አዲስ አበባ፦ ባህላዊ መድሃኒቶች ከዘመናዊዎቹ ጋር ተቀናጅተው ለታካሚዎቻቸው የሚታዘዙበት አሰራር ሊኖር እንደሚገባ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ::
በኢንስቲትዩቱ የባህላዊና ዘመናዊ መድሃኒቶች ምርምር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ተካ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ጥናት ተደርጎባቸው ጥራትና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ የባህል መድሀኒቶች ለታካሚዎች እንዲደርሱ የጤና ባለሙያዎች ከዘመናዊዎቹ መድኃኒቶች ጋር እያቀናጁ የሚያዝዙበት አሰራር ሊፈጠር ይገባል::
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ ባህላዊ መድሀኒቶቹ ከዘመናዊው ጋር ተጣምረው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ኢንስቲትዩቱ ጥናት እያደረገ ይገኛል፤ በአሁኑ ወቅት ሙከራቸው የተጠናቀቁ ስራዎች ያሉ ቢሆንም ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ የሚያስችል ኢንደስትሪ ባለመኖሩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል::
‹ ‹ ኢ ን ዱ ስ ት ሪ ው አልደገፈንም ብለን ስራ አላቆምንም›› ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በሚቀጥሉት አመታት በኢንስቲትዩቱ ግቢ ውስጥ በተዘጋጀ ህንጻ ምርምራቸው የተጠናቀቁ መድሃኒቶችን ህብረተሰቡ እንዲያያቸው ለማድረግ እቅድ መያዙን፤ በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶችም ተሳትፎአቸውን የሚያሳዩበት እንደሚሆን ተናግረዋል::
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ፤ የኢንስቲትዩቱ ዋና አላማ በመድሃኒቶቹ ላይ ጥልቅ ምርምር በማድረግ የመጨረሻ ግቡ ፈዋሽነታቸውና ጥራታቸው ተረጋግጦ ወደ ህብረተሰቡ የሚደርሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው ፤ ከዚህ አንጸር የዘመናዊና የባህላዊ ህክምና ባለሙያዎች አብረው እንዲሰሩ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ ሲሆን፤ ጤና ሚኒስቴር እንደ ሌሎች የአለም አገራት ሁሉ ባህላዊ መድሀኒቶችን ከዘመናዊዎቹ ጋር አስተሳስሮ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ አስቀምጧል::
ዳይሬክተሯ የባህል ህክምና ሚስጥርነቱ ሰፊ ቢሆንም ኢንስቲትዩቱ ከባህል ህክምና ባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በምርምሩ ላይ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም መድሀኒቶቹ ወደ ማዕከሉ መጥተውና በምርምር ተደግፈው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለባለሙያዎቹ በማህበራቸው አማካይነት ስልጠና የሚያገኙበትና ሌሎች ድጋፎችም እንደተመቻቹላቸው ተናግረዋል::
ጤና ሚኒስቴር በተያዘው ዓመት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የባህል ህክምና ፍኖተ ካርታ ይፋ ያደረገ ሲሆን ፤ ለባህል መድሃኒት አዋቂዎች ስልጠና በመስጠት߹ የመድሃኒቶቹን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ማዕከል ግንባታ በመፍቀድና ግብዓቶችን በማሟላትም እገዛ ማድረጉን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል ::
ዳይሬክተሯ ‹‹የባህል መድሃኒቶቻችንን አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምባቸውና የካበተ ሀብት ያለን ብንሆንም የተሰጠው ትኩረት በቂ ነው ብዬ አላምንም ፤ በዚህ ውስን ስራችን መድሀኒቶቹን ለመላው ህዝብ ተደራሽ እናደርጋለን ብሎ ማሰብ ከባድ ነው:: ስለዚህም የባህል ህክምናው በኢንስቲትዩት ደረጃ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም በማድረግ ሰፊ ስራ መሰራት አለበት ” ብለዋል::
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባህላዊና ዘመናዊ መድሃኒቶች ምርምር ዳይሬክቶሬት በዘመናዊና ባህላዊ መድሀኒቶች ላይ ሰፊ የምርምር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ፣የባህል መድሃኒቶች ፍቱንነታቸውን፣ ደህንነታቸውንና ጥራታቸውን የማረጋገጥ ሥራም እንደሚሰራ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል::
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012
እፀገነት አክሊሉ