ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት ሀገር ናት:: የሀገሪቱ አምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች አሏት::
በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውናለች:: የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅም እና ዘርፉን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፣ የዘርፉ ችግሮች ደግሞ በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ ናቸው፤ እነዚህ ችግሮች ለመፍታትም የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና በአጠቃላይ የሕዝቡን የተቀናጀ ጥረት የሚፈልጉ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል::
እምቅ አቅም ካላቸውና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ከሚችሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች መካከል አንዱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው:: ይህ ዘርፍ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች መካከልም አንዱ ነው:: ኢትዮጵያ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ በዋና ግብዓትነት የሚያገለግለውን ጥጥ የምታመርት፣ ለጥጥ ልማት ምቹ የሆነ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት እና ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት በመሆኑ ለዘርፉ ምቹ እንድትሆን አድርጓታል:: ከዚህ በተጨማሪም ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ እንደ ቃጫ ተክል፣ ተልባ፣ ሐር እና ቀርከሃን ለማምረት ሰፊ አቅም አላት::
የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ በአስር ዓመት ሀገራዊ እቅድ ቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱና ዋናው ሲሆን፤ እሴት በመጨመር፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ ኤክስፖርት በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እና ገቢ ምርቶችን በመተካት ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ዘርፍ ነው:: ይህ ዘርፍ ፈትል (ድርና ማግ፣ ክር እንዲሁም የተሸመኑና የተገመዱ ጨርቃ ጨርቆችን ማምረትን፤ ጣቃ ጨርቅን፣ ክርን፣ ድርና ማግን፣ አልባሳትንና ሌሎች የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን በማንጣት፣ በማቅለም፣ በማኮማተር፣ በማፍካት፣ በማጠንከር ወይም በማስዋብ ማጠናቀቅን፤ አልባሳት (የስፖርት ልብስን ጨምሮ)፣ ሹራብ፣ ፎጣ፣ ምንጣፍ፣ ተጓዳኝ አካላትን (ቁልፍ፣ ዚፕ… ማምረትን ያጠቃልላል::
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ዘርፉን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል፤ ከግብርና ጋር ተመጋጋቢ የሆነና በቂ የሆነ የግብዓት ሀብት መኖር፤ ዘርፉ ውስብስብ ያልሆነና ወደቀጣይ ሥራ ሊያሸጋግር የሚችል ቴክኖሎጂ የሚጠቀም እንዲሁም እርስ በእርስ ሊተሳሰር የሚችል መሆኑ፤ በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ኃይል እና ከፍተኛ የሀገር ውስጥና የዓለም ገበያ መኖሩ እና በመንግሥትና በግል ባለሀብቶች የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ክላስተሮች መኖራቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ::
በዚህ ዘርፍ ከሚመረቱ ምርቶች መካከል ከተልባ እግር ክር የሚሰራው የአልባሳት ውጤት የሆነው ሊነን ቴክስታይል (Linen Textile) ይጠቀሳል:: ኢትዮጵያ ተልባ የማምረት ትልቅ አቅም ያላት ቢሆንም፣ በሀገሪቱ ከዚህ ተክል የሚመረተው የአልባሳት ምርት ጥቂት ከመሆኑ ባሻገር ምርቱ ሙሉ በሙሉ ለውጭ ሀገራት ገበያ የሚቀርብ ነው:: ለምርቱ የሚያስፈልገው ግብዓትም የሚመጣው ከውጭ ሀገር ነው:: ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባዔ (Global Linen Textile Forum) ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተካሂዷል::
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ፎረሙ ኢትዮጵያ ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ያላትን ህልምና ጥረት እንዲሁም በኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ያሉትን መልካም እድሎች ለማሳየት ሁነኛ አጋጣሚ ሆኖ እንደሚያገለግል ይገልፃሉ:: በተጨማሪም፣ ከባለድርሻ አካላት የመሰብሰቢያ መድረክነት ባሻገር ዘላቂ ትብብሮችን፣ ተጨባጭ ኢንቨስትመንቶችን እና ድንበር ዘለል ብልጽግናን እውን ለማድረግ መደላድል የሚፈጠርበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ገልጸዋል::
ኮሚሽነሩ እንደሚናገሩት፣ ሀገሪቱ ግዙፍ የሆነ የአምራች ኃይል፣ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ግብዓቶችን ለማብቀል የሚያስችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም ተስማሚ የአየር ፀባይ ባለቤት መሆኗ በዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ ገበያ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዲኖራት ያስችላል::
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ኤክስፖርት ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁሞ ከ10 ዓመታት በፊት ከነበረበት 60 ሚሊዮን ዶላር በአሁኑ ወቅት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ አድጓል:: እ.አ.አ በ2030 ደግሞ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚሻገር ይጠበቃል:: ይህ እድገት የዘርፉን ፖሊሲዎች ምቹነትና ጥንካሬ፣ የኢትዮጵያውያንን ትጋት እና ሀገሪቱ ለኢንቨስተሮች ያሏትን እድሎች የሚያንፀባርቅ ስኬት ነው::
ዓለም አቀፍ የሊነን ክር ጨርቃ ጨርቅ ገበያ (Global Linen Textile Market) በሚቀጥሉት ዓመታት በየዓመቱ ከሰባት ነጥብ ሰባት በመቶ በላይ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ ዓለም አቀፍ ሸማቾች ለአካባቢ ሥነ-ምህዳር ተስማሚ በሆኑ ምርቶች ላይ በማተኮራቸው ኢንቨስተሮች ለዚህ ምርት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ እንደሚያደርጋቸው ይገልፃሉ:: ኢትዮጵያ ደግሞ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጯን ለኢንዱስትሪ ሥራዎች ንጹህ፣ አስተማማኝና በዋጋ ተመራጭ ከሆኑ ታዳሽ ዘርፎች፣ በተለይም ከውሃ፣ እንደምታገኝ ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ ሀገሪቱ ከጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሻገረ ሰፊ የልማት ርዕይ ባለቤት እንደሆነችና በባለሀብቶች ተመራጭ የመሆን እድል እንዳላትም ተናግረዋል::
‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ለዓለም ገበያ ልዩ መዳረሻ የመሆን እድል ያጎናጽፋታል:: በኢንቨስትመንት መሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ያከናወነቻቸው ተግባራትም የዘርፉን እድገት ያፋጥናሉ›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል አዋጭ የንግድ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችሉት የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር እና የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም ለብሔራዊ የኢንዱስትሪያላይዜሽን ስትራቴጂው ስኬት ቁልፍ መሳሪያዎች የሆኑት ነፃ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢንቨስትመንት መሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ ካላቸው ግዙፍ መሠረተ ልማቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አብራርተዋል::
ኮሚሽነሩ ዘለቀ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት አስርት ዓመታት ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁሞ ተጨባጭ እድገት ማስመዝገብ ችሏል:: ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ ደግሞ መንግሥት የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ በከፍተኛ መጠን ማሳደግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎችን አድርጓል::
ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው:: የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሰው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው::
የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ የንግድ ዘርፎች ክፍት እንዲሆኑ መደረጋቸው እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈውን ውሳኔ ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው::
የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች ልማት በሕጋዊ ማሕቀፍ የተደገፈ እንዲሆን የሚያስችሉ ብሔራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ፖሊሲ እና የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ (1322/2016) ተዘጋጅተው ወደ ሥራ ተገብቷል:: ብሔራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ፖሊሲ በሥራ ላይ እንዲውል የተወሰነው ኢትዮጵያ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ ባለውና ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተስፋፋና እየጎለበተ በመጣው ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው:: ፖሊሲው የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ሥርዓት ለማሻሻል፣ የወጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበትን ለማሳደግ፣ የወጪ ንግድ አቅምን ለማጎልበት፣ ሰፊ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም በሀገሪቱ ዋና ዋና የንግድ ኮሪደሮች የደረቅ ወደቦችን ለማስፋፋትና የሎጂስቲክ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ሥርዓቶችን እውን ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ነው::
በሌላ በኩል የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጁ የውጭ ኢንቨስትመንትን በቀላሉ ለመሳብ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት፣ የምጣኔ ሀብት ትስስርን ለማጠናከር፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ እንዲሁም ተግባራዊ የተደረገውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥርዓት ዲዛይንና ትግበራ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሥርዓት በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ስለታመነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በሥራ ላይ ውሏል::
ከዚህ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ መግባቷን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት (Floating Exchange Rate) መቀየሩ የማሻሻያው አካል እንደሆነና ይህም የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት ከባቢን ለማሻሻል እንደሚግዝ ያስረዳሉ::
የተልባ እግርን ወደ ክር በመቀየር የልብስ ማምረቻ ጥሬ እቃ በማምረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የቻይናው ‹‹ኪንግደም ግሩፕ›› ኩባንያ (Kingdom Group) ነው:: ኩባንያው ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ‹‹ኪንግደም ኢትዮጵያ›› ፋብሪካውን ገንብቶ ከተልባ እግር ክር እያመረተ ይገኛል:: የኩባንያው ሊቀመንበር ረን ዌይሚንግ፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማራው በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እንደሆነ ጠቁመው፣ ሥራውን ሲጀምር ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት መልካም መስተንግዶና አቀባበል እንዳገኘ ያስታውሳሉ::
‹‹በኢትዮጵያ ሥራ የጀመርነው ሀገሪቱ እምቅ ሀብት፣ ወጣት የሰው ኃይል እና አበረታች አሠራሮች እንዳሏት በመገንዘብ ነው:: የሎጂስቲክስ ችግሮች ቢኖሩም አምርተን ለውጭ ገበያ እያቀረብን እንገኛለን:: በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ገበያ የበለጠ ክፍት እንደሚሆን እንጠብቃለን፤ በተለይም ውድድርን ለማበረታታት የሎጂስቲክስ ዘርፉን ክፍት ማድረግ ጠቃሚ ነው›› በማለት ያስረዳሉ::
የ‹‹ኪንግደም ኢትዮጵያ›› የሎጂስቲክስ ክፍል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤተልሄም ቃሲም በበኩላቸው፣ ‹‹ኪንግደም ኢትዮጵያ›› በአፍሪካ የተልባ እግርን ወደ ክር በመቀየር የልብስ ማምረቻ ጥሬ እቃ የሚያመርት የመጀመሪያው ድርጅት እንደሆነ ይገልፃሉ:: ኩባንያው የኢትዮጵያውን ፋብሪካ ጨምሮ በዓለም ላይ ተመሳሳይ ምርት (ከተልባ እግር ክር) የሚያመርቱ አምስት ፋብሪካዎች አሉት:: ፋብሪካው በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተልባ እግር ክር አምርቶ ምርቶቹን ሙሉ በሙሉ ወደ 27 ሀገራት ይልካል::
‹‹ጥሬ እቃውን ከሀገር ውስጥ ማግኘት ስላልቻልን ሙሉ በሙሉ የምናስመጣው ከፈረንሳይ ነው:: ከዚህም ቀደም ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተፈራምነው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ከተለያዩ የግብርና ዘርፎች ጋር ተገናኝተን ያለንን ልምድ አጋርተናል:: እስካሁን ግን ለእኛ የሚበቃ ጥሬ እቃ ኢትዮጵያ ውስጥ ማግኘት አልቻልንም›› ሲሉ ይገልጻሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካው የተለያዩ ዓይነት ክሮችን ብቻ ነው የሚያመርተው:: ክሮቹ ለልብስ መሥሪያ ግብዓት ይውላሉ:: የተልባ እግር ክር (Nilen Yarn) በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ውድ የሚባለው ክር ነው::
በተለያዩ ችግሮች ምክንያት (በመብራት፣ በሎጂስቲክስ… ችግሮች) አሁን ላይ ካለን የማምረትና ኤክስፖርት የማድረግ አቅም ውስጥ እየተጠቀምን ያለነው 65 በመቶውን ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ለ600 ሠራተኞች የሚበቃ የሠራተኞች መኖሪያ /ዶርም/ ግንባታ በማለቁ በሁለት ወራት ውስጥ የማምረት አቅማችንን ወደ 85 በመቶ ከፍ እናደርጋለን›› ብለዋል:: በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ በሙሉ አቅም ለማምረት ማቀዳቸውን ጠቅሰው፣ በ2016 ዓ.ም ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኤክስፖርት አድርገን በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ግንባር ቀደም ላኪ ተብለን ተሸልመናል:: በሙሉ አቅማችን አምርተን ኤክስፖርት ማድረግ እንፈልጋለን›› በማለት ያብራራሉ::
‹‹እንደ ዓለም አቀፍ ገበያና ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንደማድረጋችን በዘርፉ የተለያዩ ችግሮች አሉ›› የሚሉት ወይዘሮ ቤተልሄም፣ የቢሮክራሲ መጓተት፣ የሲስተም መቋረጥ እንዲሁም ኮንቴይነርን ጨምሮ የሎጂስቲክስ እጥረት ዋና ዋና ችግሮች እንደሆኑ ይገልፃሉ::
እሳቸው እንዳመለከቱት፣ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ቻይናውያን መጥተው እውቀት አካፍለው ኢትዮጵያውያን ሥራውን እንዲረከቡ ሲሰራ ቆይቷል፤ ይህን ተከትሎም ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበሩትን 58 ቻይናውያን ቁጥር አሁን ወደ ሰባት ዝቅ ማድረግ ተችሏል:: አሁን ሥራው እየተሠራ ያለው በሀገር ውስጥ ሠራተኞች ነው:: ኢትዮጵያውያኑ ልምድ ባዳበሩ ቁጥር ተጠቃሚነታቸውም እያደገ ይሄዳል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም