የእኛ ነገር ሆኖ የአንድን ጥፋት ወይም ወንጀል ጠንሳሽን ፈልገን የምንቀጣውን ያህል የበጎ ነገር አነሳሽን የምናሞግስበት ወይም የምንሸልምበት ልምድ ብዙም የለንም። ከዚህ አኳያ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሮ በየከተሞች ተግባራዊ የሆነን አንድ ነገር ጠንሳሹን መሸለም ባንችል እንኳ ማወቅን የምንመኝ ብዙ ልንሆን እንችላለን። ለዛሬ ለመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ሀሳቡን ላፈለቁትና መንግሥትም ይህንን ሀሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረጉ ምስጋና ልንቸረው ይገባል። በመቀጠልም የመንግሥት ሠራተኞችን ከቤት ወደ ሥራ እና ከሥራ ወደ ቤት መመላለሻ መጓጓዣን በተመለከተ ዛሬ የተወሰነ ብላችሁስ።
አውቶቡሶቹ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ባገኘነው ነፃ መጓጓዣ አገልግሎት ከመደሰት አልፎ ያለውን የትራንስፖርት ችግር እናውቃለንና፣ ‹‹ፐብሊክ ሰርቪስ እስኪጀምር ድረስ እንዴት ነበር እየተመላለስን ስንሠራ የነበረው?›› በማለት እራሳችንን እንድንጠይቅ አድርጎናል። ይህ ማለት ግን ችግሮች የሉበትም አይደለም። ለምሳሌ፤ የአውቶቡሶቹ እና የሠራተኛው ቁጥር ባለመመጣጠኑ ተጠቅጥቆ መሄዱ እና ተርፎ መቅረቱ ከአንበሳ አውቶቡስ የሚለየው በውስጡ ኪስ አውላቂ (ሌባ) ባለመኖሩ ብቻ ነው።
ይህ ከሀገራችን የኢኮኖሚ አቅም ጋር እየታየ ወደፊት ሊጨመር ይችላል በሚል ተስፋ እንያዝና አንድ ቅር ወዳለን ሌላ ጉዳይ ላምራ። ይህን አገልግሎት ለመጀመር ሲታሰብ መንግሥት ለሠራተኞቹ እና ለተቋማቱ ያሳወቀው አንድ ማሳሰቢያ ነበር፤ የራሳቸው ሰርቪስ ያላቸው ተቋማት አስረክበው ሁሉም በጋራ እንዲጠቀሙ የሚል ነበር። ይህ እርምጃ በተለይ ከመስመር ገባ ብለው ለሚገኙ መ/ቤቶች ጉዳት ያለው ቢሆንም ያን ከግንዛቤ ያላስገባ መመሪያ ከሆነ እርምጃው ለሁሉም መሥራት ይገባዋል።
እየታየ ያለው ግን የማሳመን ወይም የመመለስ አቅም ያለውና የሌለው እየታየ ማስመለስና አለማስመለስ ተስተውሎ ሠራተኞችን ለቅሬታ ዳርጓል። ለምሳሌ፤ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እና የካርታ ሥራ ድርጅት መ/ቤቶች የራሳቸው ሰርቪስ ነበራቸው፤ ነገር ግን የፐብሊክ ሰርቪስ አቅርቦት ሲጀመር ሠራተኞች በዚያ እንዲጠቀሙ ተደርጎ የነበራቸውን እንዲያስረክቡ ተደርጓል። ጡንቻቸው ስለፈረጠመ
ይሁን በሌላ ምክንያት አይታወቅም፤ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር፣ የግብርና፣ የጤና ጥበቃ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የትምህርት ሚኒስቴሮች እና ሌሎችም ዛሬም ድረስ በራሳቸውም፣ በፐብሊክ ሰርቪሱም ይገለገላሉ። ይህ ቅሬታ ‹‹ለአንተ የምሰጥህን ለጎረቤትህ እጥፍ እሰጣለሁና ምን ላድርግልህ?›› ሲባል፣ «አንድ ዐይኔን አጥፋልኝ›› እንዳለው ዓይነት ሰው ሀሳብ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል። ምክንያቱም፤ ከግብርና ሚኒስቴር በስተቀር ሌሎቹ መ/ቤቶች ጽ/ቤታቸው ዋና ዋና መንገዶች ላይ ነውና የሚገኙት።
መንግሥት የሠራተኞችን ሰርቪስ አቀረበ እንጂ ከስንት ሰዓት ጀምሮ መነሻው ላይ የተገኙትን መጫን እንደሚገባ ያስቀመጠው መመሪያ ስለሌለ ሠራተኞች መሰለፍ የሚጀምሩት ከቀኑ 10፡15 ጀምሮ ነው። የመንግሥት የሥራ ሰዓት መውጫ 11፡30 ቢሆንም እስከ 11፡00 ወረፋ በያዙ ሠራተኞች የተነሳ ከ11፡00 በኋላ ቦታው ላይ የሚደርሱ ሠራተኞች ወንበር አያገኙም፤ 11፡30 ላይ የደረሱ ደግሞ ጭራሹኑ ተርፈው ይመለሳሉ። እንደ ደንቡ ከሆነ በአውቶቡሶቹ መስተናገድ የነበረበት 11፡30 ከመ/ቤቱ የወጣ ሠራተኛ ነበር።
ነገር ግን 11፡45 ከመጫኛቸው የሚነሱት አውቶቡሶች አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ከሥራ ሰዓታቸው አስቀድመው (ፎርፈው) የሚወጡትን፤ ያውም ከ11 ሰዓት በፊትና ምናልባትም በአንዳንድ ቦታዎች እስከ 11፡ 15 የወጡትን እንጂ ሥራንና ደንበኛን አክብረው ሲያገለግሉ እየዋሉ የሚገኙትን አይደለም። ይህ አካሄድ በቶሎ መፍትሔ ካልተቀመጠለት እያደር ሁሉም ከሰዓቱ በፊት ወጥቶ ተገልጋይ የሚያስተናግደውን አገልጋይ ያሳጣዋል።
ለዚህ መፍትሔው፡-
- የሰርቪስ አቅርቦቱን ለየመ/ቤቱ ማድረግ ወይም ሁሉም በእኩል መብት የፐብሊክ ሰርቪስ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፤
- ሰርቪሶቹ በትክክል ሥራቸውን ሠርተው በሰዓታቸው የሚወጡትን ቅድሚያ እንዲሰጧቸው ማድረግ (ይህን ለማድረግ በየመ/ቤቱ በፈቃድ ከሚወጡት በስተቀር ሰዓቱን አክብረው ለሚወጡት ካርድ አዘጋጅቶ ወይም የፐብሊክ ሰርቪስ መጠቀሚያ መታወቂያን ጠዋት ወደ ሥራ ሲገቡ ተቀብሎ ሲወጡ መመለስ)፤
- ተጨማሪ አውቶቡሶች አቅርቦ ከመነሻ ቦታ ለራቁት መ/ቤቶች ቅርብ መነሻዎችን መመስረት እና
- የልጅ እና እንጀራ ልጅነት ዓይነት አስተሳሰብ ያሰረጸብንን ፍትሐዊነት የጎደለው የአንዳንድ መ/ ቤቶች የራሳቸው ሰርቪስ መኖርን ማስቀረት ናቸው። ለዛሬ አበቃሁ፤ ቸር እንሰንብት።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
በእስክንድር መርሐጽድቅ