የግጥም፣ ዜማና ተውኔት ደራሲ ታደሰ ገለታ
የሙዚቃ ግጥም፣ ዜማና የተውኔት ደራሲ ነው:: ሥራዎቹ በአብዛኛው በሚባል ደረጃ በአንጋፋና እውቅ ሙዚቀኞች እጅ ደርሰው አንቱ ያስባሉ ናቸው:: በመረዋ ድምጽ ሲንቆረቆሩ ስሜት ይኮረኩራሉ:: በተለይ እርሱም ሆነ ድምፃዊ ጸጋዬ እሸቱ ሳይደነቁ አያልፉም:: ሌሎችም በተመሳሳይ። ከብዙዎቹ ጀርባ የእርሱ የአእምሮ ውጤቶች አሉ – የሙዚቃ ግጥም፣ ዜማና የተውኔት ደራሲ ታደሰ ገለታ::
«ግጥሞቼ በአንጋፋዎቹ ሲዘፈኑ ማየት ከደስታ በላይ ነው›› ይላል:: ወጣት ቢሆንም ብዙ አንጋፋ ዘፋኞች የወደዱትና ስለ ተሞክሮው የሚናገሩለት በመሆኑ ይህንን ልምዱን ለአንባቢያን ልናቀርብ የዛሬው የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› አምድ እንግዳችን አድርገነዋል።
ልጅነትና ሙዚቃ
ብዙ ሰው በሚሰባሰብበት፣ ጎረቤት እናትና አባት ሆኖ ልጅ በሚያሳድግበት አዲስ አበባ ቤላ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው የተወለደው:: ነሐሴ ሁለት 1974 ዓ.ም ። በወቅቱ ወንድ ልጅ በመወለዱ የተነሳ በመንደሩ የነበረው ደስታ ልዩ ነበር:: ግማሹ ሕፃኑን ያቅፋል፤ ግማሹ ደግሞ ለእንግዳ ቤት ያስተካክላል:: አራስ ያርሳል። ታደሰ ይህንን የተረዳው ካደገ በኋላ ነው። የጎረቤታሞችን መተሳሰብና ፍቅር ሲያይ ደግሞም ‹‹አንተ እኮ እኔ ሳልሆን ጎረቤት ነው ያሳደገህ›› ተብሎ ሲነገረው::
የወታደር ቤት በመሆኑ በልጅነቱ በርከት ያለ ሰው ሲሰበሰብም ትዝ ይለዋል:: ታደሰ በልጅነቱ አስቸጋሪ አልነበረም:: ይልቁንም ታዛዥ፣ አመለ ሸጋ፣ ከቤት የማይወጣና ሬዲዮ ማዳመጥ የሚወድ ነው:: በተለይ ሬዲዮ ከማዳመጡ ጋር ተያይዞ የታዘዘውን ይረሳ ነበርና አባቱ ‹‹ሺ ጊዜ እሺ›› እያሉ እንደሚጠሩት ያስታውሳል:: በእርግጥ እንቢ የሚል ቃል ከአፉ ወጥቶ ባለማወቁ ዛሬ ድረስ ደስተኛ ነው:: ብዙዎች እንዲወዱትና እንዲያከብሩት ያደረገው ዋናው ምክንያት ይሄ ነው:: በዚያ ላይ ከልጆች ጋር ተጣልቶ ስለማያውቅ ልጆችም በጣም ይወዱታል:: ከእነርሱ ጋር እንዲጫወት ሁልጊዜ ይጋብዙት ነበር::
‹‹ደበበ ሰይፉን ትተካለህ›› የሚባልለት የትናንቱ ሕፃን የዛሬው ጎልማሳ ታደሰ፤ መጀመሪያ ዜና በስፋት ማዳመጥ ይወዳል:: ከዚያ ውጪ ግን የአንጋፋና ተወዳጆቹ ዘፋኞችን ሙዚቃ ጣቢያ እየቀያየረ ማዳመጡን ይቀጥላል:: ይህ ምርጫው በሬዲዮ ጣቢያዎቹ ውስጥ ካልተላለፈ ሬዲዮኑን ዘግቶ ወደ ካሴት ማዳመጡ ይገባል:: ቤተሰቡ ሳይወድ በግድ የዘፈን አድናቂ እንዲሆን ያደረገው እርሱ እንደነበርም ያነሳል:: በእርሱ ምርጫ ካሴት ወይም ሬዲዮ ይከፈታል፤ ይዘጋል::
ታደሰ የሙዚቃ ፍቅሩ ኃያል ነው:: ስለዚህም ካሴት እየደጋገመ በኤ እና ቢ በሚል አገላብጦ ይሰማል:: በቃሉም ቶሎ የመሸምደድና የማንጎራጎር ችሎታ አለው:: ይህ ደግሞ ዛሬ ድረስ ከአንጋፎቹ ሙዚቀኞች ውጪ ሌሎች ምርጫዎቹ እንዳይሆኑ አድርጎታል:: ታደሰ በፈረንሳይ ለጋሲዎን አካባቢ ጫካ ውስጥ አባሮሽ፣ ሩጫና ሸርተቴን የመሳሰሉ ጨዋታዎችን እየተጫወተ ነው ያደገው:: በተለይ በሩጫ ማንም አያክለውምና ‹‹የሩጫ ንጉስ፣ ባቡሩ›› እያሉ ነበር የሰፈር ጓደኞቹ የሚጠሩት:: ከእነዚህ ጨዋታዎች ሁሉ ግን እንደ እግርኳስ የሚወደው እንዳልነበረ አጫውቶናል:: ብዙ ጊዜም ኳስ በማቀበል ልምዱ ብዙዎች ይወዱት ነበርና ቡድናቸው ውስጥ እንዲገባ ይለምኑታል:: ያቀበላት ኳስ ግብ አትስትም:: ይሁን እንጂ ከዚህም የሚበልጥ ምርጫ በቤት ውስጥ አለውና ብዙ ጊዜ ውጪ ወጥቶ ኳስ አይጫወትም:: ትምህርትቤት ከሆነ ደግሞ የወደደው ቡድን ውስጥ ገብቶ ይሳተፋል:: የፈረንሳይ፣ የቤላ ልጆችን እየወከለ ተጫውቷል::
ታደሰ አባቱን በደንብ ሳይጠግባቸው ነበር ያረፉት:: ስለዚህም እናቱ እናትም አባትም ሆነው ያሳደጉት ልጅ በመሆኑ ቤት ውስጥ እናቱን ማገዝ የሚወድም ልጅ እንደነበር ይናገራል:: ብዙ ነገሮችን በመስራትም ቤቱ ጎዶሎ እንዳይሆን ይሰሩ የነበሩትን እናቱን ቤት ከመጠበቅ እስከ ቤትውስጥ ሥራ ድረስ ያግዛቸዋል:: በተለይም እነርሱ ከአካባቢው ልጅ እንዳያንሱ ለማድረግ ያልቆፈሩት ድንጋይ እንዳልነበረና ከሰፈሩ ልጆች እኩል እንዲያድግ ሁሌ ስለሚጥሩ እርሳቸውን ለማስደሰት የማያደርገው ነገር አልነበረም:: በዚህም በጣም ይወደድ ነበር::
ታደሰ የልጅነት ፍላጎቱ ጎበዝ ገጣሚ መሆን ነው:: በተለይ የእርሱን ግጥም እንደነ ጂጂ፣ ነዋይና ሌሎች አንጋፎች አንጎራጉረው ቢያይ ደስተኛ እንደሚሆን ያስባል:: ምክንያቱም ወደዚህ ሙያ እንዲገባ ያደረገው የአንጋፎቹ ሙዚቀኞች መረዋ ድምጽ እንደሆነ ይናገራል:: ለዛሬ አንጋፎች ዘንድ መድረስ ነዋይ ደበበ፣ እጅጋየሁ ሽባባሁና የመሳሰሉት ድምጻውያን ሥራዎች ዋጋ አለው ይላል::
ትምህርት በሽምደዳ
የመሸምደድና ነገሮችን ቶሎ የመገንዘብ ልምዱ የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር:: ሬዲዮ ላይ የሚነገሩ ማንኛውንም ሙዚቃና ዜና ቶሎ የመቅለብ አቅም አለው:: ስለዚህም ይህንን ብቃቱን በትምህርት ላይ አውሎታል:: ባያነብም በተማረው ብቻ ውጤታማ ነው:: ይህ በቃል የመያዝ ልምዱ የጎለበተው ፈረንሳይ አቦ ቤተክርስቲያን የቄስ ትምህርት በመማር ላይ ሳለ እንደነበር ያስታውሳል::
ቄስ ትምህርት ቤት ከሥነምግባር ውጪ እውቀት ላይ አቅም እንዲፈጠር በማድረግ የማይተካ ሚና እንዳለው የሚናገረው ታደሰ፤ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሲገባ እንዳይቸገር የሆነውም በዚህ ቦታ በቀሰመው ልምድ እንደሆነ ያስረዳል:: ብቃቱ እያየለ ሲመጣም ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ማለትም መካነ ሕይወት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደገባም አጫውቶናል:: በትምህርት ቤቱ እስከ ስድስተኛ ክፍል ከቆየ በኋላ ቀጥሎ ያመራው ህብረት ፍሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው:: ሰባትና ስምንተኛ ክፍልንም በዚህ ተከታትሏል::
በትምህርቱ በጣም ጎበዝ ተማሪ በመሆኑ ቀጣዩን ክፍል ለመከታተል ከፍተኛ አስራ ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደገባ የሚናገረው ባለታሪኩ፤ በትምህርት ቤቱ እስከ 12ኛ ክፍል ተምሯል:: ከዚያ በኋላ ግን ምንም እንኳን ጎበዝ ተማሪ ቢሆንም ውጤቱ ከዲፕሎማ ውጪ ለመማር ዕድል አልሰጠውም። እሱም ከዚያ በላይ መቀጠል አልፈለገም:: ከዚህ ይልቅ በሚወደው ሙያ ላይ መሰማራት ፈለገና ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የቴአትር ክበብ አቋቋመ:: በዚያም የሚወደውን ሥራ እያከናወነ የትምህርት አቅሙን በሥልጠና ያጎለብት ጀመር:: መማር ማለት ዲፕሎማ ዲግሪና ከዚያ በላይ በሚጠሩት ደረጃ ላይ ብቻ መያዝ አይደለም:: በሚወዱት ሥራ ላይ ተሰማርቶ አቅምን እያጎለበቱ መሄድም ትምህርት ነው:: ስለዚህም በሥራ ውስጥ እየተማርኩ ነው ይላል::
የጥበብ ፍቅር
‹‹ሙዚቃ ሲደመጥ በተለያየ መልኩ ውስጥ የሚቀርበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ለአብነትም በፍቅር ሕይወት ውስጥ የፍቅር ዘፈኖች ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው ያደረጋል:: ከዚያ ውስጥ ደግሞ በወቅቱ የነበሩት ሙዚቃዎች የተለየ መስፈርት ኖሯቸው ይመረጣሉ:: እኔ ግን ምንም ባላወኩበትና ግጥሙ፣ ዜማው፣ ድምጹ ስለሚመች በማልልበት ሰዓት ነበር የሙዚቃ ዜማና ግጥም ደራሲ መሆንን የምመኘው›› የሚለው ታደሰ፤ ዘፋኞችን አውቆ የወደዳቸው የውስጥ ስሜቱ የመራውን አዳምጦ እንደሆነ ያነሳል:: ይህ ስሜቱ ትምህርቱን ከመቀጠል አስቁሞ ጥበብ ውስጥ ነከረው::
ታደሰ የነዋይ አድናቂ ብቻ አይደለም:: እነብዙነሽ፤ ጥላሁን ገሰሰ ለእርሱ ተመራጮች ናቸው:: ጸጋዬ እሸቱና አምሳለ ምትኬም እንዲሁ ሁሌ ባገኛቸውና ከእነርሱ ጋር ብሰራ የሚላቸው ሰዎች ነበሩ:: እናም የመጀመሪያ ሥራዎቹን በአቋቋመው ክበብ ውስጥ ሲከውንም የእነዚህን እንቁ ዘፋኞች ግጥምና ዜማ አንድም ሳይቀር እየጻፈ እንዲጫወቱት ያደርጋል:: ከዚያ አለፍ ሲልም ዜማቸውን ይወስድና በራሱ ግጥም በመጻፍ ልክ እንደነእርሱ ሆነው እንዲዘፍኑ ያበረታታል:: ይህ ደግሞ የግጥም ችሎታውን ከፍ እንዳደረገለት ነው የሚናገረው::
አቦል ቴአትርና የኪነጥበብ ክበብ አቋቋሞ ይሰራ እንደነበር የሚናገረው ታደሰ፤ ቀጥሎ የሥራዎቹ እድገት እንዲታዩ ያደረገውን ቅዱስ ያሬድ ሙዚቃና ቴአትር ኪነጥበብ ቡድንን ተቀላቅሏል:: በዚህም ብዙዎች አብረውት ሰርተው በእርሱ እገዛ ከያኒና ዘፋኞች ሆነዋል:: ከዚያ የመጀመሪያ የሙዚቃ ግጥሙን የሰጠበትን ሥራ ለመስራት የበቃበትን አባቱ የኮርያ ዘማች ስለነበሩ ዕድሉ የፈጠረለትን የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማች የልጅ ልጆች ቴአትርና የሙዚቃ ክበብ ተቀላቅሏል:: በዚህ ሁሉ ኡደት ውስጥ ግን አሁንም ረክቶ እንደማያውቅ ይናገራል:: ምክንያቱም የእርሱ ፍላጎት የግጥምና ዜማ ድርሰቶቹ ከአገር አልፈው ዓለም እንዲያውቃቸውና እንዲያደንቃቸው ነው::
ብዙዎችን በድምጻቸው፣ በግጥም ልኬታቸው፣ በአላቸው የአገላለጽ ደረጃ እየለካ የዘፈን ግጥም ሰርቶ የሚያስረክብ እንደሆነ ያጫወተን ታደሰ፤ እርሱ ግጥም ሲጽፍ ለማይመቻል የሚለውን ጠንቅቆ ያውቃል:: በዚህ ደግሞ ከመጀመሪያ ሥራው «እርጂኝ አብሯደጌ» እስከ አሁን የአንጋፋው ዘፋኝ ጸጋዬ እሸቱ «አንድ እንሁን» ድረስ ወደውት የሚመጡበት ሁኔታ እንደፈጠሩለት ይናገራል::
‹‹ሙዚቃ ለወደዳት ባለችው ሚጢጢ መረዳት የሚመሰጥርባት ከሆነ ቅርቧ ያሉ ጎበዞችን ሁሉ ማወቂያ ናት›› የሚለው ባለታሪኩ፤ የመጀመሪያ ሥራውን የሰራላቸውን እነ ትዕግስትና አበባ ደሳለኝን ያገኘው በሰው ሰው ነበር:: ከዚያ በኋላ ግን አድናቆቱ በየአካባቢው ናኝቶ ነበርና ያም ለእኔ ያም ለእኔ ማለቱን ተያያዘው:: እርሱ ግን ለማን ምን ዓይነት የሙዚቃ ግጥም መድረስ እንዳለበት ያውቃልና ምርጫዎቹ ላልሆኑት መስራት አይፈልግም::
ታደሰ ስለ ግጥም ምንነት መናገር ይሳነዋል:: ቃላት ቢፈልግም የለኝም ከሚለው ውጪ ማንሳት አልቻለም:: ምክንያቱም ግጥም ለእርሱ እንጀራው፣ ልጆቹን ማሳደጊያው፣ የመጻፍ ጥሙና ማርኪያውና የውስጥ ደህንነቱን መጠበቂያው ነው:: ‹‹ሕይወቴና መንፈሴን ማደሻም ነው:: ስለዚህ እንዴት በአንድ ቃል ላስቀምጠው›› ይላል ::
ብዙ ሰዎች በሚባል ደረጃ ግጥምን መስጠት እንጂ ከዜማ ጋር ይገናኝ አይገናኝን አይረዱም:: በዚህም የሚጥሏቸው ግጥሞች በርካቶች እንዲሆኑ አድርጓል:: ሲጣልባቸው ደግሞ ገንዘብ የማግኘታቸው ሁኔታ ይደናቀፋል:: ይህ ደግሞ የሁለቱን አካላት
ተግባብቶ የመስራት አቅም ያዳክማል የሚለው ታደሰ፤ ከሰዎች ጋር ተስማምቶ የመስራት ዕድል ብዙ ብር ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰላምም ይዞ ይመጣል የሚል እምነት አለው:: ስለዚህም ሁልጊዜ እርሱ ደንበኞቹ በምንም መንገድ እንዲከፉበት አይፈልግም:: እርሱ ይጎዳል እንጂ የእነርሱ ፊት ከፍቶት መመልከትን እንደማይፈቅድ ያስረዳል::
ባሳለፈው የሥራ ዘመኑ ምንም ዓይነት ሰው ‹‹ለእኔ እርሱ እንዲጽፍልኝ አልፈልግም::›› ያለው እንዳልነበር የሚያስረዳው እንግዳችን፤ አብዛኞቹን ፈላጊዎቼን የሚያውቅ፣ ምን ዓይነት የዜማና የግጥም ድርሰት እንደሚያስፈልጋቸው የሚረዳ በመሆኑና ሥራውን ከመስጠቱ በፊት ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታ ስለሚናገር ቅሬታ እንዳይፈጠር እንዳደረገ አጫውቶናል:: ይህ ደግሞ በደንበኞቹ እና በእርሱ መካከል ቤተሰባዊነትና መከባበር እንዲፈጠር እንዳደረገውም ይናገራል::
ታደሰ ብዙ ጊዜ ግጥሞችን ጽፎ የሚያስቀምጥ፤ ከዚያ ለመዝፈን የሚፈልግ ሰው ሲመጣ ምን ዓይነት ዜማ እንዳለው ጠይቆ የሚመቸውን መርጦ የሚሰጥ ታማኝ ደራሲ ነው:: ስለዚህም እርሱ ጋር የመጣ ዘፋኝ ግጥምና ዜማ ተደባደበብኝ የሚል አይኖርም:: በዚያ ላይ ሀሳቦች ከመጡለት ብዕሩን ከወረቀት ሳያገናኝ አይውልምና ለማንኛውም ዜማ የሚሆን ግጥም የማዘጋጀት አቅምን ፈጥሯል:: ስለዚህ እርሱ ጋር መጥቶ አጣሁ የሚል አይኖርም:: በተለይ አሁን ደስታ ከበደ ከሚባል ሙዚቀኛ ጋር አብረው እየሰሩ በመሆኑ የዜማ ጉዳይ ብዙም እንዳይጨነቅበት አድርጎታል::
ተከፋፍለው ግጥምና ዜማውን መስራት እጅግ ፈተና እንደነበረበት የሚናገረው እንግዳችን፤ ከግጥሞቹ ውስጥ አንድም ስንኝ እንዲቀር ባይፈልግም በዜማ ምክንያት ብዙ ጊዜ ይቆራረጥበት እንደነበር ያስታውሳል:: በተለይ መጀመሪያ ግጥሙን ጽፎ ዜማ ሲሰራ ማስቸገሩ እጅግ ይፈትነው ነበር:: አሁን ግን አብሮ የሚሰራው የዜማ ደራሲ በመሆኑ ዜማውን ሰምቶ ግጥም ይጽፋል:: በዚህም ቃላት ማሰማመርና የሀሳብ ምርጫ ካልሆነ በስተቀር የሚፈትነው እንደሌለ ያስረዳል::
ለአንጋፎቹ ሲጽፍ ከሀሳብ መረጣ ጀምሮ እንደሚጨነቅ ያጫወተን ታደሰ፤ እንደነይልማ ገብረአብ ዓአይነት ጸሐፊ መሆንን ይፈልጋል:: ስለዚህም በሥራዎቹ ሁሉ አርአያ አድርጎ የሚጽፈው እርሳቸውን እንደሆነም ነግሮናል:: ከነብሱ የሚጽፍ ገጣሚ መሆንን የሚሻው ታደሰ፤ ዘወትር ከሰዎች መማርንና ልምድ መቅሰምን ይወዳል:: ባህል፣ ዘመናዊነትና ኢትዮጵያዊነትን እንዲሁም ፍቅር ሰላም የመሳሰሉት ነገሮችን አጉልቶ በግጥሙ ውስጥ እንዲታዩ የሚያደርግ የዘፈን ግጥም ጸሐፊ ነው:: ይህ እንዲታይለት ደግሞ በብዛት መርጦ ግጥሞቹን የሚሰጠው ለአንጋፎቹ ድምጻውያን እንደሆነ ይናገራል::
ሥራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ፣ መልዕክት አድራሽ እና ኮርኳሪ የሆነው ታደሰ፤ ለሀመልማል አባተ የአልበም መጠሪያ ‹‹ተው ስማኝ›› ፤ ‹‹ይቅር እንባባልን›› እና ‹‹ደሞ መሸ›› እንዲሁም በጸጋዬ እሸቱ ‹‹አንድ እንሁን›› የተሰኘው ነጠላ ዜማ ውስጥ ብቻ የተጠቀመው የአገር አገላለጽ ብዙዎችን ያስደነቀ ነው:: ብዙ አድማጭም ያገኘ ነበር:: ግጥሞቹም በተለያየ መንገድ ሊፈቱ እንደሚችሉ ያሳየ ነው:: አንድም ለፍቅር አንድም ለአገር የመሆን ዕድላቸውም ሰፊ ነው:: ለአብነት ‹‹ቅምሻ›› በተሰኘው የአልበም መጠሪያ ውስጥ ሀመልማል አባተ ያቀነቀነችው ‹‹ይቅር እንባባል›› አንዳንዱ ለፍቅረኛው አሁን የአገርን ሁኔታ የተረዳ ደግሞ ለአገር እያደረገው ያደምጠዋል:: ከዘፈን ግጥሞቹ ስንኞች ውስጥ ጥቂት ስናይ የሚከተለው ነው::
«ተስማምተን በፍቅር ለመኖር አንድ ላይ
አረፈደም ገና አልገባችም ፀሐይ
ይቅር ለመባባል ካሰብን በቀና
ደንገዝገዝ አለ እንጂ አልጨለመም ገና፤…» ይላል:: ይህ ደግሞ ይቅር ለመባባል ጊዜ፣ ተስፋ እንዳለ ያመላክታል:: ሰላም መፍጠር መልካም እንደሆነም ይናገራል:: እናም ታደሰ እንዲህ ያሉ ዘፈኖችን ጭምር ነው በድምጻውያኑ አማካኝነት ለአድማጭ እያደረሰ ያለው::
ዘመን የማይሽራቸው፣ ወቅት የማይገድባቸው በአንድነት እና በፍቅር ላይ የተሞሉ ሥራዎቹ እንደታዩለትና እንደተደመጡለት የሚቆጥረው በታዋቂና አንጋፋዎቹ ድምጻውያን እንደሆነ የሚናገረው ባለታሪኩ፤ ግጥሞቹን የሰጣቸው ሰዎች በዘመን ሲከፋፈሉ ከወጣቶቹ ትዕግስትና አበባ፣ ሄለን፣ ሸዋንዳኝ፣ ጌትሽ፣ ትዕግስት ወይሶ ተጠቃሽ ናቸው:: ከአንጋፎቹ ደግሞ እነ አምሳለ ምትኬ፣ ዘለቀ ገሰሰ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ፋንትሽ በቀለ፣ ሀመልማል አባተ ይገኙበታል::
ፈተና
በወቅቱ ምክንያት ሥራዎች ወደ ሕዝብ ጆሮ ደርሰው አለመሰማታቸው ብዙ ግጥሞች በሰዎች እጅ ላይ እንዲያዙ አድርጓል:: ሁሉም ዘፋኝ ራሱ ገጣሚ መሆኑና ቃል ብቻ ለዘፈን መፈለጉም ሌላው ችግር መሆኑን የሚናገረው እንግዳችን፤ ዜማ ብቻ ተፈልጎ በዚያ ውስጥ ይገባሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮች ብቻ መሰብሰባቸው እንዲሁም ግማሽ ጽፈው ሙላልኝ የሚሉ መብዛታቸው ፈተና ሆኖበታል::
የዘፈን ግጥሙ ሳይኖር ሁሉ ክሊፖች ከተሰሩ በኋላ ለመሙያ የሚባለው ነገርም የሙያው ፈተና ነው:: ምክንያቱም ገጣሚያን ሀሳብ እንዳያመነጩ ከማድረጉም በላይ ራሳቸው ይህ ይሞላበት የማለት አዝማሚያን ይፈጥራሉ:: ግጥምም ዜማም እኔ ሰራሁት ለማለት ሲባል የሚደረጉ ሙያዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችም እንዲሁ ምርጫዎች እንዲጣበቡ አድርገዋል:: ይህንን ደግሞ የበለጠ ፈተና የሚያደርገው የሚዲያው ማራገብና ተደማጭነትን መፍጠር እንደሆነ ያስረዳል::
ሚዲያው የተበላሸ ዘፈንን እንኳን ሳይቀር በአደባባይ ያቀርብና ሕዝቡ እንዲቀበለውና እንዲያደምጠው ያደርጋል:: ይህንን ሥራ የሰራውን ሰው መሳለቂያ እያደረጉት መሆኑን ባለመረዳት በተቃራኒው ተቀባይነት አገኘሁ በሚል ስህተቱን ይቀጥልበታል:: በዚህም ደራሲያን፣ የክሊፕና ሌሎች ሥራ የሚያከናውኑ ሰዎች ዳር ይቀራሉ:: በጣም ጥሩ ሥራ ይዞ የመጣውም በዚያው ልክ የመደመጥ አቅሙ ይቀንሳል:: ስለዚህ ሌላው ፈተና ይህ ነው ይላል::
ማህበረሰቡ መርጦ አዳማጭ አለመሆኑና ሂስ መሰጠት መቆሙም ችግር ነው የሚለው ባለታሪኩ፤ ጥሩዎች እየተጠሉ እንዲሄዱ አድርጓል:: ግጥምን ሳይሆን ክሊፑን ብቻ አይ ሰው የሚል ትዝብት እንዲፈጠርም በር ከፍቷል:: በዚህም የገጣሚያን ድርሻ ዳር እንዲቀር እንዳደረገም ያስረዳል:: አሁን ተወዳጁ ምንም ትርጉምና ይዘት የሌለው ዘፈን ነው:: ድምጻውያኑ አልተሳሳትኩም የሚለው ደረጃ ላይም ደርሰዋል:: ስለዚህ አንጋፋና ጥልቅ ይዘት ያላቸውን ዘፈኖች ይዘው የሚመጡ ዘፋኞች እንዲጠፉ ሆኗል:: ገጣሚያንም እነርሱን አግኝተው እንዳይሰሩ ገድቧቸዋል:: በወር አንድ ጊዜ ብቅ የሚለው ዘፋኝ በዝቷል:: በተከታታይ የሚደመጥ፣ ዘመን ተሸጋሪ ዘፈንም እየቀረ ነው:: ስለዚህ ችግሩ የእኛ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ነው:: ብዙዎች ሲነኩ ደግሞ አንዱ እሆናለሁና ተጠቂ ነኝ ይላል::
አብዛኞቹ አንጋፋ ዘፋኞች በመድረክ ሥራ እንጂ ዘፈን አውጥቶ የመገኘት ሁኔታቸው አናሳ መሆን የሁሉንም ሠራተኛ የመስራት ዕድል ቀንሶታል የሚለው ታደሰ፤ በተለይ ከእነርሱ ጋር መሰራት የሚፈልግ ሰው ከሌሎች ጋር ለመስራት እየተቸገረ መሆኑን ያነሳል:: ስለዚህም እርሱም የመስራቴ ሁኔታ እየቀነሰ እንደመጣና ሌሎች ሥራዎችንም በተደራቢነት እየጀማመረ መሆኑን አጫውቶናል::
ስኬት
‹‹ገንዘብ ብቻ የውስጥ እርካታ ይሰጣል ብዬ አላምንም:: ስለዚህም እያንዳንዱ ሥራዬ ለነፍሴ እርካታን ሊሰጠኝ ይገባል:: ሥራዬን የምሰራው ከገንዘብ ይልቅ ለነፍስ እርካታ ተጨንቄ ነው›› የሚለው እንግዳችን፤ ስኬቱ ሁልጊዜ በአንጋፎች ውስጥ የሰራው ሥራ ነው:: ውጤቱን በመድረክ አይቶ ምላሽ ሲሰጠው ደግሞ በጣም እንደሚደሰት ይገልጻል::
ቶሎ አንጋፎቹን አግኝቶ ከእነርሱ ጋር ተመሳስሎና ተስማምቶ መስራቱም ለእርሱ ስኬቱ እንደሆነ የሚናገረው ባለታሪኩ፤ የተመለሰብኝ ሥራ አለመኖሩ ያስደስተኛል፤ ስኬታማ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል:: ከዚያ ባሻገር “ህልመኞቹ፣ ያልተጠገነ ልብ” እና መሰል የቴአትር ድርሰቶቹ በመድረክ ተተውነው መልካም ምላሾችን በማግኘቱ ከግጥም ባሻገር የቴአትር ጽሑፍ ብቃት እንዳለው እንዲረዳ ስላደረገው ይህን እንደስኬት ይቆጥረዋል::
ታደሰ እንደሚለው፤ ብዙ ስኬት ሊኖር አይችልም:: ብዙ ውድቀት ግን ይኖራል:: ከውድቀት መማርና መነሳት ስኬትን ያመጣል:: ስለዚህም እኔም ይህንን በማድረጌ ስኬታማነኝ ብዬ አስባለሁ::
ድምጽ የመሰረተው ቤተሰብ
ከባለቤቱ ጋር የተዋወቁት አቦል ክበብ ውስጥ በሚሰራበት ወቅት ነበር። ድምጽ ደግሞ በጣም ይስበው እንደነበር ያነሳል:: ፍቅራቸው በትዳር እንዲታሰር የሆነውም በዚህ አማካኝነት ነበር:: ዛሬ የሦስት ልጆች ወላጆች ሆነዋል:: የመጀመሪያ ልጁ በአካውንቲንግ ተመርቋል፤ ሁለተኛዋ ልጅ ደግሞ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ናት:: ሦስተኛዋ ገና የሰባት ወር ልጅ ናት:: ታደሰ ከሙዚቃ ውጪ ቤተሰቡ ውስጥ የሚወራ ነገር የለም:: የነዋይ አድናቂ በመሆኑ ምክንያትም ልጁን ሳይቀር ነዋይ ብሎ ጠርቶታል:: ራሱ ነዋይም ቢሆን ብዙ ነገሮችን ከእርሱ ጋር ይሰራልና በቤተሰቡ ውስጥ ኪነጥበብ ከአባት ብቻ ሳይሆን እናትም ልጅም ሆኖ እየኖረ ነው:: እንደውም ወሬው ሁሉ እንደዚያ እንደሆነ አጫውቶናል::
ምስጋና
‹‹እስካሁን ግጥም የሰራሁላቸው ድምጻውያን አቅም ያላቸውና በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁ እና የሚመረጡ ናቸው:: ሁሉም በሚባሉ ደረጃ ወዶና ፈቅዶ በቅናሽ ዋጋ ማሰራት ይችላሉ:: ነገር ግን እኔን መርጠውና አምነው በመምጣታቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ:: ምክንያቱም ገጣሚውም ሆነ የዜማ ደራሲው በእነርሱ ውስጥ እራሱን እንዲያይ ይሆናል›› የሚለው ባለታሪኩ፤ ለእነርሱ መስራት ጠንካራ ያደርጋል፣ ፈተናን በቀላሉ እንዴት ማለፍ እንደሚቻልም ያስተምራል:: ስለዚህም በእነርሱ ውስጥ ራሴን እንዳይና እንዳጠነክር ስላደረጉኝ አመሰግናቸዋለሁ ይላል::
ታደሰ በአንድ ቀን የተሰሩ የዘፈን ግጥሞች እንዳሉት ይናገራል። ይህ የሆነው በእነጸጋዬ እሸቱና ነዋይ ደበበ አበረታችነት እንደሆነ ይናገራል:: ብዙ የማመሰግናቸው ሰዎችም አሉ። በተለይ የመጀመሪያ ሥራዬን እንድሰራ ያበረታታኝ ምስጋና ይድረሰው ይላል:: ግጥም በቀላል አማርኛ የሚገለጥም አይደለም:: የልብን ምት ከእስትንፋስ ጋር አዋህዶ ለውስጥ እርካታ የሚፈነጠቅ ብርሃን ነው:: በአጠቃላይ ግጥም ሕይወት ነው:: የግጥምን ሕይወትነት ያሳዩኝ ሁሉ ምስጋና ይድረሳቸውም ይላል::
መልዕክት
የመጀመሪያው መልዕክቱ መገናኛ ብዙኃን ላይ ያነጣጠረ ነው። ጥበብን ሲያስተዋውቁ ጥበበኛ ሊሆን ይገባል። መጥፎውን ማስተቸት፣ ጥሩውን ደግሞ ማበርታታትና ተደማጭነት እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርባቸዋል:: አንድን ዘፈን ደጋግሞ በመልቀቅ ሰዎችን ማሰልቸት የለባቸውም:: ምክንያቱም ሕዝብ አዲስ ነገር ይፈልጋል:: በይዘትም ሆነ በትርጉም እርሱን የሚለውጥ ሙዚቃን ይሻል:: ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ይህንን ማድረግ አይቻልምና ጉዳዩን ልብ በሉት ይላል::
ሌላው ለኅብረተሰቡ ያስተላለፈው መልዕክት ነው። አድማጭ መራጭ መሆን አለበት:: ሙዚቀኞችን ለመግራት እንደሕዝብ ጠበቃ መሆን ይገባል፤ ባህላችንን ያልጠበቁና ለእኛ ጠቃሚ ያልሆኑ ነገሮችን ማስወገድ እንጀምር ሲል ይመክራል። ትልልቆቹን የምናከብረው ታላቅ ሥራ ሰርተው ያለፉትን ጀግኖች በሚገባው ልክ የሚያከብር ትውልድ ስንፈጥር ነው:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ ተተኪዎችን መግራት ላይ ሊሰራ ይገባል ባይ ነው::
ሁልጊዜ የጥንት ዘፋኝን ማን ያክላል የሚባለው ያለምክንያት እንዳልሆነ የሚያነሳው እንግዳችን፤ ገድል በማንሳት ብቻ የሚኖር ዘፋኝ ለመፍጠር መስራት አይገባም:: አዳዲስ ጥላሁኖችን፣ ነዋዮችን፣ ጂጂና ሀመልማሎችን ማፍራት ይገባል:: ለዚህ ደግሞ እነርሱን ትልቅና እውቅ ዘፋኞች ያደረጋቸውን እውቀት ማስጨበጥ ያስፈልጋል የሚለው የመጨረሻ ምክረሃሳቡ ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው