የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ዘመን ለጋስ ሆኖ በኪራይ ቤቶች ዋጋ ላይ እጁን አሳርፎ አያውቅም፡፡ በዚህ የተነሳም የኪራይ ዋጋው ደርግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ እንደተከለው ሆኖ ቆይቷል፡፡ በእዚህም በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በወር የሚከፈለው ኪራይ መንግሥት ቤቱን ሠርቶት ቢሆን ኖሮ ያንን አይነት የኪራይ ዋጋ አያስቀምጥም ነበር፡፡ የወረሰው ቤት ስለሆነ ግን በነጻም ቢሰጥ ችግር የለበትም፡፡ ኪራዩን በዓመት አጠራቅመው ቢከፍሉት እንኳ አያምም፡፡
ኮርፖሬሽኑ በቁጭት የተነሳሳ ይመስል በቅርቡ በንግድ ቤቶች ኪራይ ዋጋ ላይ ተከራዩን ክፉኛ ያነጋገረ ጭማሪ አድርጓል፡፡ በእርግጥ ተከራዮች ክፉኛ ተደናግጠዋል፤ ተንጫጭተዋል፡፡ ለነገሩ የጭማሪው መጠን ከፍተኛነት ሲታሰብ ለሰሚውም ቢሆን ግራ ያጋባል፡፡
የመንግሥት ቤት የግል ቤት ያህል ነው፡፡ የኪራዩ ርካሽነት ብቻም ሳይሆን በብዙ መልኩ ምቹ ነው፡፡ ይህን ምቾት ምናልባትም ሊያስከትል የሚችል እርምጃ ሲመጣ አሜን ብሎ መቀበል ለማንም ይከብዳል፡፡ እነዚህ ተከራዮች የተከራዩበት ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ለሰዎች ሲገልጹ ጮክ ብለው የሚናገሩ አይመስለኝም፣ ቀስ ብለው ‹‹የሠይጣን ጆሮ አይስማ›› ብለው የሚናገሩም ነው የሚመስለኝ፡፡ አሁን ይህ እርምጃ ሲመጣ ቢደናገጡ የሚይዙት የሚጨብጡት ቢያጡ ብርክ ቢይዛቸው አይገርምም፡፡
የመንግሥት ቤት እንዴት አይመች፡፡ አራት ኪሎ እምብርት ላይ የሚገኝ አንድ የተንጣለለ ካፌ በወር ከአንድ ሺ ብዙም ያልዘለለ ኪራይ እየከፈለ ብር እንደቅጠል ሲሸመጥጥ ኖሮ በአንድ ጊዜ በአዲሱ የኪራይ ዋጋ በወር ከ40 ሺ ብር በላይ እንዲከፍል ሲጠየቅ እንዴት ዝም ብሎ ሊቀበልስ ይችላል፡፡ በወር ከ70 ሺ ብር በላይ ተጠየቅሁ ያለ የመንግሥት ሲኒማ ቤትም እንዳለም ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሰምቻለሁ፡፡
እነዚህ ወገኖች ሁሉ የኪራዩ ጭማሪ በጣም አስቆጥቷቸዋል፡፡ በእርግጥም የቁጣው መጠን ይለያይ ይሆናል እንጂ ያስቆጣል፡፡ እንዲያም ሆኖ ታዲያ በኪራይ ዋጋ ጭማሪው ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው ተከራዮቹ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
እንደሚታወቀው የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቶች ሲጠቅሙ የኖሩት ቤቶቹን ከሠሯቸውና ከተወረሱትም ፣ ከወረሳቸው መንግሥትም (እዚህ ላይ መንግሥት የሠራቸው ቤቶች እንዳሉም ልብ ይሏል) በላይ ተከራዮችን ነው፡፡ ቤቶቹ በትርፍ ቤትነት የተወረሱትም በመሬት ላራሹ አርሶ አደሩን መጥቀም እንደታቻለ ሁሉ እንደ መሬት ላራሹ ተከራዮችን ለመታደግ የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡
አሁንም ደግሜ አነሳዋለሁ፤ አራት ኪሎ እምብርት ላይ የተንጣለለ የንግድ ቤት ከዘመኑ የንግድ ቤት ኪራይ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ በማይባል ኪራይ ይዞ ከመሥራት በላይ ለዚህ ምን ማሳያ ሊኖር ይችላል፡፡ እርግጠኛ ነኝ እነዚህ ተከራዮች ለአከራዩ ካልሆነ በቀር በዚህን ያህል ብር ነው የተከራየሁት ብለው አውርተው የሚያውቁም አይመስለኝም፤ ቢያወሩ የሚቀሙ ያህል ሊሰማቸውም ይችላል፡፡
በተለይ የቤት ኪራይ ዋጋ በናረበት አዲስ አበባ ከተማ መሀል ላይ ለሰሚው ግራ በሆነ ገንዘብ ተከራይቶ መሥራትም ሆነ መነገድ በእጅጉ መታደል ነው፤ በየወሩ የሚወጣ ሎተሪ ማለትም ነው፡፡ ቦሌ መንገድ፣ ስታዲየም እና መስቀል አደባባይ አካባቢ ያሉ የመኖሪያ አፓርታማዎች እኮ ከ200 ብር ብዙም እልፍ ባላለ ገንዘብ ነው የሚከራዩት፡፡ ከዚህ በላይ ተጠቃሚነት ከየት ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ጠባብ ቤቶች ፣ በዶክተር አርከበ እቁባይ የአዲስ አበባ ከንቲባነት ዘመን በአነስተኛ ጥቃቅን ለተደራጁ ዜጎች ተሠርተው የተላለፉት በተለምዶ ‹‹አርከበ ሱቅ›› የሚባሉት ዛሬ ሦስትና አራት ሺ ብር እየተከራዩ ባሉበት ሁኔታ የተንጣለለ የኮርፖሬሽኑ ቤቶች በእዚህን ያህል መጠን መከራየታቸው መንግሥት በቤቶቹ ዙሪያ ሥራውን በተገቢው መንገድ ይሠራ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የኮርፖሬሽኑ ተከራዮች ይህን በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ይህን የሚያውቅ ታዲያ ቅሬታውን ለሚመለከተው አካል ማቅረቡ መብቱ ቢሆንም ተረጋግቶ ማቅረብ ግን ይኖርበታል፡፡ መረጋጋቱ በቤቱ ምን ያህል ሲጠቀም እንደኖረ ለማሰብ የሚያስችል በመሆኑ ብዙም ቁጣ የተቀላቀለበት ቅሬታ ውስጥ እንዳይገባ ያደርጋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት ብዙ ሠራተኛ እንደሚያስተዳድሩ፣ ግብር እንደሚከፍሉ ወዘተ ገልጸው፣ አስተያየት እንዲደርግላቸው መጠየቃቸው ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ ‹‹ቅሬታው ካልታየልን ሠራተኛ እንበትናለን›› እያሉ ማስፈራራት የሚመስል ነገር ውስጥ መግባታቸው ግን ትክክል አይደለም፡፡
የገበያ ዋጋ በማያውቀው የኪራይ ዋጋ በነጻ ሊባል በሚችል መልኩ እየተከራየን እየሠራን በመሆኑ ብለው ለሠራተኞቻቸው ጥሩ ደመወዝ ያልከፈሉ የቤቶቹ ተከራዮች፣ የሠራተኛን ጉዳይ ከፊት ይዘው እንዲሁም ግብር ለመክፈል እንደሚቸገሩም ጭምር በመጥቅስ ቅሬታ ለማቅረብ መነሳታቸው አግባብም የሚያዋጣም አይሆንም፡፡
ይባስ ብለው ውሳኔው በአሁኑ ወቅት መንግሥትን እንድናማርር የሚያደርግም ነው ሲሉም ተደምጧል፤ ምንድነው እሱ ይህን ሲሉ እንግዲህ ጉዳዩን ‹‹ፖለቲሳይዝ›› ማድረጋቸው (ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋላቸው) ነው፡፡ ቤቶቹ እንዲሁ ‹ፖለቲሳይዝ›› ሲደረጉ ነው የኖሩት፡፡ ይህ ቢሆን አይደንቅም፡፡
እነዚህ ሰዎች የኪራዩን ዋጋ ያውቁታል፡፡ አጠገባቸው ከግለሰብ ተከራይተው የሚሠሩ ሰዎች አያውቁም ተብሎም አይጠበቅም፡፡ በዚህ ውሳኔ አቧራ ለማስነሳት መሞከር ታዲያ ምን ይሉታል፡፡ እርምጃውን እንደሚቀበሉት ጭማሪው ግን የማይችሉት መሆኑን እንደጠቀሱ ሁሉ ጭማሪው እንደገና ይታይልን፣ አከፋፈሉ ላይ አስተያየት ይደረግልን ብለው ቢጠይቁ አግባብ ይሆናል፡፡
በምንሰጠው አገልግሎት ላይም ዋጋ እንጨምራለን የሚል ማስፈራሪያም ሲሰጡ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ይህም ትክክል አይደለም፡፡ መጀመሪያ ውንም ቢሆን የመንግሥት ቤት ውስጥ ነን ብለው ያደረጉት የዋጋ ቅናሽ ስለሌለና ሲሸጡ የኖሩትም የአካባቢውን ዋጋ መሰረት አድርገው እንደመሆኑ አሁን ማስፈራራት ውስጥ መግባት የለባቸውም፡፡
ደንበኞቹ ከ40 ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከመሸጥ መለወጥ በቀር ቤቶቹን ተጠቅመውባ ቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ቤቶች በቁልፍ ሽያጭ ሰበብ ከአንዱ ወደ አንዱ እየተላለፉ ጥቅም ሲሰበሰብባቸው መኖሩ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አሁን አሁን አላውቅም እንጂ ክፍል ቀይሰው ወይም ሙሉ ለሙሉ በውስጠ ታዋቂ የሚያከራዩም ነበሩ፡፡
ከዚያ በመለስ ተከራዮቹ ለበርካታ ዓመታት ያለጠያቂ ገበያው ከሚጠይቀው በታች በሆነ ዋጋ በውላቸው መሰረት ሲከፍሉ ኖረዋል፤ ጥፋት የለባቸውም፡፡ አሁን መንግሥት የባነነ ይመስለኛል፡፡ እነሱም መንግሥት ገበያን መሰረት ያደረገ ጭማሪ ሲያመጣ ሲሆን ሲሆን መንግሥትን አመስግነው ነው ወደ ቅሬታ ማቅረብ ያለባቸው፡፡
መንግሥት ኖሮ ኖሮም ቢሆን ወደ ትክክለኛው አሰራር መምጣቱ መልካም ነው፡፡ በአንድ ጣሪያ ስር የሚገኙ ሁለት ቤቶች አንዱ የግለሰብ ሌላው የመንግሥት በመሆናቸው ሳቢያ አንደኛው ቤት ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ ሲከፈል ሌላው በነጻ የሚያሰኝ አይነቱን ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ ይህ ኢ-ፍትሃዊ አሰራር ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ በተገነቡ እና በመንግሥት እጅ ባሉ በተመሳሳይ አካባቢ በሚገኙ ቤቶች መካከል ያለው ልዩነትም የትየለሌ መሆኑን ያስቀረዋል፡፡
ከዚህ በተረፈ ሀገሪቱ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋት ማወቅም ይገባል፡፡ ይህን አይነቱን ገቢ መሰብሰብ ባልተቻለበት ሁኔታ የሀገሪቱ ገቢ ቀነሰ ብሎ መናገርም ትክክል አይደለም፡፡ ቤቱ የመንግሥት ቢሆንም ግፍ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለማደሻ የማይሆን ኪራይ እየተከፈለ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ተኖሮበታል፡፡ መንግሥታት ለፖለቲካም ይሁን ሌላ ዓላማ ሲሉ ቤቶቹን ዘንግተዋቸው ኖረዋል፡፡ መንግሥት አሁን አስቦበት መነሳቱ ሊደነቅ ይገባል፡፡
በንግድ ሥራም ሆነ በመኖሪያ ቤት ተከራይቶ የሚያውቅ ይነስም ይብዛ የተከራይ ችግር ይገባዋል፤ በተከራይ የሚጨክንም የሚቀልድም አይመስለኝም፡፡ ቤት ሠርቶ ከኪራይ የወጣም ቢሆን በእንዲህ ያለው እሳት አይጫወትም፡፡ እነዚህ ወገኖች ቤቱን ልቀቁ አልተባሉም፡፡ ቀስ ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡ ጥያቄውን በየደረጃው ላለ አካል ቢያቀርቡም ጥሩ ነው፡፡
እኔ የማምነው ሲሆን ሲሆን በቃንን አናውቅም እንጂ እኛ ሰው ሆነንበታል፤ ሌሎች ደግሞ ይጠቀሙበት፤ የመንግሥት ሀብት ነው ቢባል መልካም ነበር፡፡ ለእዚህ የተቀመጠ ህግ የለምና ይህ ይቅር፡፡
አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ለተወሰነ ዓመት ብቻ ማምረቻዎችን ተጠቅመው እነሱ ሰው ሲሆኑ፤ ማምረቻዎቹ ለሌላ እንደሚተላለፉ ህግ እያለ ባልተፈጸመበት ሁኔታ እነዚህ ተከራዮች በሌለ ውል ይህን የጽድቅ ሥራ እንዲሠሩ አይጠበቅም፡፡ አሁን የሚሻለው በጭማሬው ቅሬታ የለንም እንዳሉት የሆነውን ተቀብሎ ቅናሽ እንዲደርግላቸው መጠየቅ እንዲሁም በአፈጻጸሙ ላይ መነጋገሩ ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡
ኪራዩ በገበያ ዋጋ ተመርቶ አያውቅምና ገበያ መጎብኘቱ ጥቅሙ ለሀገርም ጭምር ነው፡፡ ዜጎች ፍትሃዊ በሆነ አግባብ እንዲታዩም ያስችላል፡፡ የቤቶቹ ኪራይ ለእድሳት እንኳ የማይበቃ ነው፡፡ የቤቶቹን የውስጥ ክፍል ቀለም ነክ የሆኑትን ተከራዮቹ በራሳቸው ፍላጎት ሲያድሱ ይስተዋላል፡፡ ከውሃ ከመብራት ከመጸዳጃ ቤት እና ከመሳሰለው በተለይ ደግሞ አፓርታማዎች ከሆኑ ከአጠቃላይ የውጭ ቅብ ጋር የተያያዙት እድሳቶች የሚደረጉት በመንግሥት ቢሆንም እድሳቱ ግን እንዳልኩት ከልብ የሚደረግ አይደለም፡፡
የኪራይ ቤቶች ጭማሪ ተገቢ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ግን ጭማሪው የሚደረግበት ጊዜ በምዕራፍ በምዕራፍ እየተከፋፋለ ቢደረግ ግን ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ለምሳሌ ለዓመት ወይም ለስድስት ወር ከዚያም ደግሞ ሌላ የጊዜ ገደብ እየተባለ የታሰበው የጭማሪ መጠን ላይ እንዲደርስ ቢደረግ ጥሩ ነበር፡፡
ኮርፖሬሽኑ ጭማሪውን ያደረገው በጥናት ላይ ተመስርቶ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ጥናቱን መተግበር ላይም ተሞክሮዎችን መመልከት ነበረበት፡፡ ይህን ውሳኔ ሲያሳልፍ እንዴት መፈጸም እንዳለበትም ማጤን ነበረበት፡፡ ሌሎች ድርጅቶች ትንሽ ወጣ ያለ አዲስ ታሪፍ ይዘው ሲመጡ ስለሚፈጽሙበት መንገድም ያስባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቅርቡ ታሪፉን በአራት እጥፍ እንደሚያሳድግ ይፋ ሲያደርግ ያልተቆጣ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ታሪፉን በምዕራፍ በምዕራፍ እንደሚተገብር ጠቁሞ፣ የሚመለከታቸውን አካላት አስታውቆ ነው ወደ ትግበራ በመግባቱ ቁጣው ረግቧል፤ በርዷል፡፡
ኮርፖሬሽኑም ይህን መንገድ መከተል ይኖርበታል፡፡ ይህን በመተግበር ቀስ በቀስ ወደሚፈ ልገው ዋጋ መግባት ይችላል፡፡ ይህም ቅሬታውን ይቀንሰዋል፡፡ ይህን ሳያደርግ ትግበራውን ከቀጠለ እርምጃው ለዓመታት ያጣውን ገንዘብ በአንድ ጀምበር ለመሰብሰብ እንደማሰብ ይቆጠራል፡፡ እናም እርምጃው የኮርፖሬሽኑን መነቃቃት የሚያመለክት እንደመሆኑ ለዘመናት የዘለቀን የአሠራር ችግር በአንዴ ለመፍታት ሲሞከር በደንበኞች ላይ የሚያስከትለውን ጫናም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የሚሠራው ለሀገር ለዜጎች ነው፡፡ እርምጃውን በሂደት ቀስ በቀስ የሚተገበር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
ዘካርያስ