“ልማድ ውሎ ሲያድር ባህል ይሆናል” ይላሉ ቀደምት አበውና እመው ሲተርቱ፡፡ አባባሉ ቀደም ብሎ ስለተነገረ በቀደምትነት ፈረጅነው እንጂ ዛሬም ቢሆን ጥበባዊ አነጋገሩ የተሸከመው መልዕክት ዝጓል፣ አርጅቷል፣ ነፍሶበታል ማለት አይቻልም። እንዲያውም እውነትነቱ ከትናንት ይልቅ ዛሬ ፀሐይ እየሞቀው፣ ጀማው እያጨበጨበለት ደምቆ የሚተገበር ይመስላል። ወደ እንዴታው ተንደርድረን ከመግባታችን በፊት በመጀመሪያ ስለ “ሌባ ሻይ” ምንነት ማስተዋወቂያ ማድረግን ግድ ይሏል፡፡
የ“ሌባ ሻይ” ዕድሜና የትመጣ
ለምሥጢሩ አክብሮት አለን የሚሉ ወገኖች “ሌባ ሻይ”ን ሺህ ዘመናት ያስቆጠረ ዕድሜና ታሪክ ያለው ሆኖ ከባህል መድኃኒት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ሀገራዊ “የዕፅ ጥበብ” ነው ይሉታል፡፡ ይህንን ጥበብ ተብዬ “ሌባ ሻይ” ወይንም ነገረ ሥራይ (ሥራይ፤ በሰው ላይ ጉዳት፣ ሞት የሚያስከትል መርዝ፣ መድኃኒት) ጥንተ አመጣጥ ካብራሩልን ደራስያን መጻሕፍት ላይ የተወሰደው አጭር ገለፃ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
“ሌባ ሻይ” በኢትዮጵያ ምድር የተጀመረና ጥንታዊያን ነገሥታት ሳይቀሩ የተጠቀሙበት ጊዜን ጊዜ ሲሽረው በአንድ ወቅት ሲገን፤ በሌላ ወቅት ደግሞ ሲደክም የኖረ “ረቂቅ የነገረ ሥራይ እኩይ ጥበብ ነበር።” ምዕላደ ጥበብ የተባለው በግዕዝ የተጻፈ መጽሐፍ “ሌባ ሻይ” ጠቃሚነቱ ታውቆ በቤተ መንግሥት ሳይቀር በሥራ ላይ የዋለው በአፄ መራ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ መንግሥት በ902 ዓ.ም ገደማ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይሉናል ለማመሳከሪያነት ያነበብናቸው መጻሕፍት፡፡
የ”ሌባ ሻይ” ትርጉም
ሌባን ከደህናው ለይቶ የሚያሲዝ ጥበብ መጠሪያ ስም ሲሆን፤ “ሌባ ሻይ” ማለትም ሌባ ፈላጊ ማለት ነው። ሌባውን ከንፁህ ሰው አጣርቶ ለመያዝም ያስችላል። ይህንን ዘዴ ቀደም ሲል አገሪቱን ለመምራት ዕድል የገጠማቸው ነገሥታት ሳይቀሩ ሌባና ወስላታ ሕዝቡን እንዳይዘርፈው የሚጠበቅበትና የሚያስጠብቅበት “ትልቅ ጥበብ” በመሆኑ ነገሥታቱ ለሰላም ዘበኛቸው ድጋፍ ሰጭ በማድረግ በዚሁ ዘዴ ሲጠቀሙ ኖረዋል የሚል ምስክርነትም ተሰጥቶታል፡፡ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” እንዲሉ፡፡
የ”ሌባ ሻይ” አዘገጃጀት
ከተለያዩ ዕፅዋቶች ቅጠል በመውሰድ፣ ሥሩን በሥር፣ ቅጠሉን በቅጠል በመለየት በወተት ዘፍዝፎ ከ10 እስከ 14 ዓመት ለሚሆን ከሴት ካልደረሰ ወንድ ልጅ ወይንም ከወንድ ያልደረሰች ዕድሜዋ ከዘጠኝ ዓመት ላልበለጠች ሴት ልጅ አጠጥቶ መጠቀም ይቻላል – ይሉናል ለማመሳከሪያ ያገላበጥናቸው ዋቢ መጻሕፍት፡፡
የ”ሌባ ሻይ” አተገባበር
ዕቃ የተሰረቀበት ወይንም የጠፋበት ሰው ለ“ሌባ ሻይ” ዳኛ አመልክቶ “ሌባ ሻይ” በጠጣ ጊዜ አብዶና ራሱን ስቶ “ሌባ ሻዩ” ከአንድ ሰው ቤት ገብቶ የተኛ እንደሆነ የቤቱ ጌታ (ንፁህ ቢሆንም እንኳ) ለጠፋው ዕቃ አላፊ ሆኖ ይከፍልና እርሱ ዋና ሆኖ እንደገና “ሌባ ሻይ” ያጠጣ ነበር፡፡ አሁንም “ሌባ ሻዩ” ከሌላ ሰው ቤት ቢተኛ የቤቱ ጌታ ለፊተኛው ሰው ዕዳውን ከፍሎ (ያለ ኃጢያቱ መሆኑን ልብ ይሏል) “ሌባ ሻይ” ያጠጣና ለሦስተኛ ጊዜ “ሌባ ሻይ” ከሚተኛበት የቤቱ ጌታ ላይ ዋጋውን ይቀበል ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት እየተከታተለ “ሌባ ሻይ” እየጠጣ ሕዝቡ ያልበላውን ዕዳ በመክፈል ተቸግሮ ይኖር ነበር፡፡ ደግሞም የ“ሌባ ሻዩን” ጣጣ በመፍራት እንግዳ መቀበልና ማሳደር ተጠልቶ ነበር፤ ይለናል የመሸበት ትርክት፡፡
የ”ሌባ ሻይ”ኢ-ሳይንሳዊ እኩይ ተግባር
በሀገራችን ሥር ሰዶ እንደ ጠቃሚ ባህል ለሺህ ዘመናት በእሶሶ ተከብሮ ሲተገበር የኖረው ይህ የግፍ ተግባር በማኅበረሰቡ ዘንድ አሳድሮት የነበረው አሉታዊ ስሜትና መቃቃር በቀላሉ የሚታይ እንዳልነበረ መገመት አይከብድም፡፡ በጸሐፊው የግል እምነት ድርጊቱ ሰይጣናዊና አረመኔያዊ እኩይ ተግባር እንደነበር መግለፁ ያንስበት ካልሆነ በስተቀር የሚበዛበት አይሆንም፡፡ ምክንያቱን ላብራራ፤
በመጀመሪያ፤ “ሌባ ሻይ” እየተባለ የሚንቆላጰሰው ሰይጣናዊ ጥበብ ተቀምሞ የሚዘጋጀው ሊያሳብዱና ጨርቅን አስጥለው አቅልን ማሳጣት ከሚችሉ ልዩ ልዩ ዕፅዋቶች ነበር፡፡ “ሌባ ሻይ” የጠጣ ሰው ራሱን ይስታል። አዕምሮውን ይሰውረዋል፡፡ የሚያደርገውንም አያውቅም፡፡
ሁለተኛ፤ “ዕቃ ጠፋብኝ፤ ወይንም በማላውቀው ሰው ተሰረቅሁ” በማለት በተንኮልም ሆነ በእውነት አቤቱታ የሚያቀርበው ግለሰብ ከሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር ካፈነገጠና የማኅበረሰቡን ሥነ ምግባር በሚፃረር መልኩ ለአላፊና ጠፊ ቁስ ሲል ክቡሩን የሰው ልጅ አሳብዶ አቅልን እንዲስት ማድረግ በምድርም ይሁን በሰማይ የሚያስፈርድ የኩነኔ ተግባር ነው፡፡
ሦስተኛ፤ ለዚህ እኩይ ድርጊት ፈፃሚነት የሚመረጡት ግራና ቀኛቸውን የማይለዩ የዋህ ታዳጊ ብላቴኖች ነበሩ፡፡ እነዚህ ታዳጊ ሕፃናት ይህንን ሥራይ የዕፅ ጭማቂ እንዲጠጡና እንዲያብዱ የሚፈረድባቸው በማያወቁትና ባልገባቸው ምክንያት የጦስ ዶሮ (Escape Goat) እየተደረጉ ነበር፡፡
አራተኛ፤ ተግባሩ ባወጣው ያውጣው ይሉት ዓይነት የግፍ ተግባር መገለጫ ስለሆነ “አዕምሯቸውን እንዲስቱ” የተፈረደባቸው ታዳጊ ሕፃናት ይታመንበት እንደነበረው ንፁሀን ሰው ከአጥፊው የመለየት “ልዩ መገለጥ” በርግጠኝነት ስለማይኖራቸው ከእነርሱም አልፎ በማኅበረሰቡ ውስጥ ይደርስ የነበረው መመሰቃቀል ይህ ድንበርህ የሚባል አልነበረም። “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ይሉት ዓይነት ድርጊት ስለነበር ልጆቹ ጣር ይዟቸው እንኳ የቀረቡትና በጭንቀት ጨርቁን የዳሰሱት ሰው ሁሉ ሌባ እየተባለ በመፈረጅ ክብሩና መብቱ በጠራራ ፀሐይ ስለሚገሰስ የሚያደርሰው ስብራት በቀላሉ የሚገመት አልነበረም፡፡
አምስተኛ፤ የ“ሌባ ሻይን” ጣጣ በመፍራት ማኅበረሰቡ ባልፈፀመው ድርጊት ዕዳ እንዲከፍል መገደዱ እንዳለ ሆኖ የማኅበረሰቡን አብሮ የመኖር ዕሴት በመሸርሸር ላለመተማመን ምክንያት ይሆን ስለነበር በአጭሩ ድርጊቱ ሳጥናኤላዊ የትራዤዲ ተውኔት ነበር ማለቱ ይቀላል፡፡
ስድስተኛ፤ ሕዝብን ለማስተዳደር ሥልጣን የተሰጣቸው መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ በዚህ ድርጊት ውስጥ መሪ ተዋንያን መሆናቸው የእንቆቅልሹን ክብደት ያገዝፈዋል፡፡
ይህ ዘመን ያሸበተና ማኅበረሰብን እያቃቃረ በንፁሃን ላይ ሲፈፀም የኖረ የሐሳዊ መሲህ (የአሳሳች እና የሐሰተኛ ነብይነት ድርጊት) ዛሬ ላይ እንደ አዲስ ክስተት በሀገራችን ፖለቲካ አካሄድ ላይ ግብሩ ተመሳስሎ፣ ድርጊቱ ይበልጥ ተሻሽሎ ሲተገበር ማየት ያስፈራልም፣ ያሳፍራልም፣ ያስደነግጣላም፡፡ እንዴታውን ላብራራው፡፡
ዛሬ፣ ዛሬ የፖለቲካውንና የአክቲቪዝምን ሚና እየተጫወቱ ያሉትን አብዛኞቹን ሐሳዊያን ሥልጣን ናፈቂዎችን የሚመስለው ከ”ሌባ ሻይ” ሰይጣናዊ ግብር ጋር በማመሳሰል ነው፡፡ ለምን ወደዚህ ድምዳሜ ላይ እንደደረስኩ ምክንያቴን ላስረዳ፡፡
የሀገራችን የፖለቲካ ቅኝትና እንጉርጉሮ ማጠንጠኛው “የእኛ ብቻ መሆን የሚገባው ሀብትና ንብረት፣ ሥልጣንና ክብር፣ ዝናና ታዋቂነት በማይገባቸው ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች ተጠልፎብናል” ከሚል ራስ ወዳድነትና ራስ አምላኪነት የተላቀቀ አይመስልም፡፡ ይህንን የ“እኔ ብቻ!” እንጉርጉሮና መዝሙር ደግሞ በነጋ በጠባ እስኪሰለቸን እያደመጥን፣ እያነበብን፣ እየጻፍንና እየተገረምንበት መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ “በዓይን አውጣነት” ድፍረትም ያዙኝ ልቀቁኝ እየተባለ ሲፈከርም እያስተዋልን ነው፡
የ“ሌባ ሻይ” መንፈስና ድርጊት ገዢያቸው የሆነው ሥልጣን ናፋቂዎች የእኩይ ዓላማቸውን እንክርዳድ በማኅበረሰቡ ውስጥ እየዘሩ የጠብ መጠጥ በመጥመቅ ንፁሐንን ለማሳበድና ህሊናቸውን ለመንጠቅ እየሞከሩ ያሉት የነገን ተስፋ የተሸከሙ ልጆቻችንን ከፊት ለፊት በማስቀደም ነው፡፡
በዚህ ስልጡን በሚባል ዘመን በሃሳብና በውይይት ልዕልና ተነጋግሮ ከመተማመን ይልቅ በዱላና በስለት፣ በድንጋይና በጦር መሣሪያ እያበዱ እንዲፋለሙ ተግቶ በመሥራት የጥንታዊውን “ሌባ ሻይ ጥበብ” በሚገባ እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡
የእኔን ምኞት፣ የተነጠቀብኝን ቅዠት፣ የሥልጣን ጥምና የዝና ጉጉት “አርኩልኝ! ታደጉኝ!” ብሎ በዘረኝነትና በጎጥ ወጣቶቻችንን “ሌባ ሻይ” በማጠጣት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ዘልቆ በመግባት፣ ወይንም በአካባቢያቸው የተለያዩ ስሞችን በመስጠት በማያውቁት ነገር ለክፋት ማሳበድና አዕምሯቸውን መዝረፍ ምን ይሉት ክፋት ነው? የጥፋት መልዕክተኞቹ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች በረጅም ዓመታት የተገነባውን ማኅበራዊ ዕሴት እንዲያፈርሱና በመከባበር ላይ የተመሰረተውን የሕዝቡን ባህል እንዲንዱ “ጃስ!” እያሉ ተስፈኛውን ትውልድ ማገንገንስ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል?
ቀደም ሲል የጥንታዊውን የ“ሌባ ሻይ” አተገባበር በዝርዝር ለማመልከት እንደተሞከረው አዲሱና ዘመናዊ የ“ሌባ ሻይ” ስልትም የመጨረሻ ግቡ ከቀዳሚው የሚለይ እንዳልሆነ ለመረዳት አይከብድም፡፡ እንዴት አሰኝቶ የሚያስጠይቅ ከሆነም ምክንያቱን እንደሚከተለው ማብራራት አይገድም፡፡
አንደኛ፤ አዲሶቹ የ”ሌባ ሻይ” አጠጭዎች ወጣቱን ትውልድ እብሪትና ተንኮል እየጋቱ ማሳበድ ዋነኛ ተልዕኳቸው አድርገዋል፡፡ ስሱ ስሜታቸው ላይ ዕሳት እየጫሩ በማካለብ ከጠያቂነት ወደ አጥቂነት እንዲሸጋገሩ እየጎተጎቷቸው ይገኛሉ፡፡
ሁለተኛ፤ ለግል ሥልጣናቸው ህልምና ቅዠት ሲሉ ብቻ ወጣቱን ትውልድ ከፊት ለፊት አሰልፈው “ማንነትህ ተሰርቋል፣ ብሔርህና ጎሳህ ተንቋል፣ ቋንቋህ ተዋርዷ ወዘተ…” እያሉ ከሕዝብ ጋር እንዲጋጭ፣ ከታሪክ ጋር እንዲላተምና ተከባብሮና ተፈቃቅሮ በኖረው ሕዝብ መካከል የጠብ እንክርዳድ እንዲዘሩ ማሳውን ያመቻቹላቸዋል፡፡
ሦስተኛ፤ ለዚህ መሰሉ እኩይ ተግባራቸው የሚመለምሏቸው ደግሞ ግራና ቀኛቸውን ለይተውና አገናዝበው የማይሞግቷቸውን በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችንን መሆኑን ማስመሩ ተገቢ ይሆናል፡፡
አራተኛ፤ የሚመለምሏቸው ወጣቶች በነፍሳቸው እየተወራረዱ በስምሪታቸው መስክ ተገኝተው ወደ ጥፋት ሲማገዱ እነርሱ ግን በተቀናጣ ኑሯቸው ዓለማቸውን ይቀጫሉ፡፡ ወጣቱ ባቀጣጠለው ዕሳት ሲለበለብ እነርሱ በተደላደለ ሕይወት ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ኑሯቸውን እየኖሩ “ነፍሴ ሆይ! እነሆ ሐሴት አድርጊ!” እያሉ የውስኪ ብርጭቆ ያጋጫሉ፡፡
አምስተኛ፤ ማኅበረሰቡ ርዕስ በርዕሱ የጎሪጥ እንዲተያይና እንዲፋለም “ሆይ በል!” በማለት እያቅራሩና እያስፎከሩ ወጣቱን ለጥፋት ካሰማሩ በኋላ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሲጠረጥሩ በመጠባበቂያ ፓስፖርታቸው ለክፉ ቀን ወደ ቆፈሩት ጎሬ በመግባት ከለላ ያገኛሉ፡፡ “እኛም ነቅተናል፤ ጉድጓድ ምሰናል” አሉ እንደሚባለው የቤት እንስሳት ወደ መሸሸጊያቸው ገብተው ክፉውን ቀናቸውን ያሳልፋሉ፡፡
ትውልድ ሆይ ልብ በል! ዘመናዊዎቹ “የሌባ ሻይ” ጠጪና አጠጪዎች፣ ፈፃሚና አስፈፃሚዎች እነርሱ ለራሳቸው ሞትን በሽሽት እየገዘቱ ለትውልዱ የመቃብር ሳጥኖች ያዘጋጃሉ፡፡ እነርሱ የባንክ ሂሳባቸውን እያሳበጡ የሕዝቡን የዕለት እንጀራ ማዕድ ይገለብጣሉ፡፡ እነርሱ በዘረጉት ብዙኃን መገናኛና ማኅበራዊ መስተጋብር ዱታ ነን እያሉ እየፎከሩ ወጣቱን ለጥፋት ከማገዱና ለንፍር ውሃ ከዳረጉ በኋላ የእነርሱ ልጆችና ዘመዶች በየውጭ አገራቱ “በደም ዋጋ” ያንፈላስሷቸዋል፡፡
“ሌባ ሻይ” አጠጪዎች ሆይ በቃችሁ! እየተባሉ ሊገሰፁና ሊናቁ ይገባል፡፡ ከቁራኛቸው ለመላቀቅም መድፈር፣ መጠየቅና መወሰን ግድ ይሏል፡፡ “ሌባ ሻይ” የሚግቱ ጨካኞች ዋሾ ብቻ ተብለው የሚታለፉ ሳይሆኑ ራሳቸውም በአብሾ የሰከሩ ራስ ወዳድ የህሊናና የእውነት ድኩማን ጭምር ናቸው፡፡ ስለዚህም ወጣት ሆይ መንቃቱ ይበጃል፡፡ ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2012