እንደመንደርደሪያ
በኮድ -3 ተሽከርካሪ የተፈቀደው የሥራ አይነት የኪራይ አገልግሎት እንጂ የታክሲ ሥራ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ ስምሪት(የኤታስ) አገልግሎት አሰጣጥ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 05/2011 መመሪያ ይገልጻል:: የኪራይ አገልግሎት የሚባለውም በውለታ መኪናን ማከራየት እንጂ የታክሲ ሥራን እንደማይጨምር ያስረዳል::
በአንጻሩ የኮድ -3 አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች የኪራይ አገልግሎቱ በሰዓት ወይም በቀን ያልተገደበ መሆኑን ይጠቁማሉ:: በኪራይ አገልግሎት ስር ሆነው ዘመኑ በፈጠረው ቴክኖሎጂ ህብረተሰቡ በሚፈልገው መልኩ በጊዜም በርቀትም አገልግሎት ማቅረባቸውን ይናገራሉ:: አገልግሎታቸው የትራንስፖርት ችግር የሚቀርፍ በመሆኑ በጥሞና ተመልክቶ እነርሱንም ያቀፈ፣ ሊያሠራቸውና ሊያካትታቸው የሚችል አሠራር እንዲዘረጋ ነው ምኞታቸው::
በከተማው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ ለደንበኞቻቸው ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ማቅረብ መቻላቸውን የሚጠቁሙት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ግልጽ መመሪያ ወጥቶ ባለመተግበሩ አንዳንድ የኮድ -1 የታክሲ አሽከርካሪና ባለቤቶች ዛቻና ማስፈራራት እያደረሱባቸው እንደሚገኙና በሥራው የደህንነት ስጋት በመፈጠሩ ጉዳያቸው ታይቶ ውሳኔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይናገራሉ::
በ2008 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና የተመረቀችው ወይዘሮ ሰሚራ መሀመድ፤ በተመረቀችበት ዘርፍ ሥራ ለማግኘት ባለመቻሏ በኮድ -3 ትራንስፖርት አገልግሎት ለመሰማራት መወሰኗን ትናገራለች:: ሥራው ነፃነት ያለው በመሆኑ ልጇንም ተንከባክባ ለማሳደግ ጥሩ ዘርፍ ሆኖ አግኝታው ነበር::
ወይዘሮ ሰሚራ ሰማያዊ በነጭ የተቀቡ አንዳንድ የኮድ -1 ታክሲ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች እያስፈራሯቸው እንደሚገኙ፣ በተለይ በምሽት ሰዋራ ቦታ ላይ የተሽከርካሪ መስኮት እንደሚሰብሩባቸውና ድርጊቱ በጓደኞቿ እየደረሰ መሆኑን ትናገራለች:: ‹‹ብራስ አካባቢ ሰው ወደ መኪናዬ ሲገባ ተመልክተው ተጠግተው ‹‹ሁለተኛ እዚህ ቦታ ላይ እንዳትጭኚ:: ብትጭኚ አይንሽን እናጠፋዋለን፣ መኪናሽን እንሰባብራለን ብለው ዝተውብኛል:: ታክሲዎች ካሉ ደንበኞቼን ለማሳፈር ደህንነት አይሰማኝም›› ትላለች:: ፍትሐዊ ክፍያ የሚጠየቅበትና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን፣ ለብዙዎችም የሥራ ዕድል መፈጠሩን በመግለጽ፤ እነዚህን ግምት ውስጥ በማስገባት በነፃነት ለመሥራት ስርዓት እንዲበጅለት ትጠይቃለች::
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆነው አቶ ኢዮኤል ተሾመም ቀደም ሲል በጥቃቅንና አነስተኛ በብሎኬት ማምረት ሥራ ተደራጅቶ ሲሠራ መቆየቱን ይናገራል:: በሥራው ኑሮውን ለመምራት ከብዶት እንደቆየ በማስታወስ፤ ከስድስት ወራት በፊት የትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ ለመሥራት ወስኖ በብድር መኪና በመግዛት በኮድ- 3 ተሽከርካሪ ዘርፉን መቀላቀሉን ይጠቁማል::ይሁን እንጂ አንዳንድ ቦታዎች ነጭ በሰማያዊ የቀቡ የኮድ አንድ የታክሲ አሽከርካሪዎች ደንበኞቻቸውን ለመጫን እንደሚከለክሏቸው፤ ዛቻና ማስፈራራት እያደረሱባቸው በመሆኑ ድርጊቱ በሥራው ላይ ስጋት እንደፈጠረበት ይጠቁማል::
አቶ ቴዎድሮስ መስፍን በሆስፒታሎችና ሰማያዊ በነጭ በተቀቡ ታክሲዎች ተራ በሚይዙባቸው ስፍራዎች ደንበኞቻቸውን ለማውረድም ሆነ ለመጫን እንደሚያስቸግ ሯቸው፤ እነርሱ ባሉበት ቦታ ከጫኑ ዘለፋ፣ ስድብ እና ዛቻ እንደሚደርሰባቸው ይናገራል:: አሽከርካሪውን ብቻ ሳይሆን ደንበኞቻቸውንም ሰድበው የሚያባርሩ እንዳሉ፣ በሌሎቹ ጓደኞቻቸውም ተመሳሳይ እና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባሮች መድረሳቸውን ፤ማታ ላይ ሁኔታው የባሰ መልክ እንዳለውና ድንጋይ እንደሚወረወርም ያስረዳል::
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደንበኛቸው ጠርቷቸው ለመጫን ሄደው እንደከለከሏቸው፤እንዲያውም ኃይል በተቀላቀለበት መንገድ ፌሮ ብረት አውጥተውበት እንዳባረሩት ፤ፒያሳ አካባቢም ተመሳሳይ ድርጊት እንደደረሰበት ይገልጽና፤ ጉዳዩ ዕልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራል::
ሌሎች አሽከርካሪዎችም በዘርፉ የተፈጠረውን የሥራ ዕድል፣ ለህብረተሰቡ ያስገኘውን ደህንነቱ የተጠበቀና በዋጋ ቅናሽ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ግምት ውስጥ በማስገባት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ይላሉ:: ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ንብረት ላይ እየተቃጣ ያለው ድርጊት ከቀጠለ አስቸጋሪ እንደሚሆንም ይጠቁማሉ::
የችግሩ መነሻና አቤቱታ
በኮድ -3 ሜትር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የቦርድ አመራር ሃሚድ እና ቤቲ (ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀይሯል) የሰሌዳ ቁጥራቸው ኮድ ሦስት በሆኑ 55 ተሽከርካሪ ባላቸው ባለንብረቶች የተመሰረተ መሆኑን ያስረዳሉ:: የአባላቱ ቁጥር አሁን 100 እንደደረሰ፤ አባል ያልሆኑ በተመሳሳይ ሥራ ላይ የተሰማሩ 10ሺ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች መኖራቸውን ያመለክታሉ::
አባሎቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እያቀረቡ ቢገኙም፤ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ አገልግሎት የሚሰጡት አባሎቻቸው የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ:: ወደ ዝግጅት ክፍሉ ለመምጣት መነሻ የሆናቸው ጉዳይም በአባሎቻቸው ላይ ከዛቻና ማስፈራራት አንስቶ እየደረሰ የሚገኘውን ጥቃታ በተመለከተ አቤቱታ ለማቅረብ መሆኑን ይናገራሉ::
እንደ አመራሮቹ ገለጻ፤ ባለፈው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ የወጣው ‹‹የኤሌክትሮኒክ የታክሲ ስምሪት(የኤታስ) አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ 05/2011›› አንቀጽ ሦስት የኢታስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎቱን መስጠት የሚችሉት በኮድ -1 ሰሌዳ የተሰጣቸው ናቸው ይላል:: ይህም ኮድ -3 የምናሽከረክረውን እንደህገ ወጥ የሚያስቆጥር ነው ባይ ናቸው::
አሽከርካሪዎቹ ሥራውን ቀድመን ጀምረን እየተገበርን የምንገኝ በመሆኑ መከልከላችን ተገቢነት የለውም ሲሉም ይቃወማሉ:: ሆኖም መመሪያው እነርሱ ደንበኞቻቸውን በጊዜም ሆነ በሜትር የተተመነ አገልግሎት ለመስጠት እንደማይከለክላቸውም ነው የሚገልጹት::
ችግሩ የተፈጠረው የመመሪያውን አንቀጽ ባግባቡ ባለመገንዘባቸው ነው የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ አንዳንዶች መመሪያውን ለኮድ -1 የተፈቀደ ለኮድ -3 የተከለከለ አድርገው እንደወሰዱት ይናገራሉ:: በእዚህም ኮድ -3 ን ህገ ወጥ በማለት ፈርጀዋል፣ የተለያዩ ጥቃቶችም ሰንዝረውብናል ሲሉ አቤት ብለዋል::
እንደ እነርሱ ማብራሪያ፤ ህጋዊ በመሆናችን እኛም መብታችን መጠበቅ አለበት:: አባሎቻቸው ከንግድ ቢሮ የንግድ ፍቃድ ያወጡ፣ ከመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሊብሬ የተሰጣቸውና በየዓመቱ እስከ አስር ሺ ብርና በላይ ግብር ከፍለው የሚሠሩ ህጋዊ እውቅና ያገኙ የንግድ ተቋም መሆናቸውን ይጠቅሳሉ:: ተሽከርካሪዎቻቸው ለግል አገልግሎት የሚውሉ ሳይሆኑ፤ ለንግድ አገልግሎት የሚውል የመኪራ ኪራይ አገልግሎት የሚል ሊብሬ የያዙ የተሽከርካሪ ባለቤቶች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ:: ‹‹የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀት፣ ቲን ነምበር፣ ንግድ ፍቃድ አውጥተን የምንሠራ እና የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን አገልግሎት ይዘን በህጋዊነት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን›› ሲሉም ነው የሚናገሩት::
እነዚህ ከተለያዩ ቢሮዎች የወሰዷቸው ፍቃዶች ከተማው ላይ እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ለመሥራት የሚያስችለን ህጋዊ ባለመብት የሚያደርጉን ናቸው:: ሆኖም በኮድ -1 አገልግሎት የሚሰጡ በተለምዶ ላዳ የሚባሉት አንዳንድ አሽከርካሪዎች የኢታስ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ኮድ -1 ብቻ ናቸው የሚለውን ይዘው ‹‹ህጉን መንግሥት ይተግብርልን›› ወደሚል ገብተዋል ሲሉ ያመለክታሉ::
‹‹መንግሥት ካላስተገበረ ደግሞ እራሳችን ህጉን እናስከብራለን›› በሚል መልኩ የተለያዩ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመፈጸም ጫና እያደረሱባቸው እንደሚገኙ፤ እንዲሁም በርካታ ችግሮች እያደረሱባቸው መሆኑን ይገልጻሉ:: ከዛቻ እና ማስፈራሪያ አንስቶ በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ጉዳት እየደረሰ፣ ደንበኞቻቸውም እየተሸማቀቁና እየተጉላሉባቸው እንደሚገኙ ያብራራሉ:: እንደአቤቱታ አቅራቢዎቹ ከሆነ፤ የተሽከርካሪ መስታወት ከመስበር አንስቶ አሽከርካሪዎችን በጩቤ መውጋትና ድብደባ የደረሰባቸው እንዳሉም በምሬት ይገልጻሉ::
‹‹ግብር በመክፈል ግዴታችንን ባግባቡ እየተወጣን እንገኛለን፣ እንደማንኛውም ዜጋ በነፃነት ተንቀሳቅሰን የመሥራት መብታችን ሊነፈገን አይገባም›› ይላሉ:: እውቅና ባልተሰጠው አካል እየደረሰብን ያለው ህገ ወጥ ድርጊት በመሆኑ፣ ሂደቱም ህጋዊ ስላልሆነ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጥቃቱን ሊያስቆሙ ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ::
ድርጊቱ እየተባባሰ እንዳይቀጥል በመስጋት በተለያዩ ብዙሃን መገናኛ ቀርበን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሞክረናል የሚሉት የአክሲዩን ማህበር አመራሮቹ፤ መመሪያና ደንቡ ምን እንደሚልና በህጋዊነት መንቀሳቀስ የሚችሉ መሆናቸውን ግንዛቤ ለመፍጠር መሞከራቸውን ይናገራሉ::
አቤቱታ አቅራቢዎቹ በየደረጃው የሚገኙና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለጉዳያቸው ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ያመለክታሉ:: የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀልን መከላከል የመጀመሪያው ተግባሩ መሆኑን በመጥቀስ፤ ወንጀሉ ሲፈጸምባቸው ይዞ ማሰር ሳይሆን እንዳይፈጸም ሊከላከልላቸው እንደሚገባ ይጠቁማሉ::
የአዲስ አበባ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ፤ ለኮድ -3 ለንግድ አገልግሎትና ለግል ንግድ ፍቃድ እንደሚሰጥ በማመልከትም፤ የኪራይ አገልግሎቱም በሰዓት ወይም በቀን ያልተገደበ መሆኑን ይጠቁማሉ:: መመሪያውን መሰረት አድርገው ለሚጠይቁ አንዳንድ የኮድ -1 አሽከርካሪዎች ልዩነት ያለው ንግግር ከማድረግ ሊቆጠቡ እንደሚገባ፣ ግልጽ አድርጎ ማብራሪያ እንዲሰጥና ህጋዊ መሆናቸውን እንዲያሳውቅላቸው ጠይቀዋል::
በመመሪያው ክልከላ ተደርጎብንም ቢሆን እንኳ የሚፈጸመው ጥቃት ተገቢ አይደለም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ባለስልጣኑ በጥሞና ተመልክቶ እኛንም ያቀፈ፣ ሊያሠራንና ሊያካትተን የሚችል መመሪያ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል:: በኪራይ አገልግሎት ስር ሆነው አሠራሩን በማዘመን ህብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ በጊዜም በርቀትም ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ማገልገላቸው አሁን ያለውን የትራንስፖርት ችግር የሚቀርፍ በመሆኑ እልባት እንዲሰጠው ያመለክታሉ::
የከተማው የትራንስፖርት ባለስልጣን
ምን ይላል?
የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮማንደር አህመድ መሀመድ፤ የኤሌክትሮኒክ የታክሲ ስምሪት(የኤታስ) አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያው ተፈጻሚነቱ ታክሲ እና ታክሲዎችን እናሠራለን ብለው ሲስተም ያበለጸጉት ላይ መሆኑን ይገልጻሉ:: ታክሲ ማለት ኮድ -1 የሆኑትን ብቻ መሆኑን ያመለክቱና፤ ኮድ -3 ወይም ሌላን አያካትትም ባይ ናቸው::
እርሳቸው አሁን ባለው ሁኔታ ሲስተሙን ካበለጸጉ ተቋማት ወይም ድርጅቶች ጋር በመሆን የተለያዩ መኪኖች ተግባር ላይ እንደሚገኙ፣ ኮድ -2 እና ኮድ -3 ጭምር እየሠሩ መሆኑን፣ ቴክኖሎጂው ሲመጣ የታክሲ ሥራንና ሌሎች ሥራዎችን መጀመራቸውን፣ ቀደም ሲል የነበሩ በኮድ -1 ተደራጅተው የተቀመጡ ታክሲዎች እያሉ ሌሎቹ ሲስተሙን መጠቀማቸውን ያስታውሳሉ::
ኮማንደር አህመድ ‹‹ኮድ -1 አሽከርካሪዎች ‹ሥራችን እየተነጠቀ ነው፣ ህጋዊ ሆነን ተደራጅተን ግብር እየከፈን እየሠራን ግብር የማይከፍሉና ከተቋቋሙበት ዓላማ
ውጪ የሚሠሩ መኪናዎች ወደ ሥራ እየገቡ ነው› የሚል አቤቱታ አቅርበዋል:: ቴክኖሎጂው ነገሮችን የሚያቀልል ሆኖ በመገኘቱ ጥሩ ነው፣ እንደመንግሥት ህግን ማስከበርና አሠራሩን በህግ መምራት ስለሚያስፈልግ ግን መመሪያውን አውጥተናል›› ይላሉ::
መመሪያው ከእዚህ በፊት ተከልክሎ የነበረውን በማንሳት ወደ ኮድ -1 በማስቀየር ታክሲ ሆነው ለመቀጠል ለሚፈልጉ ፍቃድ ይሰጣል የሚሉት ኮማንደሩ፤ ታክሲ ለመሥራት ኮድ -1 መሆንና ቀለማቸውን መቀየር እንደሚኖርባቸው ይጠቅሳሉ:: ኮድ -3 ም ሆኑ ኮድ -2 የተቀመጠውን አነስተኛ መመዘኛ ማሟላት ከቻሉና በቴክኖሎጂ ለመመራት የሚችሉ ከሆኑ ወደ ኮድ -1 ቀይረው የታክሲ ሥራ መሥራት ይችላሉ:: ሲስተም ያበለጸጉትም ማንኛውንም መኪና እየመዘገቡ ማሠራት የለባቸውም:: የታክሲ ሥራ ስለሚያሠሩ ታክሲዎችን ብቻ መዝግበው እንዲያሠሩ የሚያደርግ መመሪያ መሆኑን ያስረዳሉ::
የመኪና ኪራይ እና የታክሲ ሥራ ይለያያል የሚሉት ኮማንደሩ፤ ባይለያዩ ኖሮ ሁለቱን ዘርፎች በአንድነት ኪራይ ወይንም ታክሲ በሚል ዘርፍ ሊመደቡ ይችሉ እንደነበር ይጠቅሳሉ::
የመኪና ኪራይ ‹‹ውል›› ያስፈልገዋል:: የኪራይ ውሉ በሚጠቅሰው መሰረት የኪራይ ሥራ መሥራት ይችላሉ:: ከዚህ በፊትም ሥራው የነበረ አሁንም የሚሠሩት ሥራ ነው:: የከለከላቸው የለም ኮድ -3 የሚያሽከረክሩ የታክሲ ሥራ መሥራት ከፈለጉ መስፈርቱን አሟልተው መሥራት ይችላሉ እንጂ ሁለቱን ሥራዎች በአንድነት መሥራት አይቻልም:: ‹‹ስንፈልግ ታክሲ ስንፈልግ ደግሞ ኪራይ እንሥራ›› የሚለው አያስኬድም ይላሉ::
የኤሌክትሮኒክስ ታክሲ ስምሪት አገልግሎት አሰጣጥን ለመቆጣጠር የሚያስችል መመሪያ መውጣቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት የቢሮ ኃላፊው ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም እንደተናገሩት፤ በዘርፉ ለታክሲ አገልግሎት የሚሰማሩ ተሽከርካሪዎች የታርጋ ቁጥራቸውን ወደ ኮድ -1 እንዲቀይሩ እና ቀለም እንዲቀቡ፣ የታክሲ አገልግሎቱን የሚሰጡ አካላት በድርጅት መታቀፍ እንዳለባቸው በመመሪያው መቀመጡን ገልጸው ነበር:: ከዚህ ቀደም ተክልክሎ የነበረው ኮድ -1 ታርጋ ማውጣት መፈቀዱንም መግለጻቸው የሚታወስ ነው::
ክፍተቱን ምን ፈጠረው ?
ወደ አፈጻጸም ለመግባት በመዘግየቱ ችግሩ መፈጠሩን ኮማንደር አህመድ ይናገራሉ:: ባለስልጣኑ በሚፈለገው ደረጃ ተዘጋጅቶ ወደ አፈጻጸም አለመግባቱ ችግሩ አሁን የያዘውን ገጽታ እንዲይዝና በእዚህ ደረጃ እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን፤ መመሪያውን ለማስፈጸም የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸውም ይጠቅሳሉ:: አሁን አገልግሎቱን ለመስጠት ሲስተም ያበለጸጉና ቴክኖሎጂው የሚፈለገውን መስፈርት ያሟሉትን አምስት ድርጅቶች መለየታቸውን፣ በቀጣይም ሌሎች እያሟሉ ፍቃድ እየወሰዱ እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ::
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ታርጋ እና ቀለም ለመቀየር ፍላጎት ያላቸውና የጠየቁ ድርጅቶችም ወደእዚሁ ስርዓት ይገባሉ:: ህጋዊ መንገዱ ለሁሉም ግልጽ ነው:: ሆኖም ሁኔታውን እየተገነዘቡ እንዳልተረዱ ሆኖ የመቅረብ ሁኔታ አለ:: አብዛኞቹ ሁሉንም ነገር ያውቁታል:: ከለመዱት ምቹ ሁኔታ ለመውጣት ያለመፈለግ ዝንባሌ ነው:: ይሄ ሁኔታ ደግሞ ለአንዱ ምቹ ቢሆንም ለሌላው የማያመች ነው:: በመሆኑም በቀጣይ ሁኔታውን ስርዓት የማስያዙ ሂደት በጣም ይጠናከራል::
ህጋዊ ሆነው የታክሲ ሥራን ቢሠሩ ተመራጭ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ በህጋዊ ሥራ ማንም ተጎጂ አይሆንም፣ ህገወጥ ሆኖ በቀጠለ ቁጥር ይለመድና ለመውጣትም ይቸግራል፣ የታክሲ ሥራ እሠራለሁ የሚል ዓላማ ያለው ሰው በጊዜ ኮዱን እና ቀለሙን ቀይሮ በህጉ መሰረት ወደ ስርዓቱ ገብቶ መሥራት ይኖርበታል ባይ ናቸው::
የትራንስፖርት ዘርፉ ገና ብዙ ሰው ይፈልጋል:: ለምን መተናነቅ እንደተፈ ጠረበትም ግልጽ አይደለም:: ሁሉም ሰው፤ ሲስተም ያበለጸገውም ሆነ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ወደህጋዊ ስርዓቱ ገብተው መሥራት ይችላሉ ሲሉም አቶ አህመድ አስረድተዋል::
በቅርቡ ፈቃድ ያላቸውን ድርጅቶች ይፋ እናደርጋቸዋለን:: ህብረተሰቡ ትክክለኛውን አሠራር በመለየት መጠቀም ይኖርበታል:: ተመጣጣኝ በሆነ የአገልግሎት ክፍያ የሚጠቀሙበት ታሪፍ ይቀመጣል:: ታሪፉ አገልግሎት ሰጪና ተገልጋዩን በሚዛናዊነት የሚመለከት ይሆናል ይላሉ::
ሁሉም ወደህጋዊ መስመር ገብቶ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት መንገድ ይኖራል:: ቴክኖሎጂውን ተቀብለናል:: በህግ እየተደገፈ መሄድ እንዳለበትም እናምናለን:: ሲስተም ያበለጸጉትን እየደገፍን እንቀጥላለን:: ሰው በቀላሉ ግንኙነት ፈጥሮ የሚፈልገውን የትራንስፖርት አገልግሎት ሲያገኝ ደስተኞች ነን:: አገልግሎቱ በህጋዊ መንገድ እንዲሰጥ እና ከለላ እንዲያገኝ በማሰብ መመሪያ አውጥተናል ሲሉም ያብራራሉ::
ሲስተም ያበለጸጉ ስርዓቱን መተግበሪያ መሰረተ ልማት እና የመረጃ ቋት በአገር ውስጥ መሆን እንዳለበት በመመሪያ መስፈርት ሆኖ መቀመጡን በመጠቆም፤ የመረጃ ቋት ውጭ አገር አድርጎ መሥራት የማይቻል መሆኑን አቶ አህመድ ይጠቁማሉ::
ቅሬታ አቅራቢዎቹ
ቀድሞ ኪራይ አገልግሎት ፈላጊው መኪና ለመከራየት ቢሮ ባላቸው ዘንድ በአካል እየቀረበ ወይም አየር በአየር እየተገናኘ በመደራደር ሥራው ሲሠራ መቆየቱን ያነሳሉ:: አሁን የቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ በሲስተም በመጠቀም ግንኙነት ተፈጥሮ በሜትር ርቀት በመደራደር የተፈለገውን ርቀት ተጉዞ መነሻ ገንዘብ ጨምሮ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጥበት አሠራር እንደኪራይ መታየት እንዳለበት ያመለክታሉ::
‹‹ቀለም እንድንቀባ መደረጉ ትክክል አይደለም›› በማለት የሚጠቁሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህ መደረጉ ለወጪ እንደሚዳርግ፣ ማህበረሰቡ የሚፈልገውን ምቾትም እንደሚቀንስና ተሽከርካሪያቸውን አቆይተው ለመሸጥ ቢፈልጉ ዋጋው እንሚቀንስባቸው ይናገራሉ:: ሌላው ያልታየ ነገር አለ በማለትም በኮድ -3 በአውቶ ሞቢል መንጃ ፍቃድ ማሽከርከር የሚቻለውን፤ ቀለም ተቀብቶ ኮድ -1 ከሆነ ግን ህዝብ አንድ የሚባል መንጃ ፍቃድ ማውጣት ይጠይቃል:: ይህንን ሁሉ አሽከርካሪ ህዝብ አንድ የሚል መንጃ ፍቃድ እንደገና አውጡ ማለትም ተገቢ አይደለም ይላሉ::
በተጨማሪም ባለስልጣኑ ከተማው ላይ በኮድ -3 በሞተር ሳይክል አንድ ሰው ማጓጓዝ እንዲቻል የትራንስፖርት አገልግሎት ፈቅዶ፣ በከተማ ትራንስፖርት ድጋፍ ሰጪ ተብለው የተለያዩ ተሽከርካሪዎች የከተማውን ትራንስፖርት እንዲቀርፉ ታሳቢ በማድረግ ተካትተው እንዲሠሩ መደረጋቸውንም ያስታውሳሉ:: እኛን በሥራው ለማሳተፍ ቢያስፈልግ እንዲህ ዓይነት አማራጮች ቢታዩ መልካም ነው ሲሉም ይናገራሉ::
የኤሌክትሮኒክ የታክሲ ስምሪት(የኤታስ) አገልግሎት አሰጣጥ ለመወሰን የወጣው መመሪያ 05/2011 ምን ይላል?
በመመሪያው የተፈጻሚነት ወሰን በሚለው አንቀጽ ስር፤ ይህ መመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ስምሪት መተግበሪያ ስርዓትን በመጠቀም የታክሲ አገልግሎት የማሰማራት ሥራ የሚያከናውኑ ድርጅቶች እና በኮድ -1 የተመዘገቡ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ የታክሲ ማህበራት እና ግለሰብ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል::
ሌሎች ህጎች?
ስለተሽከርካሪ መለያ፣መመሪያና መመዝገቢያ የወጣው አዋጅ ቁጥር 681/20002 ነሐሴ 5 ቀን 2002 ዓ.ም የወጣ አዋጅ ትርጓሜ በሚለው ስር ቁጥር 10 ‹‹የመለያ ቁጥር ሰሌዳ›› ማለት ተሽከርካሪውን በመንገድ ላይ በቀላሉ ለመለየት እንዲያስችል በተሽከርካሪው ላይ የሚደረግ መለያ ቁጥሮች የተጻፈበት ሰሌዳ ነው፤ ብሎ ደንግጓል::
የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሠሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶችን አስመልክቶ የቀለም ኀብርና መለያ ቁጥር/ የፊደላት ጥምርታ በማለት በትርጉም አስደግፎም አመልክቷል:: በተራ ቁጥር አንድ የታክሲ በሚለው ስር ነጭ መደብ ከቀይ ፊደላትና ቁጥሮች ጋር፣ በግራ ክንፍ በኩል በቀይ ክብ ውስጥ ‹‹1›› ቁጥር መለያ የተጻፈበት መሆኑን አመልክቶ፤ በትርጉም ክፍሉ በታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ተሽከርካሪዎች የሚሰጥ መሆኑን አስቀምጧል::
በሌላ በኩልም በሦስተኛ ተራ ቁጥር የንግድ ሰሌዳ አስመልክቶ የቀለም ኀብርና መለያ ቁጥር/ የፊደላት ጥምርታ ስር ነጭ መደብ ከደማቅ አረንጓዴ ፊደላትና ቁጥሮች ጋር በግራ ክንፍ በኩል በአረንጓዴ ክብ ውስጥ ‹‹3›› ቁጥር መለያ የተጻፈበት መሆኑን ያመለክታል:: በትርጓሜው ክፍል በንግድ የመንገድ ማመላለሻ ለተመዘገቡ ወይም ለሚከራዩ ተሽከርካሪዎች የሚሰጥ ብሎ አመልክቷል::
በትራንስፖርት ባለስልጣንም አገር አቀፍ የንግድ ተሽከርካሪዎች የኪራይ ትራንስፖርት ደረጃ እና አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 25/2011 በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ወጥቷል:: መመሪያው አሁን በዚህ ጽሑፍ የተነሳው አለመግባባት ከተነሳ በኋላ መሆኑ ልብ ይሏል:: በመመሪያው ‹‹ኪራይ›› ማለት ለሰው እና ለጭነት(ዕቃዎች) ማጓጓዥያነት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን የማከራየት አገልግሎት ማለት እንደሆነ ጠቁሟል:: ‹‹የንግድ ተሽከርካሪ ኪራይ ትራንስፖርት አገልግሎት›› ማለት የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ወስደው የመቀመጫ ልካቸው ከአራት ሰው በላይ ወይም ድርብ ተግባር አገልግሎት የሚሰጡ እና የጭነቱ ልክ ከ10 ኩንታል በላይ የሚጭኑ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማከራየት አገልግሎት መስጠት ማለት ነው ሲል አመልክቷል::
የጋዜጠኛው ትዝብት
የታክሲ አስከባሪ ማህበራት ኮድ ሦስት አሽከርካሪዎች ደንበኞቻቸውን እንዳይጭኑ የመከልከል ተግባራትን ይፈጽማሉ:: አልፎ አልፎ ጉልበት በተቀላቀለበት መንገድ ‹‹ህግ ካልተከበረልን ህጉን በራሳችን እናስከብራለን›› የሚል አካሄድን ተከትለው ህገ ወጥ የሆኑ ተግባራትን ሲከተሉ ታዝቧል::
ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አካባቢ ችግሩ በተደጋጋሚ ይከሰታል የተባለው ስፍራ አንዱ ሲሆን፤ ሁኔታውን ለመመልከት ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም 5:00 ሰዓት ገደማ ወደ ስፍራው ተጉዣለሁ:: በስልክ የጠራሁት ተሽከርካሪ ደርሶ ለመግባት ወደ በሩ ስጠጋ የታክሲ ተራ አስከባሪ ማህበራት አባላት ለሦስት ሆነው በሩን ይዘው እንዳልገባ ከልክለውኛል ተረባርበው ሰድበው አሽከርካሪውን ከአካባቢው እንዲርቅ አባርረውታል:: ምክንያቱን ጠይቄያቸው ‹‹እነርሱ ህጋዊ አይደሉም፤ ህግ ወጥቷል:: መንግሥት ህግ ካላስከበረ እኛ እናስከብራለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል:: ይህ ደግሞ እያደር አጥቂና ተከላካይን በመፍጠር የሰላም ጠንቅ እስከመሆን የሚደርስ ችግር ሊፈጥር ይችላል::
ተመሳሳይ ርቀት አገልግሎት የሚሰጥበት የሁለቱ አገልግሎት የክፍያ ሁኔታም ልዩነት አለው:: ያከፋፈል ስርዓቱ ፍትሐዊና ህብረተሰቡን ያማከለ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል::
የሚደርሱ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን ብዙዎች የነገሩኝ ቢሆንም በዚህ ሰበብ አድርጎ ፖሊስ ጣቢያዎች የተመዘገበ በተሽከርካሪ ላይ የደረሰ ጉዳት፣ ጥቃት፣ ማስፈራሪያ ወይም ዛቻ ካለ አባላቱ መረጃ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ምላሽ አላገኘንም::
ሌላው የተዘበራረቀ ነገር ሆኖ የተመለከትነው ኮድ -2 ተሽከርካሪ ለግልና ለቤተሰብ አገልግሎት እንዲውል ታስቦ የተመዘገበ ቢሆንም የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ መኖራቸውንም መታዘብ ችለናል:: ይህ ደግሞ አገልግሎት ሰጪው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ለስርቆት ሊዳረጉ ይችላሉና ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል:: አገልግሎቱን የሚሰጡት ለመንግሥት ግብር ከፍለውበት ባለመሆኑ ሌላ ገጽታ ይኖረዋልና ከሚመለከተው አካል ቁጥጥር ያሻዋል::
ህጉ እንዲከበር የተኬደበት
የተሳሳተ መንገድ
ህግን ለማስከበር በተሰጠ ስልጣን ልክ መሆን አለበት:: ህግ የሚጣስ ከሆነ ህግ የጣሰውን በጉልበት ማስቆም ተገቢ አይሆንም:: ድርጊቱን ለሚመለከተው አካል መጠቆም፣ ማስረጃ ሆኖ መቅረብና ክስ እንዲመሰረት ማገዝ ይቻላል:: እኔ አስቆማለሁ ማለት መስመሩን የሳተ ነው:: ጉልበት መጠቀም ቀጥሎ ወደ ድብድብና ወደ ጉዳት ያመራል ይላሉ ኮማንደር አህመድ::
ዝግጅት ክፍሉም አንድ ሰው በህግ እንዲጠየቅ በህግ የተከለከለ እና በህግ የተፈቀደ ነገር ሊቀመጥ እንደሚገባ ያምናል:: የታክሲ ሥራ መሥራት እንደማይቻልም ተጠቅሶ በህግ ቢቀመጥም እንኳን ማንኛውም ግለሰብ፣ የተደራጀ ቡድን ወይም አካል ተነስቶ ‹‹መንግሥት ህጉን ስላላስከበረልኝ…›› በማለት ህግ ለማስከበር መነሳት ተገቢነት የሌለው ህገ ወጥነት ነው:: በየደረጃው ህግን ለማስከበር ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት ሊተው የሚገባ ጉዳይ ነው:: የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ቢኖር ህግ ተጥሶ ቢገኝ እንኳን ህግ ለማስከበር ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት ጉዳዩን መጠቆም ነው::
በእዚህ ጉዳይ ድርጊቱ ልክ ነው ወይም አይደለም ማለት የሚችሉት የትራፊክ ፖሊስና የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አካላት ብቻ መሆናቸው ግንዛቤ ተይዞ ህጉን ለማስከበር በሚመስል መንገድ የሚደረጉ ያልተፈቀዱና ህገ ወጥ ድርጊቶች እንዲቆሙ የሚመለከተውም አካል በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን::
አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 24/2012
ዘላለም ግዛው