ፈረንጆቹ የገና በዓላቸውን ካከበሩ ሳምንት ሆኗቸዋል፤ ዛሬ ደግሞ አዲስ ዓመታቸውን እየተቀበሉ ነው። በኢትዮጵያዊያን የቀን መቁጠሪያ መሰረትም ከሳምንት በኋላ የገና በዓል ይከበራል። ለበዓላት ማድመቂያ ከሚውሉት ነገሮች መካከል ምግብና መጠጥ ቅድሚያ ተጠቃሽ ነው። በእኛ ባህል መሰረት ስጋ ነክ ምግቦች፣ ዳቦ እንዲሁም ጠላና ጠጅን የመሳሰሉ መጠጦች ይዘጋጃሉ። ከወቅቱ የኑሮ ሁኔታ ጋር ተያይዞም ባህላዊውን ምግብ ማዘጋጀት ያልቻሉ ዜጎችም በፋብሪካ የሚመረቱትን በአማራጭነት መጠቀም እየተለመደ ነው።
የምግቡን አቆይተን ለዛሬ ስለ መጠጡ እናንሳ፤ በበዓላት ወቅት በፈረንጆቹም ሆነ በእኛ ዘንድ የወይን ጠጅ ተመራጭ የሆነ መጠጥ ነው። ታዲያ ደስታ አየር በሚነፍስበት የበዓል ቀን በተለያዩ ምክንያቶች እንደሌላው ሰው አልኮል ያላቸውን መጠጦች የማይቀምሱ ሰዎች ያጋጥማሉ። መጠጣት ባለመቻላቸውም ሊከፉ ይችሉ ይሆናል፤ ከዚህ በኋላ ግን «መፍትሄ ተገኝቷልና ማንም ሰው ወይን መጠጣት እያማረው አይቀርም» ይላል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ።
በስፔን የሚገኝ አንድ ድርጅት እንዳስታወቀው ከሆነ የወይን ጣዕም ያለው ውሃ ማዘጋጀት ችሏል። ውሃው ምንም ዓይነት የአልኮል ይዘት የሌለው ሲሆን፤ በቀይ እና በነጭ አማራጭ መቅረቡም ነው የተሰማው። ይህንን ውሃ ለመስራትም የወይን ጠማቂዎች እንዲሁም በከፍተኛ ምርምር ላይ የተሰማሩ ሳይንቲስቶች ለሁለት ዓመታት በሙከራ ላይ ቆይተዋል። በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ይፋ ያደረጉትን ውሃ የትኛውም ሰው በየትኛውም ቦታ ሊጠጣው ይችላል፤ የአሰራር ሂደቱ ግን በሚስጥርነት ተጠብቆ የሚቆይ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በመጠጡ የምርት ምርምር ከተሳተፉት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የባይሎጂ ምሁሩ ዶክተር ካርመን ማርቲኔዝ፤ ውሃው ከወይን የሚዘጋጅ እንደመሆኑ የወይን ፍሬ ሊያስገኝ የሚችላቸውን የጤና ጥቅሞች ሊሰጥ እንደሚችል በአስተያየታቸው ላይ ጠቁመዋል። ውሃው የሚዘጋጀው ከሁለት የወይን ዝርያዎች ሲሆን፤ ሜንሲያ (ለቀይ የወይን ውሃ)፣ ጎዴሎ ደግሞ (ለነጭ የወይን ውሃ) ነው ይሆናል በዝግጅቱም ምንም ዓይነት ኬሚካል አይገባም። በወይን ምርት ታዋቂ ከሆነው አካባቢ የተገኘ የወይን ፍሬ እንዲሁም የምንጭ ውሃ ደግሞ ዋንኛዎቹ ግብአቶች ናቸው።
ስሙ ያልተጠቀሰ ሌላ በምርቱ ላይ የተሳተፈ ግለሰብም «ወይን እንደመጠጣት ነው፤ ነገር ግን አልኮል የሌለው በመሆኑ ጤናማ የሆነ ውሃ ነው» ብሏል። መጠጡ እስካሁን ወደ ገበያ ያልወጣ ቢሆንም፤ በቅርቡ ከስፔን አልፎ ወደ ጃፓንም ለመላክ ታስቧል። የተለያዩ አየር መንገዶችም በምርቱ ላይ ያላቸውን ፍላጎት ከወዲሁ በማሳየት ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል። ስፔን በወይን ጠጅ ምርት የታወቀች ሃገር ስትሆን ሰማያዊ እና ሌሎች ቀለማት ያላቸውን የወይን ጠጆች በማምረት እንዲሁም አልኮል አልባ ቢራ በመጥመቅ ቀዳሚ ሃገርም ናት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
ብርሃን ፈይሳ