አዲስ አበባ፡- ከሐምሌ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የጄ.አይ.ጄ የደመወዝ ክፍያ ማስተካከያ እንዲደረግ የተፈቀደ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ባለመሆኑ ቅር መሰኘታቸውን መምህራን ገለጹ::
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው መምህራን “የጄ.አይ.ጄ ማስተካከያው ከሐምሌ ጀምሮ ይተገበራል የሚል መረጃ ደርሶን የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በምን ምክንያት እንደዘገየ አልገባንም፤ ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ ከመጀመሪያውም ወሬውን ባንሰማ ይሻል ነበር” በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች ከሰሞኑ የደመወዝ ማስተካከያው እንደተሰራላቸው የጠቆሙት መምህራኑ፤ “የእኛም በአፈጣኝ ሊስተካከልልን ይገባል፤ መንግስት ከፈቀደ በኋላ ተፈጻሚ የማይሆንበትን ምክንያት የሚመለከተው አካል ሊያሳውቅ ይገባል” ብለዋል::
የዝግጅት ክፍላችን ደውሎ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት በበኩላቸው፤ “ጄ.አይ.ጄውንም ሆነ ማንኛውንም የመምህራን ጥቅማ ጥቅም በተመለከተ የቢሮው ኃላፊነት ጥያቄ ማቅረብ ነው፤ ይህንንም አድርጓል፤ ከዚህ ባለፈ ቢሮው ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የለውም:: ውሳኔ የሚሰጠው አካል ሌላ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል::
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ሪፖረተር ቅሬታውን ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሲያቀርብ “ይህንን ጉዳይ የሚመለከተው ኮሚሽነሩ ነው፣ ወደ ኮሚሽነሩ ቢሮ ሲደወል ደግሞ የህዝብ ግንኙነቱን ጠይቅ” በሚል ምላሽ ሳይሰጡ ለቀናት ካስጠበቁት በኋላ በመጨረሻ “ኮሚሽነሩ የሉም፣ እርሳቸው ከሌሉ ደግሞ መረጃውን ማግኘት አትችሉም” በማለት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል::
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012
ይበል ካሳ