በአዲስ አበባ ከተማ ከ700 ሺ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። የከተማ አስተዳደሩም ለዚህ የሥራ አጥ ቁጥር የሚመጥን የሥራ አድል ለመፍጠር በርካታ ገንዘብ መድቧል። በቅርቡም ሥራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። አብዛኛዎቹ የሥራ አድል መስኮችም ብዙሃኑን የከተማዋ ወጣቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶቹ የሥራ እድል ከተፈጠረባቸው መስኮች መካከል አንዱ በከተማዋ በሚገኙ ክፍት ቦታዎች ላይ አነስተኛ ሱቆችን በመክፈት በተለያዩ የንግድ ስራዎች እንዲሰማሩ ማድረግ ሲሆን በዚህም በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን ሥራ አጥ ወጣቶች በጊዚያዊነት እንዲጠቀሙባቸው ማድረጉ በበጎ የሚታይ በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ ነው። በተለይም ለዚሁ የሥራ አድል ፈጠራ አመቺ ናቸው ፤በቀጣይም ወጣቶቹ እንዳስፈላጊነቱ ቦታዎቹን እያሻሻሉ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ በሚል የተመረጡት ቦታዎች የከተማዋን ውበትና ጸጥታ ከማጓደል አኳያ የሚያበረክቱት አሉታዊ አስተዋጽኦን በተመለከተ በቂ ጥናቶች የተደረጉባቸው ናቸው ለማለት ያስቸግራል።
በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ላይ ወጣቶቹ እንዲሰሩባቸው የተፈቀዱ ቦታዎች በቀጣይ በነዚህ ቦታዎች ላይ ሊከናወኑባቸው የሚችሉ ስራዎችንና የአካባቢውን የእድገት ደረጃ ከግምት ውስጥ ያስገቡ አይደሉም። ለአብነትም ከሳሪስ ወደ ቡና ቦርድ፣ ከሳሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ወደ ኮተቤ ካራ በሚወስደው መንገድና አየር ጤና አደባባይ ጫፍ ላይ ባለው የመንገድ ዳርቻ ላይ ወጣቶቹ የላስቲክ ቤት ሰርተው እንዲነግዱባቸው የተፈቀዱ ቦታዎች የተሰጡት በግብታዊነት እንጂ ቦታዎቹ የሚገኙባቸውን አካባቢዎችና ያሉበትን ደረጃ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ አይደለም።
ክፍት ቦታዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ የተሻሉ ግንባታዎችና ሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎች ሊከናወኑባቸው ይችላሉ ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር
የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ብቻ ታላሚ ባደረገ መልኩ ለሥራ አጥ ወጣቶቹ ተፈቅደዋል። ይህንንም ተከትሎ በቦታዎቹ ላይ ሥራ አጥ የነበሩ ወጣቶች ሱቆችን በላስቲክ በመከለል የተለያዩ አነስተኛ ንግዶችን እያከናወኑባቸው ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ በላስቲክ የተከለሉት እነዚሁ ሱቆች በማታ የትራንስፖርት አገልግሎት አጥተው በእግራቸው ለመጓዝ ምርጫው ላደረጉ ሰዎች የደህንነት ስጋት እየሆኑ መጥተዋል። ሱቆቹ የተሰሩት በላስቲክ በመሆኑና ቀን ቀን አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ባዷቸውን ያለበር ክፍት ስለሚሆኑ እነዚህን ሱቆች መጠለያ የሚያደርጉ ደጅ አዳሪዎች ተበራክተዋል። በምሽት በሱቆቹ ውስጥ በመመሸግ በስፍራው በሚያልፉ መንገደኞችም ላይ ጥቃት በመሰንዘር የዝርፊያ ወንጀሎችን ጭምር እየፈፀሙ ነው። ይህ ተግባር ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ከሚያልፉ መንገደኞች ባለፈ ለነዋሪዎችም ስጋት ሆኗል።
በከተማ አስተዳደሩ የተጀመረው ክፍት ቦታዎችን ለወጣቶች የሥራ እድል የማዋሉ ተግባር በአንድ በኩል የሚደገፍ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን የአካባቢዎችን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ ለወጣቶች የተላለፉ ቦታዎች መልሰው ለከተማዋ ውበት መጓደልና ለመንገደኞችና ለነዋሪው የስጋት ምንጭ ለመሆን በቅተዋል። በነዚህ አካባቢዎች ላይ በላስቲክ ሱቆችን ገንብቶ ጥቃቅን ነገሮችን ለተጠቃሚው ማቅረብም ከአካባቢዎቹ አድገት ጋር ተመጣጣኝ ነው ተብሎ አይታሰብም፤ የከተማዋን ማስተር ፕላንም የተከተለ አይደለም። በቀጣይ በቦታዎቹ ላይ የተሻሉ ግንባታዎችን ለማከናወን ቢፈልግ እንኳን ወጣቶቹን ከቦታው ላይ የማስነሳቱ ስራም ቀላል ፈተና አይሆንም።
በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ለአብነት ከተጠቀሱት ቦታዎች በተጨማሪ በሌላ አካባቢዎች ላይም ያለአግባብ የተሰጡ ቦታዎችን ከወዲሁ ተመልሰው ወደ ነባር ይዞታቸው እንዲገቡ ማድረግና ለወጣቶቹም
ተመጣጣኝ ቦታዎችን በቅያሬ መስጠት ይኖርበታል። ከዛም ባለፈ ግን የከተማ ቦታ ውድ እንደመሆኑ መጠን ለጥቃቅን ስራዎች ታላሚ ተደርገው የተሰጡትን ቦታዎች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላላቸው ለተሻለ ልማት መዋል ይገባል።
ሱቆቹ የተገነቡባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ ነዋሪዎች የኑሮ ደረጃ ሻል ያለ በመሆኑና ሱቆቹ የሚያቀርቧቸውን አገልግሎቶች የመጠቀም ዝንባሌያቸውም በእጅጉ ያነሰ ሊሆን ስለሚችል በአካባቢው የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ነግደው ለማትረፍ ይቸገራሉ። በመሆኑም ወጣቶቹ በትክክለኛው ቦታ ነግደው እንዲያተርፉ ቦታዎችን በአግባቡ መርጦ ማስተላለፍ ይገባል። ከተቻለም ለወጣቶቹ የተሻለ ብድር በማመቻቸት ለቦታዎቹ የሚመጥኑ ከአነስተኛ አስከ መካከለኛ ህንፃዎችን ወይም ሼዶችን በመገንባት በውስጡ ገብተው እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል።
በከተማዋ የሚገኙ ማናቸውም ሥራ አጥ ወጣቶች ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ባሉ የሥራ አድል ፈጠራ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተካተው ተጠቃሚ የመሆን መብት ስላላቸው ለእነርሱ በሚያዋጣቸው መስኮች ውስጥ አንዲሳታፉና ትርፋማ እንዲሆኑ በባለሞያዎችና በጥናትም ጭምር የተደገፈ አሰራር ሊኖር ይገባል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በከተማዋ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን ያለጥናትና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለወጣቶች እንዲተላለፉ ማድረጉ የከተማዋን ገፅታ ከማበላሸት ባለፈ ለነዋሪዎችም የደህንነት ስጋት ስለሚሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሊያጤኑበት ይገባል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012
አስናቀ ፀጋዬ