“ተስፋ መቁረጥ ትልቅ ውድቀት ነው ። ” ጃክ ማ
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ የኢህአዴግን ውህደት በግንባሩ ምክር ቤት መፅደቅን እና የአዲሱ ውህድ ፓርቲ ስያሜ ” የብልፅግና ፓርቲ ” መሰኘቱን በነገሩን ወቅት “… ብልፅግናን ለኢትዮጵያ በቁስ ብቻ ሳይሆን በክብርም በነፃነትም በሁለንተናዊ መልክ ማረጋገጥ ነው ። … ” ብለው ነበር ። ይህን ባሉን በቀናት ልዩነት በዓለማችን በዲጂታል / በኤሌክትሮኒክ / ግብይት ታዋቂ የሆነውን ፤ የቻይና አንደኛውን ቢሊየነር እና የአሊባባ መስራችና ባለቤትን ጃክ ማ ወደ ሀገራችን በማምጣት አከበሩን ።
ሀገራችንንም ሆነ ዜጎቿን በክብርም በቁስም የማበልፀጉን ሥራ አሀዱ ብለው ጀመሩ ። በፓርቲው ውህደት ማግስት የተከናወነ የመጀመሪያ እና ፋና ወጊ የብልፅግና ጉዞ ስለሆነ ነው አሀዱ ያልሁት ። በክብር የማበልፀጉን ሥራማ በአደባባይ የጀመሩት በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ለፓርላማው ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ‘ ኢትዮጵያ ‘ የሚለውን ንዑድ ቃል ከወደቀበት በክብር አንስተው ደጋግመው የጠሩት ጊዜ እና ” ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን ። “ያሉ ጊዜ ነው ።
ጃክማ የአሊባባን ቅርንጫፍ ከሩዋንዳ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ለመክፈት መወሰኑ እና ሌሎች ሶስት ስምምነቶችን መፈራረሙ እጅግ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የሚያረጋግጥ ከመሆኑ ባሻገር የቴክኖሎጂ ፣ የዕውቀትና የክህሎት ሽግግርን ያሳልጣል ። በሁከት እና በአጉራ ዘለልነት ጠልሽቶ የነበረውን የሀገራችን ገፅታ መልሶ እንዲያገግም በማድረግም ትልቅ ሚና ይጫወታል። ዛሬ በዓለማችን አሉ የሚባሉ ኩባንያዎች የፋይናንስ መናኸሪያዎች ጃክ ማን ሸሪክ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ። ጃክን የኒዮርክ፣ የሎንደን፣ የፓሪስ ፣ የዱባይ ፣ የቶክዮ ፣ የጆሀንስበርግ፣ ወዘተ . የሽርክና ገበያዎች ሆኑ ሀገራቱ የፋርስ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው እጃቸውን ዘርግተው በቤተ መንግሥታቸው ደግሰው አደግድገው ጠብ እርግፍ ብለው የሚቀበሉት የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ንጉስና ከዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በቀዳሚነት ስሙ የሚነሳ የቻይና ስኬት ምሳሌ icon ነው ።
አሊ ባባ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ማርሽ ቀያሪ ውል እየተፈጣጠመ ሳለ በሆንግ ኮንግ የሽርክና ልውውጥ ገብያ የአሊባባ የሽርክና ተመን 7 በመቶ በማደግ አዲስ ሪከርድ ሰብሯል ። በዓለማችን በአንድ ቀን በላጤዎች ቀን singles day በኤሌክትሮኒክ ግብይት አሊባባ ያስመዘገበውን ሽያጭ አማዞንና ኢቤይ ተደምረው በቫላንታይስ ፣ በአዲስ ዓመት ፣ በጥቁሩ ሰኞ እና በሌሎች በዓላት ካስመዘገቡት ሽያጭ በላይ ነው ። በአግባቡ ከተጠቀምንበት ከአሊባባ ጋር መስራት በዓለም ገብያ ያለከልካይ የመቅዘፍ ያህል ነው ። ለመሆኑ ጃክ ማ ማን ነው ? ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ በebs ቴሌቪዥን የTeckTalk አዘጋጅ ” ግርምተ ሳይቴክ ” በተሰኘው ድንቅ መፅሐፉ ” ዓለምን የቀየሩ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን 20 ምርጦች ” በሚል ንዑስ ርዕስ እንዲህ ያስነብበናል ።
” … ‘ አሊ ባባ ‘ የተሰኘው ግዙፍ የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ከድሀ ቤተሰብ በመስከረም 1964 ዓ ም ተወለደ ። በትውልድ ስሙ ማን ዩን በፕሮፌሽናል የስም አጠራሩ ጃክ ማ በመባል ይታወቃል ። በበርካታ የህይወት ፈተና ያለፈው ጃክ ማ እንኳን ግዙፍ የሆነ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤት እንደሚሆን ሊያስብ ቀርቶ በሒሳብ ትምህርት ደካማ እንዲሁም እስከጉልምስናው ኮምፒዩተር ባለበት ድርሽ ብሎ አያውቅም። በወጣትነቱ በቱሪስት አስጎብኝነት ተሰማርቶ የነበረው ጃክ ማ በህይወቱ በርካታ ውድቀቶችን አስተናግዷል ።
የኮሌጅ መግቢያ ፈተናን ሶስት ጊዜ ወድቆ በአራተኛው ነበር የተሳካለት ። ኮሌጅ ገብቶ የተማረውም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ነበር ። ከጨረሰ በኋላ ለ30 የተለያዩ መስሪያ ቤቶች አመልክቶ ሳይሳካለት ቀረ ። በአንድ ” KFC ” በሚባል ምግብን በርካሽ የሚሸጥ ምግብ ቤት በአነስተኛ ደመወዝ ለመቀጠር ከ24 ሥራ ፈላጊዎች ጋር አመልክቶ ሁሉም ሲቀጠሩ እሱ ብቻ ሳይሳካለት ቀረ ። ለፖሊስነት ለመቀጠር ተወዳድሮም ወድቋል ። “ተስፋ መቁረጥ ትልቅ ውድቀት ነው ። ” የሚለው ጃክ በዚህ ሁሉ ፈተና እና ውድቀት ቢያልፍም እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ከብዙ ልፋትና ውጣ ውረድ በኋላ ተሳክቶለት በወር 12 ዶላር እየተከፈለው በእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርነት ተቀጠረ ።
በዚህ ከባድ ፈተና በማለፍ ላይ ሳለነው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1994 ዓ ም ስለኢንተርኔት የሰማው ። ከአንድ ዓመት በኋላ በተፈጠረለት መልካም አጋጣሚ ወደ አሜሪካ አቀና ። በዚያም ስለኢንተርኔት አጠቃቀም መሰረታዊ ግንዛቤ እንዳገኘ ስለሀገሩ ቻይን ለማወቅ ጉጉት አድሮበት መረጃ ሲያስስ እንደሌሎች ሀገራት የደለበ መረጃ ማግኘት አለመቻሉ ቁጭት ፈጠረበት ። በዚህ በመነሳሳት ከጓደኛው ጋር ስለ እናት ሀገሩ የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጥ ድረ ገፅ ፈጠረ ።
በጥቂት ሰዓታት የአብረን እንስራ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው ጎረፉለት ። በዚህ ጊዜ ነበር ጃክ የኢንተርኔትን ኃይል የተረዳው ። ከባለቤቱ እና ከጓደኛው ጋር 20ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወረት በማሰባሰብ በሚያዚያ 1995 ዓ ም ” ቻይና የሎ ፔጅን / chaina yellow page ” አቋቋመ ። በሶስት ዓመቱ 800ሺህ ዶላር አተረፈ ። 1999 ዓ ም ከ18 የስራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የዛሬውን ” አሊ ባባ ” መሰረተ ። በጥቂት ወራት ውስጥም ከባለሀብቶች 25 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አሰባሰበ ። በ2005 ዓ ም ያሁ / yahoo / አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ ከአሊባባ የ40 በመቶ ድርሻን ገዛ ። ነጮች የተቀረው ታሪክ ነው ቢሉም የጃክ ጉዳይ ከታሪክ በላይ ስለሆነ እንቀጥል ።
በ2006 ዓ.ም አሊ ባባ በታዋቂው የኒዮርክ የአክሲዎን ሽያጭ / New York Stock Exchange / ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ሲቀርብ ነጮች Initial Public Offering / IPO / ይሉታል ። 25 ቢሊዮን ዶላር የተተመነለትን ሽርክና በመሰብሰብ ከአንጋፋ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተርታ ተሰለፈ ። በ2008 ዓም የ463 ቢሊዮን ዶላር ግብይት አከናወነ ። የቅርብ ጊዜ ተመኑም ከግማሽ ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገመታል ። ዛሬ ተአምረኛው ጃክ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሀብት ባለፀጋ ነው ። በዓለማችን በቁጥር አንድነት በሚታወቀው የአሜሪካው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለመከታተል 10 ጊዜ አመልክቶ ውድቅ እንዳልተደረገበት በኋላ ላይ በክብር ጥሪ ተደርጎለት የክብር ተናጋሪ ለመሆን በቅቷል ። ታዋቂውና ተነባቢው የTIME መፅሔት በ2009 ዓ ም ከዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አንዱ አድርጎ መርጦታል። …”
” ስለአላደርግህልኝ ነገር አመሰግናለሁ ” የሚለውን የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሸጌ ወግ ማስታወስ የዚህ ጊዜ ነው ።
ወደ ጃክ ማ ሰሞነኛ የሀገራችን ታሪካዊ የሥራ ጉብኝት ስንመለስ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ሚያዚያ ወር በቻይና ስለ ” አንድ መንገድ እና መቀነት ” ፕሮጀክት በሚመክር ዓለምአቀፍ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ቤጂንግ በተገኙበት ወቅት ከጎበኟቸው ኩባንያዎች ቀዳሚው የጃክ ማ አለማቀፍ የኢንተርኔት ግብይት ኩባንያ አሊ ባባ ነበር ።በጉብኝታቸውም መስራቹ ጃክ ማን ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ እና ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆነውን ወጣት እና ሰፊውን ገብያ ታሳቢ በማድረግ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጋብዘውት ነበር ። በቀረበለት ግብዣ መሰረት በብልፅግና ፓርቲ ምስረታ ማግስት ስለብልፅግና ለመምከር በሳምንቱ መጀመሪያ አዲስ አበባ ተገኝቷል ።
ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን የጎበኘው ጃክ ማ ኢትዮጵያዊ ወጣት የሥራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ ዝግጁነኝ ከማለቱ ባሻገር ለአፍሪካ ወጣት የሥራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ይሰጠው የነበረውን 10ሚሊዮን ዶላር ወረት በ10 እጥፍ አሳድጎ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማድረጉን አብስሯል ። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ የተመለከተው አስደናቂ ለውጥና የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ቁርጠኝነት ለዚህ ውሳኔ እንዳነሳሳው ተናግሯል ። ብዙዎች ለምን ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት እንደመረጥኋት ይጠይቁኛል ። መልሴ ለምን አልመርጣትም ? የሚል ነው ። ጃክ ማ ወጣቱ ለፈጠራ እንዲነቃቃና መፃኢ እድሉን እንዲተልም መልዕክት አስተላልፏል ። በማከልም አፍሪካ እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያሉ መሪዎች ያስፈልጓታል ብሏል ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ በበኩላቸው አዲሱ የዲጂታል ግብይት ስርዓት ኢትዮጵያን የተቀረው ዓለም ከደረሰበት ተርታ የማሰለፍ አቅም እንዳለው እና የግብይት ስርዓቱም ለአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ስራዎች ፍትሐዊ የመጫወቻ ሜዳ እንደሚፈጥር ተናግረዋል ። እንዲሁም ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያግዙ መረጃዎችን ለማግኘት ያስችላቸዋል ። በቀጣይ አስር ዓመታት ኢትዮጵያ በግብይት ስርዓቱ ከተሰማሩ ቀዳሚ አምስት ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ያግዛታል። በንግግራቸው ማሳረጊያም ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ግብይት ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳላት ይህን ለማሳካትም ከጃክ ማ እና ከአሊባባ ጋር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ቃል ገብተዋል ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) በአፍሪካ በሩዋንዳ ብቻ ቅርንጫፉን ከፍቶ የነበረው አሊ ባባ በኢትዮጵያም ዓለምአቀፍ የኤሌክትሪክ ግብይት ማዕከልን ለመክፈት የሚያስችለውን ስምምነቶችን መፈራረሙ የኤሌክትሪክ ዓለም የንግድ መድረኩ Electric World Trade Platform / EWTP / እውን ያደርጋል ብለዋል ። መድረኩ አራት ትላልቅ አዕማዳት አሉት ።1ኛው የኢንተርኔት ግብይት e_commerce ሲሆን 2ኛው ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር የተገናኙ ስልጠናዎችን ያካትታል ። 3ኛው ደግሞ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ጋር የተያያዘ ነው ። 4ኛው ከትራንስፖርትና ከሎጂስቲክስ ጋር የተገናኘ ነው ።
የጃክ ማ ልዑክ የተፈራረማቸው ስምምነቶች የእነዚህን አዕማዶች መሰረት ለመጣል እንደሚያግዝ ሚኒስትሩ ገልፀዋል ። የአሊ ባባ ቅርንጫፉ መከፈት የንግድ ሥራዎችን ከዓለምአቀፉ የዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር ለማስተሳሰር ይረዳል ። እንደ ቡና ፣ የቅባት እህል፣ ቅመማ ቅመም ያሉ የግብርና ውጤቶችም ሆኑ ሌሎች የፋብሪካ ምርቶች የኤሌክትሪክ ግብይቱን ተጠቅመው አማራጭ ገበያ በቻይናም ሆነ በመላው ዓለም ለማግኘት ያስችላቸዋል ። ግብይቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ኢ / ር ጌታሁን አስረድተዋል ። አሊባባ የዓለም የንግድ ስርዓት በዲጂታል ግብይት ለማስተሳሰር ዓላማ ሰንቆ እየሰራ ያለ ግዙፍ ኩባንያ ስለሆነ ለሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ።
እንደ መውጫ
ሀገራችን የገጠሟትን ውስብስብ ፈተናዎች መሻገር የምትችለው በጊዜ የለም ስሜት በቅንጅት ጉልበታችንን ዕውቀታችንን እና ሀብታችንን አስተባብረን በአንድ ጊዜ ስንሰራ ነው ። ፖለቲካዊ ቋጠሯችን ለመፍታት ስንሰራ ኢኮኖሚው የገጠመውን ተቋማዊ እና መዋቅራዊ ችግር ጎን ለጎን መቅረፍ በሌላ በኩል የዕርቅ የሰላም ሥራዎችን በጊዜ መከወን ይጠበቅብናል ። አሁን የምንገኝበት ፈታኛ ወቅት አንዱን ችግር እስክንፈታ ሌላው ባለበት አይጠብቀንም ።
ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ ስንሰራ ኢኮኖሚው አፍ አውጥቶ እኔስ ይለናል ። ወደ ኢኮኖሚው ፊታችንን አዙረን በሀገር በቀል ማሻሻያ ልናድሰው ስንጥር የደህንነት እና የፀጥታ የጎን ውጋታችን ይቀሰቀሳል ። ለዚህ ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የገጠሙን ፈተናዎች ለማለፍ ዙሪያ መለስ እይታ wholistic approch ያስፈልገናል የሚሉት። የተናጠል ሳይሆን የማዕቀፍ ዕይታን ስለሚፈልጉ።
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሰሞነኛ አዋዋል ብንመለከት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል ። ከሩሲያ መልስ በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች የተከሰተው ሁከትና አጉራ ዘለልነትን ተከትሎ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ከተለያዩ አካላት ጋር በጣት በሚቆጠሩ ቀናት ከ20 በላይ ስብሰባዎችን አድርገዋል ። ከዚህ ጎን ለጎን የውህደቱን ጉዳይ ዳር ለማድረስ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ እንደሚጠመዱ ለመገመት ነብይ መሆን አያሻም ። በማስከተል በተከታታይ የኢህአዴግን የስራ አስፈፃሚና የምክር ቤት ስብሰባዎችን አካሂደው ውህደቱን ዳር ለማድረስ ቻሉ ።
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ ጃክ ማን ከእነ ልዑኩ ተቀብለው በሀገራችን መፃኢ እድል ላይ የማይደበዝዝ አሻራ ሆኖ የሚዘልቀውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት መድረክ ስምምነት ተፈራረሙ። ጃክን ሸኝተው ኦዲፓን ለውህደቱ ወደማዘጋጀት ተመልሰዋል። እነዚህ አብነቶች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ውስብስብ የሆኖ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በአንድ ጊዜ ጠረጴዛቸው ላይ አድርገው ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ያሳያል ። ይሁንና እንደ ዜጋም ሆነ እንደ ተቋም ይህን በውል ጨብጠነዋል የሚል ዕምነት የለኝም ።
ሆኖም ይህ እንደ መና እጃችን የገባ የአሊ ባባ ሲሳይ እንዳያመልጠን ሁላችንም ኃላፊነታችንን በትጋት በጊዜ የለም ስሜት ልንወጣ ይገባል ። ዘመኑ ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ እጁ ከሰጠ የሰነባበተ ቢሆንም እኛ ግን አርፋጅ ነን ። ስለዚህ ቀድመው የደረሱት እነ ኬኒያ ፣ ቦትስዋና ፣ ሩዋንዳ ፣ ወዘተ. ላይ ለመድረስ እንደ ዜጋ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል። በተለይ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት የወደቀባችሁ መሆኑን ባይስቱትም ከታላቅ አክብሮት ጋር ማሳሰብ እፈልጋለሁ ።
የጃክ ማ የኢትዮጵያ ይፋዊ የአዲስ አበባ ጉብኝት እና የተፈረሙ ስምምነቶች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳላቸው እና የሀገሪቱንም ሆነ የዓብይን መንግሥት ገፅታ በመቀየር እንዲሁም በሀገራችን መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚያመነቱ ትላልቅ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ትልቅ አደፋፋሪ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን አፍን ሞልቶ መናገር ይችላል ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ!!! አሜን።
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012