በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከአራቱም የሀገሪቱ መዓዘን የፈጠራ ስራቸውን ለማቅረብ የተገኙ ተማሪዎች ፊታቸው ወደፊት ለመድረስ ባለሙት ህልም ፈክቶ ይታያል፡፡ ዛሬ ላይ የደረሱበትን አዕምሮዋቸው ባፈለቀላቸውና ያዩትን ችግር ለመፍታት በሞከሩበት የፈጠራ ስራ አጠገብ ቆመዋል፡፡ በእዚያ ለተገኘ ጎብኝና ታዳሚ የፈጠራን ስራቸው ምንነት ያስረዳሉ፡፡ ገና ወጣትና ከአስራዎቹ እድሜ ያልተሻገሩ፤ ሀገሪቱን በዘርፉ ትልቅ ቦታ የማድረስ ውጥን ያላቸው ታታሪ የፈጠራ ባለሙያ ብላቴናዎች ናቸው፡፡
እዚያ ቦታ ላይ የተገኘ ታዳሚ በልጆቹ የፈጠራ ስራ እየተደነቀ ወደፊት የሚደርሱበትን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ደረጃና ፈጠራ ምን ሊሆን እንደሚችል በመተንበይ ህልማቸው እንዲሳካ በመመኘት፣ በማወደስና በማበረታታት ለቀጣዩ ጎቢኚ ቦታ ይለቅቃል፡፡ ተማሪዎቹ ፈጣሪዎች ስራቸውን ማስተዋወቁንና የፈጠራ ስራቸውን ምንነት ማስረዳቱን ቀጥለዋል፡፡
ገና ወጣቶች ናቸው። ያሉበት ቦታ ደግሞ ወደ ቴክኖሊጂ የሚያስጠጋ የፈጠራ ስራ የሚተዋወቅበት፤ እነርሱ ገና አስራዎቹን ባይሻገሩም የፈጠራ ስራቸው ግን ዘመን የሚያሻግር፤ ኑሮ የሚያቀልል፤ ችግር የሚፈታ ሲሆን፤ በብሩህና በምጡቅ አዕምሮ ተቀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የብቃታቸው ማሳያ ነው፡፡
በሳይንስ መስክ የላቀ እምርታ ለማምጣት ይቻል ዘንድ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተሳታፊ የሆኑትን ወጣቶች ማበረታታትና ስራቸውን ለማህበረሰቡ የሚያቀርቡበት መድረክ ማዘጋጀት አሁን ላይ እየተለመደ መጥቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት የፈጠራ ባለሙያዎችን ከየክልሉ በመጋበዝ ስራቸውን የማስተዋወቅና የማወዳደር መርሀግብር ሲከናወን ሰንብቷል፡፡ በዚህ የፈጠራ ባለሙያዎችን እርስ በርስ ባገኛኘና ልምድ ባለዋወጠው ውድድር ወጣት ፈጠሪዎች በልዩ ሁኔታ ተስተናግደውበታል፡፡ ስራዎቻቸውንም ለውድድር አቅርበዋል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ ከተገኙ ወጣቶች መካከል ለዛሬ ሁለት ተማሪዎች አነጋግረን ስራቸውን ለዚህ አምድ በሚመች መልኩ ለማቅረብ ሞክረናል፡፡ በውድድሩ ላይ ተገኝተው የፈጠራ ስራቸውን ያቀረቡ ሌሎች ወጣቶችን በቀጣዩ ጊዜ በተከታታይ የምናቀርብ ይሆናል፡፡
ከፊት ለፊት ባለ ጠረጴዛ ላይ ሁለት የተለያዩ የፈጠራ ስራዎቹን አስቀምጦ ምንነታቸውን ይገልፃል፡፡ አሁን ያቀረባቸው የፈጠራ ስራዎቹ ምን ጥቅም እንደሚሰጡና ወደፊት በምን መልክ ሊያሻሽልና ሊያዘምናቸው እንደሚፈልግ ይዘረዝራል፡፡ ፊቱ ላይ ብሩህ ተስፋ በጉልህ ይነበባል፡፡ በሀገር ደርጃ እጅግ እየተስፋፋ ያለ የትራፊክ አዳጋ መቀነስ የሚያስችል መላ ዘውትር ሲያስብ ቆይቷል። ለዚህ ደግሞ በራሱ አንድ ነገር ለማድረግ ይቆርጣል፡፡
ከተለመደውና በከተማ ውስጥ ካለው የትራፊክ መብራት በተለየ መልኩ ዘመናዊና ተራራማ በሆኑ ጠመዝማዛ መንገዶች ላይ የሚያገለግልና የተሽከርካሪዎችን ግጭት ሊቀንስ የሚችል መረጃ ሰጪ ፈጠራ ሞከረና ተሳካለት፡፡ ይህ ፈጠራ አሽከርካሪዎችን ጠመዝማዛ መንገድ ላይ ከፊታቸው የሚመጣውን መኪና ርቀት እና ሁኔታ በመጠቆም ከሚደርስባቸው አደጋ ይጠብቃል፤ ያስጠነቅቃል፡፡
ትንሳዔ ብርሀኑ ይባላል፤ መኖሪያው በደብረማርቆስ ከተማ ነው፡፡ ገና የ18 ዓመት ወጣትና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ተማሪ ትንሳዔ ከልጅነቱ ጀምሮ ፍቅር ወዳደረበት የፈጠራ ስራ የሚያቃርበውን አጋጣሚ በመፍጠር፤ ዛሬ ላይም በመተግበርና የራሱን ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ትንሳዔ ከትራፊክ መብራት በተጨማሪ ሌሎች ስራዎች የፈጠረ ሲሆን፤ የከተማ ቆሻሻ ማፅዳት የሚያስችል መኪና ሞዴል ለውድድር ይዞት የመጣው ሌላኛው ፈጠራው ነው፡፡
ዛሬ ላይ አሳሳቢ በመሆን ላይ ያለውን የከተማ ንፅህና እጅጉን መለወጥና ፅዱ ከተማ መፍጠር የሚያስችለው ይህ መኪና ወደ ምርት ደረጃ ደርሶ አገልግሎት ላይ ከዋለ ትልቅ ለውጥ የሚያስገኝ የፈጠራ ስራ መሆኑን ተማሪ ትንሳዔ ይገልፃል፡፡
ትንሳዔ ለምርምር ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ተገቢ ድጋፍ ቢያገኝ ሌሎች የፈጠራ ስራዎች የመስራት እቅድ እንዳለውና በተለይም የማህበረሰቡ ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡
ተማሪ ትንሳዔ በፈጠራ ስራዎቹ በዞን፤ በክልልና በሀገር ደረጃ ለውድድር በመቅረብ የሰርተፍኬት የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማቶች እንዳገኘ ይገልፃል። ወደፊት በፈጠራ ስራው የላቀ ሚና መጫወትና ለሀገሩ ትልቅ ጠቀሜታ የማስገኘት አላማም አለው፡፡
ሌላው በዚሁ የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ ስራውን ይዞ የቀረበው አብዱል ሰላም ታሪኩ ይባላል። የቤንሻጉል ጉሙዝን ክልል ወክሎ የተገኘ፤ አሶሳ ከተማ የሚኖርና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ፤ ሸቀጣ ሸቀጥ እያዘዋወሩ መሸጥ የሚያስችል ተሽከርካሪና ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ማሽን ለውድድሩ ያቀረባቸው የፈጠራ ስራዎቹ ናቸው፡፡ አብዱል ሰላም ለውድድር ያቀረባቸው ስራዎች ከሌሎች መሰል የፈጠራ ስራዎች በብዙ መልኩ የሚለዩ እንደሆኑ ጠቀሜታቸው በመግለፅ ያስረዳል፡፡
አካል ጉዳተኞችን በስራ ተሳታፊ ሊያርግ የሚችለውና ቁጭ ብለው ማንቀሳቀስና ቁሳቁሶችን መሸጥ የሚያስችላቸው ተሽከርካሪ ከዚህ በፊት ከነበሩ የፈጠራ ስራዎች የሚለይ ሲሆን፤ ሁለገብ አገልግሎት መስጠት የሚችለው ማሽን ደግሞ በርካታ የምግብ ዓይነቶችን በተለያየ ቅርፅና ይዘት ማብሰል የሚያስችል ነው፡፡ ትኩስ ነገር ማፍላት፤ ኬክና ዳቦ መጋገር፤ በቆሎ መጥበስ እና በእንፋሎት ምግብ ማዘጋጀትም ያስችላል፡፡
የተማሪ አብዱል ሰላም የፈጠራ ስራዎች በአቅም እጥረት ምክንያት ለሌሎች ደርሰው አገልግሎት መስጠት ባይችሉም፤ ድጋፍ አግኝቶ ስራዎቹ ወደ ምርት ቢገቡ ማህበራዊ ፋይዳቸው የላቀ መሆኑንና ሁሉንም ማህበረሰብ የሚያገለግሉ እንደሆኑ ባለሙያው ይገልፃል፡፡
ምርምር የጀመረው ገና የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ በተመለከተው የፈጠራ ስራ ተማርኮ እንደሆነ የሚናገረው አብዱል ሰላም፤ በትምህርት የሚያገኘውን እውቀት በመጠቀም የተለያዩ ፈጠራዎችን በመሞከር ትርፍ ሰዓቱን እንደሚያሳልፍም ይናገራል፡፡ ወደፊት የተለየዩ የፈጠራ ስራዎችን የመስራት እቅድ እንዳለው በመግለጽ የቁሳቁስና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ እንዲደረግልት ጠይቋል፡፡
ወጣት አብዱል ሰላም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የፈጠራ ስራ ውድድሮች ተካፋይ መሆኑንና ከአራት በላይ ሜዳሊያዎች ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መሸለሙን፤ በክልልና በልዩ ልዩ ሀገራዊ ውድድሮች ላይም በርካታ ሽልማቶች ማግኘቱን ይገልፃል፡፡
የወጣቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ መሳተፍና የፈጠራ ስራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ አጋጣሚዎች መፍጠር ሀገሪቱ ወደፊት ልታሳካው የምትፈልገውን የቴክኖሎጂ እድገት መሰረት ነውና በዘርፉ ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶችን ማበረታታት ተገቢ መሆኑን ማሳሰብ እንወዳልን፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም5/2012
ተገኝ ብሩ