በመዝገብ ቁጥር 43511 ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በመሄድ የሟች አቶ ዋሲሁን መኮንን ሚስት እና 10 ወራሾች የህገ መንግሥት ትርጉም ይሰጠን ሲሉ ይጠይቃሉ። በዚህ መዝገብ ተከራካሪ ወገኖች የሟች አቶ ዋሲሁን መኮንን ሚስት እና ወራሾች ሲሆኑ በመዝገቡ ተጠሪ የሆነው ደግሞ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ነው።
የመከራከሪያ ፍሬ ነገሩ ደግሞ ጥቅምት አምስት ቀን 2002 ዓ.ም የተፃፈ የይግባኝ ቅሬታ መሰረት ከአዋጅ ቁጥር 46/47 ድንጋጌ ውጭ የተወረሰብንን እና በአሁኑ ወቅት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/15 የቤት ቁጥር 703 የሆነው ንግድ ቤት ያለ አግባብ የወሰደ በመሆኑ ይመለስልን የሚል ነው።
በዚህ መዝገብ ቁጥር የህገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ጥያቄ ያቀረበበት ጉዳይ-ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የፕራይቬታይዜሽን ቦርድ ውሳኔ አስተዳደራዊ ስለሆነ ለማየት ስልጣን የለኝም በማለቱ ነው። በመሆኑም አመልካቾች ያቀረቡትን አቤቱታ ባለመቀበል የሰጠው ውሳኔ የህገመንግሥቱን አንቀጽ 37/1/ ድንጋጌ የሚጋፋ ውሳኔ በመሆኑ ተገቢ ህገመንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥበት አቤቱታ ቀርቧል።
ለህገመንግሥት ትርጉምም ጥያቄ በነተነሳበት ጉዳይ የተጠቀሱ የህግ ድንጋጌዎችም የህገመንግሥት አንቀፅ 37(1)፣ እና አንቀፅ 80/3/ (ሀ)፣ አዋጅ ቁጥር47/67፣ አዋጅ ቁጥር 87/86 እና አዋጅ ቁጥር 110/87 አንቀፅ2/3እና አንቀፅ 5/3 ናቸው። በዚህ መዝገብ ክርክርች ሲደረጉ ቆይተው የህገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ውሳኔ ሰጥቷል።
የህገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሰጠው ወሳኔም፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የፕራይቬታይዜሽን ቦርድ ውሳኔን በሰበር ለማየት የሚያስችል የህግ መሰረት የሌለ(ው) በመሆኑ አመልካቾች ያቀረቡት አቤቱታ የህገመንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው አይደለም የሚል ነበር። ጉዳዩ ከዚህም አልፎ ወደ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመራ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በራሱ የሚከተለውን ውሳኔ ይሰጣል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ አስተዳደራዊ ስለሆነ የማየት ስልጣን የለኝም ማለቱ የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 37/1/ የተደነገገውን ፍትህ የማግኘት መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተገቢነት የለውም፤ በመሆኑም የህገ መንግሥት አንቀፅ 37(1)፣ እና አንቀፅ 80/3/ (ሀ) በተደነገገው መሰረት ጉዳዩ ሊስተናገድ ስለሚገባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በሰበር የማየት ስልጣኑ እንዲመለከተው ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ሰጥቷል የሚል ይሆናል።
በዚህም መነሻነት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክር ቤቱ በአራተኛ የፓርላማ ዘመን ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት በአዋጅ ቁጥር 250/1993 ዓ.ም አንቀፅ 18 መሠረት የቀረበለትን የይግባኝ ቅሬታ መርምሮ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል።
የይግባኝ አቤቱታ አመልካቾች ጥቅ ምት አምስት ቀን 2002 ዓ.ም የተፃፈ የይግባኝ ቅሬታ ለምክር ቤቱ ማቅረባቸውን አስታውሷል። በአቤቱታዎቹም ከአዋጅ ቁጥር 46/47 ድንጋጌ ውጭ የተወረሰብንን እና በአሁኑ ወቅት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/15 የቤት ቁጥር 703 የሆነው ንግድ ቤት እንዲመለስልን በአዋጅ ቁጥር 110/1987 ዓ.ም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ አመልክተን ኤጀንሲው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ መልስና ማስረጃዎችን እንዲያቀርብ ካዘዘ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ቤቱ ከአዋጅ ውጭ የተወረሰ ስለሆነ ይመለስላቸው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በውሳኔው ላይ ይግባኝ በማቅረቡ ማመልከቻው ከቦርዱ መጥሪያ ጋር ደርሶን የክርክሩ ተካፋይ እናደርጋለን ብለን ብንጠብቅም፤ ቦርድ ይግባኝ ባዩን አቤቱታ ብቻ መርምሮ ውሳኔ በመስጠቱ መልስ የመስጠት ህገመንግሥታዊ መብታችን ተጥሶብናል በማለት አቤቱታ ብናቀርብለትም ሊያስተናግደን ፍቃደኛ አልሆነም የሚል ነበር። በመሆኑም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ዳኝነት ስልጣኑ የመከራከር መብታችን ሳይጠበቅ ውሳኔ መስጠቱ መሠረታዊ የህግ ስህተት ስለሆነ እንዲያርምልን አቤቱታ ብናቀርብም የቦርዱ ውሳኔ አስተዳደራዊ ስለሆነ የማየት ስልጣን የለኝም በማለት መዝገቡን ዝግቶ አሰናበተን ሲሉ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ያትታል።
ውሳኔው ህገ መንግሥታዊ የመሰማት መብታችንን የጣሰ ነው በማለት ለህገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ ብናቀርብም የህገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም በማለት ሳይቀበለው ስለቀረ በዚሁ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለምክር ቤቱ ይህን ውሳኔ ለማቅረብ መገደዳቸውን ዶሴው ያስረዳል።
ህገ መንግስት አንቀፅ 37(1 ሌላ የህግ ዳኝነት ስልጣን የተሰጠው አካል በሚል ታሳቢ ከሚያደርጋቸው ፍርድቤት መሰል አካላት መካከል የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ አንዱ ነው።
እነዚህ አካላት የሚሰጡትን የመጨረሻ ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ለማረም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር የዳኝነት ስልጣን ያለው በመሆኑ ኤጀንሲው ፍርድ ቤት እንዳልሆነ በመቁጠር የተሰጠው ውሳኔ ላይ ተገቢውን ህገመንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥልን በማለት ያመለክታሉ።
ለምክር ቤቱ የቀረበው የይግባኝ ቅሬታ ከላይ የተመለከተው ሲሆን፤ ምክር ቤቱም የህገ መንግሥትና የክልሎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበለት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያየ። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በአስፈፃሚው ስር የተደራጀ አካል ቢሆንም ከጉዳዩ መረዳት እንደተቻለው አመልካቾች ጥያቄ ሲያቀርቡ ኤጀንሲው አቤቱታውን ምርምር በአዋጅ 110/87 አንቀፅ2/3/ ከአዋጅ ውጭ የተወሰደ ንብረት የሚለውን ትርጓሜ ወስዶ እንዲመለስላቸው ወስኗል ሲል ያትታል።
ይህንን ያደረገው በአዋጁ አንቀፅ 5 ንዑስ ቁጥር 3 ላይ የባለቤትነት ጥያቄን በሚመለከት በሚቀርቡለት አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ በመደንገጉ ነው። ኤጀንሲው ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ቤቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ መልስና ማስረጃ ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ መሆኑን ያወሳል።
በዚህ መሰረት ኤጀንሲው የተከተለው አካሄድ መደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚከተሉትን ሥነ ሥርዓት በመጠኑም ቢሆን የተከተለ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ከፊል የዳኝነት ስልጣን ያለው አካል ነው ማለት የሚቻልበት ሁኔታ አለ። በሌላ በኩል የኤጀንሲው የቦርድ አዋጅ ቁር 87/86 አንቀፅ 8/5/ እንደተደነገገው የኤጀንሲውን ውሳኔ በሚመለከት ማንኛውም ግለሰብ ወይንም ድርጅት የሚያቀርብለትን ይግባኝ ህጋዊነቱን መርምሮ ይወስናል።
ይህም ሆኖ ቦርዱ ጉዳዮችን በይግባኝ ሲመለከት ሊከተል የሚገባው ሥነ ሥርዓት እንዲሁም የሚሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ቢኖረው ስህተት መደበኛ ፍርድ ቤት ወይንም ሌላ ቦታ ሄዶ ሊታረም እንደሚችል በአዋጁ በግልጽ የተገለፀ ነገር ባይኖርም በዚህ ሁኔታ የመሰማት መብት ያላገኙ አቤቱታ አቅራቢዎች ከቦርድ ውሳኔ በኋላ የት ይሂዱ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት በሚል የመከራከሪያ ነጥቦችን ይተነትናል ዶሴው።
ምክንያቱ ደግሞ ቦርዱ ተገቢውን የፍትህ ሥነ ሥርዓት ሳይከተልና አቤቱታ አቅራቢዎችን መልስ ሳይሰማ ውሳኔ መስጠቱ በይግባኝ ባዮች ላይ የመብት መጣበብ እንደፈጠረባቸው ግልፅ ስለሆነ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 80/3/ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበትን ማንኛውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ስልጣን ያለው ከመሆኑም በላይ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲውም እንደ ፍርድ ቤት መሰል አካል ይወሰዳል ከተባለ ጉዳዩ አስተዳደራዊ ነውና የማየት ስልጣን የለኝም ማለት ተገቢነት የለውም ሲል ይተነትናል።
በህገመንግሥቱ አንቀፅ 37/1/ ላይ የተቀመጠው የዜጎች በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ሌላ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል ቀርቦ የማስወሰን መብት የሚጋፋ ነው ሲል አንቀጹን ጠቅሶ ያስረዳል።
በመሆኑም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 37/1/ ፍትህ የማግኘት መብት እና በአንቀፅ 80/3(ሀ) የተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣንን የሚመለከተው ድንጋጌ ተዛምደው በዚህ አግባብ ጉዳዩ ሊስተናገድ ስለሚገባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በሰበር በማየት ስልጣኑ እንዲመለከተው ምክር ቤቱ በሙሉ ደምጽ ውሳኔ ሰጥቷል ሲል ዶሴው ይደመድማል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር