙም ካሉ ወደ ፊት ማግኘታቸው አይቀርምና ያኔ ይገነዘቡታል ተብሎ ይታሰባል። የስነ ቃል አቅምና ፋይዳም የትና የት ድረስ እንደሆነም እንደዛው።
በእርግጥ ስነ ቃላችንን በመጠቀም በኩል የሚያክለን የለም። ንግግራችን በተረት የታጀበ፣ በሰምና ወርቅ ቅኔ የተለወሰ ነው። የቱንም ያህል እናውራ “አንድ አባባል አለ . . .” ብለን በስነ ቃል ካላስደገፍን አይሆንልንም። የኛ ችግር ምንድ ነው? የራሳችንን አናከብርም፤ በውስጡ የተሸከመውን ማንነታችንን፣ ታሪካችንንና ፍልስፍናችንን አንመረምርም። መመራመሩ ይቅር፤ የተመራመሩት እንኳን ሲነግሩን ልንሰማቸው አልተዘጋጀንም፤ አንዳንዴም ጭራሹን አንፈልግም። ከሁሉም የከፋው ችግራችን ይሄ ነው የሚሉት በመስኩ ብዙ የለፉ ምሁራን። የውጭዎች ግን የኛን ማንነት፣ ታሪክ፣ እምነትና ፍልስፍና ለማጥናት ሲፈልጉ ከስነ ቃላችን እንደሚጀምሩ እልፍ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ለማንኛውም እናጠቃልለው።
ሥነ ቃል፣ የቅድመ-ጽሁፍ ሥራ ቀዳሚ፣ ምናባዊ፣ ማህበረሰባዊና የማይዳሰስ ሀብት ነው። በዘመን ተሻጋሪና ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላላፊነት ልዩ ባህሪይው እዚህ እኛ ድረስ ዘልቆ እያስተማረ፣ እያነጋገረ፣ ለጽሁፋችንም ሆነ ለንግግራችን የተለየ አቅምና ጉልበትን እየሰጠ፣ ውስጣዊ ማንነትና ታሪካችንን፣ ፍልስፍናችንን ለዓለም እየነገረ ይገኛል።
ሥነ ቃል ዛሬም በዕለት ተዕለት ኑሯችንና ንግግራችን ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ የፈጠራም ሆነ ኢ-ፈጠራ ሠራዎቻችን ሳይቀር እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ፣ የየሥራዎቹ ሥጋና አጥንት በመሆን ቀጥ አድርጎ ለማቆም እየተጫወተ ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በመሆኑም ሥነ ቃል የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ከእነሱ በፊት ያሉት ምንጅላቶቻችን ውርስና ቅርስ ነውና ምሥጋና ሁሉ ለእነሱ ይሁን።
አዲስ ዘመን አርብ ህዳር 26/2012
ግርማ መንግሥቴ