ህፃን ልጃቸውን በአቢሲኒያ ጤና ጣቢያ ሲያስከትቡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ነጻነት ተረፈ የመርካቶ ሰባተኛ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ወይዘሮ ነፃነት ሁለት ጊዜም የእርግዝና ክትትል ያደረጉት በመሳለሚያ ጤና ጣቢያ እንደነበር ያስታውሳሉ። የሦስት ወር እርጉዝ ከሆኑ አንስቶ የእግርዝና ክትትል ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ዘጠነኛ ወራቸው እንደ ደረሰ የፅንሱም የእሳቸውም ክብደት ይጨምራል። በዚህ የተነሳም የደም ግፊታቸው ከፍ ማለቱ ይነገራቸዋል።
በሆስፒታል ደረጃ መታየት እንዳለባቸውም ይገለጽላቸውና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይላካሉ። ሆስፒታል ደርሰውም ምጡ ይጠናባቸውና በቀዶ ህክምና ይገላገላሉ።ሁለተኛ እርግዝናቸውንም በመሳለሚያ ጤና ጣቢያ ክትትል ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ሰባት ወር እንደሞላቸው አሁንም ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይላካሉ።የመውለጃ ጊዜያቸው ደርሶም በዚያው ሆስፒታል በሰላም መገላገላቸውን ይገልጻሉ።
የአንድ ወር ልጇን ለማሳከም በዚሁ ጤና ጣቢያ የተገኘችው የአብነት አካባቢ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዓይናለም ንጋቱም የመጀመሪያ ልጇን የሦስት ወር ነፍሰጡር ከሆነች ጀምሮ ክትትል አደርጋ የተገላገለችው በአቢሲኒያ ጤና ጣቢያ ነው። የጤና ጣቢያው የህክምና ባለሙያዎች በጥሩ ሁኔታ እንደሚሠሩ ገልጻ፣ በእርግዝና ክትትል ወቅትም ሆነ በወሊድ ወቅት ምንም አይነት ክፍያ እንዳልተጠየቀችም ትገልጻለች።
ወይዘሮ ወርቅነሽ አክመል በወለድሽ በሦስተኛ ቀን ሀኪም ሊያይሽ ይገባል ተብለው በአካባቢያቸው በሚገኘው ጃንሜዳ ጤና ጣቢያ ተገኝተዋል። የሁለት ወር ነፍሰ ጡር ከሆኑ አንስቶ እስኪወልዱ ድረስ ክትትል ያደረጉትም በዚሁ ጤና ጣቢያ ነው። ‹‹የጤና ባለሙያዎቹ በመኖሪያ ቤቴ መጥተው ለልጅሽም ላንቺም ጤና ሀኪሞች ዘንድ መጥተሽ ክትትል አድርጊ፤ መውለድ ያለበሽም በጤና ጣቢያው ነው›› መባላቸውን ጠቅሰው፣ ክትትል ማድረጋቸውን ይገ ልጻሉ።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የአቢሲኒያ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ታምሬ አዝልቄ እንደሚሉት፤ የእናቶችና ህፃናት ህክምና በተለይ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጣቸው ይገልጻሉ። አይኤምሲ በሚባል የተቀናጀ እናቶችና ህፃናት ጤና ክትትል አገልግሎት ክፍል ገብተው በሰለጠነ ባለሙያ ይስተናገዳሉ።ለነፍሰ ጡር እና ለሚወልዱ እናቶች፣ በተለይ ህፃናት ህመም ሲያጋጥማቸው በማንኛውም ፣ድንገተኛ ህክምና ሲያስፈልጋቸው ሙሉ የ24 ሰዓት የህክምና አገልግሎት ይሰጣቸዋል። በዚህም በርካቶች ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። ነፍሰ ጡር እናቶች በእርግዝና ወቅት አራት ጊዜ መከታተል ይኖርባቸዋል።ችግር ካለ ከዚያም በላይ መከታተል ይችላሉ።
እናቶች በተለይ ለነፍሰጡር ምርመራ አገልግሎት ወደ ጤና ተቋሙ በሚመጡበት ወቅት ሁሉም ኤች አይ ቪ ምርመራ ይደረግላቸዋል የሚሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፣ተመርምረው ምናልባት ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ከሆነም በደማቸው ውስጥ የሚገኘው ቫይረስ መጠን እንዲቀንስና የሰውነት የመከላከል አቅማቸው እንዲጨምር ኤአርቲ / ART/ የተሰኘ መድሃኒት እንዲወስዱ ይደረጋል ይላሉ። የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እና የቤተሰብ ጤና ቡድን አባላት በየቀኑ በየቀጠናው እየሄዱ ለእናቶችና ለቤተሰብ ግንዛቤ እየሰጡ እንዲመረመሩ እንደሚያደርጉም ይጠቁማሉ።
እንደ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገለጻ፤የወሊድ አገልግሎት ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጋር የተገናኘ ነው፤ የክትትል አገልግሎቱ ጥሩ ከሆነ እናቶች በጤና ጣቢያው እንዲወልዱ ይደረጋል። 36ኛ ሳምንት ሲደርሱ በጤና ጣቢያው ቢገላገሉ ለነርሱም ለልጃቸውም ጤና ጥሩ እንደሚሆን ይገለጽላቸዋል፤ ይህም ጤና ጣቢያን እንዲመርጡ እያደረጋቸው ነው።
‹‹ነፍሰ ጡሮች ‹‹ምጥ ሲጀምራቸው የወሊድ አገልግሎት ክትትል ያደርጋሉ፤ ረጅም ምጥ ሲያጋጥ ማቸው ወይም የልጁ ሁኔታና የእናቲቱ ማህፀን ያለመመጣጠን ሲኖር፣ ወሊድ ላይ ቅድሚያ የሚደሙ እናቶች ሲኖሩ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል በቀጥታ ሪፈራል ተደዋውለን ለአቢሲኒያ እና ሚሊኒየም ጤና ጣቢያዎች ዝግጁ በሆነ አምቡላንስ ተልከው በሰላም እንዲገላገሉ ይደረጋል›› ሲሉ ያብራራሉ።
ሜዲካል ዳይሬክተሩ መንግሥት በተለይ ለነፍሰጡር እና ለወለዱ እናቶች እንዲሁም ለህፃናት ጤና ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ለዚህም የጤና ጣቢያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹ባለፈው ዓመት በወሊድ ምክንያት በጤና ጣቢያው የሞተች እናትም ሆነች ህፃናት የሉም ፤ ምንም ዓይነት ሞት ሊያጋጥመን አይገባም በሚል እሳቤ ሰርተን ውጤታማ ሆነናል›› የሚሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ፣በጤና ጣቢያው ከሦስት ዓመት ወዲህ ያለው የነፍሰጡርና ወሊድ እናቶች አገልግሎት እየተሻሻለ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገለጻ፤በጤና ጣቢያው እናቶች ከወለዱ በኋላ ቢያንስ ስድስት ሰዓት የሚያርፉበትን ክፍል ሳቢና ማራኪ ለማድረግ ተሞክሯል። በነፍሰጡርነታቸውና ከወለዱ በኋላ ከመድኃኒት ጋር ተያይዞ ማንኛውም ህመም ቢያጋ ጥማቸው ምንም አይነት ክፍያ ሳይጠየቁ መድኃኒት ማግኘት ይችላሉ። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሪፈር ተደርገው የቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚሰጣቸውም በነፃ ነው።
እነዚህ አገልግሎቶች በግል የህክምና ተቋማት ከፍተኛ ክፍያ እንደሚጠየቅባቸው ጠቅሰው ከነፍሰ ጡር ክትትል እና ከወሊድ ጋር ተያይዞ ለአንዲት እናት በአማካይ ከ500 እስከ 1ሺ ብር ሊጠየቅ እንደሚችልም ያብራራሉ፤ ለማዋለድ አገልግሎት ደግሞ እስከ 30ሺ ብር ፣ ያለ ኦፕሬሽን የሚወልዱ ከሆነ ደግሞ እስከ 15ሺ ብር እንደሚጠየቅ ይገልጻሉ።
የጃንሜዳ ጤና ጣቢያ ከነፍሰጡር እናቶች ክትትል ጀምሮ ወሊድ እና ድኅረ ወሊድ አገልግሎት ይሰጣል። የጤና ጣቢያው ሚድዋይፍ ፀሐይ ሀብታሙ እናቶች እርጉዝ ነን ብለው ወደ ጤና ጣቢያው ሲመጡ፣ምርመራ እንደሚደረግላቸው ፤እርግዝናው ከተረጋገጠ ከቀናት እና ሳምንታት ጀምሮ ክትትል ማድረግ እንደሚችሉም ያብራራሉ።
እንደ ሚድዋይፍ ፀሐይ ገለጻ፤ የማኅበረሰብ ጤና ቡድን አባላትና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም ቤት ለቤት እየሄዱ ለእናቶች ምክርና ግንዛቤ ይሰጣሉ። ቀጠሯቸውንም እንዳይረሱት ያስገነዝባሉ፤ ክትትል ያልጀመሩ ነፍሰጡሮች ካሉም ክትትል እንዲያደርጉ ወደ ጤና ጣቢያው ይልካሉ።
በአሁኑ ወቅት እንደ ድሮ ቤት ውስጥ የሚወልዱ ፣ታመው ቤት የሚቀመጡ ህፃናትም የሉም የሚሉት ሚድዋይፍ ፀሐይ ፣ የእናቶች ሞት እየቀነሰ የመጣውም ጤና ጣቢያ ስለሚወልዱ ነው ይላሉ። እናቶች ከወለዱም በኋላ በሦስተኛው በሰባተኛው እና በአርባ አምስተኛው ቀን ወደ ጤና ጣቢያው ተመልሰው እንዲመጡ ተደርጎ እናቶቹም ህጻናቱም ይመረመራሉ ይላሉ።
በጤና ጣቢያው ከወሊድ ጋር ተያይዞ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር እንደሌለና ወደ ሆስፒታል በሪፈር የሚላክ አለመኖሩን ጠቅሰው፣ በቀዶ ህክምና መገላገል ያለባቸው ነፍሰጡሮች ካሉም አገልግሎቱ በጤና ጣቢያው እንደሚሰጥ ይጠቁማሉ። አልፎ አልፎ ግን በወሊድ ጊዜ ደም ላነሳቸው እናቶች በጤና ጣቢያው የደም ባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ ብቻ በሪፈር ወደ ሆስፒታል እንደሚልኩ ጠቁመዋል።በቀዶ ህክምና በማገላገል ከጤና ጣቢያው በተጨማሪ በአቅራቢያው የሚገኙት የየካቲት 12፣ የዳግማዊ ምኒልክ እና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ይገልጻሉ።
እንደ ከተማ ያለውን መረጃ አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ መረጃዎችን ለማቅረብ በቢሮው የሴቶችና ህፃናት ዳይሬክተርን በስልክም ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም መረጃውን ለመስጠት በያዙልን ቀጠሮ መሰረት ስልክ ብንደውል ሊገኙ አልቻሉም። በአካል ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም።
አዲስ ዘመን ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም
ኃይለማርያም ወንድሙ