በሙከጡሪ ጎዳና
ጎዳና እና ብርሃኑ ከበደ በጣም የሚተዋወቁ ጓደኛሞች ናቸው።አንደኛው ለሌላኛው አዛኝ፤ አንዱ ለሌላው አስታዋሽ ይመስላሉ።አብሮነታቸው ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።ጎዳናው ሲከፋ ብርሃኑ ይከፋዋል፤ ጎዳው ፀጥ ረጭ ሲል ብርሃኑም ጭጭ ይላል።ጎዳናው ሞቅ ደመቅ ሲል ብርሃኑ እንደጎዳናው ይደምቃል።ጎዳና በዝናብ ሲጥለቀለቅ የዚህ ሰው ፊትና ልብስ አብሮ ይወረዛል።አቧራ ከተማዋን ሲጎበኛት ብርሃኑንም በአፉና በአፍንጫው አቧራውን ይጋራል።በአጠቃላይ ብርሃኑ ሙከጡሪ ከተማን የሚጎበኛትን መጥፎም ሆነ ጥሩ አጋጣሚ ከእይታው አይሰወርም።
ሊስትሮዎች፣ ወዛደሮች፣ ሥራ ፈላጊዎች፣ አቅመ ደካሞች፣ መንገደኞች ሲተክዙም ከእርሱ አጠገብ ቁጭ ብለው ያማክሩታል፤ ከዚያም ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ያጽናናቸዋል።ለአንድ አፍታ ቁጭ ይሉና ሃሳባቸውን ሰብሰብ አድርገው ይሄዳሉ።መንገደኞችም እንደ ፖስታ ቤት በአደራ መልክ ዕቃ ሰጥተውት ይሄዳሉ።ትራፊኮች፣ ፖሊሶች፣ አስተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች ከብርሃኑ ዘንድ ቆም ብለው ሠላምታ መለዋወጥ የተለመደ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው።‹‹ብሬ አሻም›› ይሉታል፤ እርሱም አፀፋውን ይመልሳል።ቀልድ ቢጤ ጣል አድርጎላቸው ፈገግ እያሉ ይሄዳሉ።ብሬም አንገቱን ሰበር አድርጎ ነጠላው እየቋጫ በፈገግታ ይሸኛቸዋል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ የፀሐይ ግለት ሲበረታባቸው አንድ አንጓ አገዳ ይገዙትና እዛው እያጣጣሙት አብረውት ይጫወታሉ።ሱቅ ተልከው ትንሽ ሳንቲም እጃቸው ላይ የተረፈ ሕፃናትም ወደ ብርሃኑ ጎራ ብለው ‹‹ሸንኮራ ናኬኒ›› ብለው ገዝተውት ይሄዳሉ።ጥቂቶች የልጅነት ከፊል ትዝታቸው ከብርሃኑ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ከሌላ ሥፍራ ኖረው ወደ ከተማዋ ሲመጡ እንኳን ወደ እርሱ ጎራ ብለው ያጫወቱታል።ከትዝታ ጓዳ ጨዋታቸውን እየቀዱ ያወጉታል፤ አገዳም ይገዙታል፤ ያበረታቱታልም፡፡
በሽታ ክፉ ሰው
በአንድ ወቅት ህመም ወደ ብርሃኑ ቤቱ ጎራ አለ።ወደ ህክምና አመራ።ወገቡ ላይ ከፍተኛ ህመም አጋጥሞት ስለነበር ሆስፒታል ሄዶ መለስተኛ ቀዶ ህክምና አደረገ።በመቀጠል ወደ ቀዬው ሄዶ በግብርና ሥራው ለመቀጠል አሰበ፤ ግን አልተሳካለትም።ህመሙን መቋቋም አልቻለም።እርሱ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ መሬቱ ፆም ሊያድር ሆነ።‹‹ሰናኙ ገበሬ›› እንዳልተባለ መሬቱ ሌላ ሰው ሊያርሰው፣ ሌላ ሰው ሊጎለጉለው ሌላ ሰው ሊያርመው፣ በአውድማው ሌላ ሰው ሊያበራይ፣ ሌላ ሰው ምርቱን ሊሰበስብ ግድ ሆነ።በዚህ ጊዜ በቀዬው መቆየቱ ብዙም ስሜት አልሰጥ አለው።ይሻለኝ እንደሆነ ብሎ ወደ ሌላ ሥፍራ ፀበል ሄደ።ሌሎች አማራጮችንም ሞከረ።ምንም እንኳን መጠነኛ መሻሻል ቢኖርም ሙሉ ለሙሉ ግን ማገገም አልቻለም።
ታዲያ በዚህ ጊዜ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወሰነ።ትዳሩም እንደ ቀልድ ፈረሰ።ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ትዳር አላሰበም።ባለቤቱም ሌላ ትዳር ውስጥ አልገባችም፤ ግን አብረው መኖር አልቻሉም።እርሻውን ትቶ፤ ከቀየውም ርቆ ሌላ ሥራ ለመስራት ወሰነ።ሙከጡሪ ከተማ ከገባ በኋላ አንድ ሥራ መጣለት ሸንኮራ አገዳ መነገድ።ከዚያም ለሚ፣ ደብረፅጌ፣ ወበሪ፣ ደብረሊባኖስ ሌሎች አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ አገዳ እየገዛ ወደ ሙከጡሪ ያመጣል።እንደ ወቅቱ ሁኔታ ደግሞ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ቆቆር እና የመሳሰሉትን እየገዛ ከሙከጡሪ አስፋልት ዳር ሆኖ እየቸረቸረ ኑሮውን መምራት ጀመረ።
የተበተነ ትዳር
ብርሃኑ በህመሙ ምክንያት ከገጠር ራቅ ብሎ የከተማ መናኝ ሆነ።ፊቱን ወደ ሰፈሩ ማዞርን እርም አለ።በቃ በከተማ ውስጥ መናኝ ሆኖ ሥራው፤ ኑሮው ሁሉ ነገሩ ሙከጡሪ ከተማ ሆነች።ግን አንድ ነገር ማድረግ ነበረበት።ሁለቱን የአብራኩን ክፋዮች ይዞ መኖር።አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጁን ይዞ ሸንኮራ አገዳውን እየሸጠ ያሳድጋቸው ጀመር።እንደ ዛሬ ነገሮች ሳይወደዱ በወቅቱ የቤት ኪራይ አምስት ብር ስለነበር ብዙ አልከበደውም። እንደምንም ብሎም ልጆቹን አሳዳገ፤ ትምህርት ቤትም አስገባቸው።ዛሬ ሁለቱ ልጆቹም ለአቅመ አዳምና ሄዋን ደርሰዋል።ወንድ ልጁ ሆቴል ውስጥ ተቀጥሮ ራሱን ለማሸነፍ ይሠራል፤ ሴት ልጁም ሕይወቷን ለመቀየር ወደ አረብ አገር አመራች።ግን እርሱ ለራሱ ወጥ እየሰራ፤ ቤት እያፀዳ ብቻውን ይኖራል።ዛሬም ከመንገድ ዳር ሆኖ አገዳውን ይቸረችራል።ጎን ለጎንም ነጠላ እና ጋቢ ይቋጫል።እንዲህ እያለ ያለፉትን 20 ዓመታት የጤና እክሉን ተቋቁሞ ሕይወቱን እየመራ ነው።
የኑሮ ነገር
እንደ ብርሃኑ ኑሮን በአንክሮ የታዘበ ሰው የለም።የኑሮን መጦዝን ለማስረዳት የሌሎች ሸቀጦችን ዋጋ ዝርዝር ማየት አይሻውም።ሸንኮራ አገዳ ችርቻሮ መሸጥ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያለውን ሁኔታ ማስታወስ ብቻ ለእርሱ በቂ ነው።በእርሱ አረዳድ የኑሮ ግሽበት በጣም ጣሪያ ነክቷል።የኢትዮጵያ ገበያ ተለዋዋጭነትም ልጓም የሌለው ፈረስ ሲል ይገልፀዋል።
ለአብነት ከ20 ዓመት በፊት ሸንኮራ አገዳ ሲነግድ በቁመቱ አንድ ሜትር ከግማሽ የሚሆን ሸንኮራ አገዳ ቢበዛ ዋጋው 25 ሳንቲም ነበር።በዚያን ጊዜ አስር ሳንቲም ያለው ከቤት ውስጥ ያሉ ልጆቹን ፍላጎት ለማርካት አንድ ዘንግ አገዳ ገዝቶ ወደቤቱ ማምራት በቂው ነው።አምስት ሳንቲምም እጅግ የተከበረ ዋጋ እንዳላት ያስታውሳል።ታዲያ እነዚህ ሳንቲሞች ዛሬ በሸንኮራ አገዳ ተራ ምንም ነገር እንደማይገዙ ይናገራል።
ከ20 ዓመት በፊት በ10 ሳንቲም ይገዛ የነበረ አገዳ ዛሬ እስከ 20 ብር ይደርሳል።አንዳንዴ ከዚያም ይልቃል።ብርሃኑ ሸነጥ አድርጎት ምላስ ሰንበር ቁርስ ይበላ እንደነበር ያስታውሳል፤ ከ20 ዓመት በፊት ለዚያውም በአንድ ብር።ዛሬ ግን አንድ ብር በሥጋ ቤት አካባቢ እንኳን ዋጋ ልትሆን ስሟም የለም።ዛሬ ላይ 50 ብር ተከፍሎም ምላስ ሰንበር ከተበላ እንደ ዕድል ይቆጠራል ሲል ልዩነቱን እያነጻጸረ ነግሮናል፡፡
ከ20 ዓመት በፊት በ10 ብር የሚገዛውን ሸንኮራ አገዳ ብቻውን ተሸክሞ ማንቀሳቀስ ይከብደው ነበር።ከመብዛቱ የተነሳ ሰዎች እንዲያግዙት ይማጸናል።ሳምንቱን ሙሉም ሸጦ ላይጨርስም ይችላል።ግን ዛሬ ላይ 500 ብር ድረስ አውጥቶ የሚገዛት ሸንኮራ አገዳ ያኔ በ10 ብር ከሚገዛው ጋር ልዩነት እንደሌለው ያስረዳል።‹‹እነዚህ ነገሮች የኋሊት ሲያስባቸው አንዳንዴ ህልም ይመስለኛል›› ይላል ብርሃኑ።በእርሱ አረዳድ ኑሮ እያደገ እየተመነደገ ሰማይ ሲነካ፤ እኔ ግን ከጠቀመጥኩበት ሥፍራ ዕድሜዬ ገፍቶ ፀጉሬ ሸብቶ ዛሬም አለሁ ይላል።ከሸንኮራ ሽያጭ በቀን የሚያገኛትን 50 ብር ለቀለቡና ለቤት ኪራይ እያዋለ ነገን በተስፋ አሻግሮ ይመለከታል፡፡
የከተማዋ አንቴና
ብርሃኑ ከቅንነቱ የተነሳ ሰዎች ቦታ ሲጠፋቸው እጃቸውን ይዞ ከሚፈልጉት ቦታ ያደርሳቸዋል።በተለይ ደግሞ ከገጠር የሚመጡ ሰዎች እንዳይሸወዱ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።እርሱ ሳይንቀሳቀስ ካለበት ቦታ ሆኖ ስለከተማዋ ጥሩ ጥሩ መረጃም ይደርሰዋል።አንዳንዶች ሲቀልዱበት ይህ እኮ የከተማችን አንቴና ነው ይሉታል።ነገሮች የሚያስቁና ሰዎችን የማያጋጩ ከሆነ እስከ ጥግ ይጫወታል።ሀሜት ከሆነ ግን መስማትም ማውራትም አይፈልግም።ነገሮች ካልጣሙት ከትከሻው ላይ ያስቀመጣትን ነጠላ አሊያም ጋቢ እየቋጨ በዝምታ ይቆዝማል፡፡
አብረውት ለተወሰነ ደቂቃ የቆዩ ሰዎች ጨዋታ አዋቂነቱ፤ ብስለቱ፤ ትዕግስቱና የዓላማ ጽናቱን ያወድሱለታል።ሳቅና ፈገግታ ከፊቱ የማይለየው ይህ ሰው ሲቀልድ የተከፉ ሰዎችን የሐዘን ፅልመት በብርሃን ይተካል።ሰዎችም አጠገቡ አረፍ ብለው ገበያ እንዴት ነው ብለው ጨዋታ ይጀምሩና ብዙ ነገር ያወሩታል።እግረ መንገዳቸውንም የከተማዋን ውሎ በከፊል መረጃ ይሰጣቸዋል።ከላይኛው የከተማ ጫፍ እስከ ተቻኛው የሚሆነው ነገር ከብሬ አያመልጥም።የተለያዩ ሰዎች በአጠገቡ ሲያልፉ አሊያም ደግሞ አጠገቡ ቁጭ ብለው የሚያወሩትን፤ የሚንሾካሾኩትን ይሰማልና።
የብርሃኑ ምኞት
ብርሃኑ ዛሬ መኖርን ብቻ ሳይሆን ስለ ነገ አብዝቶ ይጨነቃል።ከምንም በላይ ግን ከእውነት ኖሮ ከእውነት መሞት የሚሉትን ነገር በሚገባ ማጣጣም ይፈልጋል።በተለይም ደግሞ ልጆቹ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸውና እርሱን ጓደኛ አድርጎት የኖረው የጎዳና ኑሮ እንዳይወዳጃቸው ይለፋል።ብዙ ዘመኑን በጎዳና ላይ ቢያሳልፍም ልጆቹ ግን ይህንን ሕይወት ፈጽሞ እንዲነካቸው አይፈቅድም።
ለዓመታት በተቻለ መጠን እየለፋ ሕይወቱን ለመቀየር ብዙ ጥረት አድርጓል።አሁንም ቢሆን ሰማይ ለነካው ኑሮ እጅ መስጠት አይፈልግም።ነጠላው እየቋጨ፤ ከአጠገቡ ያስቀመጣትን ውሃ እየተጎነጨ ከኑሮ ጋር የጀመረውን ግብግብ ቀጥሏል።እጅ ላለመስጠት የማይቆፍረው ዳገት የማይወርደው ቁልቁለት የለም።እርጅና እየተጫጫነው ኑሮም እየከበደው ቢሆንም የመሸነፍን ስሜት ለአዕምሮው መናገር አይፈልግም።ጤና ቢያስቸግረውም ካለ ሥራ መኖርን ምርጫ አላደረገም፤ ሁሌም መልፋት ሁሌም መትጋት ነው- የብርሃኑ ህልምና ምኞት።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር