አዲስ አበባን በመሰሉ የኢትዮጵያ ከተሞች በርካታ ነዋሪዎች እንደሚገኙ ይታወቃል። ነገር ግን ከነዋሪው ጋር የሚመጣጠኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የሉም። በዚህም ምክንያት ወጣቶች ተገቢ ባልሆኑ ስፍራዎች ላይ ጊዜያቸውን ሲያጠፉና ባልተገባ ቦታ ሲገኙ ይስተዋላል። የተለያዩ ውድድሮችን የማስተናገድ እድል ከተሰጣቸው በኋላም በቂ የውድድር ስፍራዎችን በማጣት ሲቸገሩም ከዚህ ቀደም በገሃድ ታይቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘም በሃገር አቀፍ ውድድሮች ላይ እንደ ከተማ የሚመዘገቡ ስፖርታዊ ውጤቶች በአንጻራዊነት ያነሰ የሚባል ነው።
በመሆኑም በዚህ ወቅት በሃገር ዓቀፍ ደረጃ ለስፖርታዊ ማዘውተሪያ ስፍራዎች የተሰጠው ትኩረት በከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ዘንድም እየታየ ይገኛል። በዚህ ረገድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ካሉት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠቃሽ ነው። አዲስ አበባ የሃገሪቷ ዋና ከተማ እንዲሁም የአፍሪካ መዳረሻ እንደመሆኗ በርካታና ዘመናዊ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ቢያስፈልጓትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያሏት ጥቂት ነበሩ። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህም የከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በርካታ ሚሊዮን ብር በማውጣት ከትንንሽ ሜዳዎች እስከ ትልልቅ ስታዲየሞች በመገንባትና ማደስ ስራ ላይ ተጠምዷል።
በከተማዋ ከአዲስ አበባ ስታዲየም በተጓዳኝ ለዓመታት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህ ስታዲየም ደረጃውን ያልጠበቀ እና መም የሌለው በመሆኑም ከሌሎች ስፖርቶች በቀር ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ ያልነበረ ነው። ቢሮውም ስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ እና ዘመናዊ እንዲሆን የእድሳት ስራ ላይ ይገኛል። በዚህ ወቅትም 80 በመቶ ስራው የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ከወራት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት ከክብር እንግዶች መቀመጫ በቀር የወንበር ገጠማው ተጠናቋል። ለመሮጫ መም ስራው የሚሆነው ግብአት በመሟላቱም አሰር ለተባለ ድርጅት ተሰጥቶ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ እንደሚጀመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ቀሪው ስራ የጣሪያ ገጠማ ሲሆን፤ ናሙናውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ግምገማ እተደረገበት ነው። የመጀመሪያው ናሙና ውድቅ በመሆኑ ሁለተኛ ናሙናው ተጣርቶ በተያዘው ሳምንት ውጤቱ የሚታወቅም ይሆናል። ግንባታው በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት በከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ የተሰጠ በመሆኑ በዚሁ መሰረት እየተሰራ መሆኑም፤ በቢሮው የወጣት ማዕከልና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ባዩ ለአዲስ ዘመን ገልጸዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም ቢሮው የሚያስገነባው ሌላኛው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ነው። በአሁኑ ወቅትም የስታዲየሙ የመዋቅር ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት ለውድድር ዝግጁ እንደሚሆን ይጠበቃል። በ2009ዓ.ም የካቲት ወር የስራ ርክክብ ቢደረግም፤ ወደ ግንባታ የተገባው ግን በዓመቱ ማጠናቀቂያ የክረምት ወራት ነበር። ሙሉ ለሙሉ ከግንባታ እስከ ማጠቃለያ ስራው ለአንድ ተቋራጭ የተሰጠው ስታድየም በአጠቃላይ 514ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። ስታዲየሙ ሲጠናቀቅ 25ሺ ሰዎችን በወንበር የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መምና የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳም ይኖረዋል። ዙሪያውን በጣሪያ የሚከበብ ከመሆኑም ባሻገር ለንግድ የሚውሉ ሱቆችንም ያካትታል።
በአሁኑ ወቅትም የግንባታ ምዕራፉ ከግማሽ በላይ ሲደርስ፤ የተመልካች መቀመጫ ኮንክሪት ግንባታው ተጠናቆ የተለያዩ ክፍሎችና የሜዳ ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል። የጣሪያው ዲዛይንም ማጣራት ላይ ይገኛል። ቀሪዎቹ ወንበር ገጠማ፣ የጣሪያ፣ የሜዳ እና የመም ስራዎችም በተያዘው ዓመት መጠናቀቅ እንዳለበት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አቅጣጫ ተቀምጧል። ግንባታውን ሊገቱ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው ከውጪ የሚመጡ ዕቃዎች እንደመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ ማገዝ ያለበትን እንደሚያደርግም ምክትል ከንቲባው መግለጻቸውን ዳይሬክተሩ ያስታውሳሉ። ግንባታውን በማከናወን ላይ የሚገኘው ተቋራጭም የውለታ ጊዜው የሚጠናቀቀው በዚህ ዓመት እንደመሆኑ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ኃላፊነት ወስዶ እንደሚሰራም አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ያለው የወጣት ፍላጎት ምን እንደሆነ ይውቃል ቢሮው ደግሞ እስካሁን ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ የነበረው በ1ለ3ሜዳዎች ላይ ነው። ይህም እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስና ቮሊቦል ነው፤ ወጣቱ የሚፈልገው ደግሞ እግር ኳስ መጫወት ነው በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ስታዲየም አስፈላጊ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። ወጣቶች እንደየፍላጎታቸው በተለያዩ ስፖርቶች ላይ ተሳታፊ ከመሆናቸውም ባሻገር በግንባታ ላይ የሚገኙት የትምህርትና ስልጠና ማዕከል በመሆናቸው ተጠቃሚ በመሆን ተተኪነታቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ።
በመሆኑም የተያዙት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ተጠናቀው ወጣቶችና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት በማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ተገኝተው ጉብኝት ያደረጉት ምክትል ከንቲባውም የሚያስፈልገው ነገር ተሟልቶ በአፋጣኝ ወደታለመላቸው ዓላማ እንደሚውሉ መግለጻቸውንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
ብርሃን ፈይሳ