በአካባቢው ነጭ ድንኳን ተጥሏል፡፡በምስልና በጽሁፍ የተደገፈ የተለያየ መልዕክት ያላቸው ባነሮች እይታን በሚስብ ቦታ ተሰቅለዋል፡፡ከክልል፣ከዞንና ከወረዳ የተጋበዙ እንግዶች አድናቆታቸውን እየገለጹ ነበር በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም አዋበል ወረዳ ውስጥ በማህበር ተደራጅተው በንብ ማነብና የማር ልማት የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች በወረዳው ሉማሜ ከተማ ደረጃን ጠብቆ በተለያየ መጠን ለማር መያዣ በተዘጋጀ ዕቃ በማሸግ በፌስቲቫሉ ላይ ያቀረቡትን የጎበኙት፡፡የቻሉም በመሸመት።
ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የማር ምርት ገበያ ላይ የተለመደ ባለመሆኑና በዘርፉ ለተሰማሩ ወጣቶችም የሥራ ዕድል በማስገኘቱ ጭምር ነው የፌስቲቫሉን ታዳሚዎች ትኩረት የሳበው፡፡ኢንተርፕራይዞቹ ባህላዊ የሆነውን የማር ግብይት ብቻ ሳይሆን፣ዘመናዊ የንብ ማነብ ዘዴን በመከተል ማምረታቸውም የማር ልማት ሥራውን እያዘመነው ይገኛል፡፡
ከኢንተርፕራይዞች መካከል ወጣት ቁሜ ውድነህ በማር ልማቱ የተካነ መሆኑን ወለላውን ከሰፈፉ የሚያጣራበትና የሚሸጥበት ሱቅ ድረስ ወስዶ በማሳየት ነበር ንብ ማነብና የማር ልማት ውስጥ እንዴት እንደገባ ያጫወተኝ፡፡በሚኖርበት አዋበል ወረዳ ዳበና ቀበሌ ‹ቁሜና ጓደኞቹ› በሚል ስያሜ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ተደራጅተው ነው ሥራውን የጀመሩት።
ቁሜ የማህበሩ መሪ በመሆኑ ‹ማህበሩን ውጤታማ ለማድረግ እንቅልፍ አይወስደኝም› ይላል፡፡ማህበሩ ከሚያመርተው በተጨማሪ ከሌሎች አምራቾች እንጀራ ማር በመግዛት ጭምር አቅርቦቱን ለማሳደግ እየተጋ ይገኛል፡፡ በተጓዳኝም ገቢ የሚያስገኝ የንግድ ሥራም ያከናውናሉ፡፡ጥረታቸው ከማህበሩ አባላት ባለፈ የአካባቢውን ወጣቶችም በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡
የ‹ቁሜና ጓደኞቹ› ማህበር አባላት ያሰቡት ደረጃ እንደሚደርሱም የእስካሁኑ እንቅስቃሴያቸው ተስፋ ሰጪ ሆኖ ነው ያገኙት፡፡ማህበሩ በቀን ሁለት መቶ ኪሎ ማር በማጣራት ለገበያ የማቅረብ አቅም ፈጥሯል። አንዱን ኪሎ ማር እስከ ሁለት መቶ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ማህበሩ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለሥራ ከሚያንቀሳቅሰው 30ሺ ብር ሌላ በባንክ ውስጥ 27ሺ ብር መቆጠብ ችሏል፡፡የማር ማጣሪያ ማሽን ጨምሮ ማህበሩ በመቶ ሺ ብር የሚቆጠር ሀብት አለው። ወጣት ቁሜ የአርሶአደር ልጅ ቢሆንም ማር እንዴት እንደሚመረት ግንዛቤው አልነበረውም። ዘመናዊ የንብ ማነብና የማር ልማት ሥራ ጊዜንና ጉልበትን የሚቆጥብ እንደሆነ አልገመተም፡፡ለሙከራ የጀመረው ሥራ የሙያ ባለቤት እንዳደረገው ይናገራል፡፡የሥራ መስክም ይሆናል ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡ሥራ የለም ለሚሉ ወጣቶች ዘርፉ ሰፊና ያልተነካ በመሆኑ በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡የሥራ ዕድሉን ላመቻቸው ለክልሉ፣የሙያ ባለቤት በማድረግና ድጋፉ ላልተለያቸው ዓለምአቀፍ ሥነነፍሣት ሣይንስ ሥነምህዳር ማዕከል(አይ ሲ አይ ፒ ኢ) የሺ ፕሮጀክት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
‹ኪሮስና ጓደኞቹ› በሚል ስያሜ የተቋቋመው ማህበር ሰብሳቢ ኪሮስ ቢተው በበኩሉ እንደገለጸው፤ከእያንዳንዱ የማህበር አባላት አምስት መቶ ብር ተሰብስቦ በተገኘው 9ሺ አምስት መቶ ብር ወጪ በሰባት ቀፎ በ2010ዓ.ም ነው ሥራ የጀመሩት፡፡በምርት ወቅትም 15 ኪሎ ማር ማምረት የቻሉ ሲሆን፤ከምርቱም ሁለት መቶ ሃያ ሺ ብር ገቢ አግኝተዋል፡፡ይሁን እንጂ ከመካከላቸው ብሩን መካፈል የፈለጉ በመኖራቸው እንዳሰቡት ቆጥበው ለመለወጥ ያደረጉት አልተሳካም። ከስህተታቸው ተምረው በመመካከር ሥራቸውን በማጠናከር አሁን ካፒታላቸውን ወደ 75ሺ ብር ማሳደግ ችለዋል። ቀፎአቸውንም 63 ማድረስ ችለዋል፡፡ዳግም ተሰባስበው ለውጤት የበቁት አይ ሲ አይ ፒ ኢ የሺ ፕሮጀክት ባደረገላቸው የአቅም ግንባታ፣የቀፎ፣የማር ማጣሪያና አልባሳት ድጋፍ እንደሆነ ወጣቱ ተናግሯል፡፡
ለማር ቆረጣ የሚጠቀመውን ልብስ ለብሶ የንብ ማነቢያውን እያስጎበኘ የወደፊት እቅዱን ያጫወተኝ ሌላው ወጣት ያብባል ቢያድጌ፣በ2010ዓም በ10ኛ ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ወደ ሚቀጥለው ክፍል ማለፍ ባለመቻሉ በወቅቱ ልፋቱ ከንቱ እንደሆነበት ነበር የተሰማው፡፡
ወጣት ያብባል አዕምሮው የተረጋጋው በንብ ማነብ እና የማር ልማት ከጓደኞች ጋር በመደራጀት ሥራውን ከጀመረ በኋላ ነው ፡፡እስካሁን በገንዘብ ያገኘው ጥቅም ባይኖርም፡፡የማር ቆረጣ ጊዜ በመድረሱ ተስፋ አድርጓል። ወጣት አበባው የንብ ማነብ ስራ ከባድ ይሆናል በሚል ግምት ሥራውን እስኪጀምር ቸኩሎ ነበር፡፡በአጭር ጊዜ ስልጠና ክህሎት እንዳገኘና ሥራውም አድካሚ እንዳልሆነ በተግባር እንዳየው ይናገራል። ጠንክረው ከሰሩ በሁለትና ሶስት አመት ውስጥ መለወጥ ይቻላል ይላል፡፡የማህበሩ አባላት የንግድ መኪና ለመግዛትና በአካባቢያቸው የእህል ወፍጮ ቤት ለማቋቋም በማቀዳቸው ከወዲሁ ጠንክረው ለመስራት ለራሳቸው ቃል ገብተዋል፡፡በሥራ ወቅት ከመካከላቸው የሚያለምጥ ወይም ኃላፊነቱን የማይወጣ ቢኖር እንኳን በመመካከርና ያጠፋውን በመገሰጽ እንዲታረም በማድረግ ችግሮችን ይፈታሉ። ንብ ማነብ ያልተቋረጠ ክትትል ስለሚያስፈልገው አባላቱ መተባበራቸው ግድ ነው፡፡በመሆኑም ሳምንታዊ የምክክር ጊዜ አላቸው፡፡
በሥፍራው ተገኝቼ የወጣቶቹን እንቅስቃሴ እንዲህ በቃኘሁበት ወቅት ዓለምአቀፍ ሥነነፍሣት ሣይንስ ሥነምህዳር ማዕከል(አይ ሲ አይ ፒ ኢ)የሺ ፕሮጀክትና የአማራ ክልል በጋራ በክልሉ ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም በአዊና ዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች ያደረጉት ድጋፍ ወጣቶቹን ለውጤት እንዳበቃቸው ለመረዳት ችያለሁ፡፡
በአይ ሲ አይ ፒ ኢ ከንብ ማነብ ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶች አስተባባሪ ዶክተር ወርቅነህ አያሌው እንደገለጹት፤ወጣቶችን አደራጅቶ በንብ ማነብና የሃር ልማት በሀገር አቀፍ የተጀመረው የሥራ ዕድል ፈጠራ ውጤት እያስገኘ በመሆኑ ይሄን ሞዴል በመጠቀም የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና መስሪያ ቤቱ ካናዳ ከሆነው ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በቅርቡ ባደረገው ስምምነት መሰረት በአማራ፣በትግራይ፣በኦሮሚያና በደቡብ ለአንድ መቶ ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የአምስት አመት ፕሮጀክት ጸድቆ ከጥቅምት ወር 2012ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። ዕድገት ተኮር ተብለው ከተለዩት የሥራ ዕድል ዘርፎች ግብርና ከፍተኛውን ድርሻ መያዙ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2012
ለምለም መንግሥቱ