በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአፈር ንጥረ ነገሮችን ለመለየት የሚያስችል የካርታ ስራ መሰራት ተጀምሯል። እንደየአካባቢው አፈር ለምነት እና የጥቅም ሁኔታ ዘርዝሮ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መረጃዎችን የማደራጀት ስራ በግብርና ተቋማት እየተከናወነ ይገኛል። በተለይ ለዕፅዋት ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ እንደ ፎስፎረስ፣ ፖታሺዬም፣ ዚንክ፣ ናይትሮጅን፣ ቦሮን፣ ማግኒዥዬም የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮች በምን ያህል መጠን በአፈር ውስጥ እንደሚገኙ ባለሙያዎች አጥንተው ለአርሶ አደሮች ያቀርባሉ።
ይህ ጥናት የአፈር ካርታ የሚል መጠሪያ ሲሰጠው፤ የጥናቱን ውጤቱን ተከትሎ ደግሞ አርሶ አደሩ እንደ አፈሩ ለምነት የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ መጠን እየተጠቀመ ይገኛል። በዚህ አሰራር በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሉሜ ወረዳ ላይ የተከናወነው የአገር ካርታ ጥናት ምን ውጤት ተገኘበት የሚለውን ለመመልከት ሰሞኑን ጉብኝት ተካሂዶ ነበር።
አርሶ አደር ጸጋዬ እምሩ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሉሜ ወረዳ ካራ ፊንጫ ውሃ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። አንድ ሔክታር መሬት አላቸው። ቀድሞ በመሬታቸው ላይ ስንዴና የተለያዩ ሰብሎችን ሲዘሩ ማዳበሪያን የሚጠቀሙት በግምት ነበር። ሆኖም በምርት መሰብሰቢያ ወቅት ግን ማዳበሪያው በዛም አነሱም የሚያገኙት ምርት የሚጠብቁትን ያህል አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ አስር ኩንታል ስንዴ፤ ሌላ ጊዜ ዘጠኝ ኩንታል ቢያገኙም የተሻለ ለውጥ ግን አላዩም።
አሁን በወረዳቸው በተሰራው የአፈር ካርታ መሰረት የግብርና ባለሙያዎች ለአካባቢው ጥቁር አፈር የሚሆን የተመጣጠነ የማዳበሪያ አይነት እንዲጠቀሙ ምክር ሰጥተዋቸዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ከባቱ ግብርና ምርምር ማዕከል የመጡ ባለሙያዎች ከማሳቸው ላይ ለናሙና የሚሆን አፈር ወስደው ወደ ቢሯቸው አመሩ። የአፈሩን ይዘትና ምን እንደሚያስፈልገው በመለየትም በጥቂት ቀናት ውስጥ ተመልሰው ሙያዊ ምክራቸውን አቀበሉ።
ካለፈው ክረምት ጀምሮ ጥናቱን በመቀበል የአካባቢው አርሶ አደር ዘር ሲዘራ በግምት ሳይሆን የማዳበሪያ መጠኑን እንደ አፈሩ ለምነት በኪሎግራም በማመጣጠን ሆኗል። በውጤቱ አሁን ላይ ያማረ ሰብል ታይቷል። ስንዴው በመስመር ተዘርቶ ያማረ ፍሬ አፍርቶ በመታየቱ አርሶ አደሩ በቀጣይ ጊዜያት ያለማንም ቀስቃሽ ተገቢውን የማዳበሪያ ምጠና በማድረግ ለማምረት ፍላጎቱን አሳይቷል።
በሉሜ ወረዳ የቱሉ ረኤ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሴት አርሶ አደር ወይዘሮ የሺ ሞገስ ደግሞ ማሳቸው ላይ ጤፍ ዘርተው ጥሩ ምርት አግኝተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት 13 አርሶ አደሮች በቡድን ተደራጅተው በቂ የማዳበሪያ ምጠናና የሚያርሱት አፈር የለምነት መጠን ላይ ግንዛቤ ተሰጥቷቸዋል።
13ቱም አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ጤፍ በመዝራት ዩሪያ እና ዳፕ ማዳበሪያዎችን በማመጣጠን ጥቅም ላይ አውለዋል። የማዳበሪያ ምጠናው አሁን ለተገኘው ውጤታማ ምርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን፤ በጋራ ጥቅም ላይ ማዋሉ ደግሞ ይባክን የነበረውን ማዳበሪያ ለተጨማሪ መሬት ለማዋል አስችሏል።
‹‹አንዱ አርሶ አደር የዩሪያን ማዳበሪያ አብዝቶ ሲጠቀም፤ ሌላው ደግሞ ዳፕ የተባለውን ማዳበሪያ ሲጠቀም ምርቱም ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ሆኖ ቆይቷል›› የሚሉት ወይዘሮ የሺ። አሁን በተዘጋጀው የወረዳው የአፈር ካርታ በጥናት ካልተደገፈ የግምት ስራ ያላቀቀ በመሆኑ በካሬ ሜትርና በአይነት የተመጠነ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። በዚህም ከቀድሞው የበለጠ በአንድ ጥማድ ከአምስት ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ተስፋ መደረጉን ይናገራሉ።
‹‹የሰው ልጅ የተለያየ ጂን እንዳለው ሁሉ አፈርም የተለያየ ንጥረ ነገር የያዘ በመሆኑ የሚያስፈልገውን መርጦ መመገብ ይገባል የሚሉት›› ደግሞ በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባቱ አፈር ምርምር ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን አበራ ናቸው። የአፈር ምርምር ጥናት እንደሚለው 17 አይነት ንጥረ ነገሮች ለተክል እድገት አስፈጊ ናቸው። በዋናነት ደግሞ ናይትሮጂን እና ፎስፈረስ አስፈላጊ በመሆናቸው በሉሜ ወረዳ ምን ያህል መጠን የንጥረ ነገሮች ጉድለት አለ የሚለው ተጠንቶ ለየቀበሌው ካርታ ተሰርቷል። አምስት ዓይነት የአፈር ለምነት አይነቶች በወረዳው ተገኝተው የተለያየ የማዳበሪያ ምጠና እንዲጠቀሙ ተደርጓል።
ለአብነት ፊንጫ ውሃ በተባለው አካባቢ ፎስፈረስ አስፈላጊ በመሆኑ በአንድ ሔክታር ዳፕ ማዳበሪያን ብቻ እስከ 150 ኪሎ ግራም እንዲጠቀሙ ምክር ተሰጥቷል። ከዚህ ቀደም አንዱ አርሶ አደር 100 ኪሎ ግራም ሌላው ደግሞ 70 ኪሎ ግራም በግምት ሲጠቀሙ ከነበረበት ወቅት አሁን የተሻለ ውጤት መገኘቱን አርሶ አደሩም እንዳመነበት አቶ ጥላሁን ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ጥላሁን ከሆነ፤ ከካርታ ጥናቱ ጋር የተዛመደ የማዳበሪያ ምጠና ጥቅም ላይ እንዲውል ለአርሶ አደሩ ለዘንድሮ ዓመት ምርት የሚያገለግል በነጻ የማዳበሪያ አቅርቦት ተደርጓል። አቅርቦቱ በዓለም ባንክ በሚደገፈው የኤጂፒ ፕሮጀክት በኩል ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፤ የምርቱ ከፍተኛነት በመታየቱ በቀጣይ የማዳበሪያ ድጋፉ የሚቀጥል ባይሆን እንኳ በራሱ እየገዛ ለመስራት ፍላጎት አሳይቷል። ይህም የአፈር ካርታ ጥናቱ ውጤታማነት ላይ አርሶ አደሩ ያሳየውን እምነት የሚያመላክት በመሆኑ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2012
ጌትነት ተስፋማርያም