ባለፈው ሳምንት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት ሲያልፍ አስር ተማሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል። በወልድያ ተከስቷል የተባለው የተማሪዎች ግጭት ወደ አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መዛመቱም ይታወቃል። ያም ሆኖ ግን የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል። ሆኖም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘላቂ ሰላም እንዲኖርና ተማሪዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
እንደሚታወቀው የዘንድሮው የትምህርት ዘመን ሲጀመር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በየትኛውም ተቋም የፀጥታ ችግር እንደማይኖር እየሰራ እንደሆነ ገልፆ ነበር። ሆኖም ገና ትምህርት ተጀምሮ ከሁለት ወር ሳይዘል እንዲህ አይነት ችግር መከሰቱ አስደንጋጭ ነው።
የፀጥታ ችግሮቹ ከውጭ በሚመጡ ሰዎች የተቀናበረ ነው ይባል እንጂ በተማሪዎች መካከል ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ይነገራል። በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢው ህብረተሰብና ተቋማቱ ተናበው በመስራታቸው ያለምንም የፀጥታ ችግር እያስተማሩ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ይገኛሉ። ሁሉንም ተቋማት በአንድ መንፈስ ተማሪዎቻቸውን እንዲያስተምሩና ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆኑ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ይናገራሉ።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነዓ እንደሚናገሩት፤ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ያለው የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ሰላማዊ ነው ማለት ይቻላል። አልፎ አልፎ የትምህርት መቋረጦች ይታያሉ። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን ግጭት ለማስቆም መፍትሄ የሚሆን ነገር ከሁሉም ሰው ይጠበቃል። በተቋማት ውስጥ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ለህግ እንዲቀርቡ መደረግም አለበት። አንድ ተቋም ግጭት ተከስቷል በሚል በሌሎች ቦታዎች ግጭት መነሳት የለበትም። በየተቋማቱ በቂ የሆነ ጥበቃ መደረግ አለበት ይህ ሲሆን ወንጀል የሚሰሩ ሰዎችን በፍጥነት በቁጥጥር ስር ማዋል ይቻላል።
አንዳንድ ሰዎች ተማሪዎች በየክልላቸው ቢማሩ ኖሮ ግጭት አይከሰትም ነበር በሚል ሃሳብ እንደሚያነሱ የሚናገሩት ዶክተር ታደሰ ሆኖም ይህ ሀሳብ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት ተማሪዎቹ መጥተው እየተማሩ የሚገኙት አገራቸው ላይ እንጂ ሌላ ቦታ አይደለም። በየተቋማቱ ውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማራመድ የሚፈልጉ ሰዎች የሚያስነሱት ግጭት በየጊዜው እየጨመረ እንደሚገኝ እና አፋጣኝ ርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ያስረዳሉ።
የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በሁሉም ተቋማት ውስጥ እየተስፋፋ ይገኛሉ። በአምቦ ዩኒቨርሲቲም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ይስተዋላሉ። ይህን ለመቀየር እየተሰራ ይገኛል። ከጸጥታ ኃይሎች፤ ከህብረተሰቡና ከተማሪው ጋር በጋራ እየተሰራ ሲሆን የትም ተቋም ያሉ ችግሮች በአምቦ ዩኒቨርሲቲም እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ኤርሚያስ እንደሚናገሩት፤ ተቋሙ ከተማሪዎች አቀባበል ጀምሮ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል አደረጃጀት እንዲፈጠር አድርጓል። ከከተማው፣ ከዞንና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል። በአሁኑ ወቅት በተቋሙ ምንም አይነት የሰላም ስጋት የለም። በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር የየራሳቸው አደረጃጀት እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል። ተማሪዎችን ያቀፈ የሰላም ፎረሞች እንዲዘጋጁ በማድረግ ውስጣዊ አሰራሮችን እየገመገመ ይገኛል።
በተቋሙ ቅድሚያ የተመሰረተ አደረጃጀት በመኖሩ በሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግጭት ሲከሰት እንዳይስፋፋ ማድረጉን አቶ ውብሸት ይናገራሉ። በተቋሙ ከተሾሙ ወጣት የሰላም አምባሳደሮች ጋር አብሮ በመሰራቱ ተቋሙ ውስጥ የሰላም መደፍረስ እንዳይኖር ወጣቶቹ እየጠበቁ እንደሚገኙ ያመለክታሉ። የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና የሃይማኖት አደረጃጀቶች በጥምረት እየሰሩ እና በየጊዜው ባሉ ሁኔታዎች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተቋሙ ሰላማዊ እንዲሆን ማድረጉን ያስረዳሉ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በወልዲያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በመቱ፣ መዳወላቡ፣ ጅማ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠረው ችግር የተማሪዎችን መታወቂያ በመቀማት እና በህገወጥ መንገድ መታወቂያ በማዘጋጀት ወደ ግቢ የገቡ ግለሰቦች ተማሪዎችን ለሁከት ማነሳሳት፣ ተማሪዎች ምግብ እንዳይበሉ፣ ወደክፍል እንዳይገቡ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር እንዲጋጩ የመቀስቀስ ሥራ ሲያከናውኑ ነበር።
የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ወደነበረበት ለመመለስና የመማር ማስተማር ሥራውን ለማስቀጠል የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ኃይሎች የተጠናከረ ሥራ በመስራት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአባ ገዳዎችና ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ። በውይይቱ ላይ ተማሪዎቹ አደጋ ይደርስብናል፣ መማር አልቻልንም፣ አልተረጋጋንም፣ አስተማማኝ ጥበቃ የለንም የሚል ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።
ይህንን ስጋት ለመቅረፍ ከሚደረገው ውይይት በተጓዳኝ የክልልና የፌዴራል የጸጥታ አካላት የተቀናጀ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን እና ችግሩም ከመንግሥት አቅም በላይ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ችግሩ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ እንዳልሆነ እና ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው በቅርቡ እንደሚመለሱ፣ አጥፊዎችም በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ ያስረዳሉ።
እነዚህ አካላት በተደላደለ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ጭምብል አድርገው ድንጋይ በመወርመር፣ ተማሪዎች ሜዳ ላይ እንዲያድሩ፣ በኃይማኖት ተቋማት ውስጥ እንዲጠለሉ፣ ከትምህርት ቤታቸው ለቀው እንዲወጡ፣ ተቋማቱ የብጥብጥና የሁከት ቦታ እንዲሆኑ፣ተማሪው እንዳይረጋጋ ማድረጋቸውን ይጠቁማሉ። ‹‹በየአካባ ቢያችሁ መማር ትችላላችሁ›› የሚል ቅስቀሳም በማድረግ ወላጆችንም እያሸበሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ። ተማሪዎችን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ አካላት ይህን በማድረጋቸው የሚያገኙት ትርፍ እንደሌለ ተገንዝበው እጃቸውን ከተማሪዎች ላይ እንዲያነሱ ዶክተር ሳሙኤል አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2012
መርድ ክፍሉ