አዲስ አበባ፡- እየተዘጋጀ ባለው የቀጣይ 10 ዓመታት የትራንስፖርት ስትራቴጂ ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች እንደሚሰሩ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።
በኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ በፍሎኔ ኢንሼቲቪ እና በዓለም ሀብት ተቋም በጋራ የተዘጋጀው ሁለተኛው ዓመታዊ “ሴቶች እና ትራንስፖርት በአፍሪካ” ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ካፒታል ሆቴል ሲካሄድ፣ በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደተናገሩት፤ የሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፍ ለሴቶች አመቺ አይደለም።
የህብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች ደህንነት፣ ፍላጎትና የስራ ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም። ለዚህም እስካሁን በነበረው አካሄድ የነበሩትን ክፍተቶችን በመለየት እየተዘጋጀ ባለው የቀጣይ 10 ዓመታት የትራንስፖርት ዘርፍ ስትራቴጂ ለሴቶች ምቹ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል።
በኢትዮጵያ ሴቶችን አሳታፊ እና ማዕከል ያደረገ የትራንስፖርት አቅርቦት አለመስፋፋቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ሴቶች በተለይ በህዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚደርስባቸው ትንኮሳና እና ጥቃት ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል። ይህም ምቹ ያልሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ያመጣው ችግር መሆኑን አብራርተዋል።
ሴቶች በዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አንዱ መፍትሄ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር ሴቶችን በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተሳታፊ ለማድረግ ጅምር ስራዎች መኖራቸው ተናግረዋል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ ዳግማዊት ማብራሪያ እየተካሄደ ባለው ኮንፈረንስ የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት የትራንስፖርት ዘርፎቻቸውን ለሴቶች ምቹ በማድረግ ረገድ ያከናወኗቸው ተግባራት ተሞክሮዎቻቸውን ያቀርባሉ። በሚቀርቡ ተሞክሮዎች ላይ ውይይት ይደረጋል። የልምድ ልውውጥም ይደረጋል። ኢትዮጵያ ከሚቀርቡ ተሞክሮዎች ልምድ እንደምትቀስምም አብራርተዋል።
የዓለም የሀብት ኢንስቲትዩት በአፍሪካ (world resource institute Africa) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ኃይለስላሴ መድህን እንደተናገሩት፤ የሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፍ ሴቶችን ያገለለ በመሆኑ ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው።
በትራንስፖርት ዘርፍ ሴቶችን የሚያጋጥማቸው ችግሮች የሴቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም የህብረተሰብ ችግር ተደርጎ መወሰድ አለበት የሚሉት አቶ ኃይለስላሴ፤ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሴት ችግር ብቻ መቅረፍ ሳይሆን የህብረተሰቡን ችግር መቅረፍ ነው።
ከትናንት ጀምሮ እስከ ነገ በአዲስ አበባ በሚካሄው ሁለተኛው ዓመታዊ ሴቶችና ትራንስፖርት በአፍሪካ ኮንፈረንስ ለባለሙያዎች ፣ ለተመራማሪዎች ፣ ለፖሊሲ አውጭዎች እና ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻዎች በአቅም ግንባታ፣ ሀሳብ ለመጋራት፣ ተሞክሮ ለመለዋወጥ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በትራንስፖርት ዘርፍ ሴቶችን ለሚያጋጥማቸው ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ መፍትሄዎች ይፈልቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2012
እፀገነት አክሊሉ