ተቀራርቦ መነጋገር፣ መወያየት እና መከራከር፣ ጉዳዮችን ማንሳትና መጣልን ፣በሀሳብ የበላይነት ማመንና ምክንያታዊነትን እንደሚያጎናጽፍ ብዙዎቻችን እንስማማለን። በሀገራችን እየታዩ ያሉትን የሀሳብ ልዩነቶች ተነጋግረን ወደ አንድ ማምጣት ባለመቻላችን ለሰላማችንም አደጋ እየሆኑ ነው።በተለይም የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑት ወጣቶች ችግሮቻቸውን በሰለጠነ መንገድ ማስወገድ ተስኗቸው ግጭት ውስጥ ሲገቡ ይታያል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ ወጣት አብርሃም ይርጋ እንደሚያስረዳው የችግሩ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች በጉዳያቸው ልክ የውይይት መድረኮች እየተዘጋጁላቸው እንዳልሆነ ይናገራል። ባለንበት ወቅት ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች የሀይማኖት አባቶች እና አመራሮች በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የሚያደርጓቸውን ውይይቶች ወጣቶች በሚፈለገው ደረጃ እየተሳተፉባቸው አይደሉም ይላል።
የሰላም ጉዳይ በዋናነት የሚጎዳውም የሚጠቅመ ውም ወጣቱን እንደሆነ የተናገረው ወጣት አብርሃም፣ ወጣቱን ያላከተተ ውይይት እምብዛም ፍሬያማ ሊሆን እንደማይችል ያስረዳል። ወጣቱ ሰላሙን አረጋግጦ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ የሚያስችሉ መድረኮች ያስፈልጉታልም ብሏል። መንግሥት ለወጣቱ ትኩረት በመስጠት በማንኛውም ጉዳይ ላይ ማሳተፍ እንደሚገባውም መክሯል። ለወጣቱ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ የውይይት መድረክ አለመዘጋጀቱ በሰላም ውጤቱ ላይ ክፍተት እንዳለው ገልጿል።
በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር የወጣቶች ሰብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ አለሙ ሰይድ እንደሚገልጹት፣ በወጣቶች መካከል የዕርስ በእርስ ውይይት በሚፈለገው ደረጃ እየተካሄደ ነው ባይባልም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአስተሳሰብ ልዕልናን አስመልክቶ የተለያዩ መድረኮች እየተዘጋጁ ውይይት እንደተደረገባቸው አስታውሰዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አጋር አካላትን እና በየደረጃው ያሉ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች መዋቅሮችን በማስተባበርና በማቀናጀት በተለይ በሰላም እሴት ግንባታ ምክንያታዊ የሆኑ የወጣቶች የእርስ በእርስ የክርክርና የውይይት መድረኮችን ሲያዘጋጅ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
እድገትም ይሁን ውድቀት የአስተሳሰብ ውጤት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በየክልሉ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በመላክ ወጣቶች የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ እንዳሉም ገልጸዋል። የወጣቶችን ሰብዕና ከመገንባት አንጻር ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሰሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የአስተሳሰብ ለውጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀገር ግንባታ ጉዳይ ዋነኞቹ ተዋናዮች ወጣቶች እንደመሆናቸው በአሁን ሰዓት ለወጣቶች መድረኮችን በማዘጋጀት በችግሮች ዙሪያ እንዲወያዩ ማድረጉ ትልቅ ትኩረት እንደተሠጠው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ወቅቱን ባገናዘቡ ችግሮች ላይ መወያየት መጀመሩንም አስረድተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ በየደረጃው የወጣት ሰብዕና ልማት ማዕከላት መደራጀታቸውንም ገልጸዋል።
የወጣቶች ሰብዕና ማዕከል ከባህሪ፣ ከክህሎትና ዕውቀት እንዲሁም ከሰላም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንም ጨምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ያቀፈ መሆኑን ገልጸዋል። አሁን በሀገሪቱ እንደሚታየው በአመለካከት ተከፋፍለው የሚታዩ ወጣቶችን ወደ አንድ በማምጣት የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት እንደ ቁልፍ አማራጭ በመውሰድ መድረኮችን ለማካሄድ ከክልሎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢኒስቲትዩት ተመራማሪ እጩ ዶክተር አበበ አይነቴ እንደሚያስረዱት፣ አሁን እየታየ ያለው የወጣቱ አለመቀራረብ የፖለቲካው ነጸብራቅ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በአጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በጋራ ጉዳዮች ላይ የሠጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ሁሉም የራሱን ጉዳይ ብቻ አጉልቶ ከመግለጽ ውጭ የጋራ ሀገራዊ አስተሳሰቦች ሲንጸባረቁ አይታዩም። ከእኛነት ይልቅ የእኔነት አስተሳሰብ የሚያመዝንበት ሁኔታ ስለጎላ ወጣቱን ወደ አንድ አስተሳሰብ የማምጣትና የማቀራረብ ስራው ተዘንግቶ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በተቋማት ደረጃ አልፎ አልፎ የማቀራረብ ሙከራዎች ቢኖሩም ያን ያህል ውጤታማ እንዳልሆኑም አቶ አበበ ገልጸዋል። ወጣትነት ትኩስነት እንደመሆኑ አንድን ጉዳይ ለማመዛዘን እድል የማይሰጥ የእድሜ ደረጃ ነው፤ ስለሆነም ይህ ሃይል በስሜት ተነሳስቶ አላስፈላጊ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳይገባ አካሄዱን ሊያስተካክሉ የሚችሉ የውይይት መድረኮች ሊዘጋጁለት ይገባል ብለዋል።
ወጣቶች እኔ ካላተረፍኩ ስለሌላው አይመለከተኝም ከሚል የዜሮ ድምር ፖለቲካ ወጥተው የሁሉንም ፍላጎትና ጥያቄ ከግምት ባስገባ መልኩ እንዲተረጉሙ ተቀራርበው የሚነጋገሩበት መድረክ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተፈጠረላቸው ገልጸው፣ወጣቱ አስተሳሰቦቹን በማዋሃድ ለሀገር የሚጠቅም ራዕይ ይዞ ለመጓዝ ተገናኝቶ መነጋገር ይኖርበታል። የሚመለከተው አካል በሙሉ ይህን መንፈስ ይዞ ወጣቶቹን የማቀራረብ ሥራውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዳበረ የአብሮነትና የመከባበር እሴት ወጣቱ ትውልድ እንዲላበሰው የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ከታላላቆቹ ልምድ ማግኘት እንደሚያስፈልገውም ጠቅሰዋል። ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣አባ ገዳዎች እና አመራሮች በሀገራቸው ጉዳይ እየተገናኙ የሚያደርጉትን አይነት ውይይት ከተለያዩ ክልልች የተውጣጡ ወጣቶችም በዚያው መልክ ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በየቀበሌው ያሉ ወጣቶችን በማደራጀት ስለ ሀገራቸው ራዕይ፣ ስለአንድነት፣ ስለ ህብረብሄራዊ ፌዴራሊዝም፣ ስለሕዝቦች እኩልነት ስለሰላምና መረጋጋት ጠቀሜታ ማወያየትም ወቅቱ የሚፈልገው አጀንዳ መሆን እንደሚገባው አቶ አበበ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2012
ኢያሱ መሰለ