አቶ አልይ ዳዌ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሀብሮ ወረዳ ቀበሌ 01 ውስጥ ይኖራሉ። ከወለዷቸው ልጆች መሀል በቅርቡ አንደኛውን በሞት አጥተዋል። ልጃችው ጎበዝና ብርቱ ገበሬ ነበር። አቅምና ጉልበት ባነሳቸው ጊዜ ከጎናቸው ሆኖ ሲያበረታቸው ቆይቷል። በህይወት በነበረ ጊዜ ከመሬታቸው ገሚሱን በኮንትራት ሰጥተውት ሲገለገልበት ነበር። በጊዜ አጋጣሚ ሟች ከአካባቢው ከመራቁ በፊት ዓመታትን በመሬቱ አርሶ ተጠቅሟል።
በዚህ መሬት ያፈሰውን ምርት ሲሻው ለገበያ ሲሻው ደግሞ ለቤተሰቦች ፍላጎት ሲያደርገው ቆይቷል። ድንገቴው ሞት ግን የጠንካራውን ገበሬ ታሪክ ቀይሮ እነሆ! ወላጅ አባቱን ለሀዘን ከዳረገ ቀናትን አስቆጥሯል።
አቶ አልይ የልጃቸውን መርዶ ሰምተው ሀዘናቸውን ከወዳጅ ዘመድ ጋር እንደጨረሱ አንዱን ቀን ወደ እርሻ በድንገት ወደ ማሳው ወረዱ። በስፍራው ደርሰውም አካባቢውን በዝምታ ቃኙት። ይህኔ ትናንትና እርፍ ጨብጦ ደረቁን መሬት ይገለብጥ የነበረ ብርቱ ልጃቸውን አስታወሱት። ወዲያውም በጥልቅ ሀዘን ተውጠው አንገታቸውን ደፉ። ዓይኖቻቸው በትኩስ ዕንባ ተሞሉ።
ዛሬ ያ ጎበዝ ገበሬ በተራው ከመሬት ስር ውሏል። እንደሻው ያደርገው የነበረ እርሻውም የትናንቱን ታሪክ አይደግምም። አሁንም አቶ አልይ በጥልቅ የሀዘን ሰሜት ውስጥ ናቸው። ካሉበት ሆነው በልጃቸው ሀዘንና የሩቅ ትዝታዎች መቆዘማቸውን ቀጥለዋል።
ጥቂት ቆይቶ ሀሳባቸውን የሚሰርቅ ጉዳይ ተፈጠረ። ከደቂቃዎች በፊት ባዶ የነበረው መሬት በሰዎች አጀብ ሲሞላ ተመለከቱ። ይህ ስፍራ ሟች ከእሳቸው በኮንትራት ወስዶ ዓመታትን ሲጠቀምበት እንደቆየ ጠንቅቀው ያውቃሉ። የአሱ ታናሽ ወንድምም ሲያርስበት ስለመቆየቱ ነጋሪ አያሻቸውም። አሁን ግን የእነሱ ያልሆኑ ጥማድ በሬዎች ውለውበት ሌሎች ሰዎች እያረሱበት ነው። ይህ ለምን እንደሆነ እየገረማቸው ወደ ሰዎቹ ቀርበው ጠየቁ። በፍጥነት የተሰጣቸው ምላሽ ግን አልይን ከድንጋጤ ጥሎ ባሉበት ክው ለማድረግ ጊዜ አልፈጀም።
በነገሩ እጅጉን ተገርመው ደጋግመው ጠየቁ። ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ጉዳዩ በዋንኛነት ይመለከተዋል ከተባለ አንድ ሰው ጋር ፊት ለፊት እየተያዩ በጥያቄና መልስ ሊፋጠጡ ግድ ሆነ። ሰውዬው አቶ ሙመድ ይባላል። በስፍራው የቆሙት የሟች ወላጅ አባት መሆናቸውን እንዳወቀ እውነታውን ለማስረዳት ቀረባቸው።
አቶ አልይ አሁንም ከግርምታ ሳይወጡ መሬቱን በምን አግባብ እያረሰበት እንደሆነ ጠየቁ። አቶ ሙመድ ጥያቄያቸውን በወጉ ካደመጠ በኋላ ተገቢ ነው ያለውን ምላሽ ሰጠ። መሬቱን ከሟች ልጃቸው በኮንትራት እንደወሰደና እሱ ከሞተ በኋላም በሟች ታናሽ ወንድም ስም ስለ መዞሩ በእርግጠኝነት ተናገረ። ይህ ከሆነ በኋላም መሬቱን ከወንድምዬው መግዛቱን፣ ለዚህም ህጋዊ ውል እንዳለውና ክፍያ የፈጸመበትን ማስረጃ ማቅረብ እንደሚችል አስረዳቸው።
አቶ አልይ ይህን በሰሙ ጊዜ በሀዘን ተውጠው ስለምን ሲሉ ደጋግመው ሞገቱ። አሁንም ግን አቶ ሙመድ በመሬቱ ላይ ሙሉ መብት ያለው እሱ እንጂ እሳቸው ያለመሆናቸውን ጠቅሶ ከአካባቢው እንዲርቁ አስጠነቀቃቸው።
አቶ አልይ ከልጃቸው ሞት ያላነሰ ከባድ ሀዘን ማስተናገድ ከጀመሩ ጊዚያት ተቆጥረዋል። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የተነጠቁትን መሬት ለማስመለስ ያደረጉት ሙከራ ደግሞ ተሳክቶላቸው አያውቅም። ብዙዎችን አማክረው የተሰጣቸው ምላሽ ጉዳዩን በሕግ አግባብ እንዲፈቱት ማድረግ ብቻ ሆኗል።
ሀዘን የተፈራረቀባቸው አባወራ አሁን ራሳቸውን አረጋግተው ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ወስነዋል። ሀብሩ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳዩን ካስረዱ በኋላም በተሰጣቸው ቀነ ቀጠሮ ተጠሪውን አስቀርበው ክርክራቸውን ቀጥለዋል። ተጠሪው አቶ ሙመድ አደም መሬቱን ከሟች አህመዴ አልይ ለታናሽ ወንድሙ እንደተላለፈና ይዞታውንም በህጋዊ መንገድ እንደገዛው፣ ለዚህም ተገቢ የሚባል ክፍያ እንደፈጸመ መናገር ጀምሯል።
አቶ ሙመድ መሬቱን ከሟቹ ታናሽ ወንድም በግዢ ስለመረከቡ በመግለጽ ያስረዱልኛል የሚላቸውን ምስክሮችና አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎች እያቀረበ ነው። አመልካቹ አቶ አልይም ተጠሪ የሚያቀርባቸው ማስረጃዎች በሙሉ ከእውነት የራቁ መሆናቸውን እየጠቀሱ መቃወማቸውን ቀጥለዋል።
በተጠሪና በአመልካች መካከል የተጀመረው ውዝግብ ቀጥሏል። ‹‹ህጋዊ ነኝ …›› ‹‹አይደለህም…›› ይገባኛል …›› ‹‹አይገባህም …›› ይሏቸው ክርክሮችም በፍርድ ቤት ውሎዎች ሁሉ መሰማታቸውን ቀጥለዋል። ችሎቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ሀሳብ እያደመጠ ለቀጣይ ቀናት ቀጠሮዎችን ይሰጣል።
በተባለው ቀን በችሎቱ የሚቀርቡት አመልካችና ተጠሪም ‹‹አለን…›› የሚሏቸውን ማስረጃዎች እያቀረቡ በፍርድ ቤቱ መመላለሳቸውን ቀጥለዋል። ይህ ጊዚያትን ያስቆጠረ ውዝግብ በበርካታ ሰዎች ምክርና ሀሳብ ታጅቦ ሁለቱን ወገኖች ያከራክር ይዟል። ፍርድ ቤቱም ከየአቅጣጫው የሚቀርቡለትን የማሳያ ሀሳቦች እያገናዘበ የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ቀን ቆርጦ ቀጠሮውን አሳውቋል።
ሰኔ 10 ቀን 2003 ዓ.ም
ይህ ቀን የሀብሮ ወረዳ ፍርድ ቤት ለዓመታት ሲከራከሩ የቆዩትን አመልካችና ተጠሪን አቅርቦ ውሳኔውን የሚያሳውቅበት ነው። በዕለቱ የሚሰጠውን የመጨረሻ የፍርድ ሂደት ለማድመጥ ከችሎቱ የተገኙት ሁለቱ ወገኖች በራሳቸው ሀሳብ ተጠምደው የመጨረሻውን ውሳኔ ይጠባበቃሉ። ዳኛው አስከዛሬ በአመልካችና በተጠሪው መካከል ሲያከራክር የቆየውን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ከስር መሰረቱ ዘርዝረው ካስደመጡ በኋላ የመጨረሻውን የውሳኔ ሀሳብ በማሳወቅ መዝገቡን ዘግተው እንደደንቡ ባለጉዳዮቹን አሰናበቱ።
የመጨረሻው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አመልካች አቶ አልይ ዳዌ የልጃቸው አቶ አህመዴ አልይ ታናሽ ወንድም ለተጠሪው አቶ ሙመድ አደም በተገቢው ውልና ማስረጃ መሬቱን በሽያጭ ስለማስተላለፉ ጠቅሶ ይህም በበቂ ማስረጃዎች ስለመረጋገጡ ይጠቁማል። በዚህም ምክንያት አመልካች ያቀረቡት የይገባኛል ጥያቄ ውድቅ ሆኖ የእርሻ መሬቱ ለተጠሪው አቶ ሙመድ አደም እንዲጸድቅላቸው ሆኖ መወሰኑን ያረጋግጣል።
አቶ አልይ የሀብሮ ወረዳ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ካረጋገጡ በኋላ የተባለውን አምነው ለመቀበል ልባቸው አልፈቀደም። ከወዳጅ ዘመድ መክረውና ከቤተሰባቸው ተስማምተው ጉዳዩን ካቆመበት ለመቀጠል አሰቡ። ይህም ይሆን ዘንድ የውሳኔ ግልባጫቸውን ይዘው ‹‹አቤት›› ለማለት ወደ ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ገሰገሱ።
ፍርድ ቤቱ ‹‹ፍትህ ተጓደለብኝ›› ሲሉ ይግባኝ ያሉትን ባለጉዳይ ማመልከቻ ተቀብሎ መመርመር ጀምሯል። አቶ አልይ ያቀረቡትን ቅሬታ መሰረት አድርጎም አሉ የተባሉ ሰነዶችን በሙሉ እየፈተሸ ፍትህ ስለመጓደል ያለመጓደሉ በጥንቃቄ እያጣራ ነው።
በበቂ ማስረጃዎች ተሰንዶ የቀረበለትን ፋይል ከስር መሰረቱ መመርመር የጀመረው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀደም ሲል የሀብሮ ወረዳ ፍርድ ቤት ካሳለፈው ውሳኔ በተለየ የለወጠው ጉዳይ አልነበረም። መሬቱ ለተጠሪው በሽያጭ መተላለፉንና ይህም በበቂና ተጨባጭ ማስረጃዎች መደገፉን አረጋግጧል።
ፍርድ ቤቱ ከወረዳው የተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ በመመርመር ለአመልካችና ለተጠሪው ይገባል የሚለውን የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ይዟል። ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ባደረገው ሙከራም ከሀብሮ ወረዳ መሬት አስተዳደርና አካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት ማብራሪያ ጠይቆ በቂ የሚባል ምላሽን አግኝቷል።
ለውሳኔው ተጨባጭነት እንደማሳያ የተጠቀመባቸው ማስረጃዎችና የተጠሪውን የመከላከያ ምስክሮች አጣምሮ ባገኘው ውጤትም ክርክር የተነሳበት የእርሻ መሬት ለተጠሪ መሸጡን በማረጋገጥ መሬቱ የከሳሹ መሆን እንደማይገባ አስታውቋል።
ፍርድ ቤቱ መሬቱን በሽያጭ የተቀባበሉት የሟች ወንድምና ተጠሪ ይጠያየቁ ሲል በሰጠው ምላሽ ለተጠሪው ቀደም ሲል የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ዳግመኛ አጽንቷል። የአመልካችንም የይግባኝ ጥያቄ በ‹‹አይገባዎትም›› ውሳኔ አጽድቆ መዝገቡን በመዝጋት አሰናብቷል።
አመልካቹ አቶ አልይ ዳዌ ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው ይግባኝ ያሉበት ጉዳይ ዳግመኛ አለመሳካቱን አውቀዋል። አልይ አሁንም በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር እንደተሰኙ ነው። መሬቱ የእሳቸው ሆኖ ሳለ ‹‹ ፈጽሞ አይገባዎትም›› በመባላቸው ዕንቅልፍና ሰላም ካጡ ቆይተዋል።
አልይ በሁለቱ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ከልብ ቢያዝኑም አስከመጨረሻው ግን ተስፋ አልቆረጡም። በተቻላቸው አቅም ደንብና ህጉን ተጠቅመው መሬታቸውን ለማስመለስ ቆርጠው ተነስተዋል። አሁንም በየፍርድ ቤቶቹ እየሄዱም ‹‹አቤት›› ማለታቸውን ቀጥለዋል። ከይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ዘንድ ቀርበው ቅሬታቸውን ከማሰማታቸው የተሰጣቸው ተመሳሳይ ምላሽ ደግሞ ሆድ አስብሷቸዋል። አሁንም ግን ፈጽሞ ተስፋ መቁረጥን አይሹም።
በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ቀርበው ያገኙትን ምላሽ እንደያዙ በኦሮሚያና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ችሎት ተገኝተው ‹‹ፍትህ ተጓድሎብኛል››ሲሉ አቤቱታቸውን አሰሙ። በየተራ ቅሬታቸውን ያደመጡት ፍርድ ቤቶች ግን ከቀድሞዎቹ ፍርድ ቤቶች በተለየ አንዳች የማሻሻያ ለውጥን አላደረጉላቸውም። የስር ፍርድ ቤቶቹ ቀደም ሲል ያሳለፉት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አልተፈጸመበትም ሲሉ መዝገቡን ዘግተውና ውሳኔውን ዳግመኛ አጽንተው አሰናበቷቸው።
አቶ አልይ በፍርድ ቤቶቹ የተሰጣቸው ምላሽ ዳግመኛ ቢያሳዝናቸውም ‹‹በዚሁ ይብቃኝ›› ሲሉ መቀመጥን አልመረጡም። ራሳቸውን አረጋግተውና የህግ ባለሙያዎችን አማክረው የመጨረሻውን አማራጭ ለመሞከር ትግላቸውን ቀጠሉ። ቀደም ሲል በየፍርድ ቤቶቹ የተሰጣቸውን ውሳኔዎች በማያያዝና ማመልከቻቸውን በማዘጋጀትም ለኢፌዲሪ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታቸውን አሰሙ።
የጉባኤው ውሎዎች
ጉባኤው በሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ አቅራቢ አመልካች አልይ ዳዌ የቀረበውን የቅሬታ ሀሳብ ተቀብሎ መመርመር ጀመረ። ጥያቄ የተነሳባቸውን የህግ ድንጋጌዎችን በማጣቀስም የሁለቱን ወገኖች ፍላጎትና ሀሳብ በዝርዝር ለይቶ አስቀመጠ። የስር ፍርድ ቤቶች ያሳለፉትን ውሳኔና በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት የጸናውን ውሳኔ መመርመር ግድ ይል ነበር።
በጉባኤው ሰብሳቢውን ክቡር አቶ ተገኔ ጌታነህንና ምክትል ሰብሳቢውን ክቡር አቶመድህን ኪሮስን ጨምሮ አስራ አንድ የህግ ባለሙያዎች ተገኝተዋል። የክርክር መነሻ የሆነው የገጠር መሬት በአመልካችና በተጠሪ መካከል ያስነሳው የይገባኛል ጥያቄ እንዳለ ሆኖ በወረዳው፣ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቶች የጸናው ውሳኔ ተገቢ ያለመሆኑን የአመልካቹ አቤቱታ ይጠቁማል።
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ
በአቤቱታው በህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ መሆኑ እየታወቀ ጥበቃ የተደረገለት ህግ የተጣሰ መሆኑንና ለዚህም የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት ጥያቄ ቀርቦበታል። ጉባኤውም የቀረበውን የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄን በጥንቃቄ ፈትሾ በአግባቡ መርምሮታል።
ክርክር የተነሳበት መሬት በሽያጭ ከአንዱ ወደ ሌላው መተላለፉ ተጠቅሶ ከወረዳው ፍርድ ቤት የተላለፈውና በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች የጸናው ውሳኔ አግባብ ያለመሆኑን ጉባኤው አረጋግጧል። ለዚህም ያስቀመጠው ምክንያት መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት መሆኑን ነው።
በአመልካች ላይ የተላለፈው ውሳኔ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 3 ጋር የማይጣጣምና የአመልካችን ህገ መንግስታዊ መብት የጣሰ በመሆኑ ጉዳዩ የሕገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልገው ነው በማለት ጉባኤው በአንድ ድምጽ ተስማምቷል። ይህ ውሳኔም ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍ ሲል ሀሳቡን በጋራ አጽድቆ አሳልፏል።
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012
መልካምስራ አፈወርቅ