በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት የተሻለ ተሳትፎና ውጤት ካላቸው ሃገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወቃል። ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በሚዘጋጁ እንዲሁም በተለያዩ ሃገራት በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ እንደሚሳተፉ ይታወቃል። ዛሬ በሚጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመትም በመምና በጎዳና ላይ ውድድሮች የኢትዮጵያ ውጤት ምን ይመስል ነበር የሚለውን እንደሚከተለው እናስታውስ።
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ወራት ያካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው። በእንግሊዟ በርሚንግሃም በተካሄደው 17ኛው ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ አምስት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አሜሪካንን በመከተል በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ገንዘቤ ዲባባ በሁለት ርቀቶች፤ ሳሙኤል ተፈራ እና ዮሚፍ ቀጄልቻ የወርቅ እንዲሁም ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ደግሞ የብር ሜዳሊያ ያጠለቁ አትሌቶችም ናቸው።
3የወርቅ፣ 2የብር እና 4 የነሃስ በድምሩ 9ሜዳሊያዎች የተሰበሰቡት ደግሞ በፊንላንዷ ቴምፕሬ በተካሄደው ከ20ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮና ነው። ታከለ ንጋት፣ ድርቤ ወልተጂ፣ አልማዝ ሳሙኤል፣ መሰሉ በርሄ፣ እጅጋየሁ ታዬ፣ በሪሁ አረጋዊ፣ ጌትነት ዋሌ፣ ጽጌ ገብረሰላማ እና ግርማዊት ገብረእግዚአብሄር ደግሞ የሜዳሊያዎቹ ባለቤቶች ናቸው። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ኬንያ፣ ጃማይካ እና አሜሪካን ተከትላም አራተኛ ደረጃ ይዛ ነው ያጠናቀቀችው።
14መዳረሻዎች ባሉት የዳይመንድ ሊግ ውድድርም በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተሳታፊዎች ሆነዋል። ውጤቱ ሲጠቃለልም በተለይ በወንዶች 5ሺ ሜትር የተመዘገበው ውጤት የተሻለ ነበር። አትሌት ሰለሞን ባረጋ በዓመቱ ካስመዘገባቸው ውጤቶች መካከል 12:43.02 የሆነው ሰዓት ከ20ዓመት በታች በሆነ አትሌት የተመዘገበ ፈጣን ሰዓት በሚል ሲመዘገብ የዳይመንድ ሊጉ አሸናፊም ነበር።
የወጣቶች ኦሊምፒክ ሌላኛው በዓመቱ በአርጀንቲናዋ ቦነስ አይረስ የተስተናገደ መድረክ ነው። በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በሁለት የስፖርት ዓይነቶች ተሳታፊ ብትሆንም ሜዳሊያ ያስመዘገበችው በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ነው። በአጠቃላይም 2የወርቅ፣ 2የብርና 4የነሃስ በድምሩ 8ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተገኝታለች።
23ኛው የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናም በዓመቱ በስፔኗ ቫሌንሺያ የተካሄደ ውድድር ነው። በዚህ ውድድር ላይ በተለይ የሚጠቀሰው በሴቶች ውድድር አሸናፊ የሆነችው አትሌት ነጻነት ጉደታ የዓለም ክብረወሰኑን ከእጇ ማስገባቷ ነው። እአአ በ2014 እና 2016 ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌቷ፤ በሶስተኛ ተሳትፎዋ አሸናፊ ብቻም ሳትሆን በርቀቱ ፈጣኗ ሴት አትሌት ለመባልም ችላለች። ነጻነት 1ሰዓት ከ06ደቂቃ ከ11ሰከንድ በሆነ ሰዓት የመጨረሻውን መስመር መርገጧም የክብረወሰን ባለቤት አድርጓታል። ከዚህ ባሻገር አትሌቶቹ በቡድን የሴትና ወንድ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆናቸው በሶስት ወርቅ ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ስፍራ እንድትቆናጠጥ አስችሏል።
በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ወራት በተካሄዱት ሰባት የሃገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ላይ ከተሳተፉት አትሌቶች መካከል አራት አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያ ወስደዋል። በናይጄሪያ በተካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይም 2የወርቅ፣ 3የብርና 5የነሃስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። ይህም ኢትዮጵያ፤ ኬንያን፣ ደቡብ አፍሪካን እና ናይጄሪያን በመከተል በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓል። በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ደረጃ በተሰጣቸውና በተለያዩ ሃገራት በሚካሄዱ የጎዳና ላይ ሩጫዎችም ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች በርካታ ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ሃገራቸውን ያስጠሩበት ዓመትም ነው።
በተጠናቀቀው ዓመት የሃገር ኩራት ከሆኑት አትሌቶች በተቃራኒ ኢትዮጵያን በመጥፎ ያስነሱም አልጠፉም። ይኸውም በዚህ ወቅት ስፖርቱን አደጋ ላይ እየጣለ ያለው የአበረታች መድሃኒት ጉዳይ ነው። በዓመቱ ሰባት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የአበረታች መድሃኒት ተጠቅመው መገኘታቸው በመረጋገጡ ከ2-4ዓመት ከስፖርቱ እንዲገለሉ ተደርጓል። አበረታች መድሃኒቶችን መሸጡ የተረጋገጠበት አንድ የመድሃኒት መደብርም በተመሳሳይ ለእገዳ የተዳረገበት ዓመትም ነበር።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
ብርሃን ፈይሳ