በቅርቡ የዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ዋና ኃላፊ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከፌዴራል ፖሊስና ከኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር ጋር መወያየታቸው ይታወቃል፡፡ በአገሪቱ ወንጀል ሰርተው በተለያዩ አገሮች የተደበቁ ተጠርጣሪዎችም ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡም የበኩላቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን በወቅቱ አረጋግጠዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል ማንኛውም ተጠርጣሪ ወንጀለኛ በአገር ውስጥ ይኖር አሊያም በውጭ አገር ተጠርጣሪ ሆኖ እስከተፈለገ ድረስ ለህግ የማይቀርብበት ምክንያት አለመኖሩን መናገራቸውም ይታወሳል፡፡ ከገቡበት ስፍራ ተይዘውም ለህግ እንደሚቀርቡም አጽንኦት ሰጥተው መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በለውጥ ላይ የመሆኗን ያህል ቀደም ባለው ጊዜ ግን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የተሳተፉና ሌሎች ወንጀሎችንም የፈጸሙ አካላት በአገር ውስጥ እንዲሁም ከአገር ውጪ ተሰውረው እየኖሩ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ይሁንና ህግ ተላልፈው ተደላድለው መቀመጥ ስለማይችሉ በውጭ ሀገር የሚገኙት እምጥ ይግቡ ስምጥ በኢንተርፖል አማካኝነት ተይዘው ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ኢንተርፖል በሚሰራቸውና እየሰራ ስላለው ጉዳዮች ከኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር ዳይሬክተር ከሆኑት ምክትል ኮማንደር ጸጋዬ ኃይሌ ጋር በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቆይታ ያደረገውን እንደሚከተለውም አቅርቦታል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
ዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል)
የዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1904ዓ.ም ሲሆን፣ እድሜው አንድ ምዕተ ዓመት ደፍኗል፡፡ ከተቋቋመ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም በመጀመሪያው ዓለም ጦርነት መቋቋም አልቻለም ነበር፡፡ እንደገና ተመልሶ በ1923 ዓ.ም ነው መቋቋም የቻለው፡፡
ኢንተርፖል በዋናት በዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር ድንበር ዘለል የሆኑ ወንጀሎችን የመቆጣጠር፣ አገራትን የማስተባበር፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስራዎችን ይሰራል፡፡
ኢትዮጵያም የዚህ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖል/ አባል አገር የሆነችው እ.ኤ.አ በ 1958 ዓ.ም ነው፡፡ አገሪቱ ኢንተርፖልን ከተቀላቀለችና አብራ መስራት ከጀመረች እነሆ የስድስት አስርት ዓመታት ታሪክ አስመዝግባለች፡፡
ኢንተርፖል ቢሮዎችን የሚከፋፍልበት መንገድ
መዋቅሩን በአግባቡ ለማስኬድ ያመቸው ዘንድ ቢሮዎችን በራሱ መንገድ ይከፋፍላል፡፡ ቀጣናዊ ቢሮ፣ ተጠሪ ቢሮና ዋና ቢሮ በማለት ለስራው ምቹ እንዲሆን የማድረግ ተግባር አለው፡፡ ለምሳሌ ቀጣናዊ ቢሮው ሲባል የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ቢሮን መጥቀስ የሚቻል ሲሆን፣ ይህም በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው መስሪያ ቤቱ ዙምባቤ የሚገኝ ሲሆን፣ የምዕራብ አፍሪካው ደግሞ ካሜሩን ይገኛል፡፡
ኢንተርፖል፣ ከዚህ ከየቀጣናዎቹ ቢሮዎች በተጨማሪ ሶስት ተጠሪ ጽህፈት ቤቶችም አሉት፡፡ እነርሱም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚገኘው ተጠሪ ጽህፈት ቤት አንዱ ሲሆን፣ ይህም ጽህፈት ቤት መቀመጫው ኒውርክ ነው፡፡ በአውሮፓም ተጠሪ ጽህፈት ቤቱ በብራስልስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ሶስተኛው ተጠሪ ጽህፈት ቤቱም ደግሞ በአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ከተማ ከፍቷል፡፡
በአዲስ አበባ የተከፈተው ተጠሪ ጽህፈት ቤት
በአፍሪካ ህብረት ተጠሪ ጽህፈት ቤቱ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ እንዲከፈት ስምምነት የተደረገው እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ ኢንተርፖል ይህን ስምምነት ያደረገው ከአፍሪካ ህብረት ጋር ነው፡፡ ቀጥሎም እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም ጥር ላይ ኢትዮጵያም አፍሪካን ወክላ ከኢንተርፖል ጋር ስምምነት አደረገች፡፡ ይህ ስምምነት ኢንተርፖል ተጠሪ ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ላይ እንዲኖረው መቀመጫ ለመስጠት ነው፡፡
ስምምነቱ ከተደረገ በኋላ እ.ኤ.አ 2016 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ጽህፈት ቤቱ በይፋ ተከፈተ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠሪ ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተው ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ ጽህፈት ቤቱም ለጊዜው በሚል የተከፈተው በፌዴራል ፖሊስ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ የአፍሪካ ህብረት ቦታ ሰጥቶት እሰከሚገባም በዚያው ውስጥ የሚቆይ ይሆናል፡፡ በዚህ መልኩ ተጠሪ ጽህፈት ቤቱ ስራ እየሰራ ነው፡፡ ይህም ተጠሪ ጽህፈት ቤት ተጠሪነቱ እንደ አፍሪካ ሲሆን፣ በአፈጻጸምም ሆነ በተልዕኮ ደረጃ ከቀጣናዊ ቢሮ ይልቅ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፡፡
የተጠሪ ጽህፈት ቤትና ቀጣናዊ ጽህፈት ቤት ተግባር
ሁለቱም ተቀራራቢ የሆነ ተግባር ያላቸው ሲሆን፣ ተጠሪ ጽህፈት ቤቱ በዋናነት ተግባሩ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ አፍሪካዊያን መሪዎች ከኢንተርፖል ጋር የፖሊስን ስራ ተባብረው እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ማንኛውም ወንጀል የፈጸመ ሰው በፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን የመሪዎቹ ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ እነዚህን በአገራቸው ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ተባብረው ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ለመስራት እንዲነሳሱ የሚያደርግ ነው፡፡ በአጭሩ በኢንተርፖል ስራዎች ላይ መሪዎቹ እውቅና እንዲሰጡና እንዲተባበሩም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ ጽ/ቤቱ በአቅም ግንባታ ላይ ይሰራል፡፡
ቀጣናዊ ጽህፈት ቤት ዋና ተግባሩ ለምሳሌ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ትብብር ህብረት የሚባል አለ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፖሊስ አዛዦች ህብረት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ፖሊስ አዛዥ የሚባልም አለ፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ወደ 13 አገራት ያሉ ሲሆን፣ ከነታንዛኒያ ጋር ደግሞ ወደ 15 አገራት አሉ፡፡ እነዚህ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ደግሞ በተለየ ሁኔታ ድንበር ዘለል የሆኑ በአካባቢያቸው የሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የራሳቸው የሆነ ስምምነት ኖሯቸው እንዲሁም የራሳቸው የሆነ ህገ መንግሥት ኖሯቸው ከኢንተርፖል ጋር በመሆን የኢንተርፖልን አሰራር በመከተል የሚንቀሳቀሱ ይሆናል፡፡ ኢንተርፖል ደግሞ ለሁሉም ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ምስራቅ አፍሪካ ያለው ቢሮ በተመረጡ ሰባት የወንጀል አይነቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡ ለአብነትም ከሽበርተኝነት፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ከሙስና፣ ከህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ጋር፣ በህጻናትና ወጣቶች ላይ ከሚፈጸም ወንጀል ጋር ተያይዞ ለምሳሌ ልቅ የሆነ ወሲብ (ፖርኖግራፊ) ጋር ተያይዞ እና መሰል ትኩረት በሚደረግባቸው የወንጀል አይነቶች ላይ ከኢንተርፖል ጋር የሚሰራ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን የወንጀል አይነቶቹ ሰባት ብቻ ናቸው ማለት ሳይሆን ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚሰራባቸው መሆናቸውን ለመጥቀስ ነው ፡፡ማንኛውም በወንጀል ሊያስጠይቅ በሚችል ነገር ላይ ተቋሙ ይሰራል፡፡ በጥቅሉ ድንበር ተሻጋሪ ነው፡፡ ወንጀለኞችን በጋራ ነው ለመቆጣጠር የሚሰራው፡፡
እንደ ተጠሪ ጽህፈት ቤቱም የአቅም ግንባታ ስልጠናም ይሰጣል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ፖሊስ ለፖሊስም የልምምድ ልውወጥ የሚያደርግ ነው፡፡ ለአብነት በኢትዮጵያ ያለው ቢሮ በዋናነት የኢትዮጵያን ፖሊስ አቅም መገንባት ላይ ይሰራል፡፡
ለምሳሌ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የወንጀል አይነቶችን በተመለከተ ከአሜሪካም ከኤፍ.ቢ.አይ በኢንተርፖል አማካይነት ትብብር እየተደረገ እየመጡ ስልጠና ይሰጣሉ፡፡ አንደኛው ወንጀል መካላከሉ እንዳለ ሆኖ ስልጠናና የአቅም ግንባታን የተመለከተ ነው፡፡ ተጠሪ ጽህፈት ቤቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በመቋቋሙ አገሪቱ የምታገኘው ጥቅም
በኢትዮጵያ ተጠሪ ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ መከፈቱ በርካታ ጥቅም እንድታገኝ ያስችላታል፡፡ እንደሚታወቀው ኢንተርፖል 194 አባል አገራት አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን፣ እዚህ ኢትዮጵያ ውሰጥ ደግሞ ከመላ ዓለም የሚመጡ መረጃዎች ኢትዮጵያ ከሌሎቹ አገራት ጋር የምትለዋወጥበት ራሱን የቻለ ስርዓት አለ፡፡ ማንኛውም መረጃ በጣም ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ ደቂቃዎች ባልሞሉበት ጊዜ ውስጥ የሚስተናገድበት ስርዓት አለ፡፡ ኢትዮጵያ መረጃ በምትለዋወጥበት ጊዜ ዓለም አቀፍ ትብበር እያደረገች ከመሆኗም በተጨማሪ እርሷም የተለያዩ መረጃዎችን ከማግኘት እና የምትፈልገውን ተጠርጣሪ ከመያዝ አኳያ ትልቅ ድጋፍ ማግኘት ያስችላል፡፡
መረጃ የምትቀባበልበት ሁኔታም በማንም የማይጠለፍና እጅግ ሚስጢራዊ በሆነ መንገድ ይከናወናል፡፡ የመረጃ ስርዓቱ በቀን 24 ሰዓት የሚሰራና ስርዓት ያለው ነው፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ ስርዓት ነው ከዓለም ጋር የምትገናኘው፡፡
ለምሳሌ አንድ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ከኢትዮጵያ ወደ ሌላ አገር ቢሄድ ወደሄደበት አገር መረጃዎች ይላካሉ፤ ያም አገር ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ አሳልፎ እንዲሰጥ ይጠየቃል፡፡ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ከዓለም አባል አገራት ጋር ሆና ተላልፈው እንዲሰጧት የምትፈለጋቸው ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ካሉ አሊያም አሳልፋ የምትሰጠው ተጠርጣሪ ካለ ለመስጠት እንዲያስችላት የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱ ትልቁን ሚና ይጫወትላታል፡፡
ኢንተርፖል በወንጀለኛ፣ በተጠርጣሪና በተፈላጊ ላይ የሚሰራው
ወንጀል ሰርቶ ተፈርዶበት አምልጦ የወጣ ግለሰብ ሊኖር ይችላል፤ ይህ ግለሰብ ወንጀለኛ ይባላል፡፡ በወንጀል የሚጠረጠር ግለሰብ ደግሞ አምልጦ ሊወጣ የሚችልበት ሁኔታ አለ፤ እርሱ ደግሞ ተጠርጣሪ ይባላል፡፡ እንደ አጠቃላይ ደግሞ ተፈላጊ የሚባሉ አሉ፤ ሁሉንም አይነት ኢትዮጵያ ከኢንተርፖል ጋር ተባብራ ትሰራለች፡፡
እነዚህ ሰዎች እንዴት ነው መምጣት የሚችሉት ቢባል የሚወጡ ማስታወቂያዎች አሉ፡፡ እነዚህም ማስታወቂያዎች ሰባት ሲሆኑ የተለያየ አይነት ቀለማት ያሏቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከእነዚህ ውስጥ ተፈላጊዎች የሚፈለጉበት ‹‹ቀይ ማስታወቂያ›› የሚባል አለ፡፡
ይህ ቀይ ማስታወቂያ አንድ ሰው ወጣበት ማለት በዓለም ላይ ያለው የሰውዬው እንቅስቃሴ ተገታ ማለት ነው፡፡ እንደፈለገው በማንኛውም አገር የመግባትም ሆነ የመውጣት እንዲሁም በተሸሸገበትም አገር እንደልቡ የመኖር መብት አይኖረውም ማለት ነው፡፡
ቀይ ማስታወቂያ የሚወጣበት የራሱ የሆነ አካሄድ አለው፡፡ ለምሳሌ ኢንተርፖል የማይገ ባባቸው ማለትም የሚወሰንባቸው አሊያም ጣልቃ የማይገባባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ለምሳሌ አንድ ሰው ባለው የፖለቲካ አመለካከት ላይ ወንጀለኛ ነው በሚል እንዲያዝ ቢፈለግ ኢንተርፖል ትብብር አያደርግም፡፡ አሊያም ደግሞ አንድ አገር ከሌላው አገር ጋር ውጊያ ቢያደርጉ ከዘር ጭፍጨፋ ጋር የተያያዘ ካልሆነ በስተቀር ለምን ሰራዊት አሰለፍክ አሊያም ይህን አደረክ ብሎ ጣልቃ አይገባም፡፡
ኢንተርፖል በዋናነት የሚከታተላቸው ጉዳዮች
ኢንተርፖል በዋናነት የሚከታተላቸው ወደ 12 አይነት ወንጀሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ከእነዚህ ውስጥ አንኳር የሚባሉት ከሽብርተኝነት፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ከሙስና፣ አጠቃላይ ከተደራጁ ወንጀሎች ጋር እንዲሁም ከህገ ወጥ መንገድ ዝውውር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይከታተላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ፈጽሞ ከአገር ቢወጣ የተሸሸገበት አገር ወንጀሉን ሰርቶ ትቶት ወደመጣት አገር እንዲመለስና የሄደበት አገር መንግሥት አሳልፎ እንዲሰጥ የሚያስችል ስምምነት አለ፡፡
ተጠሪ ጽህፈት ቤቱ ከመከፈቱ በፊትና ከተከፈተ በኋላ የተከናወኑ ተግባሮች በጥቂቱ
ለኢትዮጵያ እ.ኤ.አ 2014 ዓ.ም እና 2015 ዓ.ም አካባቢ ወደ ዘጠኝ ሰው ከተለያዩ አገሮች ተላልፈው ተሰጥተዋታል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ሁለት ሰዎች ተላልፈው ለኢትዮጵያ ተሰጥተዋል፡፡ አንደኛው ከባንክ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ በሰራው ወንጀል ተላልፎ የተሰጠ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በኢንተርፖል የሚደረጉ ስምምነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከኢንተርፖል ውጭ ደግሞ የሁለትዮሽና የሶስትዮሽ ስምምነቶች በአገሮች መካከል ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ስምምነቶች አንዳንዴ የኢንተርፖል መስመርን በመከተል የሚደረጉ ይሆናል፤ አንዳንዴ ደግሞ የኢንተርፖልን መስመር መጠቀም ሳያስፈልግ ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡ ግን በዋናነት የዚያ ትብብር ለኢንተርፖል ስራ ደጋፊ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ወንጀለኛ ስምምነቱን አገሪቱ ካደረገችበት አገር ውስጥ ቢኖር አሳልፎ እንዲሰጣት ከኢንተርፖል አባልነቷ ውጭ ደግሞ ወንጀለኛውን ለማምጣት የስምምነቱ መኖር በጣም ይጠቅማል፡፡ በመሆኑም ስምምነቱ ድንበር ዘለል ስለሆነ እንደ አንድ ትልቅ አጋዥ የሚቆጠር ነው፡፡
በህገ ወጥ መንገድ የተዘዋወረ ገንዘብን ከማስመለስ አኳያ ያለው ተስፋ
እንደሚታወቀው ኢንተርፖል በትኩረት ከሚከላከላቸውና ከሚቆጣራቸው የወንጀል አይነቶች አንዱ ሙስና መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በህገ ወጥ መንገድ የሚካሄዱ የገንዘብ ዝውውሮችን መከላከልና መቆጣጠር ላይም ይሰራል፡፡ በመሆኑም የራስ ያልሆነ ሀብትን የሚጠቀሙ ሰዎችን አሳልፎ ከመስጠት አኳያ በትኩረት የሚሰራ በመሆኑ ህገ ወጦችን በቁጥጥር ስር በማዋል በኩል ትልቅ ተሰፋ አለው ማለት ይቻላል፡፡
ገንዘቡን ከማስመለስ አኳያ መንግሥትም በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢንተርፖል በራሱ በኩል በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህም የተወሰነ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል እንጂ ማንኛውም ሰው ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡
ክልሎች ተጠርጣሪ ወንጀለኞች እንዲያዙላቸው የሚጠይቁበት ሂደት
በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ክልሎች ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ይቅረቡልን ሲሉ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄውን በሚያቀርቡበት ሰዓት ድግሞ በኢንተርፖል በኩል መሟላት የሚገባቸውን ጉዳዮች ሁሉ እንዲያሟሉ የሚሰጣቸው እና የሚሞሉት ቅጽ ይኖራል፡፡ ያንን ቅጽ እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡ ያንን ተጠርጣሪ አሊያም ተፈላጊ፣ ተፈላጊነቱን ሊያሳምን የሚችሉ መረጃዎች ተሟልተው ሲገኙ ለኢንተርፖል ይለካሉ፡፡ የተላከውን መረጃ ሲያምኑበት ተጠርጣሪ ወንጀለኛው ተፈላጊ ስለመሆኑ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡
በዚህም የተፈላጊው እንቅስቃሴ በሁሉም አገራት በሚያስብል ደረጃ ይገታል፤ ከአንዱ ወደሌላው የሚያደርገው ጉዙም ይቀጫል፡፡ ተፈላጊው የሄደበት አገር ከታወቀ ደግሞ ለዛ አገር ኢትዮጵያ ስለ ሰውዬው ተጨማሪ መረጃዎችን ለኢንተርፖል ትሰጣለች፡፡ ያም አገር ሰውዬውን ለኢትዮጵያ አሳልፎ ይሰጣታል፡፡ ልክ እንደዚህ ኢትዮጵያም መስፈርቱን ተከትሎ ለመጣው ጥያቄ ተመሳሳይ ነገር ታደርጋለች፡፡
ኢትዮጵያ አሳልፋ የሰጠችው ተጠርጣሪ ወንጀለኛ
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ለኢንተርፖል አሳልፋ የሰጠቻቸው ተጠርጣሪ ወንጀለኞች አሉ፡፡ እንደሚታወቀው የየአገራቱ ህግ የተለያየ ነው፡፡ አገራቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብሄራዊ ህጋቸው ልዩ ልዩ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደየህጋቸው አይነት ለአንዱ ቀላል የሆነ ወንጀል ለሌላው አገር ደግሞ ከባድ ወንጀል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደ አንድ ስምምነት ተላልፈው የሚሰጡ ሰዎች ይኖራሉ፡፡
በዚህ ዓይነት ሂደትም ኢትዮጵያ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ለፈላጊ አገሮች አሳልፋ የሰጠችባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ለአብነት ያህልም በቅርቡ አንድ ቻይናዊ ተጠርጣሪ አሳልፋ ሰጥታለች፡፡ ይህም ተጠርጣሪ ተላልፎ የተሰጠው ለፊንላንድ ነው፡፡
ይህ ቻይናዊ፣ ፊንላንድ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበር ፈጽሞ ገንዘቡን ወደ አገሩ ቻይና ልኮ ኢትዮጵያ መጥቶ ይሰራ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም ይሰራ የነበረው በቀላል ባቡር ላይ ነበር፡፡ የሰውዬውን አድራሻ የፊንላንድ መንግሥት በማወቁ ለኢትዮጵያ ሙሉ መረጃውን ላከ፡፡ ይህን ተከትሎም ኢንተርፖል ቀይ ማስታወቂያ አወጣበት፡፡ ኢትዮጵያም ከቻይና መንግሥት ጋር መክራ ተፈላጊውን ለፊንላንድ መንግሥት በ2018 ዓ.ም አሳልፋ ስጥታለች፡፡
የኢንተርፖል ዋና ጸኃፊ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት
የኢንተርፖል ዋና ጸኃፊ ባለፈው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር ጋር መክረዋል፡፡ እንደሚታወቀው ደግሞ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በለውጥ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ለውጥ በርካታ ሰዎች የመደሰታቸውን ያህል የተወሰኑ ደግሞ ከሰሩት የማጭበርበር ድርጊት ጋር ተያይዞ ለውጡ እያስፈራቸው ለመውጣትም ያሰቡና በውጭም ያሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች የትም ሆነ መቼም ቢሆን በሰሩት ወይም በተጠረጠሩበት ወንጀል ከህግ አያመልጡም፡፡ አብዛኛዎቹ ደግሞ ተሰሩ ተብለው የሚታሰቡ ወንጀሎች ኢንተርፖል ከሚተባበራቸው የወንጀል አይነቶች ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ እዛ ዝርዝር ውስጥ ያለ ወንጀልን አሳልፎ የመስጠት አንዱ የኢንተርፖል አባል አገራት ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አንጻርም ነው ኃላፊው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር የተወያዩት፡፡
በኢንተርፖል ተይዘው ስለመጡ ሰዎች
ኢንተርፖል በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎችን በራሱ ፍላጎት ብቻ ካሉበት አገር አንጠልጥሎ አያመጣም፡፡ አንድ ሰው ተፈላጊ ነው ተብሎ ለማለት በራሱ ወንጀሉ የተሰራበት አካባቢ ያለ ፖሊስ ነው መረጃውን ማምጣት የሚጠበቅበት፤ መረጃውን ሲያመጣ ደግሞ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ተከትሎ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ መልኩ የመጡ ሰዎችን የምታስረክበው ለጠያቂው አካል ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ ክልል አንድን ሰው ከአንዱ አገር እንዲመጣ ጠይቆ ከሆነ ለጠየቀው ክልል ነው ተጠርጣሪው የሚሰጠው ማለት ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ያለውን ሂደት የሚያስቀጥለው ክልሉ ነው እንጂ ኢንተርፖል አይሆንም፡፡ ኢንተርፖል ከማስረከብ በተጨማሪ ሂደቱ ውስጥ አይገባም፤ ነግር ግን እየተከናወነ ስላለው ሂደት ክልሉ ለኢንተርፖል ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ተይዞ እንዲመጣ ኢትዮጵያ የጠየቀችው ተጠርጣሪ፣ በኢንተርፖል ከተያዘ በኃላ እዛው በነበረበት አገር በእስር ቤት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ አገር ቤት ከገባ በኋላ ግን በነበረበት አገር በእስር ላይ እንደነበር ስለሚገልጽ በእስር ላይ የቆየበትን ሁኔታ በማጣራት ለፍርድ ቤት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ይህም በአገር ቤት የሚፈረድበትን የእስር ጊዜ እንደ ወንጀሉ ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስልት ይችላልና ነው፡፡ ይህ ግን የኢንተርፖል ስልጣን ሳይሆን የፍርድ ቤቱ ስልጣን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
አስቴር ኤልያስ