በ42 ሄክታር መሬት ላይ ተንሰራፍቶ፤ ወዲያና ወዲህ የሚዘናፈለው የጤፍ አዝመራ ዓይን ያሳሳል። በማሳው ውስጥ ለቆመ ሰው ደግሞ የጤፉ ቁመት ወገብ ላይ ይደርሳል። ለአላፊ አግዳሚው ግርምት፤ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ሆነ ለባለቤቶች ተስፋ የፈጠረ አዲስ ክስተት ነው።
በኤጀርሳ ለፎ ወረዳ ጀምጀም ለገባቱ ቀበሌ በጤፍ ኩታገጠም እርሻ ከተደራጁ 61 አርሶ አደሮች ውስጥ ከተካተቱት 12 እማወራዎች አንዷናቸው። ወይዘሮ ፋንቱ መንገሻ፤ አርሶ አደሯ ባለቤታቸው በሞት ከተለዩዋቸው ወዲህ በዘልማዳዊ እርሻ ሰባት ልጆቻቸውን እንዳሳደጉ ይናገራሉ። በዚህ መሬት ‘እዚያው ሞላ፤ እዚያው ፈላ’ የሆነውን የግብርና ህይወታቸውን ለመደጎም ሲሉ የቀን ሥራ ጭምር ለመሥራት ተገድደው ነበር። ዛሬ ግን መሬታቸው የዘመናት ድካማቸውን ሊክሳቸው ይመስላል።
ወይዘሮ ፋንቱ ለ20 ዓመታት መሬቱን ሲጠቀሙ እንደዘንድሮ አይነት አዝመራ እንዳላዩ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ለዚህም የኩታገጠምን የአስተራረስ ዘዴ በባለውለታነት ያነሳሉ። “አርሶ አደሩ ከዘልማዳዊው አስተራረስ ውጭ ያለውን አዲስ አሰራር መከተል ውጤታማ ያደርጋል ብሎ ስለማያስብ ነው” የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ራሳቸውን ማሳያ በማድረግ ነው። የግብርና ባለሙያዎች ያለመታከት የሚሰጡትን ትምህርት ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ የወሰኑት ግን አምና ነበር።
61 አርሶ አደሮች ተቀናጅተው በሆለታ ግብርና ማዕከልና በወረዳው የልማት ባለሙያዎች ታግዘው ወደ ዘመናዊ አሰራር እንደገቡ ይናገራሉ። አርሶ አደሮቹ 42ቱን ሄክታር መሬት ደጋግመው አረሱ። የምርምር ውጤት የሆነውን “ኮራ” የጤፍ ምርጥ ዘር በመስመር ዘሩ፤ ማዳበሪያ፣ የአረም መድሀኒትና አስፈላጊ የተባለውን ግብዓቶች በሙሉ አሟልተው በዞኑ ምሳሌ የሆነ የጤፍ አዝመራ ማግኘት ቻሉ።
አርሶ አደሮቹ በመደራጀታቸው ምርታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ በሴትነታቸው የሚገጥማቸውን ፈተና በአንድነት ቀርፈውታል። ይህ አሰራር በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ቢተገበር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዋነኛ አማራጭ እንደሆነ አስረድተው ተሞክሮውም መስፋት እንዳለበት ወይዘሮ ፋንቱ አስረድተዋል።
አቶ ድንበሩ ታደሰ የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ የኤክስቴንሽን ሥራ ሂደት አስተባባሪ ናቸው። ዘንድሮ በወረዳው ስምንት ሺህ 370 ሄክታር ማሳ በጤፍ መሸፈኑን ገልፀዋል። በ14 ቀበሌዎች ሦስት ሺህ 240 ሄክታር በኩታ ገጠም እርሻ ተሸፍኗል። ባለሙያው ከአርሶ አደሩ ጎን በመሆን ድጋፍ ሲሰጡ እንደነበር አስታውሰው በ42 ሄክታር የጤፍ እርሻ ላይ 49 አባወራዎችን እና 12 እማወራዎችን በማደራጀት ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ይናገራሉ።
አርሶ አደሮቹን አሳምኖ ለማደራጀት ግን ብዙ ውጣ ውረዶች ማሳለፋቸውን ገልጸዋል። በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት የባለሙያ ድጋፍ ሰጥተዋል። በባለሙያ ድጋፍ ከቡቃያው ጀምሮ የተለያዩ የጸረ አረም መድሀኒቶች ጥቅም ላይ ውለዋል ይላሉ። በዚህም ጤፍ በሄክታር ከ23 እስከ25 ኩንታል እንደሚገኝም ሙያዊ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ከአሁን በፊት በዘልማዳዊ አሰራር ከአንድ ሄክታር ከ10 እስከ 15 ኩንታል ይገኝ ነበር ብለዋል።
በዚህ ሂደት የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በቴክኒክ፤ በስልጠናና በምርጥ ዘር አቅርቦት፤ አርሶ አደሮች ፓኬጆችን በሙሉ እንዲጠቀሙ በማድረግ ክትትሉ እንዳልተለያቸው ጠቅሰዋል። ኩታ ገጠም እርሻ በማሳዎች መካከል የሚኖረውን እዳሪ ቦታ ጥቅም ላይ ለማዋል፤ ተባብሮና ተቀራርቦ ለመስራት፤ ልምድ ለመካፈልና ተፈላጊውን የባለሙያ አገልግሎትና ግብዓት በተመሳሳይ ቦታና ጊዜ ለማግኘት ይረዳል ይላሉ። በተበጣጠሰ መንገድ ከማረስ ይልቅ አንድ ላይ አካትቶ ማረሱ የመካናይዜሽን ተጠቃሚ ለመሆንም አስችሏል።
የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደጀኔ አቢ እንዳስረዱት፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የግብርናው ዘርፍ ትልቅ አቅም ነው። በመሆኑም፤ በወረዳው ጥቅም ላይ ከዋለው 19 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ውስጥ ከሦስት ሺህ ሄክታር በላይ በኩታ ገጠም እርሻ በጤፍ መሸፈኑን ጠቁመዋል። በወረዳው በጤፍ ብቻ 2014 ኩታገጠም ቅንጅቶች እንዳሉ የጠቀሱት አስተዳዳሪው፤ በወረዳው ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን የሚያመርቱ ከ400 በላይ ክላስተሮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
ኢያሱ መሰለ