ሰሞነኛ ከሆኑትና የብዙዎቻችንን ቀልብ ከሳቡ አወዛጋቢ ጉዳዮች ውስጥ የኢህአዴግን ውህደን ያህል ሰፊ ሽፋን ያገኘ ወቅታዊ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም።በተለይም ጉዳዩ እጅግ አወዛጋቢ ከሆነባቸው ጉዳዮች ውስጥ በኢህአዴግ አባል ደርጅቶች መካከል በጉዳዩ ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም አለመያዙ ነው።
ከ22 ዓመታት በላይ አጀንዳ ሆኖ በኢህአዴግ ጉባኤዎች ላይ ሲቀርብ የነበረው የውህደትጥያቄ ዛሬ ለምን አዲስ ሆኖ የውዝግብ ማዕከል እንደሆነ ብዙዎቻችንን ግራ ያጋባ ጉዳይ ነው።ጉዳዩ ያደረ ብሎም የከረመ መሆኑንም የምንረዳው በየወቅቱ የነበሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት ውህደቱን በተመለከተ ሲሰነዝሯቸው ከነበሩ ሀሳቦች ነው። ለአብነትም የሚከተሉት ጉምቱ ጉምቱ ባለስልጣናት በኢህአዴግ ውህደት ዙሪያ ሰነዘሯቸውን ሀሳቦች በጥቂቱ እንመልከት፤
አቶ መለስ ዜናዊ (1999 -አዲስ አበባ)
ኢህአዴግ አንድ ወጥ ፓርቲ የመሆኑ አቅጣጫ ከዚህ በፊት በኢህአዴግ ጉባኤዎች አቋም የተወሰደበት ጉዳይ ነው።
ዶ/ር አብዱል መጂድ ሁሴን(የሶኢዴፓ አባል፤-(1994)
ማስታወስ የምፈልገው የአጋሮቻችን ጉዳይ ነው። ከእናንተም ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር የምናቀርበው አንድ ጥያቄ አለ። በሚቀጥለው የኢህአዴግ የመጀመርያ ስብሰባ አጀንዳችሁ ላይ የአጋሮችን ጥያቄ እንድትጨምሩ እንጠይቃችኋለን።
ኃይለማርያም ደሳለኝ(1996 ሃዋሳ)
ክልላዊ ፓርቲዎች ወጥ ሆነው ክልላዊ መንግስትን የሚመራ ክልላዊ ፓርቲ መኖሩ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡: ይህ በሂደት ኢህአዴግም በራዕይ መልክ ያስቀመጠውን ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት የሚደረገውን ጉዞ የሚያግዝ ነው።ኢህአዴግም በረዘመ ሂደት ወደ አንድ ፓርቲነት የመሸጋገር ዕቅድ አለው፡:በ4ተኛው ድርጅታዊ ጉባኤም የተወሰነ ጉዳይ ነው።
አቶ ስዩም መስፍን (2005-ባህርዳር)
አጋር ድርጅቶች ጋር አጋርነት የሚለውስ እስከ መቼ ድረስ ነው።ኢህአዴግን ወደ ውህድ ፓርቲነት የመቀየሩን ጉዳይ ማን ያንሳው፡ ይህ ጉዳይ 22 ዓመታት ሞላው እኮ።
እንግዲህ ከእነዚህ ባለስልጣናት በላይ የዚችን ሀገር ጉዳይ ያውቃል ተብሎ የሚታሰብ ሰው የለም። በወቅቱም ሁሉም ባለስልጣን በሚባል መልኩ ውህደቱ ጥያቄ አንገብጋቢ መሆኑንና ቶሎም ሊፈጸም እንደሚገባ ሲሞግቱ አዳምጠናል።
የኢህአዴግ ውህደት መነጋገሪያ ከሆነ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ጉዳይ ነው። ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ውህደት ያስፈልገዋል የሚለው ጉዳይ በ5ኛው የግንባሩ ጠቅላላ ጉባኤ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ተዘግቦ እናገኘዋለን። ስለዚህም እንደሚባለው አዲስ ክስተት አይደለም። በኢህአዴግ ጉባኤ ሲሳተፉ የቆዩ አንዳንድ ነባር አመራሮች እንደሚያስረዱትም ይህ የውህደት ጥያቄም ከ5ኛው ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ በተደረጉ ጉባኤዎች ሳይነሳ የማያልፍ ጥያቄ ሆኖ መቀጠሉንና በሁሉም የድርጅቱ አባላት ጭምር የግንባሩ የውህደት አስፈላጊነት ጉዳይም በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ መሆኑን ነው የገለጹት።
በ2008 በመቀሌ በተካሄደውም 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ይህ የውህደት ጥያቄ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ውይይት እንደተደረገበት የሚታወስ ነው። በዚሁ በመቀሌ በተደረገው ጉባኤም ጉዳዩ በተደጋጋሚ ስለተነሳና የብዙዎች ጥያቄም ስለነበረ የውህደቱ አፈጻጸም ተጠንቶ ለሚቀጥለው ጉባኤ እንዲቀርብ አቅጣጫ መሰጠቱ ይታወሳል።
ይህንኑ መሰረት በማድረግም ሀዋሳ ላይ በተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ውሳኔው ወደ ውጤት ይቀየር የሚለው ግፊት አይሎ መጥቷል። በወቅቱም ከየትኛውም ድርጅት ተቃውሞ አልገጠመውም ነበር። ታዲያ ዛሬ ለምን እንደ አዲስ መወዛገብ አስፈለገ።
ለመሆኑ ከ5ተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ጀምሮ ሲታሽ የመጣን ጉዳይ ዘገየ ሊባል ካልሆነ በስተቀር በምን መመዘኛ ነው የተቻኮለ ሊባል የሚችለው። እንደውም ኢህአዴግ መወቀስ ካለበት ይህን ሁሉ ዓመታት ጉዳዩን ችላ ብሎ በመዘግየቱ ነበር። የብሶተኞችን ጩኸት ቀምቶ ነው እንጂ አጋር ድርጅቶችን ባገለለ መልኩ ይህን ሁሉ ዓመታት ብቻዬን አስተዳድራለሁ ብሎ አግላይ አካሄድን መከተሉ ሊያስወቅሰውም ይገባ ነበር። ስለሆነም የአሁኑ ውሳኔ ዘገየ ካልተባለ በስተቀር የተዋከበበት መንገድ ለእኔ አይታየኝም።
ውህደቱ ያስጨነቃቸው አካላት ለምን ይህን ያህል መቃወም አስፈለጋቸው ብለን ስንጠይቅ የለውጥ አመራሩን ህዝባዊ ተቀባይነት ለማሳጣት የሚደረግ እሩጫ ሆኖ እናገኘዋለን። ውህደቱ ህብረ ብሄራዊነትን ይደፈጥጣል፤ አሀዳዊ መንግስትን ያነግሳል የሚሉ ከጉዳዩ ጋር አብረው የማይሄዱ አሉባልታዎች ሲሰነዘሩ ይደመጣል። በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ባለፉት 27 ዓመታት ሲተገበር የቆየው ፌዴራሊዝም ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር አሀዳዊ ባህሪ የነበረውና ከአንድ ማዕከል በሚወርድ የዕዝ ሰንሰለት አድርግ አታድርግ የሚሉ ቀጭን ትዕዛዞች በሁሉም ክልሎች ሲተገበሩ ቆይተዋል።
ስለዚህም በምንም አይነት መልኩ ከቀድሞው በከፋ መልኩ የጌታና የሎሌ ግንኙነት ሊፈጠር እንደማይችል እየታወቀ እና ይደረግም ቢባል አሁን ካለው የለውጥ አስተሳሰብና ከህዝቡ ንቃተ ህሊና አንጻር ተቀባይነት እንደማይኖረው ግልጽ ሆኖ ሳለ ይህንን አመክኒዮ ይዞ መቅረብ ውሃ የሚቋጥር ሆኖ አላገኘሁትም።
ይልቁንም የኢህአዴግ ውህደት በሀገሪቱ ለ27 ዓመታት ያህል ሰፍኖ የቆየውን የአዛዥ ታዛዥ ድራማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ የሚያደርግና የሴራ ፖለቲካ አራማጆችን ግብዓተ መሬት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለአንዳንዶች ላይዋጥ ይችላል። የሆነው ሆኖ ግን የኢህአዴግ ውህደት ላለፉት 27 ዓመታት ከፖለቲካ መድረኩ ዕርቀውና የበይ ተመልካች ሆነው የቆዩትን የአፋር፤ የሶማሌ፤ የሀረሪ፤ የቤኒሻንጉልና የጋንቤላ ህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ኢትዮጵያዊነት የሚያረጋግጥ ነው። ስለዚህም ውህደቱ ኢትዮጵያዊነት በበለጠ መሰረት እንዲይዝና ሁሉንም በእኩል መጠን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ኢህአዴግ የጀመረውን የቤት ስራ በአፋጣኝ ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል።
ከላይ በመግቢያችን ላይ እንደተመለከትነው ባለሥልጣኖቻችን በአንደበታቸው ሲጠይቁት የነበረውን ጥያቄ ዛሬ መካድ ለምን አስፈለጋቸው። ወይስ ይህን ጉዳይ ሲሞግቱ የነበሩ ሰዎች ማሊያ ቀይረው ይሆን። እንደዛ ከሆነ በግልጽ ይንገሩን፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012
እስማኤል አረቦ