ከሰባ ዓመታት በላይ መድኃኒቶችን፣ የላብራቶሪ ግብዓቶችንና የሕክምና መገልገያዎችንና መሳሪያዎችን በመላ አገሪቱ ሲያቀርብ የቆየው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በዘርፉ አንጋፋ ድርጅት ነው፡፡ ምንም እንኳን ስያሜው በተለያዩ ጊዜያት የተቀያየረ ቢሆንም መድኃኒት አቅርቦት ሁሌም ቢሆን ዋነኛ ተግባሩ ሆኖ ቆይቷል፡፡
መድኃኒቶችን በማቅረብ ሥራው ላይ በርካታ ስኬቶች ቢኖሩትም እዚህም እዚያም የሚነሱ ቅሬታዎችም ያሉበት ተቋም ነው። በኤጀንሲው የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያም ከዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ሎኮ አብርሃ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፦ የተቋሙ የሥራ ድርሻና ያለበት ኃላፊነት ምንድን ነው?
ዶክተር ሎኮ፦ ተቋሙ ከተመሰረተ 80 ዓመት ገደማ ይሆነዋል፤በነዚህ ዓመታት ደግሞ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ በማለፍ አሁን ያለበትን ቅርጽ ይዞ ከተቋቋመ 12 ዓመቱ ላይ ነው። በተልዕኮ ደረጃ ዋናው ስራው ህይወት አድንና መሠረታዊ የሆኑ መድኃኒቶች ፈዋሽነታቸውን አረጋግጦ ለመንግሥትና ለግል ጤና ተቋማት ማቅረብ ነው።
መድኃኒት ብለን ስንል ግን የህክምና መገልገያ ግብዓቶችን ፣ ኬሚካሎችና ሪኤጀንቶች እንዲሁም ከካንሰር ጨረር መርጫ መሳሪያ ጀምሮ ትልልቅ ዋጋና አገልግሎት እስካላቸው ማሽኖች ድረስ እናቀርባለን። እኛ የመንግሥት ተቋም ነን ግን ተመሳሳይ ሥራን የሚሰሩ ከ 380 በላይ የተመዘገቡ የግል ተቋማትም አሉ።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው ይህንን ተግባርና ኃላፊነቱን ተወጥቷል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ሎኮ፦ በሌሎች ዘርፎች ላይ ብናይ ሦስት ወይም አራት በዛ ከተባለ አስር ዓይነት ግብዓቶችን ቢያስተዳድሩ ነው ። የጤና አገልግሎት ግብዓት ግን በጣም ውስብስብ ነው፤ ሌሎቹን እንኳን ትተን መድኃኒትን ብቻ ብንወስድ ዓይነታቸው 15ሺ የሆኑ መድኃኒቶች በዓለም ላይ አሉ፤ እንደ አገር ደግም የእኛን የግልና የመንግሥት ተቋማቱን ፍላጎት ስናይ ከአስር ሺ በላይ የተለያዩ ዓይነት ግብዓቶች ያስፈልጋሉ። ኤጀንሲው አብዛኛውን ህዝብ የሚጠቅሙ መድኃኒቶችን ለይቶ በማውጣት 1 ሺ 284 ዓይነት የህክምና ግብዓቶችን በቋሚነት ያቀርባል። በቂ ባይሆንም እንደ አገር ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንጻር ጥሩ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ ሆስፒታሎች ለአካባ ቢው ብቸኛ ይሆኑና አልያም በሌላ ምክንያት በርካታ ሰዎችን የማስተናገድ ግዴታ ይኖርባቸዋል፤ በዚህን ጊዜ ችግር ሆኖ ከሚነሱ ነገሮች መካከል መድሀኒትና የላብራቶሪ ግብዓቶች ናቸው ፤ ይህንን እንዴት ነው የምታጣጥሙት?
ዶክተር ሎኮ፦ በተመረጡና የታካሚ ጫና በሚበዛባቸው ሆስፒታሎች ላይ በየሁለት ሳምንቱ ምን መድኃኒት አላቸሁ ? የቱስ ነው የጎደላችሁ? የሚል ቁጥጥር በማድረግ ሪፖርት እንቀበላለን ። ከዚህ አንጻር ጥሩ መሻሻል ቢኖርም አርኪ ሥራ ለመስራት ብዙ ይቀረናል።
አዲስ ዘመን ፦ የሚፈለጉትን መሻሻሎች ለማምጣት ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር ሎኮ ፦ የዛሬ ሁለት ዓመትንና ዛሬን ስናወዳድር በወቅቱ ጓንት እንኳን እጥረት ሆኖ ይነሳ ነበር፤ አሁን ላይ ይህ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል። ይህንን ወደሌሎቹ የመድኃኒት ዓይነቶች ለማስፋት ግን ሥራ ይጠይቃል።
እዚህ ላይ አቅርቦት የላይኛውና የታችኛው ሰንሰለት በማለት በሁለት እንከፍለዋለን፤ የላይኛው የአቅርቦት ሰንሰለት የግዢ ፍላጎት ከመተንበይ ጀምሮ ግዢ መፈጸም ፣ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት፣ ማጓጓዝ ፣ የጉምሩክ ስነ ስርዓቱን ጨርሶ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ፣ ዋናው መጋዘን ድረስ ማድረስ ነው።
እዚህ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ መርከብ ድርጅት፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ ብሔራዊ ባንክና ንግድ ባንክ ፣ የመንግሥት ግዢዎች ኤጀንሲ ይሳተፋሉ፤ ሌላው ዓለም ላይ ያሉ መድኃኒት አቅራቢዎች ጋር ሁሉም አገር ግዢ ስለሚፈጽም ያንን ተወዳድሮ ወረፋ ጠብቆ በጊዜው መድኃኒቱን ወደ አገር ማስገባት ስለሚያስፈልግ ጥምረቱና አብሮ መስራቱ አስፈላ ጊ ነው።
አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ከዋናው መጋዘን ወጥቶና ባሉት 19 ቅርንጫፍ መጋዘኖች ገብቶ ፣ ወደ ሆስፒታሎች የሚሄደው ሄዶ ፣በወረዳ በኩል ወደ ጤና ጣቢያ ከጤና ጣቢያ ወደ መድኃኒት ቤት ከዛ ወደ ህሙማን የሚሄደው ሂደት ደግሞ የታችኛው የአቅርቦት ሰንሰለት እንለዋለን።
አዲስ ዘመን፦ በተለይ የላይኛው የግዢ ሰንሰለት ረጅምና ብዙ ውድድር የሚጠይቅ ነው ፤ግን ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ሻጩ ባይሸጥ ወይም ሌላ ችግር ቢፈጠር ምንድን ነው የሚደረገው?
ዶክተር ሎኮ፦ አዎ ግዢው በጣም ረጅም ነው፤ ብዙ ጊዜ ይወስዳል፤ ጊዜ መውሰድ ብቻ አይደለም ሂደቱን ከጨረስን በኋላ ይሄንን መድኃኒት ማቅረብ አንችልም የሚባልበት አጋጣሚም ይፈጠራል። መድኃኒት ህይወት እንደመሆኑ እነሱ አላቀርብም ስላሉ ህዝቡንም የለም ማለት አይቻልም፤ በመሆኑም አሁን መፍትሔ አድርገን ያቀረብነው ለተመረጡ 380 ወሳኝ መድኃኒቶችና ግብዓቶች የሦስት ዓመት ግዢ መፈጸምን ሲሆን ለዚህ ሂደት ደግሞ ሦስት አቅራቢዎችን በተመሳሳይ ዋጋ ይዘናል ።
አሰራሩ እጥረት እንዳይፈጠር ከማድረግ ባሻገር እንደ አገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድንቆጥብ ፣ በየዓመቱም የጨረታ አዙሪት ውስጥ እንዳንገባ አድርጎናል ።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙን ህዝቡ እንዲያውቀው የማድረግ ሥራ ተሰርቷል? ይህንን ያልኩት ብዙ ጊዜ ስማችሁ የሚነሳው ከችግር ከእጥረት ጋር ስለሆነ ነው፤
ዶክተር ሎኮ፦ ሰዎች ወደ ውስጥ እንዲመለከቱ ማድረግ መቻል አለብን ብለን እየሰራን ነው። አሁን ላይ የተቋሙን ዳታ ማንኛውም ሰው ማየት የሚችልበት የቴክኖሎጂ አማራጭም ዘርግተናል፤ በዚህም ህብረተሰቡ ያለና የሌለን መድኃኒት ማወቅ የሚችልበት መንገድ እውን ሆኗል። ይህ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ህዝቡ ምን እየተሰራ እንዳለ እንዲያውቅ ፣ ጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ ነው።
በመሆኑም ወደ ዳታው ያለምንም የይለፍ ቁጥር በመግባት ሀዋሳ ወይም አዲስ አበባ ላይ ያለውን የመድኃኒት ዓይነት ማወቅ፤ ከሌለም ለምን የለም? የሚለውን ለመጠየቅ ፣ የለም ያሉትንም አካላት ተጠያቂ ለማድረግ እየተጠቀምንበት ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሰራሩን ምን ያህሉ የኅብረተሰብ ክፍል ያውቀዋል? ለእኔም አዲስ በመሆኑ፤
ዶክተር ሎኮ፦ እንግዲህ ትልቁ የእኛ ችግር ወደ ጆሯችን ለማስገባት የምንፈልገው እንዲህ ዓይነትን ዜና አለመሆኑ ነው እንጂ ይህ አሰራር ከተጀመረ ቆይቷል፤ ዜና መግለጫም ሰጥተንበታል። በማህበራዊ ገጻችን፣ በዌብ ሳይታችን፣ በቲውተር ገጻችን ፊት ለፊት ላይ ቁጭ ብሏል ፤ ግን አሁን እንዳየነው በአገልግሎቱ የሚጠቀሙት ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ሰዎች ናቸው፤ ግን ወደፊት ከዚህ የተሻለ ኅብረተሰቡ ጋር መድረሻና ማስተዋወቂያ መንገድ ካለ እንሄድበታለን።
አዲስ ዘመን፦ መድኃኒቶች ከአገር ውስጥና ከውጭም ሲገዙም ሆነ በእርዳታ ሲገኙ ሊያሟሉት ይገባል ተብሎ የተቀመጠው መስፈርት ምንድን ነው?
ዶክተር ሎኮ፦ እኛ አቅርቦቱ ላይ ነው የምንሰራው ቁጥጥሩን የሚሰራ በአዋጅ የተቋቋመ አካል አለ፤ ይህ አካል ከሞላ ጎደል ዓለም ላይ ያሉትን መድኃኒቶች መዝግቧል። ወደ አገር ስናስገባም የምናየው ይህንን ነው። ግን እንደ አገር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባይመዘግባቸውም ለህዝቡ የሚጠቅሙ ከሆኑና የአሜሪካን ፣የአውስትራሊያና የጃፓን እንዲሁም የሌሎች አገሮች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ከመዘገቧቸው እንዲገቡ በማድረግ ባለሥልጣኑ እውቅና እንዲሰጣቸው ይሆናል ፤ከዚህ ውጪ የሚገቡ መድኃኒቶች የሉም። እዚህ ላይ ሳልናገር የማላልፈው ኢትዮጵያ ከሌላው አገር የተሻለ ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ የሚሰራ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ያላት መሆኑን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ የሚሰራ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ካለን እንዴት በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡትንና መጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፎም ከገበያ ያልወጡትን መድኃኒቶች መቆጣጠር ያቃተን?
ዶክተር ሎኮ፦ እኛ ኮንትራታችን ውስጥ ያለው አንድ መድኃኒት ቢያንስ 80 በመቶ ይህ ማለት ሲመረት 5 ዓመት ከሆነ የመጠቀሚያ ጊዜው ወደእኛ ሲመጣ ቢያንስ አራት ዓመት ፣ አንድ ዓመት ከሆነ ደግሞ የስምንትና ዘጠኝ ወራት ጊዜ ኖሮት ሊገባ ይገባል የሚል ነው።
ሆኖም አንዳንዶቹ ለምሳሌ የላብራቶሪ ግብዓቶች ሲመረቱም ጀምሮ የሦሰት ወራት ጊዜ ሊኖራቸው ይችላል ፤ እነዚህ እንግዲህ ቶሎ መሰራጨት ያለባቸው ናቸው ። እንግዲህ ይህም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ተሳክቶ እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስ ጥቅም ሰጥተው ያልቃሉ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቀድመው ሊያልቁ ይችላሉ፤ ብዙ ጊዜ ግን የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ይደርስና ተርፈው ይቀራሉ ነው። ሌላው በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡ መድኃኒቶችን መቆጣጣር ምናልባትም የቁጥጥር ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፦የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ደርሶ ተርፈው የቀሩት ናቸው ማለት ነው ገበያ ላይ የሚወጡት በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ሎኮ፦ እንደ አገር የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ደርሶ ተርፈው የሚቀሩ መድኃኒቶች ከፍተኛ ችግር ሆነው ነው የቆዩት፤ ምክንያቱም የብቃት ማረጋገጫ ያለው የማስወገጃ ማዕከልም ስላልነበር ። እነዚህን ደግሞ አንዳንድ ጥቅም ፈላጊዎች ማሸጊያዎቻቸውን ብቻ እየቀየሩ ለገበያ የሚያወጡበት አጋጣሚም እንዳለ እናውቃለን።
አዲስ ዘመን፦ ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶችን ማስወገጃ መታጣቱ ለዚህ ችግር ከዳረገን እንደ መፍትሔ የተቀመጠው ምንድን ነው?
ዶክተር ሎኮ፦ አዎ ባለፉት 16 ወራቶች አካባቢ ወደ ስምንት የሚጠጉ መድኃኒትንና ከሆስፒታል የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን ሊያስወግዱ የሚችሉ ማዕከላት ተገንብተዋል። ከነዚህም በአሁኑ ወቅት አምስቱ ወደ ሥራ ገብተዋል።
አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፉ መድኃኒቶች አወጋገድ ስጋት ላይሆን ነዋ?
ዶክተር ሎኮ፦ ስጋት የሚሆንበት መጠን ይቀንሳል እንጂ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም በየተቋማቱ እ ኤአ ከ2010 ጀምሮ በእኛ ተቋም፣ በጤና ቢሮዎች ፣ዞን ጤና መምሪያ ፣ ወረዳ ከዛም ጤና ተቋማት ላይ መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ ሆኖም ያልተወገዱ በርካታ መድኃኒቶች አሉ፤ አሁን እነዚህን ተራ በተራ የማስወገድ ሥራ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ስድስት ሰባት ዓመት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፉ መድኃኒቶችን ይዞ ከመቀመጥ ይልቅ ሌላ መፍትሔ ለምን አልተፈለገም?
ዶክተር ሎኮ፦ ሌላ መፍትሔ ሆኖ የተገኘው ሰዎች በማይደርሱበት አካባቢ በአንድ ክፍል ውስጥ ዘግቶ ማስቀመጥ ነው፤ይህ ምናልባት በሰው ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት መቀነስ አስችሏል ፤ ግን በተጣበቡ የጤና ተቋማቶቻችን ላይ አንድ ክፍል ለሞቱ መድኃኒቶች መስጠት በራሱ ትክክል አይደለም። ግን ደግሞ ትልቁ ችግር ማስወገጃ ሌላ መንገድ አለመኖሩ ነው። አውጥተን ሜዳ ላይ እናቃጥለው ወይም እንቅበረው ቢባል ጉዳቱ ይብሳል ። ይህንንም ከማድረግ ቆልፎ ማስቀመጡ የተሻለ አማራጭ ነበር በወቅቱ።
እኛ ስለ መድኃኒት አወራን እንጂ ማዳበሪያዎች ፣ ዲዲቲና ሌሎች ለግብርና ሥራ ይጠቅማሉ ተብለው የገቡ ኬሚካሎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፎ ተቀምጠዋል ። በመሆኑም ተቋማቱን እነዚህን ሁሉ ነገሮች የማስወገድ ኃላፊነት ስላለባቸው መንግሥትም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ የምታውቋቸውን ታስወግ ዳላችሁ፤ ግን እኮ አሁንም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፉ መድኃኒቶች ለገበያ ይቀርባሉ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ሎኮ፦ በዋናነት ገበያው ውስጥ ያለውን ችግር ሊፈታ የሚገባው የቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ነው። ግን አሁንም ቢሆን እነዚህ አገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ካልተወገዱ ለገበያ መቅረባቸው የማይቀር ነው። አንዳንዴም እንደገና ታሽገው የሚሸጡበት አጋጣሚ አለ። በመሆኑም ትክክለኛ መፍትሔው የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዳለፈ ማስወገድ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ ችግር ሆኖ ያለው መድኃኒቶች በጊዜው አለመድረስ አንዳንዴም ወደብና ጉምሩክ ተቋም ላይ መቆየት ነው፤ አሠራሩን ቀልጣፋ ለማድረግ ምን ታስቧል?
ዶክተር ሎኮ፦ በዚህ ዓመት አንደ አማራጭ ይህንን ሊሰሩ የሚችሉ ተቋማትን እያናገርን ነው ፤ ምክንያቱም ቢያንስ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ እንኳን
አስፈላጊውን መስፈርት በቶሎ ጨርሰን ወደ ተጠቃሚው መድረስ ስላለበት ፤ ሌላው እነዚህ መድኃኒቶች መጋዘን ከገቡ በኋላም ይቆዩ ስለነበር ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ መጋዘኖቻችንን በአዲስ መልክ እያደራጀን ነው፤ ይህ ደግሞ እቃዎች የት እንዳሉ እንዲታወቅ ቶሎ ገብተውም ቶሎ እንዲወጡ ያስችላል ። ይህንንም በአዳማ ቅርንጫፍ ጀምረነዋል ወደ ሁሉም ለማዳረስ ስራው እየተሰራ ይገኛል። በዚህ አሰራርም ተቋማት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እስከምንሰጣቸው የሚያገኙበትን ጊዜ ከቀናት ወደ ሰዓታት ለማውረድ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው የሚያስመጣቸው መድኃኒቶች ወደማዕከል ሳይደርሱ ከወደብና ከጉምሩክ በቀጥታ ወደሚመለከታቸው አካላት እንዲሰራጭ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነውና ይህ ለሙስና በር ከፋች አይሆንም ይላሉ?
ዶክተር ሎኮ፦ ሌሎች ዓለማት ላይ በተለያዩ ቦታዎች ላይ መጋዘኖች ሊኖሯቸው ይችላሉ ግን የክምችት አስተዳደሩ ማዕከላዊ ነው የሚሆነው፤ የእኛ ኤጀንሲም 19 ቅርንጫፎች አሉት ፤ እዚህ ላይ ከወደብ የሚነሱትን አዲስ አበባ ያለው መጋዘን ሳይደርሱ ወይ አዳማ አልያም አዋሳ ወዳለው መጋዘን ሊጓጓዙ ይችላሉ። አዳማ ላይ ሲገባ ግን ደረሰኝ የሚቆረጥለት ዋጋ የሚወጣበት አዲስ አበባ ካለው ማዕከል ነው።
አንዳንድ ጊዜ በጣም የሚገርም ሥራ ይሠራል። ከሞጆ ወደ አዲስ አበባ መድኃኒት መጥቶ ተራግፎ እንደገና ተጭኖ አዳማ ይሄዳል፤ ሥራው የተጀመረውም ይህንን ለማስቀረት ነው። በሳይንስም በልምድም ሌላው ዓለምም ሆነ አገር ውስጥ ያሉ ሌሎች ተቋማት የሚሰሩበት አካሄድ ነው።
እዚህ ላይ ከወደብ የተነሳው መድኃኒት ምናልባት በቀጥታ ጤና ተቋማት ላይ ቢሄድ ኖሮ እንዳልሽው ለሙስናው በር ከፋች ይሆናል የመረጃ ክፍተትም ይፈጥር ነበር ግን አሰራሩ እንደዛ አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ ብዙ ጊዜ በትልልቅ የጤና ተቋማት ላይ ሳይቀር የላብራቶሪ ግብዓት እጥረት ተፈጠረ ሲባል ይሰማልና ይህ ግብዓት ተለይቶ የመጥፋቱ ምክንያት ምንድን ነው? በእናንተ በኩል የተሰጠው ትኩረትንስ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ሎኮ፦ የላብራቶሪ ኬሚካል እጥረት ተፈጠረ ሲባል ነው እንጂ ብዙ ጊዜ ምክንያቱ ምንድን ነው? ብሎ የሚጠይቅ የለም። ለምሳሌ የደም ምርመራ ሁለት ዓይነት ነው። አንዱ የደም ዓይነትን ለማወቅ የሚሰራ ሲሆን ሌላው ደግሞ የደም ውስጥ ኬሚስትሪ ነው ፤ በሁለተኛው ዓይነት ምርመራ የጉበት ፣ ኩላሊት ፣ ስኳርና ሌሎችም ዓይነት ችግሮች ይታያሉ። ለዚህ ምርመራ በአገር ውስጥ ከ30 በላይ መመርመሪያ ማሽኖች አሉ ፤ የ30ዎቹም አምራቾች የተለያዩ ከመሆናቸው አንጻር የሚፈልጉት ግብዓትም ይለያያል አንዱ ለአንዱ ፍጹም አይሆንም ፤ አንድ ኬሚስትሪ ለመስራት ደግሞ ከመቶ በላይ ኬሚካሎች ሊዋሀዱ ይገባል ። ሌላው ችግር ግማሾቹ ኬሚካሎች ጭራሽም የማናውቃቸውና በእኛ ተቋምም የማይገቡ ይሆናል፤ ስለዚህ ችግሩን በዚህ መልክ ማየት ያስፈልጋል።
ሰው የላብራቶሪ ግብዓት ችግር አለ ሲባል በአንድ ፓኬጅ ሊፈታ የሚችል ይመስለዋል። ግን እንደዛ አይደለም መሰረታዊ የሆነ ችግር አለው። በእኛ በኩል ችግሩን ለመፍታት ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ሁለት ዓይነት አማራጮችን ነበር ስናስብ የነበረው።
አንዱ መንግሥት አስቦበትና አምኖበት ከተወሰኑ አምራቾች ብቻ ማሽን መግዛት ነው። ይህ እንግዲህ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁለት ወይም ሦስት ማሽን ስለሚኖሩ ለእነሱ ግብዓት ማቅረብ ችግሩን ቀላል ያደርገዋል። ሁለተኛው ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየሰራንበት ሲሆን አምራቾች 279 ለሚሆኑ ሆስፒታሎች ማሽኖችን በነጻ ሊያቀርቡ እኛ ግብዓቶችን ልናቀርብ ተስማምተን እየሰራን ነው። ከዚህ በፊት ማሽንና ግብዓትም የምንገዛበት ሁኔታ ነበር የነበረው። ይህ አሰራር አዲስ አበባ ላይ ሙሉ በሙሉ በማስጀመር እየሰራን ሲሆን እስከ ያዝነው ዓመት መጨረሻም በመላ አገሪቱ ያሉ ሆስፒታሎች ላይ ለማዳረስ ይሰራል።
አሰራሩ እጥረቱን ከመፍታትም በላይ ገንዘብም እንዲቆጠብ ያደርጋል። የማሽኖቹ ባለቤቶችም ሙሉ ኃላፊነቱን ወስደው ጥገናንም ያደርጋሉ ። ይህ መሻሻል ጥሩ ቢሆንም አሁንም ገና ብዙ የሚቀሩን ስራዎች አሉ።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎችን ይገዛል። ሆኖም መለዋወጫና የጥገና ባለሙያ ስለማይኖር በብዙ ቢሊየን ብር የተገዙ መሳሪያዎች ተፈላጊውን አገልግሎት ሳይሰጡ በየሆስፒታሉ ጓሮ ተጥለው ይቀራሉ፤ በዚህ ላይ ምን ሀሳብ አልዎት?
ዶክተር ሎኮ፦ ትክክል ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና መሳሪያዎች ከፊውዝ መቃጠል ጀምሮ በሚከሰቱ ጥቃቅንና ከፍተኛ ችግሮች ተበላሽተው ይቆማሉ፤ ስለሆነም ቀደም ብለንም እንዳነሳነው መሳሪያዎቹ አገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ አንዱ መፍትሔ ነው፤ ሌላው ግን ዓለም ላይ ያሉ ትልልቅ አምራቾች በአገራችን የጥገና ማዕከል እንዲከፍቱ ማድረግ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ታዋቂ የሆነ የአልትራሳውንድ ማሽን አምራች ጃፓን ካለ እዚሀ አገር የጥገና ማዕከል (ወርክሾፕ) እንዲያቋቁም መግፋት ስለሚያስፈልግ አሁን እቃ ስንገዛ ጎን ለጎንም ይህንን እየተዋዋልን አንዳንድም እያስገደድን ነው።
ይህ ሙሉ በሙሉ እስከሚሳካ ድረስ በጣም አስፈላጊና ውድ የሆኑ ማሽኖች በመዘርዘርና ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ለሦስት ዓመት የጥገና ውል ለመግባት እየሄድንበት ነው። ይህ ተገዝተው አገልግሎት ላይ ያሉትንም ያጠቃልላል።
አዲስ ለሚገዙት ግን የ10 ዓመት የጥገና ዋስትና እንዲገቡልን እያደረግን ነው። ግን እንደ እኛ ላለ ደሀ አገር ማሽኖችን በውድ ገዝቶ አስር ዓመት ውል ማሰር በቂ አይደለም 20 ና 30 ዓመት ማገልገል ይኖርበታል። ይሁንና ለጊዜው በቂ ነው በማለት እየሄድንበት ነው።
አዲስ ዘመን፦ መድኃኒቶችም ሆኑ ሌሎች ግብዓቶች ወረፋ ጠብቀን ከሌሎች አገራት ገዢዎች ጋር ተደራድረን ስናመጣ መዘግየቱም መቆራረጡም ሊፈጠር ይችላል እንበል። ግን በእርዳታ የምናገኘው ክትባት አንዳንድ ጊዜ የለም በዚህ ቀን ተመለሱ የሚባልበት ሁኔታ ለምን ይፈጠራል?
ዶክተር ሎኮ፦ ክትባት በዩኒሴፍ በኩል መጥቶ ወደ መጋዘን ይገባል። ከዛ ወደ ቅርንጫፍ መጋዘኖች ይሄዳል፤ ከእነሱ ደግሞ ወደዞን ይወርዳል። ከዛም ወደ ወረዳ፤ በመጨረሻ ነው እንግዲህ ጤና ጣቢያ የሚደርሰው። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ክትባቶች ዞን ላይ ብዙ ይኖሩና ጤና ጣቢያ ላይ አይኖሩም። በሌላ ጊዜ ደግሞ ዞን ላይም ጤና ጣቢያም ጠፍተው ወረዳ ላይ ግን ይከማቻሉ። ይህንን የፈጠረው ደግሞ መቀባበያ ሰንሰለቱ ረዥም በመሆኑ ነው። ይህንን ሙሉ በሙሉ በመቀየር በቀጥታ ከእኛ ወደ ወረዳ እንዲሄድ በመሆኑ አሁን ላይ መሻሻሎች እየታዩ ነው።
በተያዘው ዓመት እንደ አቅጣጫ የተያዘው ከመጋዘን በቀጥታ ተቋማት ጋር የሚደርስበትን አሰራር መዘርጋት ነው ።
አዲስ ዘመን፦ መድኃኒትን በመንግሥት ግዢ ኤጀንሲ መመሪያ መሰረት መግዛት ከባድ አይሆንም?
ዶክተር ሎኮ፦ መድኃኒት ልዩ ባህርይ አለው፤በተለይ አንዳንዶቹ በዓለም ላይ አንድ አምራች ብቻ ያላቸው አሉ፤ ስለዚህ ቀጥታ ነው መገዛት ያለበት፤ ሌላው ደግሞ 15 ቀን ብቻ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለውም አለ፤ በመሆኑም የመንግሥት የግዢ ኤጀንሲ አሰራር ሙሉ በሙሉ ይመለከታቸዋል የሚል እምነት የለኝም። የግዢ መመሪያ ብዙ ነገሩ መልካም ቢሆንም አንዳንድ የተለየ ባህሪ ያላቸውን የመድኃኒት ዓይነቶችን ግን አይወክልም።በመሆኑም አሁን አዋጁ እንደገና እየታየ ከመሆኑም በላይ በወረርሽኝ መልክ የሚነሱ በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግሉትን በፍጥነት ለመግዛት የሚያስችል አንቀጽ ጨምረንበታል።
አዲስ ዘመን፦ ብዙ ግዢዎቻችሁ ዓለም አቀፍ ናቸው። ከአገር ውስጥ አምራቾች ጋር ያላችሁ ግንኙነት በምን ደረጃ ላይ ነው?
ዶክተር ሎኮ፦ መልካም ነገር ባይሆንም አብዛኞቹ መድኃኒቶች ከውጭ አገር የሚገቡ ናቸው። በአገር ውስጥ ብናመርት ከማጓጓዣ ወጪ ፣የአገልግሎት ጊዜን ረዘም ከማድረግ ፣ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር ጥሩ ነበር። ነገር ግን ከ 80 በመቶ በላይ መድኃኒቶችን ከውጭ አገር ነው የምናስገባው።
አዲስ ዘመን፦ ከአገር ወስጥ አምራቾቹ ጋር ተቀራርቦ የመስራት ፍላጎት ስለሌለ ነው ?
ዶክተር ሎኮ፦ የአገር ውስጥ አምራቾች መንግሥት የሰጣቸውን እድል እንዲጠቀሙ በአገር ውስጥ ለሚመረቱ መድኃኒቶች ዓለም አቀፍ ጨረታ አናወጣም ። ስለዚህ በየዓመቱ ለአገር ውስጥ አምራቾች መጠይቅ እንበትናለን። የሚያመርቷቸውን ምርቶች ዝርዝር ይሰጡናል፤ በዛ መሰረት ደግሞ ለብቻቸው ጨረታ እንዲሳተፉ ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ መንግሥታት ድጋፍ የሚገዙ መድኃኒቶች ሲኖሩ ጨረታው ዓለም ዓቀፍ እንዲሆን ስለምንገደድ እናወጣለን። ግን ለአገር ውስጥ አምራቾች 25 በመቶ የታክስ ከለላ፣ እንዲሁም የውጭ አቅራቢው በአንድ ብር አቀርባለሁ ቢል እነሱ አንድ ብር ከሀያ አራት ሳንቲም ቢያቀርቡ ያሸንፋሉ። ይህም ብቻ አይደለም የመጓጓዣና ሌሎች ወጪዎችን በመጨመር አንድ ብር ከአርባ አራት ሳንቲም ቢሰጡ እንኳን ያሸንፋሉ።
ሌላው ኮንትራት ከፈረሙ በኋላ 30 በመቶ ድጎማ ይሰጣቸዋል ለቀሪው 70 በመቶ ደግሞ ከባንክ ጋር አብረን እንፈርምላቸዋለን ። በውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ዙሪያም አቅማችን የፈቀደውን ያህል እንደግፋለን። በዚህ መልኩ ድጋፍ እናደርግላቸዋለን። ይህ ሁሉ ሆኖ የባለፉትን ሁለትና ሦስት ዓመት አፈጻጸማቸውን ብናይ አጥጋቢ አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ አፈጻጸማቸው ሊወርድ የቻለበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር ሎኮ ፦ በዋናነት የሚያነሱት የውጭ ምንዛሪ ችግርን ነው። ሌላው ደግሞ እውነተኛ የሆነው የማምረት አቅማቸው እንዴት ነው የሚለው የሚለውም እንደ እኔ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፤ ምናልባት ማምረት ከሚችሉት በላይ ተንጠራርተው ከእኛ ኮንትራት እየወሰዱ ሊሆን ይችላል ። ግን በአጠቃላይ አቅርቦታቸው ከ 90 በመቶ በላይ እንዲሆን ብንፈልግም አንድም ጊዜ ሆኖ አያውቅም።
እኛ ድጋፉ ትልቅ እንደሆነ እናምናለን። ለምሳሌ የመቶ ሚሊየን ብር ኮንትራት ፈርሞ የ30 ሚሊየን ብር አድቫንስ ተሰጥቶት 70 ሚሊየኑ ላይ ደግሞ ከባንክ ጋር ከተፈረመ ሌሎች የታክስ ማቅለያዎችም ከተሰሩ አገር ውስጥ ላለ መስሪያ ቤት ማቅረብ ለምን እንደከበደ ይገርመኛል። ከእኛ አገር የተሻለ ድጋፍ የሚሰጡ አገሮችም መኖራቸውን አላውቅም ።
ይህ ሆኖ ግን እንደ አገር የተጣራ ውሃ (አይ ቪ ፍሉድ) ፣ ጓንት፣ የልጆች ላንቃ ማያ እንጨት (ስፓቹላ) ከውጭ ነው የምናስገባው ይህን ማሰብ ያስቆጫል ።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ሁሉ ድጋፍ ተደርጎላቸው ውጤታማ ያልሆኑበትን ምክንያት አንስታችሁ ተወያይታችሁ አታውቁም?
ዶክተር ሎኮ፦ በየዓመቱ አጋማሽ ውይይት እናደርጋለን። እኔ ከመጣሁ እንኳን 12 ጊዜ ተወያይተናል፤ አፈጻጸማቸውን በማሳየት ምን እንርዳችሁ ብለናል ግን ትልቅ ጉዳይ አድርገው የሚያነሱት የውጭ ምንዛሪ ችግርን ሲሆን ተራ የሆኑ የግብዓት ችግሮችንም ያነሳሉ ። እኛ ደግሞ የውጭ ምንዛሪም ቢሆን በ 2009 ዓም ከነበረው በ 2011 ዓም ላይ እንደተሻሻለ እናውቃለን። ግን እነሱ ከዓመት ዓመት የተሻለ አቅርቦት አልነበራቸውም። ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ችግር ቢሆን ኖሮ በ 2011 ዓም የተሻለ አፈጻጸም ይኖራቸው ነበር ።
ሆኖም መንግሥት የሰጣቸውን እድል ተጠቅመው አቅማቸውን አሟጠው ተጠቅመዋል የሚል ምዘና የለኝም።
አዲስ ዘመን፦ እንደዚሁ ትንሹንም ትልቁንም ከውጭ እያስገባን ነው የምንቀጥለው ? ወይስ የታሰበ መፍትሔ አለ?
ዶክተር ሎኮ፦ ለረጅም ዓመታት 10 እና 11 አምራቾች ናቸው በዘርፉ የሚንቀሳቀሱት፤ አሁን አዳዲስ አንድ ሁለት ትልልቅ አምራቾች ገብተዋል፤ አሥሩ ደግሞ በመንገድ ላይ ናቸው፤ ምናልባት እነዚህ ሲገቡና ውድድር ሲጀመር መነቃቃቱ ሊፈጠር ይችላል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ በአገራችን ውድ ከሆኑ ነገሮች መካከል መድኃኒት ግንባር ቀደሙን ተርታ ይይዛል ፤ይህ ደግሞ የኅብረተሰቡን አቅም እየተፈታተነ ነው፤ መፍትሔው ምንድን ነው?
ዶክተር ሎኮ፦ ብቸኛው መፍትሔ እንደ አገር ራሳችን አምርተን መጠቀም ነው። በሰው ላይ ተንጠልጥለን መቆየት አንችልም። ቀላል የሚባል የኢኮኖሚ አቅማችንንም አይደለም እየወሰደ ያለው፤ በመሆኑም የችግሩ ግዝፈት በመንግሥት ስለታመነበት ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ውስጥም ይህንን የሚደግፍ አካል ተቋቁሟል። በእኛ በኩልም ዝግጁነቱ አለ፤ እንግዲህ በርከት ያሉ የውጭ ባለሀብቶች መጥተው ፋብሪካዎችን አቋቁመው እንዲነቃቃ ማድረግ ያስፈልጋል ።
ዘንድሮ በሚጠናቀቀው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተቀመጠው 50 በመቶ ራሳችንን እንችላለን የሚል ነበር ግን አሁን ያለነው ከ 20 በመቶ በታች ነው።
ሌላው የሚገርመው እኛ ዛሬም እያወራን ያለነው በጣም የቆዩትን እንደ አሞክሳሲሊን ያሉ መድኃኒቶች ላይ ነው ፤ግን ዓለም በየዓመቱ አዳዲስ መድኃኒት እያመጣ የተማረው ሀኪም ደግሞ እነዚህን አዳዲስ መድኃኒቶች ለታካሚዎቹ ማዘዝ ጀምሯል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ስኳር፣ ደም ግፊትና ኮሌስትሮል እየጠቁን ነው የእነዚህ መድኃኒቶች ዋጋ ደግሞ ከአቅም በላይ ነው፤ ኤጀንሲው በዚህስ ዘርፍ ምን እየሰራ ነው?
ዶክተር ሎኮ፦ አዎ አሁን ትልቁ ችግራችን ይህ ነው። እኛ 50 እና 60 ዓመት ያለፋቸው በሽታዎች ሌላ ተጨማሪ ሸክሞቻችን ናቸው፤ ዛሬም ለእከክ ፣ለኮሌራ፣ ለወባ መድኃኒት እናመጣለን፤ በሌላው ጎን ደግሞ ስኳር ፣ደም ግፊት ፣ካንሰርና ኮሌስትሮል መጥተዋል፤ ሆኖም ኤጀንሲው መሠረታዊ የሆኑትንና አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ጤና ሊጠብቁ የሚችሉት ላይ ነው ትኩረት አድርጎ የሚሰራው።
የግል ሆስፒታሎች ላይ የስኳር ወይም ሌላ በሽታን ክትትል የሚያደርጉ ሰዎችን ብትጠይቂ እኛ በምናቀርበው መድኃኒት ሊረኩ አይችሉም ፤ እነሱ የሚፈልጉትን እኛ አናመጣም ያለችንን ውስን ገንዘብ አብዛኛው ህዝብ የሚጠቀምባቸውን መድኃኒቶች በማምጣት ነው የምንጨርሰው።
አሁን በከተማው ውስጥ አንድ ስድስት የልብ ህክምና መስጫ ተቋማት ሥራ ስለጀመሩ ለእነሱ ብቻ በአንድ የእርዳታ ድርጅት ተደግፈን መድኃኒቶችን ገዝተን እያቀረብን ነው። እንግዲህ ውስን ሀብት ያላትና በዓመትም በቂ ያልሆነ በጀት ለሚመደብለት ዘርፍ ከጫፍ ጫፍ ሁሉንም ነገር ማዳረስ አይቻልም።
እንደ ምሳሌ ብነግርሽ የካንሰር መድሃኒት አንዱ ፍሬ 18 ዶላር የሚያወጣ አለ፤ አንድ ህመምተኛ ደግሞ በቀን አራት ፍሬ መዋጥ አለበት፤ የሚወሰደው እድሜ ልክ ነው፤ እንግዲህ በቀን 72 ዶላር ማውጣት አለበት ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነት መድኃኒቶችም አሉ፤ የሚፈልግ አካልም አለ ግን ማምጣት አንችልም ። ወደፊት የሚደግፈን አካል ካገኘት በፓኬጅ እናመጣለን።
ብዙ ጊዜ የተጻፈልንን መድኃኒት ማግኘት አልቻልንም፤ በከተማው ጠፍቷል የሚባለው መድኃኒቱ ጠፍቶ ሳይሆን እኛ የምናመጣውና ዘመን የወለደው ስላልተገናኘ ነው።
አዲስ ዘመን፦በአገሪቱ አቅም ወድ የተባሉት ግን ደግሞ ብዙ ፈላጊ ያላቸውን መድኃኒቶች አጋር አካላትን እየጠየቅን ማምጣት አይቻልም? ምክንያቱም መድኃኒቱን የሚፈልጉት ሰዎችም መሞት ስለሌለባቸው ፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ሎኮ፦ እንደሚታወቀው የወባ ፣የቲቢ፣ የኤች አይ ቪ ህክምና ነጻ ነው። ከሁሉም ህክምናዎች የመጨረሻ ውዱ ኤች አይ ቪ ህክምና ነው ግን ግሎባል ፈንድ የሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ይረዳናል ፤ ሆኖም ተላላፊ ያልሆኑት በሽታዎች ላይ ያለው የአጋር አካላት የተሳትፎ ፍላጎት በጣም ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ አገሪቱ በራሷ ኢኮኖሚ ነው እየደገፈች ያለችው።
አዲስ ዘመን ፦ መድኃኒቶች በመንግሥት በጀት ይገዛሉ ከዛ ደግሞ በእርዳታ የሚገቡም አሉ፤ የኦዲት ስራው ምን ይመስላል?
ዶክተር ሎኮ፦ በመጀመሪያ ደረጃ በእርዳታ የተገኙ መድኃኒቶች በነጻ የሚታደሉ ናቸው። በመንግሥት በጀት የተገዙት ኦዲት ይደረጋሉ፤ እርዳታ የሰጡም አካላት ለታለመለት አላማ መዋሉን ማረጋገጫ ይወስዳሉ።
አዲስ ዘመን፦ በውስን በጀት የሚገዛ መድኃኒት ደግሞ ይባክናል ወይም አንዱ ጋር ይከማችና ሌላው ጋር ይጠፋል፤ ይህንንስ ለማሻሻል የሚሰራው ሥራ ምን ይመስላል?
ዶክተር ሎኮ፦ ይህ እንዳይሆን 152 ሆስፒታሎችን በአንድ ቋት አስተሳስረን እየሰራን ነው። በዋናነት ግን ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችለው የመረጃ አያያዝ ስርዓታችን በመሆኑ እየሰራንበት ነው ። አሁን ከተቋማት በየሁለት ሳምንቱ ሪፖርት እንቀበላለን፤ በዛ መሰረት ደግም የት ምን አለ ማን ጋር የቱ ተከማችቷል የሚለውን በመለየት የማሰራጨት ስራን እናከናውናለን።
አዲስ ዘመን፦ በቅርቡ ከኤጀንሲው የባንክ አካውንት ላይ በህገ ወጥ መንገድ 14 ሚሊየን ብር ተወስዷል፤ ይህ እንዴት ሆነ? አሁን ያለበት ደረጃስ ምን ላይ ነው?
ዶክተር ሎኮ፦ የንግድ ባንክን ቼክ አስመስሎ በመስራትና የእኛን ፊርማ አስመስሎ በመፈረም የተካሄደ ዘረፋ ነው፤ እንግዲህ ሲባል እንደሰማነው የባንክና የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች እጃቸው አለበት። ከተቋምም መረጃ ሰጪ ሠራተኞች አሉ ተብሏል። አሁን ላይ ጉዳዩን አቃቤ ህግ ይዞታል ፤ ችግሩ ያጋጠመንም እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎች ተቋማትም ናቸው። ቼኩን አጭበርብረዋል የተባሉት አካላትም ተይዘዋል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
ዶክተር ሎኮ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2012
እፀገነት አክሊሉ