ደብረብርሃን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየተስፋፋባቸው ከሚገኙ ቀዳሚ ከተሞች መካካል ትጠቀሳለች። ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም በርካታ ባለሀብቶችን በተለያዩ ዘርፎች በመሳብ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን በማቀላጠፍና የስራ እድል በመፍጠር ነዋሪዎቿን ተጠቃሚ ስታደርግ ቆይታለች።
ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ አንዳንድ ከተሞች ላይ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ሲታይ ደብረብንርሃን በአንፃሩ በጀመረችው ፍጥነት በመጓዝ ላይ ትገኛለች። ለዚህ ደግሞ ከተማዋ ካላት የኢንቨስትመንት አመቺነት ባሻገር በመስተዳድሩ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተሰሩ ስራዎችና የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንቅስቃሴው ሳይቀዛቀዝ እንዲቀጥል እንዳስቻለው የከተማዋ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃን ገብረህይወት ይናገራሉ።
እንደሃላፊው ማብራሪያ፤ የደብረ ብርሃን ከተማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እስካሁን ተሟሙቆ እንደቀጠለ ነው። ለዚህ ደግሞ በከተማዋ ያለው ሰላም መጠበቅ አንዱ ምክንያት ነው። የከተማው ህዝብ ወጣቱን ጨምሮ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር መዋቅር በመፍጠር በመጠበቅና በኢንቨስትመንት ረገድ የሰላም አምባሳደር በመሆን በማስተዋወቅና በመደገፍ በርካታ ስራዎችን ይሰራል። በተጨማሪም የከተማው አስተዳደር በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍና ባለሀብቶች ሲመጡ ያለምንም ድካም ሊሰሩት በፈለጉት መስክ በፍጥነት ወደ ስራ መግባት የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቷል።
በመሬት አቅርቦት ረገድ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፤ በጨርቃጨርቅና ልብስ ስፌት፤ በእንጨትና በብረታብረት ስራ፣ በኬሚካልና በኮንስትራክሽን መስኮች ለሚሳተፉ የኢንዱስትሪ ክላስተር ተዘጋጅቶና መሬት ተከልሎ የተቀመጠ በመሆኑ ባለሃብት ሲመጣ በመሬት ምርጫና ማቅረብ ስራ የሚጠፋ ግዜ እንደማይኖር ተገልፃል። በተለይ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በ134 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኗ ለአገር ውስጥ የገበያ ትስስር ለመፍጠርም ሆነ ለወጪ ንግድ ምቹ አድርጓታል፡፡ በዚህም በአዲስ አበባ ያሉ ባለሀብቶች ተጨማሪ ፋብሪካ ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጽህፈት ቤቱ ያለፉትን አመታት ተሞክሮ በመውሰድና በመቀመር በሰራቸው ማሻሻያዎች በአሁኑ ወቅት ባለሀብት የሚጠበቅበትን መስፈርት አሟልቶ ከቀረበ ከሁለት እስከ ሶስት ቀን ባለ ጊዜ ውስጥ መሬት የሚረከብበት ስርዓት ለመዘርጋት ተችሏል። በመሰረተ ልማት አቅርቦት ረገድም የወቅቱን ኢንቨስትመንት ከግምት ያስገባ የመንገድ፣ የውሃና የስልክ አቅርቦት እንዲኖር እየተሰራ ይገኛል።
በሌላ በኩል ባለሀብቶች ቦታ ተረክበው ግንባታ አጠናቀው ማሽን ያስገቡ ቢሆንም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር በመኖሩ ወደስራ ያልገቡ መኖራቸው ተነግሯል። በከተማው የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ ሰብስቴሽን ቢገነባም ኢንዱስትሪዎቹ እስካሉበት የክላስተር ቦታዎች ለማዳረስ አልተቻለም። ከዚህ ጋር በተያያዘም አንዳንድ ባለሀብቶች በወቅቱ ብድር ማግኘት ባለመቻላቸው በተወሰነ ደረጃ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ቆይቷል።
ይህ እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ባለሀብቶች መሬት ተረክበው በተቀመጠው የሊዝ አዋጅ ስምምነት መሰረት በወቅቱ ወደስራ ሳይገቡ መቆየታቸውም እንደ ችግር ተነስቷል። በዚህም ባለፈው አመት ብቻ 35 ባለሀብቶች የያዙትን ቦታ እንዲለቁ በማድረግ ለሌሎች ባለሀብቶች ተዛውሯል። አሁን ላይ በከተማው ከ2 ሺ 500 ሄክታር በላይ መሬት ለኢንዱስሪ ማስፋፊያ ለማዘጋጀት እየተሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሁለት መቶ ካሬውን በመከለል መሰረተ ልማት እንዲሟላና ካሳ እንዲከፈል እየተሰራ ይገኛል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት ብቻ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ130 በላይ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያወጡ ሲሆን ከ86 በላይ የሚሆኑት ቦታቸውን ተረክበው ወደስራ በመግባት ላይ ይገኛሉ። በከተማዋ ባጠቃላይ ከ29 ቢሊየን ብር በላይ በማስመዝገብ ከ461 በላይ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየተካሄደ ሲሆን፤ እነዚህም 250 በኢንዱስትሪ፤ 197 በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም ስምንቱ በግብርና ናቸው።
ሁሉም ፕሮጀክቶች ወደስራ ሲገቡ ከሀምሳ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩ ሲሆን እስካሁን ከአስር ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በተለያየ ዘርፍ በግዚያዊነትና በቋሚነት የስራ እድል መፈጠሩንም ሀላፊው ገልጸዋል። በተጀመረው በጀት አመትም ከ140 በላይ ባለሀብቶች ወደከተማዋ ይመጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ከ60 በላይ ፕሮጀክቶች ወደስራ በመግባት ላይ ይገኛሉ።
የከተማ መስተዳድሩ በከተማዋ ባለሀብት ሊሰራባቸው የሚችላቸውን መስኮች በመለየት ረገድ ከ74 በላይ ዘርፎች በመለየት ጥናት አካሂዶ የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ ይገኛል። ከነዚህም መካከል የምግብ አግሮ ፕሮሰሲንግ፤ ፓስታና መኮሮኒ ማምረት፤ የወተት ማቀነባበሪያ ትኩረት የተሰጣቸው መስኮች ናቸው። በተጨማሪ ለቤትና ለቢሮ እቃዎች መስሪያ የሚውለውን (የኤም ዲ ኤፍ) ጣውላ ማምረቻ ቦታ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
በተፈጥሮ ማዕድን አቅርቦት ረገድ በአካባቢው ሴሊካ ሳንድ የተባለው ለብርጭቆ ምርት የሚውል ጥሬ እቃ ቢኖርም በከተማው ትልልቅ የቢራ ፋብሪካዎች ጠርሙስና ብርጭቆዎችን ከውጪ የሚያስገቡ በመሆናቸው ምርቱን እዛው ለማስጀመር እየተሰራ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለፋብሪካዎቹ በቅርበት በቂ የቢራ ገብስ አምራችና ብቅል ፋብሪካ ለማምረት ለሚያስቡ ባለሀብቶች ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።
በሰለጠነ የሰው ሀይል ረገድ ያለውንም ክፍተት ለመቀነስ ከደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ ጋር በስራ ላይ ከሚገኙት ኢንዱስትሪዎች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሰራ ይገኛል። በተጨማሪም በቴክኒክና ሙያ የሰለጠነ የሰው ሀይል በማቅረብ ረገድ ተቋማቱ በአካባቢው ያለውን የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ከግምት ያስገባ ስልጠናና ትምህርት እንዲሰጡ እየተደረገ ሲሆን በማስተዋወቅም ረገድ ክልሉ ከሚሰራው በተጨማሪ ለባለሀብቶችን ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ራሳቸው አምባሳደር እንዲሆኑ የማስተባበሩ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሽመልስ ጥበቡ በበኩላቸው ደብረ ብርሀን በየጊዜው ለውጥ የሚታይባት ከተማ መሆንዋን ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ የደብረ ብርሀን ህዝብ ለሰላም መቆሙ አንደኛው ምክንያት ሲሆን ወጣቱም ሆነ ህብረተሰቡ ጥያቄ ሲኖር በአግባቡ ያቀርባል እንጂ ወደ ጥፋት አይሄድም በማለት ያለውን ምቹ ሁኔታ ይጠቁማሉ። ህብረተሰቡ ከኢንቨስትመንቱ ብዙ ተስፋ ስለሚጠብቅ ትብብሩም ከፍተኛ ነው።
በተጨማሪም ኢንቨስትመንቱ ከሚመለከታቸው የክልልና የከተማዋ አካላት ጋር ካለው የቅንጅት ስራ በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ይህም በየ አስራ አምስት ቀኑ በመሰብሰብና ችግሮችን በመለየት አቅርቦ ውሳኔ ያሰጣል።
ሃላፊው ጨምረው እንዳብራሩት በ2011 እንደ ሀገር ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር ወጣ ገባ የማለት አካሄድ ቢኖርም በተያዘው በጀት አመት ከሚጠበቀው በላይ እየጨመረ ይገኛል። በተያዘው በጀት አመት እንደ ዞን 232 ለሚደርሱ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ የእቅዱን 89 በመቶ 201 ለማከናወን ተችሏል። ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የደብረ ብርሃን ከተማ ነው።
በዘንድሮው አመት የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው ፕሮጀክቶች ናቸው። ከ30 ሺ በላይ የስራ እድል የሚፈጥሩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የአምራች ኢንዱስትሪው ድርሻ ከ75 በመቶ በላይ ይይዛል። እንደ ክልል የኢንዱስትሪው ድርሻ እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ነው።
በኤሌክትሪክ አቅርቦትና መቆራረጥ የሚፈጠረውን ችግር ለመቅረፍም ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ግምት የሚያስፈልግ ሲሆን ከክልልና ከፌዴራል ጋር በመቀናጀት ይህም ካልተሳካ ባለሀብቱን አደራጅቶ ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ሃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 12/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ