ህዝብ ዥንጉርጉር ባህርይ አለው፡፡ በመልክና በአካላዊ ቅርፅ የመለያየቱን ያህል በግላዊ ባህርይውም የተለያየ ገጽታ ይኖረዋል፡፡ ይህንን እውነታ ማስወገድ አይቻልም፡፡ ከሰፊው ህዝብ ውስጥም ጥቂት ስለህዝብ የሚሠው ይፈልቃሉ፡፡ በአንጻሩ ከሰፊው ህዝብ ውስጥ፤ ጥቂት ግለሰቦች ለራስ ጥቅም ይሸነፋሉ፤ ከህዝብ ውስጥ ፈልቀው ህዝብን የሚጠቅሙ እንዳሉ ሁሉ ህዝብንም የሚጎዱ ዜጎች ይፈጠራሉ፡፡ የግጭት ወይም የጦርነት ተዋናዮችም ህዝቦች ናቸው፡፡ አንዱ ህዝባዊ ባህርይ ሲኖረው ሌላው ከዚህ ተቃራኒ በመሆን በሚፈጠር ልዩነት ግጭት ይፈጠራል፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ ቢያንስ አንዱ ግንባር ወይም አንዱ ተጋጣሚ ህዝባዊነት ስሜት ሊኖረው ይችላል፡፡ አንዳንዴ እንደዕድል ሆኖ ሁለቱም አካላት ህዝባዊነት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ጦርነት ወይም ግጭት የሚለኰሰው ለራስ ጥቅም በማሰብ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ለህዝብ ደህንነት ተብሎም ጦርነት ይታወጃል፡፡ ያም ሆነ ይህ፤ በመጨረሻ ህዝቡ በአሸናፊው ኃይል መዳፍ ውስጥ ይወድቃል፡፡ እንደኢትዮጵያ የመሳሰሉት ሀገሮች ማለትም ብዙ ባህላዊ ልዩነቶች ያላቸው ህዝቦች ያሏቸው እና ብሔረ መንግስት ግንባታ ያላጠናቀቁ ሀገሮች፤ ዜጎች በአንድነት ለሰላምና ለመለወጥ ካልቆሙ፤ ህዝቦች ይበታተኑና በድህነት ወደ ታጀበ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ በተለይ በዚህ ረገድ የመንግስትና የምሁራን ሚና ከፍተኛ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በአገራችን ዩኒቨርቲዎች ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ከባድ ደረጃ ላይ ይገኛል። በዚህም ዩኒቨርስቲዎች አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ወደቤታቸው የሄዱ አንዳንድ ተማሪዎች ጥሪ ቢደረግላቸውም መመለስ እንዳልቻሉ የመንግስት ሪፖርት ያመለክታሉ። እናም ችግሩ መፍትሄ ካላገኘ የባሰ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ሪፖርቱ ይገልጻል። በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ግጭት ተቀስቅሶ በነበረባቸው ዩኒቨርስቲዎች በመዟዟር ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የመንግስት ግብረሃይል ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከታዩት ችግሮች ውስጥ ተቋማቱ በምክትል ፕሬዚዳንቶችና በተወካዮች መመራታቸው በተለይ በዲላ፣ በአዲግራት፣ በአሶሳ፣ ጋምቤላና ወላይታ ሶዶ፣ በተቋማቱ ውስጥ የቦርድ አመራሮች መጓደል፣ የተመደቡባቸውም የቦርድ አመራሮቹ በተደራራቢ ሥራ መጠመድ፣ ቦርድ አመራሩ ከተቋማቱ ፕሬዚዳንቶች ጋር ተቀናጅቶ አለመስራት፣ የተቋማቱ አመራር በተማሪዎች ተቀባይነት ማጣት ናቸው፡፡
ከላይ የተቀመጡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በቦታው አለመኖር ችግሮች ሲነሱ መፍትሄ ለመስጠት አስቸጋሪ ማድረጉን ይናራሉ፡፡ የተቋማቱ የቦርድ አመራሮች በፖለቲካ ስራና በተመደቡበት ስራ በመጠመዳቸው ተቋማቱ ችግር ሲገጥማቸው በፍጥነት ለመፍታት አስቸጋሪ ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡ አንዳንድ ተቋማት ውስጥ ብጥብጥ ሲነሳ ፕሬዚዳንቶች ስልካቸውን እንደሚዘጉም ይነገራል፡፡ ከግብዓት ችግር ደግሞ የላቦራቶሪ እቃዎች አለመሟላት፣ የመምህራን እጥረትና የመቅጠር ስራው መጓተት፣ የውጭ መምህራን የአገሪቱን የትምህርት ስርዓት ባለመረዳታቸው የአቅም ማነስና የውሃና የመጸዳጃ ቤቶች አለመኖር እንደሚገኙበት የጠቀሱት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ፤ እነዚህ ጉዳዮች ተማሪዎቹ እንዲበጠብጡ መነሻ ምክንያት እንደሆናቸው ያስረዳሉ፡፡
ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች በአካባቢው ቤት በመከራየት ዘረፋና በሁከቶች ላይ ዋነኛ ተሳታፊ መሆን፣ በተቋማቱ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል ለማፍራት እንቅስቃሴ መብዛት፣ የመውጫ ፈተናዎች እንደየ ተቋማቱ የተለያየ መሆን፤ ከአንድ ክልል የመጡ ተማሪዎች ተመሳሳይ ትምህርት ክፍል መመደብ፣ ተማሪዎችን በፆታና በሀይማኖት እንዲሁም በብሄር መከፋፈል እና ተማሪው ስራ አላገኝም በሚል መንፈስ ለመማር ተዘጋጅቶ አለመምጣት ችግሩን አባብሶታል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ሰላም ደፍርሶ የመማር ማስተማሩ ስራው ተስተጓጉሏል፡፡ በክልሉ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው የመማር ማስተማር ሁኔታው ምን እንደሚመስልም የክልሉን ትምህርት ቢሮ የስራ ሃላፊ አነጋግረናል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ተሰማ እንደሚናገሩት፤ በ2010 ዓ.ም ማጠቃለያን በማየት በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለማስጀመር እቅድ ወጥቶ በክልል ውስጥ ወደ 16 ሺ 500 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማር ማስተማር ስራው እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ በ2011 ዓ.ም የትምህርት እቅድ በስርዓቱ እንዲተገበር በትምህርት ሳምንት እንደተለመደው በሁሉም ትምህርት ቤቶች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በዓመቱ የትምህርት ሁኔታ ላይ የ2010 ዓ.ም የትምህርት ዓመት አፈፃፀም እንዲገመገም ተደርጎ የ2011 ዓ.ም እቅድ ላይ አሳታፊ በሆነ ሁኔታ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የትምህርት ሁኔታውን በስኬት ለመምራት ምክክር ተደርጓል፡፡ በተያዘው ዓመት ወደ 10 ሚሊዮን ተማሪዎች በሁሉም ደረጃዎች ቅበላ ተደርጎ ወደ ማስተማር ተገብቷል፡፡
በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ በተወሰኑ ቦታዎች ማለትም ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚዋሰኑ አካባቢዎች በምዕራብና በምስራቅ ወለጋ ድንበር አካባቢ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች መቋረጣቸውን አቶ ኤፍሬም ይናራሉ፡፡ በአካባቢዎቹ የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት በስርዓት የማይሄዱባቸው ድንበር ላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች አሁንም ድረስ ዝግ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በምዕራብ ወለጋ 13 ትምህርት ቤቶች እና በምስራቅ ወለጋ 26 ትምህርት ቤቶች በሰላም እጦት ምክንያት ተዘግተዋል፡፡ እነዚህን ተማሪዎች በአቅራቢያው ተፈናቅለው በሚገኙባቸው ቦታዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተቀብለው እንዲያስተምሯቸው እና የተቃጠሉት ጊዜያት እንዲካካሱ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡ ማህበረሰቡ ደግሞ ልጆቹን እንዲንከባከብ እና መምህራንም በተለየ ሁኔታ እንዲይዟቸው ውይይት መደረጉን ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ኤፍሬም ማብራሪያ፤ በተያዘው ሳምንት ውስጥ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ገባ ወጣ የማለት ሁኔታዎች አሉ፡፡ በተለይ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ አሁንም ድረስ ችግሩ አለ፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስጋቶች በመኖራቸው ትምህርት ቤቶች በስርዓት እያስተማሩ አይደለም፡፡ ቀደም ብሎ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል በነበረው ግጭት በተፈጠሩ የትምህርት መስተጓጉሎች ማካካስ ስራዎች አምና ተከናውኗል፡፡ በተያዘው ዓመትም እንደመፍትሄ የተወሰደው ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች የማካካሻ ትምህርት ክፍለ ጊዜዎች ተዘጋጅቶ ተማሪዎቹ የሚጠበቀውን ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት አስፈላጊው እርምጃዎች እንዲወሰዱ ከአስተዳደር፣ ከፋይናንስ እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመነጋገር እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
«አሁን ያለው ሁኔታ ጊዜያዊ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሁኔታው እንዳይረጋጋና አካባቢው ሰላም እንዳይሆን የሚፈልጉ ለክፉ ዓላማ የተሰለፉ የተወሰኑ አካላት አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ጥቅማቸውን ሊያገኙ የሚችሉት ሰላም በማይኖርበት አካባቢ ነው፡፡›› የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ ጥቅም ለማግኘት ህዝቡን ማወናበድ ያልሆኑ ነገሮች እንደተፈጠሩ በማስመሰል እንዲሁም ባላቸው ገንዘብ በጥቅም የተገዙ ግለሰቦች በማሰማራት ማወናበዶች እንደበዙ ይገልፃሉ፡፡ ለትምህርት እያንዳንዱ ደቂቃ ዋጋ አለው፡፡ በመሆኑም ወጣቱ በተለይ ተማሪ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ቤተሰብና የትምህርት አስተዳደሮች ተረድተው ተማሪዎችን እንዲያበረታቱ ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ ማድረግ እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ሰላም አስከባሪዎችም በዚህ ላይ ተባብረው የትምህርት ሁኔታው ሰላም እንዲሆንና ትምህርት በሰላም እንዲሰጥ ስራቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡
በአሁን ወቅት የኦሮሚያ የጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር አለሙ ዋቅጋሪ እንደሚናገሩት፤ በወለጋ ዩኒቨርስቲ አንድ ሳምንት ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በተፈጠረው ረብሻ ትምህርት እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ካሳለፍነው ሳምንት በፊት ደግሞ ተከፍቶ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ ተቋርጧል፡፡ መቋረጡ በምዕራብ ነቀምት ያለው የሰላም ችግር ያመጣው ነው፡፡ በአሁን ወቅት በምዕራብ ነቀምቴ እንቅስቃሴዎች ቆመዋል፡፡ በአካባቢው መኪናዎች ስለማይንቀሳቀሱ ስራዎች በመቆማቸው በዩኒቨ ርስቲውም የመማር ማስተማር ስራው ተስተጓጉሏል፡፡
እስካሁን በዩኒቨርስቲው ውስጥ በተማሪ መካከል የተፈጠረ ችግር እንደሌለ የሚናገሩት ዶክተር አለሙ፤ በአቅራቢያ ከተሞች የሚኖሩ ተማሪዎች ወደየቤታቸው የሄዱ ሲሆን የተቀሩት ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ወስጥ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ፡፡ በአሁን ወቅት ዩኒቨርስቲው ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኝም ያመለክታሉ፡፡ ቀደም ሲል በተፈጠሩ ብጥብጦች የተገደሉ ተማሪዎች እንደነበሩ የሚያስታውሱት ዶክተር አለሙ፤ መከላከያ ሰላም ለማስጠበቅ ገብቶ በነበረበት ወቅት የተከሰተ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ በተጨማሪም ከሶስት ሳምንት በፊት ባልታወቀ ምክንያት አንድ ተማሪ መሞቱንና ከውጭ የሚገቡ አካላት ውጪ በተማሪዎቹ መካከል እርስበርስ የተነሳ ችግር እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡
በቀጣይ ዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ሊሾምለት እንደሚገባ በመጥቀስ፤ በአሁን ሰዓት በምክትል ፕሬዚዳንት መመራቱ ስራዎች እንዲደራረቡ ማድረጉን ይናራሉ፡፡ የአካባቢው ባለስልጣናት ከተማሪዎች ጋር ውይይት በማድረግም ተማሪዎቹ የራሳቸው ጥያቄዎች ሊኖሯቸው ስለሚችሉ መመለስ እንደሚገባም ይጠቅሳሉ፡፡ የመንግስት ኃላፊዎችም በቅርቡ ተማሪዎቹን ለማነጋገር ከመጣ ተማሪዎቹ ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
መርድ ክፍሉ