አዲስ አበባ፦ አገሪቱ ከስጋና የስጋ ተዋጽዎ ውጤቶች ማግኘት የነበረባት የውጭ ምንዛሬ በአቅርቦት እጥረትና በተከሰተው ግጭት ምክንያት ዝቅተኛ መሆኑን የእንስሳት፣ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደበሌ ለማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የእንስሳት ሃብቱ ከአገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች በተለይም ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ከሱማሌ ክልል የሚገኝ ቢሆንም፤ በግጭት ምክንያት መንገዶች በመዘጋታቸውናለገበያ ባለመቅረቡ፤ ሥጋን በሚፈለገው ደረጃ ለዓለም ገበያ በማድረስ ከዘርፉ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልተቻለም።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከዓለም ስድስተኛ፤ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም አርብቶ አደሩ የዓለም ገበያን መስፈርት መሰረት አድርጎ ባለማምረቱ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ጫና አሳድሯል።
ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሃብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን አርብቶ አደሩ የዓለም ገበያ የሚጠይቀውን የእንስሳት አረባብ መስፈርት አሟልቶ እንዲያረባ ስልት መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት፤ የአረባብ ዘዴውም ገበያ መር እንዲሆን ማስቻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁና ትላልቅ የእርድ እንስሳት ማርቢያ ቦታዎች ማዘጋጀት፣ ለግብርናና ለስጋ የሚሆኑ እንስሳትን ለይቶ ማርባትና ሌሎች ሊሟሉ የሚገባቸውን ነገሮች ማሟላት ካልተቻለ ከእንስሳት ሀብት ተጠቃሚ መሆን እንደማይቻልም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል ።
ዳይሬክተሩ በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የወተት ፍላጎት ለማሟላት አርብቶ አደሩ የሚያመርተው ብቻውን በቂ ስላልሆነ ትላልቅና ዘመናዊ የወተት ልማት ኢንዱስትሪዎች የሚስፋፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በመንግስት በኩል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በወተትና ስጋ ምርታማነቷ በእንስሳት ሀብታቸው ዝቅተኛ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች በታች መሆኗን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የግብርናው አለመዘመንና የእንስሳቱ ዝርያ የአካላቸው መጠን አነስተኛነት መሆን ምርታማነቱን ዝቅተኛ እንዳደረገው፤ ይህን ለማሻሻልም ግብርናውን በማዘመን ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የተቋሙ የዘንድሮው ሩብ ዓመት አፈፃጸሙ የእቅዱን 64 ነጥብ አራት በመቶ ሲሆን፤ ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር 23 ነጥብ ሰባት በመቶ መቀነሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ