ሰሞኑን በማህበራዊ ገጾች አንድ ፎቶ ሲዘዋወር ነበር። ይሄውም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጓደኞቻቸው ግቢውን ለቀው ሊሄዱ ሲሉ እየተላቀሱ ‹‹እባካችሁ አትሂዱብን›› ሲሉ የሚያሳይ ነው። የማህበራዊ ገጾች ዜና ስለሆነ እውነት ነው አይደለም በሚል መጠራጠር ውስጥ ነበርኩ፤ ማታ ግን የአሜሪካ ድምጽ (ቪ ኦ ኤ) ሬዲዮ ጣቢያ በሰራው ዜና እውነት መሆኑን አረጋገጥኩ፣ዜናውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አናግሮ ነበር የሰራው።
በነገራችን ላይ ለአገር ሰላምና ዕድገት እንሰራለን የሚሉ ‹‹ሜይንስትሪም›› ሚዲያዎች እንዲህ ዓይነት በጎ ነገሮችን አይዘግቡም። የሚገርመው ግን ‹‹ግጭት ቀስቃሽ ሚዲያዎች›› እያሉ ደግሞ ዜና እና ፕሮግራም ይሰራሉ። በጎ ነገሮችን አለመዘገብ በራሱ ግን ግጭት ቀስቃሽነት እኮ ነው።
የትግራይ ክልል ተማሪዎች ወደ አማራ ክልል እንዳይሄዱ ማለቱን ተከትሎ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እናቶች ለተማሪዎች የእናትነት ኃላፊነት ወስደው ነበር። ይሄን የእናቶች በጎ ተግባር ግን የክልሉ መገናኛ ብዙኃንና አንዳንድ የግል መገናኛ ብዙኃን ሲያወሩበት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡት አልታየም፤ አልተሰማምም። እውነት ይሄ ነገር የማይበረታታ ሆኖ ነው? ለብዙ ዩኒቨርሲቲዎች አርዓያ መሆን አልነበረበትም?
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ሊወጡ የነበሩ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ከክልላቸው ውጭ ስለሆነ ለደህንነታችን ያሰጋናል ብለው ነው፤ ግን ጓደኞቻቸው ደግሞ ‹‹ከእኛ ተለይታችሁ አትሄዱም›› የሚል ነበር። እንግዲህ ልብ በሉ! እነዚህ ተማሪዎች ለዓመታት አብረው የቆዩ ናቸው። ብዙ ማህበራዊ ሕይወትን በጋራ ያዩ እና ብዙ ትዝታ ያላቸው ናቸው። አዲስ ገቢ ተማሪዎችም ገና የግቢ ሕይወትን የማየትና አዳዲስ ጓደኞችን የመተዋወቅ ከፍተኛ ጉጉት ላይ ያሉ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ተማሪዎች ሲለያዩ እንዴት አይላቀሱ?
አንድ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የሚያጓጓው ነገር አካዳሚያዊ ትምህርቱ ብቻ አይደለም፤ በዚያ ውስጥ ያለው ማህበራዊ ሕይወት ነው። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአካባቢው ሲማር የቆየ ተማሪ አገሩን ማወቅ የሚጀምረው ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ነው። በመጽሐፍና በንድፈ ሀሳብ ትምህርት ሲማረው የቆየው የአገሩን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህልና ወግ በተግባር የሚያየው ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ነው። በሬዲዮ የሚሰማውንና በቴሌቪዥን ሲያየው የነበረውን የአገሩን ድንቅ ባህሎች በተግባር የሚያያቸው ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ነው። እነዚህን ነገሮች ለማወቅ ደግሞ ተወልዶ ካደገበት አካባቢ ራቅ ብሎ መሄድ አለበት።
ጎጃም ወይም ጎንደር ውስጥ ተወልዶ ያደገ ተማሪ አገሩን ለማወቅ ባህርዳር ወይም ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አይደለም መማር ያለበት፤ መቀሌ፣ ወለጋ ወይም ጅግጅጋ ቢሄድ የበለጠ አገሩን የማወቅ ዕድል ይኖረዋል። ምክንያቱም ደብረ ማርቆስ፣ ባህርዳር ወይም ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቢገባ የሚያየው ባህልና ቋንቋ ካደገበት ማህበረሰብ ጋር ተመሳሳይ ነው። እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ እንበል። ዩኒቨርሲቲው የክልሉ ተወላጆች ብቻ የሚማሩበት እንዳልሆነ ይታወቃል። ለምሳሌ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከሁሉም ክልል የተውጣጡ የሚማሩበት ሀገራዊ ብሎም ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። ግን ልዩነቱ እሱ አይደለም፤ በዚህ በኩል የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ነው። ዋናው ልዩነት የአካባቢው ማህበረሰብ ነው።
ተማሪዎች በሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህልና ቋንቋ የሚጋሩበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ለመዝናናትም ይሁን ለተግባር ልምምድ ትምህርት የሚወጡት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ውስጥ ነው። በተለያዩ ዝግጅቶች አማካኝነት ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡት የአካባቢው ማህበረሰቦች ናቸው። የግቢው ሠራተኞች (ለምሳሌ የካፌ) በብዛት የዚያ አካባቢ ተወላጆች ናቸው። በእነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች ተማሪው ብዙ ነገር ይማራል፤ የአገሩን ቋንቋና ባህል ያውቃል ማለት ነው። አማራ ክልል ውስጥ ተወልዶ ያደገ ተማሪ የትግራይን ወይም የኦሮሚያን ወይም የሶማሌን ማህበረሰብ ባህልና ቋንቋ የሚያውቀው ባህርዳር ወይም ደብረ ማርቆስ ሆኖ አይደለም።
በተመሳሳይ ትግራይ ወይም ኦሮሚያ ወይም ሶማሌ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ተማሪ የጎጃሙን፣ የጎንደሩን ወይም የወሎውን ባህልና ቋንቋ የሚያውቀው መቀሌ ወይም ወለጋ ሆኖ ሳይሆን ባህርዳር ወይም ደብረማርቆስ ወይም ጎንደር በመሄድ ነው።
አሁን አሁን ግን እነዚህን ፀጋዎች እያጣን ነው። የምንሰማው ሁሉ የሚያስተዛዝብ ነገር ነው። በዚህ አካሄዳችን ከቀጠልን አሳፋሪ ታሪክ ማስቀመጣችን የማይቀር ነው። ቀጣዩ ትውልድ ይወቅሰናል። እየሆነ ያለው ነገር ተማሪዎች በክልላቸው ብቻ እንዲማሩ የሚገፋፋ ነው። ይሄ ሆነ ማለት ደግሞ አሳፋሪ ታሪክ አስመዘገብን ማለት ነው። ባለፉት ዘመናት የተሰሩ ጥፋቶችን የምንወቅሰው እኮ እንዲህ አይነት ስህተቶች ስለሰሩ ነው። የሰሩት አኩሪ ታሪክም ሆነ ያደረሱት ጥፋት ይመዘገባል። ባጠፉት ጥፋት ያለፉትን ስንወቅስ እኛ ግን ከዚያም የከፋ እያደረግን ነው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከክልሉ ውጭ እንዳይሄድ ከተደረገ ይሄ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ ይሆናል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ አገሪቱን የሚከፋፍልና የጋራ ጉዳይ እንዳይኖረን የሚያደርገን ነው።
እስኪ አስቡት! አንድ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቅ ተማሪ ምንድነው የሚጠብቀው? አገር መረከብ ነው አይደል? ታዲያ ምን አይነት አገር ነው የምናስረክበው? አማራን ኦሮሞ ያንተ አይደለም እያልን? ኦሮሞን አማራ ያንተ አይደለም እያልን? ትግሬውን አማራ ያንተ አይደለም ወይም አማራን ትግራይ ያንተ አይደለም እያልን? በራሱ ክልል ውስጥ ብቻ ይማር ማለት ሌላው ያንተ አይደለም ከማለት በምን ይለያል ታዲያ? ይሄ ተመራቂስ ነገ እንዴት ሆኖ አገር ሊያስተዳድር ይችላል? ዓለም አቀፍ ሰው መሆን ሲገባው ጭራሽ አገሩንም የማያውቅ ሊሆን ነው እኮ?
አንድ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመረቀ ሰው ቢቻል ቢቻል ዓለምን ጠንቅቆ የሚያውቅና በየትኛው አህጉር ወይም ዓለም አቀፍ ተቋም ቢሰራ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ዓለም አቀፍ ሰው ነው መሆን ያለበት፤ ያ! ቢቀር እንኳን አገሩን የሚያውቅ መሆን አለበት። ታዲያ በሰፈርና በቀዬ አስረናቸው ስንቀር የእነዚህን ልጆች ዕድል እያበላሸን አይደለም?
አሁን ከተማሪዎች የሚጠበቀው ብልጥ መሆን ነው። ተማሪዎች የማንም አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሆን የለባችሁም። ትምህርት አልሳካለት ብሎ ያቋረጠ ሁሉ በእናንተ እንጀራውን ሊጋግር አይገባም። ሳይንስ ላይ መመራመር ሲያቅተው ሳይንስ ላይ የሚመራመሩ አዳጊዎችን ለማጨናገፍ የሚሰራ ጥፋተኛ በየጥጋጥጉ እንደ አረም ተንሰራፍቶ ይገኛል።እናንተ የተሻላችሁ ናችሁ። እናንተ የተማራችሁ ናችሁ። እናንተ ሌላው በወረደበት መውረድ የለባችሁም። እንዲህ አይነት ሰዎችን መናቅ አለባችሁ። እንጀራውን በሁከትና ብጥብጥ ለሚጋገር ሰው ማገዶ አትሁኑ። እናንተ አገር ተረካቢ ናችሁ። ትልቅ ኃላፊነት ነው የሚጠብቃችሁ።
ተማሪዎች ብልጥ ከሆኑ እንዲህ አይነት ጥፋቶችን ማስቆም ይችላሉ። በቃ በልጦ መገኘት ነው። ከዚያ በኋላ ብጥብጥ ፈላጊው ሲያፍር መደበቂያ ያጣል። ተከታይ ሲያጣ እሱም ወደ ሰላም ይመለሳል። ለዚህ ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። ተማሪዎች እንዲህ ‹‹አንለያይም!›› ሲሉ ለመነጣጠል ያሰበ አካል አፍሮ ይመለሳል! ስለዚህ ተማሪዎች በልጣችሁ ተገኙ!
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012
ዋለልኝ አየለ