“…ሁላችሁም ተማሪዎች ወገባችሁን አጥብቃችሁ ታጠቁ፤ ሀገራችሁና ወገናችሁ እየጠበቋችሁ ነው። ጊዜ የለንም ፍጠኑ። ከትናንቱ እጅግ ዘግይተናልና ለነገ መፍጠን አለብን። መሮጥ እንጂ መሄድ ብቻ አያዋጣንም። ለአልባሌ ነገር ጊዜ የለንም። ጊዜው የትምህርት፣ የሥራና የሀገር ግንባታ ነው…”።
ይህንን አባታዊ ምክር ሰንቀው፤ ነገን ተመላክተው፤ የፍጥነት ወሰን ተበጅቶላቸው፤ ጊዜውም ተበይኖላቸው፤ ምርቱና ግርዱ ተነግሯቸው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እየገቡ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የአገራችን ነገዎች ናቸው። ናቸውናም የሚታጠቁት እውቀትና ክህሎት ብቻም ሳይሆን ደህንነታቸውም ያሳስበናል፤ ይመለከተናል። ስለሚያሳስበን ስለሚለከተንም ጭምር ብዙ ብንል ብዙ ጊዜ ትክክል ነን። የአገሪቷ ርዕሰ ብሄር መልዕክት ማዕከላዊ ጭብጡም ይሄው ነውና።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ይድረስ ለነገዎች” ሲሉ በተያዘው ወር መጀመሪያ ላይ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያስተላለፉትን መልዕክት ልብ ብሎ ላጤነና ቁብ ለሰጠ ሁሉ ነገን አሻግሮ መመልከት አያዳግተውም። ነገ የሚታጨደው ዛሬ የተዘራው ነው። ዛሬ በዩኒቨርስቲዎቻችን የምንዘራው ፍሬ ነገ ባሰብነው ልክ ጎተራችንን የሚሞላው አብዝተን ተጨንቀን አብዝተንም ደክመን ከሰራን ብቻ ነው።
ይሄንን በአግባቡ የተረዳ አገርና ህዝብ ዛሬ አብዝቶ ስለ ነገ ያስባል፤ ይጥራል፤ ይግራልም። ትናንት አብዝተው ስለዛሬ የደከሙ አገራት፤ እነሆ አሁን ላይ የተሻለ ዛሬ ባለቤቶች ናቸው። በዚህም ሳይዘናጉ ነገንም ያማረ ለማድረግ ዛሬ ሲታትሩ መመልከት ብዙም እንግዳ ነገር አይደለም። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይድረስ ለነገዎቹ ሲሉ መልዕክት ከትበው ማድረሳቸው ይሄንኑ እውነታ አበክረው ስለተረዱም ጭምር ነው።
ትናንት ዩኒቨርስቲዎቻችን የፖለቲካ መናኸሪያ እስኪመስሉ ድረስ በግልጽ የፓርቲ ፖለቲካ ስራ ሲሰራባቸው ታዝበናል። ይሄ ወደየትም የማንደብቀው የአደባባይ ገበናችን ነው። ለእውቀትና ለክህሎት ወደዩኒቨርሲቲ ይላኩ የነበሩ ተማሪዎች የማያውቁት ጠባብ ብሄርተኝነትና ፖለቲካ ተመርቆላቸው “ተመረቃችሁ” ተብለው ሲወጡ ኖረዋል። ይሄ አካሄድ ዛሬ ላይ ለምንመለከተው ዓለምን እያስደመመ ላለው አገራዊ ለውጥ እንኳን ሳይቀር የሚገዳደር ትውልድ ፈጥሮብናል። መንግስት ዘግይቶም ቢሆን ይሄንን የአካሄድ ዝንፈት ሰለተረዳ “ከዚህ በሁዋላ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት እንጂ የፖለቲካ ማራመጃ ቦታዎች አይደሉም” ሲል የብልህ ውሳኔ አስተላልፏል። ይሄ ነገን አሻግሮ ለሚመለከት ባለራዕይ መሪ፤ ስለ ነገም “ተስፋ አለኝ” እያለ በአደባባይ በልበ ሙሉነት ቃል ለሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ልኩም መልኩም የሆነ ውሳኔ ስለሆነ ይበል ሊባል፤ እውቅናም ሊሰጠው ይገባል።
የየትኛውም ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ተግባር፤ ትምህርት፤ ሁለተኛው ተግባር ትምህርት፤ ሶስተኛውም ትምህርት መሆን አለበት። ቀን ቀን የአስተሳሰብ አድማስን የሚያሰፋ ትምህርት፤ ማታ ማታ አድማስ አጥባቢና አጥፊ ትምህርት መስጠት ከዚህ በሁዋላ አይሰራም። በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ቀን ቀን የአካዳሚ እውቀት ማታ ማታ የፓርቲ ስብከትም በቃህ ሊባል ጊዜው አሁን ነው። ይህ ማለት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፖለቲካ ተሳትፎ አይኑራቸው፤ ስለአገራቸው አይወያዩ አይወቁ አይረዱ ማለት አይደለም። ሁሉም ቦታና ጊዜ ይበጅለት ለማለት እንጂ። ስለሆነም ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የወላጆች ትልቅ ኢንቨስትመንት፤ የመኖራቸው አልፋና ኦሜጋ የሆኑ ልጆቻቸውን በሀላፊነት ተረክበው ተገቢውንና ዋናውን ስንቅ ሊያቀብሏቸው የግድ ይላል። ይሄንን አለመረዳት፤ ወይንም ተረድቶ ቸል ማለት ሊያስወቅስ ሊያስጠይቅም ይገባል።
ልዩነታችን ውበታችን እንጂ ልዩነታችን የመለያየታችን ዳር ሆኖ ሊያጣላን አይገባም። መጣላት ካለብንም እንደ አገር አንድ እንዳንሆን ከሚገዳደረን ውስጣዊ ማንነታችን ጋር ብቻ መሆን አለበት። ሁልጊዜም እንደተማረ ሰው ሳይሆን የተማረ ሰው መሆን ይኖርብናል። “…የተማረ ሰው ማለት ከሌሎች ጋር ሲኖር ልዩነቶችን በሠለጠነና ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ ለመፍታት የሚችል፤ ችግሮችን በመጠናቸው ልክ የሚረዳና መፍትሔ የሚያፈልቅ፤ የራሱን ስሜትና ጠባይ እንዴት ማስተዳደር እንደሚችል የሚያውቅ፤ የሥራና የኑሮ ሥነ ምግባር ያለው ነው” ሲሉ እንድንለወጥ ምክር የለገሱትን የለውጡን መሪ ምክረ ሀሳብ ማስታወስም አስፈላጊ ነው።
ማንም መርጦ ባልያዘው፤ ፈልጎ ባላገኘው ብሄሩ የተነሳ መጋጨት ከራስ ጋር መጣላት መሆኑን ማወቅ አዋቂነት ነው። ይህንን እውነታ ባለመረዳት ትናንት እኛን የማይመስሉ ብዙ ገበናዎች አደባባይ ወጥተውብናል። አዝነናል፤ አንገታችንንም ደፍተናል። ብልህ ሰው ከሰው ይማራል፤ ሞኝ ደግሞ ከራሱ። ስለሆነም ብልህ ሆነን እኛ ከወደቁ አገራት መማር ካቃተን፤ ሞኝ ሆነን ከራሳችን የትናንት ስህተታችን ልንማር ይገባናል። ከራሳችን መማር ካልቻልን ግን ሞኝ ለመሆን እንኳን አልታደለንም ማለት ነው። ስለሆነም ከትናንቱ ተምረን ዛሬን አርመን ነገን የተሻለ ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው።
“…ፍጠኑ ጊዜ የለንም…” የተባላችሁ የአገር ነገዎችም አገራችሁ እየጠበቀቻችሁ መሆኑን አጢናችሁ ምርቱን ከግርዱ ለይታችሁም ጭምር ሙሉ ሰው ሆናችሁ ውጡልን። ይህ የሚሆነው አገር ሰላም መሆኑን ለአፍታም ያህል ሳትዘነጉ ዛሬም ነገም፤ ጥሁዋትም ቀንም ሆነ ማታ ተማሩ! ተማሩ! ተማሩ።