የወንጀል ዓይነቱ የብዛቱን ያህል ሰፊ ነው፡፡ ሰዎች በሰሯቸው ወንጀሎች ምክንያት ተገቢውን ፍርድ አግኝተው ዘብጥያ ሲወርዱ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በሰሩት ወንጀል ከህሊናቸው ጋር ሙግት ገጥመው ተሸሽገው ይኖራሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ፕላኔታችን ከቤት ሰብሮ ስርቆት እስከ ገንዘብ ዝርፊያ፣ ከአስገድዶ መድፈር እስከ ግድያ፣ በርካታ ወንጀሎችን አሁንም ማስተናገዷን ቀጥላለች፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የወንጀል ድርጊቶች በአሰቃቂነታቸው ወደር የማይገኝላቸው በመሆኑ በርግጥም በሰው ልጅ ስለመፈፀማቸው የሚያ ጠራጥሩ ሲሆን፣ ሌሎች የወንጀል ዓይነቶች ደግሞ ያልተጠበቁና እስካሁን ተፈፅመዋል ተብለው የማይታሰቡ በመሆናቸው የሰዎችን ትኩረት ይስባሉ፡፡ ከሰሞኑ በአገረ ቻይና ተፈፅሞ የተገኘው የወንጀል ዓይነትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ይመስላል፡፡
ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ መሰረት የ41 ዓመት ዕድሜ ያለው ቻይናዊ ዋንግ ፌንግ ሳይማር ሆነ እንጂ ፖሊስ የመሆን የረጅም ጊዜ ህልም ነበረው፡፡ ጎልማሳው ሳይማር ፖሊስ የመሆን ህልሙ ከንቱ ሆኖ አልቀረም፡፡
እንደዘገባው ከሆነ የዋንግ ፖሊስ የመሆን ህልም እውን የሆነው ከ12 ዓመታት በፊት ወንድሙ በገባበት የብድር ዕዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጠበቃ በፈለገበት ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱ የወንድሙ ጠበቃ ዋንግ ፍርድ ቤት እንዲቀርብና ለወንድሙ ምስክር እንዲሆን ይጠይቀዋል፡፡ ዋንግ ጠበቃውን በፍርድ ቤት ካገኘው በኋላ ፖሊስ እንደሆነና በአገሪቱ በሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንደሚሰራ በሃሰት ይመሰክራል፡፡ ማታለሉ ሰርቶለት ይህንኑ የማታለል ተግባር በሌሎች ሰዎች ላይም መሞከር ይጀምራል፡፡ ለጓደኞቹና ለሚቀርባቸው ሁሉ ፖሊስ እንደሆነ በመንገር የተሳሳተ የፖሊስ የደምብ ልብስ በመግዛት፣ ካቴና በመያዝና መታወቂያም ጭምር በማዘጋጀት የፖሊስነት ሙያውን ሀ ብሎ ይጀምራል፡፡
ዘገባው እንደሚለው በ2011 እ.ኤ.አ ዋንግ በኋላ ሚስቱ ከሆነችው ከ ዢያ ሉ ጋር ይቀ ራረባል፡፡ ዋንግ በጓደኛው አማካኝነት ጂያዢንግ በተሰኘው የወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደሚሰራ ይነግራታል፡፡ እርሷም ዋንግ በሚነግራት ልብ አንጠልጣይ የወንጀልና የፖሊስ ምርመራ ታሪኮች መመሰጥ ትጀምራለች፡፡ ዋንግ ምንአልባትም በምክትል የፖሊስ ኃላፊነት ቦታ ላይ ሳይሆን እንዳልቀረም ታምናለች፡፡
ይሁን እንጂ ግንኙነታቸው እያደረ ሲጠነክር ቤተሰቦቿ ዋንግን መጠርጠር ይጀምራሉ፡፡ ከአክስቷ ልጅች ውስጥ አንዱ ዋንግ በፖሊስ ሙያ ስለመመረቁ ለማረጋገጥ የቻይና የፖሊስ አካዳሚን ቢጠይቅም ስለዋንግ አንድም መረጃ ሳያገኝ ይቀራል፡፡ ዋንግ ታዲያ በምላሹ በቻይና ወንጀል ፖሊስ አካዳሚ ትምህርት እንደጀመረና ሌላ መታወቂያ እንደቀየረ ለሚስቱ ይነግራትና አምናው ሚስቱ ለመሆን ትስማማለች፡፡
በጋብቻው ቀን አንድ የዋንግ ቤተሰብና የሥራ ባልደረባ ብቻ መገኘት ያስገረማቸው የሙሽሪት ቤተሰቦች ይህ ለምን እንደሆነ በጥርጣሬ ዋንግ እንዲያብራራላቸው ይጠይቁታል ይላል ዘገባው ሲቀጥል፡፡ ዋንግም ከረጅም ዓመታት በፊት አብዛኛው ቤተሰቡን በሞት እንደተነጠቀ፣ በአሁኑ ወቅት ከቀሩት ቤተሰቦቹ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለውና ሁሉም የሥራ ባልደረቦቹ በሌላ ከፍተኛ የሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም እንደሄዱ በመግለጽ እውነታውን ይሸመጥጣል፡፡ ከሠርጉ በኋላም ዋንግ ጥብቅ የሆኑ የወንጀል ምርመራ ጉዳዮችን እንደሚመረምርና ይህን ለማንም እንዳትናገር ለባለቤቱ አስረግጦ ይነግራታል፡፡
ዋንግ ሁሌም የፖሊስ የደምብ ልብሱን በመልበስ ወደሥራ ስለሚሄድ፣ ያለማቋረጥ ስለወንጀል ጉዳዮች ስለሚያወራና በተደጋጋሚ ግዳጅ አለብኝ በሚል ለቀናት ቆይቶ ስለሚመለስ ሚስት ይህ ሁሉ እንግዳ ነገር መስሎ አልታያ ትም፡፡ እንዳውም ፖሊስ በተጨማሪ ሰዓትም ጭምር ግዳጅ ተሰጥቶት ይሰራል ሲባል ስለምትሰማና የዋንግ ድርጊትም ከዚህ የተለየ ባለመሆኑ በእርሱ ድርጊት ብዙም አልተደነ ቀችም፡፡ የዋንግ ሚስት የማታወቅው ነገር ቢኖር ሰውዬው ለዓመታት በሙያው ሲያጭበርብር መቆየቱንና በዚህ ቆይታው ሰፊ ልምድ መያዙን ነው ይላል ዘገባው፡፡
ዋንግ የሀሰት ፖሊስነቱን ለ12 ዓመታት በሚገባ ለማስጠበቅ ከመቻሉም በላይ ሙያውን በመጥፎ መንገድም ተጠቅሞበታል የሚለው ዘገባው፤ ለአብነትም ከሦስት ዓመታት በፊት የሚስቱ የአክስት ልጅ በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት ሲቀርብ የልጁ ቤተሰቦች ዋንግ የያዘውን የፖሊስነት ሙያ ተጠቅሞ እርዳታ እንዲያ ደርግላቸው በጠየቁት መሰረት ከጠበቃ ጋር በመሆን የልጁ ክስ እንዲቀነስለት አድርጓል፡፡ የልጁ ቤተሰቦችም የዋንግ ድጋፍ እንደነበረበት አምነዋል፡፡
በርካቶች ዋንግ በ12 ዓመታት የፖሊስ ሙያ ቆይታው በፖሊሳዊ ግዳጅ ላይ ያለ ቢመስላቸውም፤ የወንጀል ምርመራዎችን ያለ እረፍት እያካሄደ ነው ብለው ቢያስቡም ወይም ደግሞ ወንጀለኞችን ከያሉበት እያደነ ነው ብለው ቢገምቱም ዳሩ ሰውየው አብዛኛውን ጊዜውን ሲያሳልፍ የነበረው በሆቴል ውስጥ እና ብዙም ትርፋማ ባልሆነው አነስተኛ የህትመት ቢዝነስ ውስጥ ተሰማርቶ እንደነበር ታውቋል፡፡ ሀሰተኛ የፖሊስነት ሙያውን ሽፋን በማድረግ ቢዝነሱን ለመታደግ በሚልም በርካታ ገንዘብ ከግለሰቦች የተበደረ ቢሆንም ብድሩን ግን መክፈል አልቻለም፡፡
ዘገባው ሲያጠቃልልም ከ12 ዓመታት በኋላ በቅርቡ ዋንግ በእውነተኛ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡2 ሚሊዮን የቻይና ዮዋን ወይም 290 ሺ ዶላር ዕዳ እንዳለብትም ፖሊስ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
ጥቂት የማይባሉ አበዳሪዎችም ለዋንግ ያበደሩትን ገንዘብ ለመቀበል በመጠባበቅ ተሰላችተው እንደነበርና ወደ ህግ ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ነው ዋንግ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው፡፡ ፖሊስ የዋንግን መኖሪያ ቤት ሲፈትሽ በውስጡ ሀሰተኛ የደምብ ልብስና መታወቂያ፣በእጅ የተፃፈ መለማመጃ የፖሊስ ሪፖርትና ካቴና ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ዋንግ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ይህን የማታለል ተግባር ለመፈፀም ምን እንዳነሳሳው ሲጠየቅ ‹‹ ሁሌም ፖሊስ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ፤ በተለይ ከ12 ዓመት በፊት ወንድሜን ለመርዳት ስል የገባሁበት ጣጣ ሃሰተኛ ፖሊስ እንድሆን አስገድዶኛል፡፡ ለጓደኞቼና ለማውቃቸው ሁሉ ፖሊስ ሆኜያለሁ ብዬ ከተናገርኩ በኋላ ያገኘሁትን ክብር ላለማጣትም በማታለሉ ተግባር እስካሁን ልገፋበት ችያልሁ›› ሲል መልሷል ይላል ዘገባው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
አስናቀ ፀጋዬ