የህዳር ወር እየተገባደደ ነው። በዚህ ወር ከሚከበሩ በዓላት ደግሞ የዓለም አቀፉ የኤችአይቪ/ኤድስ ቀን አንዱ ነው። እ.ኤ.አ ነገ ዲሴምበር 1 የዓለም የኤች ኤቪ/ኤድስ ቀን ተብሎ ይከበራል። መገናኛ ብዙኃኑም፣ ጋዜጠኛውም ይህንኑ ዓመታዊ ዑደት ተከትሎ ወሬውን ሞቅ፣ ቀዝቀዝ ያደርጋል። ዓመቱ ዞሮ ሲመጣ ብዕሮች ሁሉ ስለኤችአይቪ/ ኤድስ ርዕሰ ጉዳይ ይጽፋሉ፣ያወጋሉ። የሚመለከታቸው ብቻ ሳይሆን የማይመለከታቸው አካላትም ጭምር መግለጫ በመስጠት ይጠመዳሉ። ስብሰባዎች፣ ዓውደ ጥናቶች፣ኤግዚቢሽኖች፣ የልምድ ልውውጦች… እንዲሁ ወሩን ታከው የሚከወኑ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች አይ/ኤድስ ቫይረስን እ.ኤ.አ በ2030 ከዓለማችን ጨርሶ ለማጥፋት ዕቅድ ይኑረው እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ ሀገራት ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው ተቃራኒውን ነው። በተለይ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላት የኤችአይቪ/ኤድስን አጀንዳ ቸል ማለታቸው በሽታው እንደገና በወረርሽኝ መልክ እንዲቀሰቀስ አንድ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።
አምና የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በኢትዮጵያ መጨመሩ ተረጋግጧል። እ.ኤ.አ በ2018 መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ ከ610 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ጋር ይኖራሉ። በጾታ ረገድ ሲታይም ሴቶች የመያዝ ዕድላቸው ከወንዶች በበለጠ መጨመሩ ያሳስባል። ሴቶች የማኀበረሰቡ ግማሽ አካል ናቸውና የእነሱ መጎዳት በእጅጉ ማሳሰቡ ተገቢ ነው።
የኤች ኤይቪ/ኤድስ ሥርጭት ለመጨመሩ የሚነገሩ ምክንያቶቹ የትየለሌ ናቸው። ከእነዚህ መካከል የለጋሾች ድጋፍ መቀነስ አንዱ ሲሆን የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት መላላት እና በባለሙያዎችና በመገናኛ ብዙሃን ስለኤችይቪ የሚሰጡ ትምህርቶች እየቀነሱ መምጣት በምክንያት ከሚጠቀሱት ቁንጮዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል። ጉዳዩን በተመለከተ የወጡ ዘገባዎች እንዲህ ይላሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ ባደረሳ መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም ከኤች- አይ ቪ ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ 30 ሺህ ዝቅ ቢልም የበሽታው ሥርጭት ግን አሁንም እየጨመረ መጥቷል። ለሞት መጠኑ መቀነስ የፀረ-ኤች አይቪ ህክምና ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት በምክንያትነት ተጠቅሷል። በአንፃሩ ግን ኤች-አይቪ ኤድስን ለመከላከልና በበሽታው እንደ አዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጧል። ችግሩ በአፍሪቃ በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ከፍተኛ መሆኑም ተገጧል። በኤች-አይቪ እንደ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከወንዶቹ ጋር ሲነጻፀርም የሴቶች በተለይም የወጣት ሴቶች የመያዝ እድል 60 በመቶ የጨመረ መሆኑን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።
ከአዲስ አበባ ከተማ የኤች-አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው የበሽታው ስርጭት በኢትዮጵያም የተለያዩ የክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ኤች-አይቪ ኤድስ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና አሁንም ድረስ ሥጋት ሆኖ መቀጠሉን ያረጋግጣል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤች አይቪ ሥርጭት ከ አንድ በመቶ በላይ ከሆነ ወረርሽኝ ተከስቷል ይባላል።«በኢትዮጵያ ቁጥሩ በጥቅሉ 0 ነጥብ 9 በመቶ ነው። ይህ ቁጥር በክልል ደረጃ ሲታይ የተለያዩ ገፅታዎች አሉት። በጋምቤላ 4 ነጥብ 8 ነው። በአዲስ አበባ በሁለተኛ ደረጃ ሥርጭቱ 3 ነጥብ የሥርጭት መጠን አለው። ሌሎች አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ደግሞ ከ 1 በመቶ በላይ የሥርጭት መጠን እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
በአዲስ አበባ የኤች አይቪ የሥርጭት መጠን እየጨመረ እንደመጣ ተረጋግጧል። በአዲስ አበባ ከጋምቤላ ቀጥሎ የሥርጭት መጠኑ 3 ነጥብ 4 በመቶ ሲሆን በጋምቤላ የኤች አይቪ የስርጭት መጠን 4 ነጥብ 8 መሆኑን ነበር። ዛሬም በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ከተያዙ መካከል ሴቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።
በከተማዋ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኙ ግለሰቦች 109 ሺህ መሆኑንና ከእነዚህ መካከል ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሚሆን ወጣቶች በከፍተኛ ቁጥር በቫይረሱ መያዛቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።
ወጣቶች ለምን ተዘነጉ?
ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል። በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ15- 24 የሚሆኑ ወጣቶች ስለኤች አይቪ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ነው። በተለይም ደግሞ በዚህ የእድሜ ክልል ከሚገኙ ሴቶች 76 በመቶ የሚሆኑት የኤች አይቪ መተላለፊያ እና መከላከያ መንገዶችን አያውቁም። ወንዶችም ቢሆን እውቀቱ ያላቸው 39 በመቶ ብቻ ናቸው።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የተለያዩ አካላት ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው ተብሎ ይታመናል። እነዚህ አካላትም የህዝብ ምክር ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ግለሰቦች ማህበራት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የጎሳ መሪዎችና አጋር ድርጅቶች ናቸው።
መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስለ ኤች አይቪ ኤድስ በንቃት በሚያስተምሩበት ወቅት የዛሬዎቹ ወጣቶች ጨቅላ ህፃናት ነበሩ።
አሁን ግን ስለኤች አይቪ መወራት በቀነሰበት ጊዜ ለአካለ መጠን በመድረሳቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ እንደሆኑ የወጡት ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።
ሥርጭቱ ለምን ሊጨምር ቻለ?
ሥራ አጥነት እና በከተሞች የኢንዱስትሪዎችና የሆቴሎች መስፋፋትም ወጣቶችን ለኤች አይቪ በሚያጋልጡ ሥፍራዎች እንዲውሉ ገፊ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የመጤ ባህሎች መስፋፋትም ማለትም የራቁት ዳንስ ቤት፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት፣ ጫት፣ ሺሻና ቡና ቤቶች መበራከታቸው ለኤች አይቪ መስፋፋት የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ ለመሰማራት ከተለያዩ ከተሞች የሚመጡ ወጣቶች ቁጥር ከፍ ማለትም የስርጭቱ መጠን ከፍ እንዲል አድርጎታል ተብሎ ይታመናል።
በአዲስ አበባ ከተማ ለኤች አይቪ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በትምህርት ቤትም ሆነ ውጭ ያሉ ወጣቶች፣ የቀን ሠራተኞች፣ የከባድ መኪና የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ በወህኒ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች፣ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ ሲሆኑ በቅርቡ በተደረጉ ጥናቶች እንደታየው ደግሞ ባሎቻቸውን በፈቱ ሴቶች የሥርጭት ምጣኔው ከፍ ያለ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶቹ በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የትምህርት ሥራውን ሊያውኩና ወጣቶቹን ለኤች አይቪ ሊያጋልጡ የሚችሉ መዝናኛዎችን ከትምህርት ቤት መራቅ አለባቸው የሚል አቋም ይኑር እንጂ አፈጻጸሙ የሚወራውን ያህል የጠነከረ አይደለም።
በአዲስ አበባ ደግሞ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት መጨመር፣ የአልኮል መጠጥ፣የራቁት ጭፈራ ቤቶች፣ከድህነት ጋር ተያይዞ የሴተኛ አዳሪነት መጨመር፣ህገወጥ የማሳጅ ቤቶችና የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ለስርጭቱ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ለመከላከሉ ሥራ ከለጋሾች ይገኝ የነበረው ድጋፍ በመቀነሱ በዋናነት ሥራው በመንግሥት ትከሻ ላይ የወደቀ በመሆኑ በዋናነት የፖለቲካ አመራሩ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ይታመናል።
በመጨረሻም ግንዛቤ ቀመስ
ነጥቦችን እናንሳ
ኤች አይ ቪ የሕመም ተከላካይ የሰውነት ክፍልን ያጠቃል። መከላከያ ካልወሰዱበት ኤች አይ ቪ የበሽታ ተከላካይ የሰውነት ክፍልን በመጉዳት ወደፊት ምንም ዓይነት በሽታ ሰውነታችን መከላከል እንዳይችል ያደክመዋል። ስለዚህም ተጠቂው በትልቅ አደጋና በሽታ ላይ ይወድቃል፤ ሊሞትም ይችላል። እንግዲህ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ኤድስ/AIDS (Acquired Immune Deficiency Syndrome) በመባል ይታወቃል።
አንድ ሰው ኤች አይ ቪ አለበት ማለት ኤድስ ይዞታል ወይም ይሞታል ማለት አይደለም። ያለ መከላከያ እንኳን ቢሆን ብዙ ሰዎች ኤች አይ ቪ ይዞአቸው ለብዙ ዘመናት ሊኖሩ ይችላሉ፣ በተጨማሪ ግን መከላከያ መድኃኒት ተዘጋጅቷል። በሽታው ተከላካይ የሰውነት ክፍልን ጎድቶ ወደ ኤድስ እንዳይቀየር የበሽታውን ኃይል አዳክሞ እንዲዘገይ (ቀስ እንዲል) ያደርገዋል። ብዙ ሰዎች ኤች አይ ቪ እያለባቸው በሕክምና በጤንነት ኑሮአቸውን በመምራትና ያሰቡትን ግብ መትተው በሥራና በኑሮ ሕይወታቸውን አሟልተው ይኖራሉ።
“ኤድስ” የኤችአይ ቪ የመጨረሻ ደረጃ ነው። ኤችአይቪ ያለበት ሰው ኤድስ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ዓመታት እንደሚወስድ በጥናት ተረጋግጧል። ኤድስ በኤችአይቪ ሳቢያ የሚፈጠረውን የሰውነት የመከላከያ አቅም መዳከም ሲሆን ለተለያዩ በሽታዎች የሚያጋልጥ ደረጃ ነው። አንድ ሰው በኤድስ ሞተ የሚለው የተለመደ አባባል የተሳሳተ ነው። ግለሰቡ በኤድስ ቢያዝም ወደሞት ደረጃ ሊደርስ የሚችለው በተለያዩ በሽታዎች ተጠቅቶ ነው። እንዲሁም ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች የፀረ-ኤች አይቪ መድኃኒቶችን ሳይጀምሩ የኤድስ ደረጃ ሳይ ሳይደርስ ብዙ ዓመት ሊኖሩ ይችላል። አንድ ሰው የኤድስ ደረጃ ላይ ደረሰ ማለት የሚቻለው የኤችአይቪ ቫይረስ የበሽታ መከላከያ ኃይል ተቋማትን ደምስሶ እና ሰውነታችን ከማንኛውም በሽታ የመቋቋሚያ ኃይሉን በማሳጣት ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች ይጋለጣል።
የሲዲፎር በመባል የሚታወቀውን በነጭ ደም ሴል ውስጥ የሚገኘውን የሴል ቁጥር (cd4 count) ከ200 በታች በማድረስ የቫይረሱ መጠን በደም ውስጥ እንዲጨምር በማድረግ ለሕይወት አደገኛ እና ምቹ ጊዜ ጠባቂ በመባል የሚታወቁትን በሽታዎች ኦፓርቸንሰቲክ ኢንፌክሽስ (Opportunistic infections) በመፍጠር የኤድስ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያደርጋል። አንድ ሰው አንድ ወይም ሁለት ኢንፌክሽኖች ሲኖሩበት እና በጣም ዝቅ ያለ የሲዲፎር ሴል ቁጥር 350 cells/mm3 ወይም በታች ሲሆን እና የቫይረሱ ብዛት (viral load) ከ 1,000 copies/mL በላይ ከሆነ የኤድስ ደረጃ ላይ ደረሰ ሊባል ይችላል።
ኤች አይ ቪ እና ኤድስ ብዙ ጊዜ እንደ አንድ ቃልና አንድ ትርጉም ሲጻፍና ሲነገር ቆይቷል፣ ነገር ግን ኤች አይ ቪ እና ኤድስ የተለያየ ትርጉም አላቸው። ኤች አይ ቪ የፊደሉ ትርጉም (Human Immune-deficiency Virus) ማለት የሰው ሕመምን ተከላካይ የአካል ክፍልን አጥቂ በሽታ ማለት ነው። ይህ በሽታ (ቫይረስ) የሚያጠቃው በሽታ ተከላካይ የሆነውን የአካል ክፍልን ነው፣ አንድ ሰው በ ኤች አይ ቪ ተመረዘ ወይም ኤች አይ ቪ ያዘው የምንለው በደሙ ውስጥ ገብቶ መሰራጨት ሲጀምር ነው።
አንድ ሰው ኤች.አይ.ቪ በደሙ ውስጥ መኖሩ ሊታወቅ የሚችለው በደም ምርመራ ብቻ ነው። ቫይረሱ ወደ ደሙ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለብዙ ዓመታት እንደማንኛውም ጤናማ ሰው ሥራውን እያከናወነ መኖር ይችላል። ምንም እንኳን በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎች ለብዙ ጊዜ የሕመም ምልክቶችና ስሜቶች ሳያሳዩ ጤናማ ሆነው ቢቆዩም ቫይረሱ በደማቸው ስለሚገኝ በቀላሉ ለሌላው የማስተላለፍ አደጋ ወይም እድል የሰፋ ነው።
ስለሆነም ቫይረሱ ያለበትንና የሌለበትን ግለሰብ ያለ ደም ምርመራ ማወቅ ስለማይቻል ልቅ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም ለቫይረሱ ሊያጋልጥ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል። ቫይረሱ ሰዎች ቀስ በቀስ የኤድስ ሕመም ስሜቶችና ምልክቶች እየታዩባቸው ሲሄዱ የኤድስ ሕመምተኛ ይሆናሉ። ኤድስ ማለት የሰውነት በሽታን የመከላከያ ኃይል/አቅም በኤች.አይ.ቪ ምክንያት በመዳከሙ የሚከሰት በሽታ ነው።
ለማስታወስ ያህል የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ከሰው አካል ውጭ ለብዙ ጊዜ መቆየት የማይችል ስለሆነ ከአንዱ ወደ ሌላው ሰው ለመተላለፍ ቀጥተኛ ንክኪን ይጠይቃል። ኤች.አይ.ቪን በተመለከተ ቀጥተኛ ንክኪ ማለት በተለይም ቫይረሱ ያለበት ሰው ደም ወይንም የብልት ፈሳሾች ከሌላው ጤነኛ ሰው ደም ጋር የሰውነት ቆዳ ቁስል /የቆዳ ክፍተት/ ባለበት ሁኔታ ሲነካካ ማለት ነው።
አብዛኛውን ጊዜ በቀጥተኛ ንክኪ ሊከሰት የሚችለው ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ስለታምና ሹል በሆነ መሣሪያዎችና እንደጥርስ ቡሩሽ አይነት… በጋራ በመጠቀም እንዲሁም ቫይረሱ ካለባት እናት ወደ ፅንስ/ ልጅ በመተላለፉ ሁኔታ ብቻ ነው። ቫይረሱ ያለበት ደም የሚለገስ ቢሆን ኖሮ ይህም ቀጥተኛ የደም ንክኪ የሚያስከትል ነው። ይሁን እንጂ በሀገራችን ያልተመረመረ ደም ለሕሙማን ስለማይሰጥ ኤች.አይ.ቪ በዚህ መንገድ የመተላለፍ ዕድሉ የመነመነ ነው። (ማጣቀሻዎች፡ – ቢቢሲ አማርኛ፣ የጀርመን ድምጽ፣ ዊክፒዲያ፣ ፋና ብሮድካስቲንግ..፤የፌዴራል እና የአዲስ አበባ የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤቶች፣ ጤና ሚኒስቴር….)
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012